የህዝባችን ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው በህዝባዊ መንግስት ምስረታ ብቻ ነው!!! – ልሳነ ግፉዓን
በሃገርችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከልሳነ ግፉዓን ድርጅት የተሰጠ መግለጫ
የህዝባችን ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው በህዝባዊ መንግስት ምስረታ ብቻ ነው!!!
የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር እያስተጋባ ላለው የዲሞክራሲና የፍትህ ትግል ምላሽ ይሆናል በሚል የህወሃት/ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ5 ቀናት ካደረገው ዝግ ስበሰባ በኋላ በነሃሴ 22, 2008 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠውን መግለጫ ድርጅታችን ልሳነግፉዓን በጥሞና ተከታትሎታል። እንዲሁም መግለጫውን ተከትሎ በማግስቱ የፋሽስቱ ህወሃት ጦር ወደ ጎጃምና ጎንደር አማሮች ላይ እንዲዘምት የተደረገ መሆኑና ወራሪው ሰራዊትም “ያለምንም ርህራሄ በህዝብ ላይ እርምጃ እንዲወስድ” በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩል ቀጭን ትእዛዝ እንደተላለፈ ከራሳቸው ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ አንደበት ሰምተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ እራሱን “የትግራይ ክልል መንግስት” እያለ የሚጠራው የወንበዴዎች ስብስብ በነሃሴ 29, 2008 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ www.tigraionline.com ባሰራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ 4060 የትግራይ ተወላጆች ከአማራ ወደ ትግራይ ክልል እንደተጓጓዙና ለዚህም ፍልሰት ምክንያቱ የአማራ ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ “የዘር ማጽዳት ወንጀል” /Ethnic Cleansing/ እየፈጸመበት መሆኑ ነው በማለት ይደሰኩራል። አሳፋሪው የሃሰት መግለጫ በዚህ ሳያበቃ በአሁን ሰአት በአማራ ክልል በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ስለሚገኙ እነሱን በአስቸኳይ ከተጋረጠባቸው “የዘር ማጽዳት አደጋ መታደግ አለብኝ” በማለት ቀጣይ የስልጣን ማራዘሚያ ክኒኑን ይዘረዝራል።
እንግዲህ እነዚህ ሁሉ መግለጫዎችና ዲስኩሮች በየአቅጣጫው የሚጎርፉት አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። በእነዚህ መግለጫዎች ህወሃት መራሹ መንግስት የወቅቱንና አንገብጋቢውን የህዝብ ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስና በቁጣና በቁርጠኝነት የተንሳውን የህዝብ አብዮት በሰላምና ህዝብን በማዳመጥ ከመፍታት ይልቅ እንደ ቀደሙት አምባገነን ስርዓቶች ሁሉ ዛሬም የህዝብን ጥያቄ ሲቻል በፍርደ ገምድልነትና በማጭበርበር ካልሆነም በጦር ሃይል በመጨፍለቅ በስልጣን ላይ ለመቆየት ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠበት ሆኖ አግኝተነዋል።
ህወሃት ለአለፉት 37 ዓመታት የአማራን ህዝብ ለማጥፋት በወልቃይት ጠገዴና በጠለምት የጀመረው ፍሽስታዊ ጉዞ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ንጽሃን አማራዎችን ከበደኖ፣ ጉራፈርዳ እስከ ቤንሻጉልና ጋምቤላ በግፍ ሲጨፈጭፋና ሲያስጨፈጭፍ ማንም ያስቆመኛል ወይም እነዚህን ግፉዓን ማንም ይታደጋቸዋል ብሎ እንዳልጠረጠረና እንዳልጠበቀ የሚፈጽመው ግፍ አይናውጣነትና መሪዎቹ በማን አለብኝነት መብቱን እንዲከበርለት በጠየቀ ህዝብ ላይ የሚያወርዱት የስድብ ናዳ መስማት በቂ እማኝ ነው።
እነሆ ዛሬ ይህ በአማራ ህዝብ ላይ ሲፈፀም የኖረው የዘር ማፅዳት ወንጀል ፅዋው ሞልቶ መፍሰስ በመጀመሩ “አከርካሪውን ሰብረነዋል” “ዳግም እንዳያንሰራራ አድርገን ቀጥቅጠነዋል” ያሉት ህዝብ እራሱንና ትውልዱን ለመታደግና የህወሃትን ፋሽስታዊ ስርዓት ታሪክ ሊያደርገው ከድንቅና ከሚያስፈራ ዝምታ በኋላ ከዳር እስከዳር ሆ! ብሎ ተነስቷል!
