September 3, 2016

(ኢ.ኤም.ኤፍ -የዳዊት ከበደ ወየሳ ዘገባ) በምርጫ 97 ሰሞን፤ በቃሊቲ የታሰሩ በመቶዎች የሚቅቆጠሩ ወጣት እስረኞች በህወሃት ጦር እንዲገደሉ ተደርጎ ነበር። በወቅቱ የተሰጠው ምክንያት፤ “ከእስር ሊያመልጡ ሲሉ…” የሚል ነው። እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። በወቅቱ በቃሊቲ እስር ቤት በርካታ የኦሮሞ እና ሌሎች የተቃዋሚ ድርጅት አባላት ታስረው ነበር። እነዚህ ወጣቶች እነማን እንደሆኑ ከታወቀ በኋላ፤ ገዳይ ኃይሎች እነዚህን ወጣቶች ከነሙሉ ትጥቃቸው ቃሊቲ እስር ቤት መጡ። ከዚያም ወጣቶቹን እየነጠሉ መውሰድ ሲጀምሩ ረብሻ ተነሳ። ይህንን ሁከት ምክንያት በማድረግ በቃሊቲ የብዙ ወጣቶች ደም ፈሰሰ።

ብዙ ወጣቶች ከርሸናው ለማምለጥ ወደ አንድ ክፍል ከገቡም በኋላ፤ የህወሃት ሰዎች ተከትለዋቸው መጡ። ብዙዎቹ ወጣቶች ህይወታቸውን ለማትረፍ አንዱ ባንዱ ላይ እንደተደራረበ፤ “እባክህ አትግደለኝ” ብለው እየለመኗቸው፤ ያለምህረት ገደሏቸው። በኋላ ላይ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽንም ጅምላ ግድያ መፈጸሙን አረጋግጧል። (ዘርዝር ግድያውን ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እንደነገረኝ አስታውሳለሁ። በኋላ ላይም በ’ቃሊቲው መንግስት’ መጽሃፉ ላይ ገልጾታል) በ97 ምርጫ ወቅት የተረሸኑት ወጣቶች እዚያው ቃሊቲ እሥር ቤት ውስጥ ዞን 5 ግቢ ውስጥ በአንድ ላይ ተቀብረዋል።

ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አሁንም ከደብረታቦር እስር ቤት ቃጠሎ ወይም ከቅሊንጦ ወህኒ ቤት ጀርባ ማን ሊኖር እንደሚችል ታዛቢዎች የየራሳቸውን ግምት ሊሰጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ቃጠሎው 3፡00 ሰዓት ላይ ከመነሳቱ በፊት ፖሊሶች ግራ በመጋባት፤ ክብ ክብ እየሰሩ ግራ በመጋባት አይነት እርስ በርሳቸው ያወሩ ነበር። እስረኛ ጠያቂዎች ጠዋት በማለዳ የመጡ ቢሆንም፤ በር ላይ “ለእስረኞች ውሃ ብቻ ነ ማስገባት የምትችሉት” ተብለው ስንቅ ማቀበል እንደማይችሉ ተነግሯቸው፤ ብዙ ጠያቂዎች በሁኔታው ግራ ተጋብተው እንደነበር፤ በስፍራው የነበሩ ሰዎች ያስረዳሉ። ይህ ብቻም አይደለም። ጠያቂዎች እስረኞቹን ለመጠየቅ ወረፋ እየጠበቁ ቢቆዩም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ፖሊሶቹ ተረብሸው፤ “መግባት አይቻልም። አንድ ግዜ ቆዩ!” እንደተባሉና ትዕዛዙ ከላይ እንደመጣ ተነግሯቸው ነበር።

