
03 Sep, 2016
በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተነሳ ቃጠሎ በማረሚያ ቤቱ ላይ ጉዳት አደረሰ፡፡
ቃጠሎው የተነሳው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል እንደሆነ የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ የአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ከረፋዱ አራት ሰዓት በኋላ መድረሱን ይገልጻሉ፡፡ አካባቢው በፌዴራል ፖሊስ አባላት በፍጥነት ተከቦ እንደነበርም ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ ወደ አካባቢው ከአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስተቀር ማንም እንዳይጠጋ በፀጥታ ኃይሎች የተከለከለ ሲሆን፣ የአደጋው መነሻ ከእስር ቤቱ ካፌ የተነሳ እሳት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ እሳቱ ከካፌው በመነሳት ዞን ሦስት የሚባለው የእስረኞች ክልል ድረስ ደርሶ እንደነበር ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አገልግሎት የአደጋ ጊዜ ሦስት ሠራተኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ በእስረኞች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ሪፖርተር በማጣራት ላይ ይገኛል፡፡
በእሳት ቃጠሎ ወቅት በአካባቢው የተገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ ሠራተኞች፣ እስረኞችን ለማስፈራራት ወደ ሰማይ ሲተኩሱ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከሚገኙ እስረኞች መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባና አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ አመራር አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ሌሎች ይገኙበታል፡፡
- ዮሐንስ አንበርብር’s blog
- 1420 reads