አሳዛኝ ሰበር ዜና!
ርሸናው ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ተሸጋግሯል
ትላንት ቅዳሜ ነሐሴ 28/2008 ለሊት 8 ሰዓት አካባቢ መንግስት ኮሚቴዎቻችን በሚገኙበት በቃሊቲ እስርቤት በዞን 1 ውስጥ ታስረው ከሚገኙ ታሳሪዎች መካከል 2 ሰዎችን የረሸነ ሲሆን ሁለቱን ደግሞ በጥይት መቶ ማቁሰሉን ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ መንግስት ከትላንት በስቲያ ለሊት በቂሊንጦ ከወሰደው ዘግናኝ የቃጠሎና የግድያ እርምጃ በኋላ ትላንት ምሽት ደግሞ በድጋሚ ተመሳሳይ አሰቃቂ ወንጀል በቃሊቲ የፈፀመ ሲሆን፤ የቃሊቲ እስርቤት አስተዳደርም ‹‹እስረኞቹ ለማምለጥ በመሞከራቸው ነው የተገደሉት›› የሚል ውንጀላ ያቀረበ ቢሆንም፤ ይህ የመንግስት ውንጀላ ግን ከእውነት የራቀ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ገልፀዋል፡፡
የተረሸኑት ሁለቱ እስረኞች ማንነታቸውን ለማጣራት እየሞከሩ እንደሆነ የውስጥ ምንጮች ያስረዱ ሲሆን፤ ሟቾቹ ታሳሪዎችም የሕዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ኡስታዝ አህመዲን ጀበልና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ባሉበት ክፍል ውስጥ ታስረው የነበሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሕዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ግን እስካሁን ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ለማወቅ ችያለሁ፡፡
የእስርቤቱ አስተዳደር በቅርቡ በቃሊቲ ዞን 1 እና ዞን 2 ‹‹አንድ ነገር ቢፈጠር እርምጃ የምንወስድባቸው ታሳሪዎች ስም ዝርዝር›› በሚል 4 የሕዝበ ሙስሊሙን ወኪሎች ጨምሮ ከ140 በላይ የሚሆኑ ታሳሪዎችን ስም ለጥፎ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በወቅቱ በእስርቤቱ ስሞቻቸው ከተለጠፉት የሕዝበ ሙስሊሙ ተወካዮች መካከል ፎቷቸው ከስር የተመለከተው፡ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል፣ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፣ ኡስታዝ በድሩ ሑሴን እና መሀመድ አባተ ይገኙበት ነበር፡፡
ቀድሞውኑ ሊረሽናቸው ያሰባቸውን አካላት አሰናድቶ ያስቀመጠው መንግስት በአሁኑ ሰዓት በየእስርቤቱ ያለምንም ሃይ ባይና ከልካይ በማን አለብኝነት ዜጎቻችንን መረሸኑን ተያይዞታል፡፡ እነዚህ እጆቻቸው ባዶ የሆኑ፣ ያልታጠቁና በሕግ ስር የሚገኙ የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ታሳሪ ኢትዮጵያውያንን በጨለማ በመረሸን መንግስት እያደረገ ያለውን አረመኔያዊ ተግባር በአስቸኳይ ሊያቆም ይገባል፡፡ ወኪሎቻችን ላይ አንዲት እንኳ ችግር ቢደርስ ከችግሩ ጋር የተያያዙ አካላት በሙሉ ከተጠያቂነትና ከሙስሊሙ ኢላማ ሊያመልጡ እንደማይችሉ አምባገነኑ መንግስት ማወቅ ይኖርበታል፡፡