ይህ ታጋሽና ጀግና ህዝብ ከድል በስተቀር የሚያቆመው ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል እንደሌለ እንኳንስ ህወሃት ቀደምት ጠላቶቻችን ሳይቀር ያሚያውቁት የታሪክ እውነታ ነው። ምክንያቱም ህዝብን ማሸነፍ አይቻልምና ነው። ይሁን እንጂ በንጹሃን ደም የሰከረው ህወሃት ዛሬም ሃገርን በማረጋጋት ሽፋን የአማራን ህዝብ በጀምላ ሊገድልና ዘራችን ሊያጠፋ በማቀድ በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ተቋማት በኩል የተለያዩ መሰረተቢስ ውንጀላዎችና ክሶችን በአማራ ህዝብ ላይ እያሰማ ይገኛል።
ውንጀላ ቁ. 1 – “የትግራይ ተወላጆች ከአማራ ክልል እየተባረሩ ነው” – ህወሃትና “….ማህበረ ተጋሩ…”
ከታሪክ ማህደር – “የአይናችሁ ቀለም አላማረንም ብለን ማባረር መብታችን ነው” ሟች መለስ ዜናዊ የኤርትራውያንን ሲያባሩ ከተናገሩት
ለዘመናት ከጎንደርና ከጎጃም ህዝብ ጋር ተዋልደውና ተዛምደው በሰላም የሚኖሩትን የትግራይ ተወላጆችን በማሸበር ያለአንዳች ተጨባጭ ምክንያት፣ በህወሃት ብቸኛ ሴራና ቀጥተኛ ትእዛዝ፣ ወልደውና ከብደው፣ በሰላምና በክብር ከሚኖሩበት አካባቢ እየተለቀሙ አንዳንዶቹ ከተወልዱ አይተውት ወደማያውቁት የትግራይ ክልል በአውሮፕላን ሳይቀር እየተጓጓዙ እንደሆነ ይሰማል። በዚህ ከፋልጎታቸውና ከእውቅናቸው ውጭ ወደ ትግራይ የሚጓጓዙት ወገኖቻችን አበርዋቸው ያረጁትን ጎረቤቶቻቸውን እንኳ በቅጡ እንዳይሰናበቱ በህወሃት በተሰጣቸው ቀጭን ትእዛዝ መሰረት እንደሌባ በድብቅ በሌሊት ሳይቀር ተጓጉዘዋል።
እርግጥ ነው ብዙ አስተዋይና በራሳቸው የሚተማመኑ የትግራይ ተወላጆች ይህን የህወሃት ሴራና የሽብር ዘመቻ ባለመቀበል ልጅ ወልደው ባሳደጉበትና በዳሩበት፣ ንጽህ ላባቸውን አንጠፍጥፈው ሃገር የሚያውቀውና የሚመሰክረው ሃብትና ንብረት ባፈሩበት፣ ከሁሉም ጋር ዘር ሳይቆጥሩ ተዋልደውና ተዛምደው በኖሩበት፣ እድሜና ክብር ጠግበው የሃገር ሽማግሌና አስታራቂ ሆነው ባረጁበት ሃገራቸው መኖርን የመረጡና ህወሃት በአማራ ህዝብ ላይ የደገሰውን መከራ ሁሉ አብረው ለመቀበል የወሰኑ የቁርጥ ቀን ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ድርጅታችን ልሳነግፉዓን በተጨባጭ መረጃ አረጋግጧል።
በመረጃ የተረጋገጠው እውነት ይህ ሆኖ እያለ ሃሰተኞቹና በህወሃት ሳንባ የሚተነፍሱት “ትላንትን ወደኋላ” “ነገን ደግሞ አሻግረው” መመልከት የማይችሉት በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙት እነ “….ማህበረ ተጋሩ…” የትግራይ ተወላጆች ከአማራ ክልል በግፍ እንደተባረሩና የቀሩትም ህይወታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ተደርጎ በየሚዲያው የመግለጫዎች ጋጋታ ሲያዥጎደጎድ፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም ሆን ቀሪው ዓለም በትዝብትና በግርምት እየተመለከተ ነው።
ህዝብን “የአይናችሁ ቀለም አላማረኝም” ብሎ በጥሩ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ ከ 77,000 በላይ ሰላማዊ ኤርትራውያን ተወልደው ካደጉበትና ካረጁበት ቀያቸው ያለአንዳች ማሰጠንቀቂያ ሲያባርርና ወደ ማያውቋት ኤርትራ መሄድን ፈርተው ለጊዜው አይናቸውን ከአይናቸው ዘወር ማድረግ የመረጡትን እንኳ ከተሸሸጉበት ጓዳ ድረስ እየገባና እያነቀ ወደ እርድ እንደሚነዳ እንስሳ እያስጓጎረና የደም እንባ እያስለቀሰ ባልና ሚስትን፣ እናትና ልጅን፣ እህትና ወንድምን የለያየውና እንዲባረሩ ያደረገው አምባገነኑና ዘረኛው ሟች መለስ ዜናዊና “ህወሃት” በሚባል የሽፍታ ድርጅት ውስጥ መሽገው ዛሬም ድረስ ህዝብን የሚያሸብሩና የሚዘርፉ የመንደር ልጆቹ እንጂ የአማራ ህዝብ አልነበረም።
