የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት አምባሳደር ፓትሪሺያ ለኤምባሲው ሠራተኞች ባደረጉት የመሰናበቻ ንግግር፣ ‹‹መልዕክታችን ግልጽ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ እንድትለማና ስኬታማ እንድትሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ጠንካራ የምትሆነው ሁሉም ድምፆች ተደማጭና መንግሥትም ለሁሉም ተጠያቂ ሲሆን እንደሆነ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ሕግን ያልተከተለ እስርና እንግልት ሊቆም ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ እየተከሰቱ ያሉ ሁኔታዎች የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እስካሁን ያደረጓቸውን መሻሻሎች የማስተጓጐል አቅም ያላቸው በመሆናቸው፣ ሥጋት እንደገባቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹የኤምባሲውን ሠራተኞች ጨምሮ በኢትዮጵያ ፍርኃትና ሥጋት እንዳለ አውቃለሁ፡፡ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን እንዲያከብሩ የኢትዮጵያ መንግሥትን እንጠይቃለን፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ ለመንግሥት ሚዲያዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተቃራኒው፣ ‹‹ይህች አገር ትፈርሳለች ብለው የሚሰጉ የኢሕአዴግን ባህሪ የማያውቁ ናቸው፡፡ በአለት ላይ የፀና የፌዴራሊዝም ሥርዓት ነው ያለው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