በዛሬው እለት በደቾች ጋዜጣ ላይ የሰፈረ
ትርጉም አገሬ አዲስ
ሰበር ዜና
ከአንድ ዓመት በፊት አስር ሚሊዬን ኤሮ ወጭ አድርጎ በኢትዮጵያ ውስጥ በአበባ ምርት የተሰማራው ኩባንያ ሥራውን አቆመ
በዓለም አቀፍ ደረጃ በትልቅነቱ የሚታወቀው በአበባ ምርት የተሰማራው ኢሳመራልድ(Esamerald)የተባለው የደቾች ድርጅት ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ፣በባሕርዳር ውስጥ በሚያካሂደው ንብረትና እርሻ ላይ በደረሰው ሕዝባዊ ጥቃት የተነሳ ሥራ ማቆሙን ይፋ አደረገ።የኩባንያው ቃል አቀባይ እንደገለጸው በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል በተፈጠረው የፖለቲካ ችግርና አለመረጋጋት፣ከመንግሥት ጋር ተባብራችዃል በሚል ምከንያት ሕዝቡ በወሰደው የጥቃት እርምጃ በእሳት ቃጠሎ ከሃምሳ በመቶ በላይ የሆነው የተቋሙ ንብረት በመውደሙና ለማንሰራራትም የማይቻል በመሆኑ ሥራውን ከማቆም የተሻለ ምርጫ አለመኖሩን አክሎ ገልጿል።
ይህ ድርጅት በዓለም ዙሪያ የሚንቀሳቀስ ሲሆን በኤኳዶር፣ኮሎምቢያ፣ኮስተሪካ፣ፔሩና ሜክሲኮ ውስጥም በስፋት ይንቀሳቀሳል።በባሕር ዳር ውስጥ ባለው ቅርንጫፍ ድርጅቱ ውስጥ ስድስት መቶ ሠራተኞችይሰሩ እንደነበረና ከውድመቱ በዃላ ሁሉም ከሥራ እንደተሰናበቱ ተገልጿል፤በኔዘርላንድም ውስጥ ከዚሁ ሥራ ጋር በተያያዘ ይሰሩ የነበሩ አስራ አራት ሠራተኞች ተሰናብተዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ መቶ ሰላሳ በላይ የደቾች ኩባንያዎች ሲኖሩ ከነዚያ ውስጥ ዘጠናዎቹ በአበባና በአትክልት እርሻ ላይ የተሰማሩ ናቸው።የቀሪዎቹ እጣፈንታ የታወቀ ባይሆንም ስጋት እንዳደረባቸው ቃል አቀባዩ አልደበቀም።ጨምሮም በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል የተፈጠረው ችግር በውይይት የፖለቲካ መልስ ማግኘት የሚገባው ነው፤እኛ ደግሞ ለዚያ የምንጫወተው ሚና የለንም ሲል አስተያየቱን ደምድሟል።
ከአንዳንድ ኢትዮጵያውያን የሚሰነዘረው ሃሳብ ንብረት ከማውደሙ ይልቅ የሠራተኛውና የከባቢው ደህንነትና ኑሮ ሳይዛባ ከመንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር ያለው ትስስር ተወግዶ ሕዝቡና አገሪቱ በሚጠቀሙበት መልኩ የሚቀጥልበት ሁኔታ ቢፈጠር ይሻላል የሚል ነው።እርግጥ ነው ሕዝቡን ጠቅመው እራሳቸውን ሊጠቅሙ የሚመጡት በሙስና ያልተጨማለቁ የንግድና የምርት ተቋማት እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል።ከሕዝቡ የሚያውቅ የለምና ወደፊት ለሚወስደው እርምጃ በቂ ጥናትና ጥንቃቄ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ።
አገሬ አዲስ