ጠያቂዎች በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው፤ ግራ ተጋብተው በነበረበት ወቅት ድንገት የተኩስ ድምጽ ተሰማ። የተኩስ ድምጹን ተከትሎ የእስረኞች ጩኸት ተከተለ። ተኩሱ በሁሉም በሮች በኩል ይሰማ ጀመር። የእሳት ቃጠሎው የታየው ከዚህ በኋላ ነው። የእሳት ቃጠሎውን ተከትሎ፤ ከእሳቱ ለማምለጥ የሞከሩ እስረኞች ያለምንም ርህራሄ ተገድለዋል።  የተቃጠሉም አሉ። የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ከአቅሙ በላይ ስለሆነ፤ ታካሚዎችን ማስተናገድ አልቻለም። የጳውሎስ ሆስፒታልም ከሃያ በላይ እስረኞች አስከሬን ተቀብሏል። ወደ ልዩ ልዩ ቦታዎች የተወሰዱ ሟች እና በተኩስ የተጎዱ እስረኞች አሉ።

የኢትዮጵያ ዜና በሬድዮ እና በቴሌቪዥን እሳት መነሳቱን አምኖ፤ እሳቱን ለማጥፋት በተደረገው ጥረት ሶስት የእሳት አደጋ ሰራተኞች መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል። ስለተገደሉት እና ስለሞቱት፤ ስለተተኮሰባቸውና ስለቆሰሉት የፖለቲካ እስረኞች ግን ምንም አላለም።

ይህ የእስር ቦታ ከቃሊቲ በላይ፤ ከዝዋይ በታች የሚገኝ በህወሃት እና ኦህዴድ ሰዎች የሚጠበቅ፤ እስር ቤት ሲሆን፤ በተለይ በኦሮሞ ንቅናቄ ውስጥ የነበሩ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አባላት፣ የሙስሊም ኮሚቴዎች እና ጋዜጠኞች የታሰሩበት ቦታ ነው።  ጠያቂዎች እስረኛን ለመጠየቅ የሚገቡበት ጠባብ በር በታጠቁ ፖሊሶች ይጠበቃል። ከነዚህ በሮች በተጨማሪ ግቢው ላይ ባሉት ማማዎች ታጣቂዎች፤ እስረኛውን እንደልባቸው ሊያዩ ወይም ሊተኩሱባቸው በሚችሉበት ሁኔታ የተሰራ ነው።

ከዚህ በፊት በቃሊቲ የተፈጸመው ግፍ ሳያንስ አሁንም በቅሊንጦ፤ ዳግም ጥቁር ሽብር በእስረኞች ላይ ተፋፋመ። ጠ/ሚንስትሩ ወይም ሌላ ቃል አቀባይ፤ በማናቸውም ግዜ ሚዲያ ላይ ወጥተው… “እስረኞች ሊያመልጡ ሲሉ እርምጃ ተወሰደባቸው” ሊሉ ይችላሉ። ይህ ግን ፈጽሞ ሃሰት ነው። ግለሰብ ሊዋሽ ይችላል። በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኙ አካላት ደግመው ደጋግመው መዋሸትን እንደመደበኛ ስራቸው ከቆጠሩት ሰነባብተዋል። ለዚህ የቅሊንጦ ጅምላ ግድያ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች ሳይውል እና ሳያድር ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባቸዋል። በአምቦ፣ በጎንደር እና በደብረ ታቦር በተመሳሳይ መልኩ እስረኞችች ላይ በቀጥታ በመተኮስ ግድያ መፈጸሙ ይታወሳል።

መንግስት ገለልተኛ  አካል አቋቁሞ፤ ስለቃጠሎውና ግድያው ተጠያቂውን አካል ለህግ የማያቀርብ ከሆነ፤ በርግጥም ከዚህ ጀርባ ህወሃት ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጭምር እንዳለበት ልንጠረጥር ይገባናል።

እስከዚያው ግን የሰብአዊ መብት ጉባኤ የእስረኞችን ቤተሰብ በመጠየቅ ይህንን አይን ያወጣ ጭፈጨፋ ለህዝብ ማቅረብ አለባቸው።

በአጠቃላይ ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ዝምታን ሊመርጡ አይገባም። የመንግስት ባለስልጣናት ይህን ጥፋት በገለልተኛ አካል አስመርምረው ሃቁን ለህዝብ ይፋ ሊያደርጉ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን የዚህ ጥቁር ሽብር ጭፍጨፋ ጦስ በቀላሉ አይበርድም።

Leave a Reply