‹‹የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጉዳይ ከአማራ ክልል ውጪ የትም አይታይም›› አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
በአማራ ብሔራዊ ክልል አብዛኛዎቹን የጎንደርና የጎጃም አካባቢዎችን ለተቃውሞ ያነሳሳውና ለበርካቶች ሕይወት ማለፍ መነሻ ምክንያት የሆነውን የወልቃይት የማንነት ጉዳይ በተመለከተ፣ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ተወያይቶ የሚያሳልፈው ውጤት እንደሚጠበቅ የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ፡፡ ለዚህም ስምምነት ላይ መደረሱ ተገለጸ፡፡
ቅዳሜ ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጎንደር ከተማ ከነዋሪዎችና ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡ አቶ ገዱ በተለያዩ መድረኮች ከሁለቱ ወገኖች ጋር በተወያዩበት ወቅት ክልሉ የወልቃይትን ጉዳይ ለምን ይህን ያህል ዓመት መፍትሔ ሳይሰጠው እንደቀረ ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት፣ ‹‹በቅርቡ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ተወያይቶ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ከውሳኔውም በኋላ የሕዝባችን ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መልስ ያገኛል፡፡ በወንድማማችነትና በሰላም የመኖር ባህላችንን እናስቀጥልበታለን፤›› ብለዋል፡፡
የስብሰባው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለምን በቀጥታ የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን አያየውም? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ጉዳዩ ለረዥም ዘመናት እየተንከባለለ የመጣ በመሆኑ በፌዴራል ደረጃ ቢታይ መልካም ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩን የአማራና የትግራይ ክልሎች ብቻ አድርጎ ከመውሰድ፣ ሌሎችም የኢሕአዴግ ድርጅቶችና አጋሮች በተገኙበት ተወያይተው ሊፈታ ይገባል ያሉት ነዋሪዎች፣ ‹‹25 ዓመታት መታሸት ነበረበት ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
‹‹ይህ ጥያቄ (የወልቃይት የማንነት ጥያቄ) በአገር ደረጃ ታውቋል፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱን ጠብቆ ነው መቅረብ ያለበት፡፡ መጀመሪያ ጥያቄው ለትግራይ ክልል መንግሥት እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡ ክልሉ የሚሰጠው ምላሽ ሕዝቡ ካልተስማማው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚቻል ስምምነት ላይ ተደርሷል፤›› ብለዋል አቶ ገዱ፡፡
የጠገዴንና የፀገዴን ድንበር ሁለቱ ክልሎች ተነጋግረው በአጭር ጊዜ ይፈቱታል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን የክልሉ ምክር ቤት (የትግራይ) የመጨረሻ ውሳኔ ሕዝብን ካላረካ ወደ ፌዴራል መንግሥት ተወስዶ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይታያልም ሲሉ፣ በተለይ በጎንደር ከተማ ለሚኖሩ የላይ አርማጭሆ ወረዳ ተወላጆች ገልጸውላቸዋል፡፡
የአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የማንነት ጥያቄ በክልል ከቀረበና አጥጋቢ ምላሽ ካላገኘ ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረብ እንደሚችል በግልጽ አስቀምጦ እያለ፣ ይህንኑ አማራጭ ለመከተል ስምምነት መደረጉ መገለጹ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቶች አጠያያቂ ሆኗል፡፡
ከዚሁ ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተለይ በጎንደር ከተማ ለነዋሪዎችና ለፀጥታ ኃይሎች መጋጨት ምክንያት እንደነበሩ የሚነገርላቸው፣ የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ አባል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን በተመለከተም ለርዕሰ መስተዳድሩ የተነሳላቸው ጥያቄም ይገኝበታል፡፡
የኮሎኔል ደመቀ ጉዳይ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የሚታይ ነው ካሉ በኋላ፣ ወደ ሌላ ቦታ ተወስደው ጉዳያቸው ይታያል የሚባለውን መረጃ ርዕሰ መስተዳድሩ አስተባብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ተቀጣጥሎ የከረመው የጎዳና ላይ ተቃውሞና የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማው በአብዛኛው ሥፍራዎች መጠነኛ መረጋጋት ቢያሳይም፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በቤት ውስጥ የመቀመጥ አዲስ ተቃውሞ መታየት ጀምሯል፡፡ በተለይ ማክሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በዶዶላ፣ በሻሸመኔ፣ በነቀምት፣ በጊምቢ፣ በሮቤ፣ በጫንጮ፣ በሱሉልታ፣ በጉደር፣ በደምቢዶሎ፣ በኮፈሌና በመሳሰሉ ወረዳዎች አብዛኛዎቹ የንግድና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተዘግተው ውለዋል፡፡
የሰሞኑ የኦሮሚያ ተቃውሞ በሰብዓዊ መብትና በፖለቲካ አቀንቃኞች በጳጉሜን ለአምስት ቀናት የሚቆይ የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በተደረገ ጥሪ መሠረት መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