ይልቁንስ ይህን አሳፋሪና ነውረኛ የህወሃት ድርጊት የተቃወመው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የጎንደርና የጎጃም ህዝብ ኤርትራውያን ወገኖቹን በጉኛው ደብቆ ለማስቀረት በሞከር ጊዜ የህወሃት ተባባሪና ፊታውራሪ በመሆን የተደበቁበት ጉራንጉር ድረስ እየጠቆመና እያሳደደ ለአውሬዎች አሳልፎ የሰጣቸው ማን እንደነበር በህይወት ያሉት ኤርትራውያን ዛሬም በቁጭት የሚመሰክሩት መራራ የታሪካቸው አካል ነው። በአንፃሩ ደግሞ ኤርትራውያን ወገኖቹን በግፍ ከመባረር በጉኛው ደብቆ ማስቀረት ባይችልም እንኳ የለበሰውን ጋቢና ነጠላ ከራሱ ገፎ ለወገኖቹ እያለበሰና እንባውን እያፈሰሰ የሸኛቸው እስላም ክርስትያኑ የጎንደር ህዝብ እንጂ ትግራውያን እንዳልነበሩ የኤርትራ ህዝብ ህያው ምስክር ነው።
ስለዚህ ህዝብን እንደ ህዝብ በጠላትነት በመፈረጅና በማሳደድ የሚታወቀውና የተካነው ህወሃት እንጂ የአማራ ህዝብ ይልቁንም የጎንደርና የጎጃም ህዝብ እንዳልሆነ በእርግጠኝነትና በኩራት የምንመሰክረው እውነት ነው። ህወሃት ሆይ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያንም ሆነ የዓለምን ህዝብ በዚህ መሰሉ ርካሽ መንገድ ማታለልና የአማራን ህዝብ መወንጀል አይቻልህምና ከድላችን ጎዳና ላይ ገለል በል!
ውንጀላ ቁ. 2 – “በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማፅዳት ወንጀል እየተፈጸመበት ነው” – የትግራይ ክልል መንግስት
ከታሪክ ማህደር – “የሃውዜን ጭፍጨፋና የህወሃት የፊልም ቀረፃ” – ከህወሃት የቅስቀሳ ፊልም ማህደር
ጨካኙ የህወህት አመራር ቡድናቸው በበርሃ ገና ዳዴ እያለ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ድንበሯን ለመቁረስ የማይተኛውን የሱዳን መንግስት እግር በመሳም ወደ ካርቱም ልኮ ያሰለጠናቸውንና በዘመናዊ የፊልም መቅረጫ መሳሪያዎች ያደራጃቸውን ባለሙያዎች ለቀረፃ አመቺ ቦታ ካስያዘ በኋላ ለደርጋማው የደርግ ደህንነት ክንፍ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ቅዳሜ ቀን ለገበያ የወጣን የሃውዜን ህዝብ በነብሰ ባላዎቹ የደርግ ጀቶች ያለርህራሄ ያስጨፈጨፈና ጭፍጨፋውንም ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንደ ሆሊውድ ፊልም በባለሙያ በጥንቃቄ ቀርፆ በማግስቱ በሱዳን ሚዲያዎች በኩል ለዓለም ገበያ (ህወሃቶች ለቅስቀሳ ይሉታል) እንዳቀረበና በዚህም በዋናነት የሃውዜንና ትግራይን ህዝብ ይልቁንም የዓለምን ሰላም ወዳድ ህዝብ እንዳጭበረበረና በእነዚህ ንፁሃን ወገኖቻችን ደም በተገኘ የሃያላን መንግስታት ቀጥተኛ ድግፍ ለስልጣን እንደበቃ የቡድኑ አባል የነበሩና ሂደቱንም በቅርብ የተከታተሉ የአይን እማኞች (ቀደምት የህወሃት አባላት) ለዓለም ህዝብ ማጋለጣቸው የቅርብ ጊዜ መሪር ትዝታ ነው።
“ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ ህዝብን በግፍ በማባረርና በማሳደድ የተካነው ህወሃት፤ ለስልጣኑ ሲል የታጋዮቹን ወላጆች ሳይቀር በአውሮፕላን የሚያስጨፈጭፈው ህወሃት፤ ዛሬ በኦሮሞና በአማራ ህዝብ አመፅ የማይቀረው ታሪካዊ የውርደት ሞት የተደገሰለትና መቀበሪያ ጉድጓዱ የተማሰለት ህወሃት፤ ለዘመናት የትግራይን ህዝብ በችግሩና በደስታው አብሮት ከኖረው የጎንደር ህዝብ በላይ ለትግራይ ህዝብ አዛኝና ተቆርቋሪ በመምሰል ዛሬም እንደ ትላንቱ የሃውዜን ድራማ ለመድገም ሲሯሯጥ ይታያል።
እውነታው ግን በየመስኩ ተሰግስገው የአማራን ህዝብ ሲዘርፉ፣ ሲሰልሉ፣ ሲያሳፍኑና፣ ሲያስገድሉ በነበሩ የህወሃት አባሎች ላይ የተቆጣ ህዝብ ዘርፈው ባከማቹት ንብረት ላይ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር የተደናገጠው ህወሃት እነዚህን በእኩይ ምግባራቸው የሚታወቁና በአማራ ህዝብ የተጠሉ ገዳይና አስገዳይ አባላቶቹን አሰልፎና በብዙ ግፊያና መጨናነቅ በቻርተርድ አውሮፕላን የሚያጓጉዝ በማስመሰል በውድ የፊልም ባለሙያዎች እያስቀረጸ “የትግራይን ህዝብ ከአማራ ጥቃት ለመታደግ ወደ ትግራይ እያጓጓዝኩ ነው” የሚል መፈክር አስይዞ በቀጥታ እይታ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በማሰራጨት ተጠምዶ እንደሰነበተ አይተናል።
ይሁን እንጂ የሃውዜን ድራማ ክፍል ሁለት የምዕራቡን ሃብታምና ሃያላን መንግስታት እንደ ክፍል አንዱ በማታለል ውጤት ማምጣት ሳይችል ቀርቷል። ይልቁንም በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋና አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞና ሂደቱን በቀጥታ ገብቶ በእራሱ ባለሙያዎች ሂደቱን ለማጣራት የኢትዮጵያን መንግስት በይፋ የጠየቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከህወሃት ፈቃድ መከልከሉ ድራማው ህወሃትን ምንያህል በዓለም ህዝብና መንግስታት ፊት እርቃኑን እንዳስቀረው አይተናል።
“ሲሉ ሰምታ . . . ” እንዲል አማራ
በእኩያን ተፀንሶ፣ በእኩያን ተወልዶ፣ በእኩያን ያደገውና፣ ዛሬም ድረስ በእኩያን የሚመራው እኩዩ ህወሃት በዓለም መንግስታት ፊት የከሸፈበትንና የተዋረደበትን “የትግራይን ህዝብ ከአማራ ጥቃት ለመታደግ ወደ ትግራይ እያጓጓዝኩ ነው” የምትለውን የአንድ ሰሞን ሴራ መልኳን ቀይሮ ዛሬ ደግሞ “በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማፅዳት ወንጀል” እየተፈጸመበት ነው በማለት “የትግራይ ክልል መንግስት” እያለ እራሱን የሚጠራው የወንበዴዎች ስብስብ በነሃሴ 29, 2008 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ www.tigraionline.com ባሰራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ 4060 የትግራይ ተወላጆች ወደ ትግራይ እንደተጓጓዘና ይህም በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል /Ethnic Cleansing/ እየተፈጸመበት መሆኑን ያሳያል ይለናል። አሳፋሪው የሃሰት መግለጫ በዚህ ሳያበቃ በአሁን ሰአት በአማራ ክልል በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ስለሚገኙ እነሱን በአስቸኳይ ከአደጋ መታደግ አለብኝ በማለት ቀጣይ የስልጣን ማራዘሚያ ክኒኑን አስተዋውቆናል።
ወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን በሃይል ከተቆጣጠረ ጀምሮ የአካባቢውን ተወላጅ አማሮች በማሳደድ፣ በማፈናቀልና፣ በመግደል ዘራቸውን ካፀዳ በኋላ በቦታውም ከ600,000 በላይ የትግራይ ተወላጆችን ያሰፈረው ህወሃት፤ ዛሬ ከዚህ ታሪካዊ የዘር ማፅዳት ወንጀል የተረፉት የወልቃይት ተወላጆች እራሳቸውን በማደራጀትና ወኪሎቻቸውን በመምረጥ “ትግሬ አይደለንም”፣ “ወደ ትግራይ ክልል ያለፈቃዳችን መካለላችን ተገቢ አይደለም”፣ “የአማራ ማንነታችን የከበርልን”ና፣ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል ሁሉ ጥያቄ ያቀረቡ “የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ” አቅራቢ የኮሚቴ አባላት እንደለመደው ለማፈንና ለመግደል ሲንቀሳቀስ በጀግናው የጎንደር ህዝብ የአጸፋ ምላሽ ተዋርዶ ለመመለስ የተገደደው አፋኙ ህወሃት በድርቅና ከገባበት የውርደት ማጥ ውስጥ መውጫ ሲያጣ “በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማፅዳት ወንጀል” ተፈፅሞበታል የምትል በ“እሳት ጨዋታ” ጀምሯል ።
ህወሃት የትግራይ ነፃ አውጭ ሆኖ ለ25 ዓመታት ሃገር በበላይነት እየመራ፤ ነፃ ባላወጣሁት ህዝብ ላይ “የዘር ማፅዳት ወንጀል” እየተፈፀመበት ነው ብሎ በህዝብ ላይ የሚያላግጥ መንግስት ምናልባትም ህወሃት በዓለማችን ታሪክ የመጀመሪያው ሳይሆን እንደማይቀር እንገምታለን።
በቅድሚያ ይህ ህወሃታዊ ቧልት ከማንም በላይ በትግራይ ህዝብ ላይ የተደረገ ቧልት እንደሆነ በፅኑ እናምናለን። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ በግለሰብ ደረጃ በህወሃት ችሮታ ከዳር እስከዳር እስከ አፍንጫው እንደታጠቀ እያወቀ፤ እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ክፍል ብቸኛና ያለማንም ተቀናቃኝ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ በድሎት እለት በእለት እየኖረ፤ ይልቁንም ህወሃት ሁሉም የሃገሪቱ መንግስታዊ ስልጣን በበላይነትና በብቸኝነት ተቆጣጥሮ በሚመራት ሃገር ውስጥ እየኖረ፤ ዘርህ በሃገሪቱ መንግስታዊ ስልጣን ውስጥ ምንም አይነት ውክልናም ሆነ ስልጣን በሌለውና ለአለፉት 25 ዓመታት በሃገሩ ላይ ባይተዋርና መፃተኛ የሆነው የአማራ ህዝብ ሊያጠፋህ ነው መባል በእርግጥም በትግራይ ህዝብ ላይ የተቀለደ የቧልቶች ሁሉ ቁንጮ ሆኖ አግኝተነዋል።
በመቀጠል ይህ ህወሃታዊ ማላገጥ በአማራ ህዝብ ላይ የተደረገ ማላገጥ እንደሆነ በእርግጠኝነት እንናገራለን። ምክንያቱም የአማራ ህዝብ የራሱ ዘር የሆነው የወልቃይት ጠገዴ፣ የጠለምት፣ የአላማጣ፣ የኮረምና፣ የራያ ህዝብ ያላባቱ ትግሬነህ ተብሎ ወደ ትግራይ ክልል ሲካለልና ልጆቹ ለ25 ዓመታት በትግርኛ ብቻ እንዲማሩና የትግሬን ባህልና ወግ ብቻ እንዲቀበሉ ሲፈረድባቸው፤ ይልቁንም ሴት ልጆቹ በግዳጅ በትግሬ ጎረምሳ እየተደፈሩ የትግሬ ልጅ እንዲታቀፉ ሲደረጉ፤ በወቅቱ ከዚህ ቅስም ሰባሪ የዘር ጥቃት ልጆቹን መታደግ አቅቶትና አቅመ ቢስ በመሆን ምንም ማድረግ ሳይችል የቀረን ህዝብና ዛሬ መከራውና ግፉ ሲበዛበት ፍትህን እሻለሁ ባለ “የትግሬን ዘር ልታጠፋነው” በማለት “በዘር ማፅዳት” ወንጀል መክሰስ የአማራ ህዝብ በእጅጉ እንደመስደብና በቁስሉም ሽንቁር ላይ እንጨት እየሰደዱ እንደማላገጥ እንቆጥረዋለን።
እልፍ ሲልም ይህን የህወሃት ታሪካዊ ድራማ በጭቆና ውስጥ ሆኖ የሚታዘበው የኢትዮጵያን ህዝብ በእጅጉ እንደመናቅ የሚቆጠር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ዳር እስከዳር በህዝባዊ አመፅ ሃገሪቱን እየናጣት ባለበት በዚህ ቀውጢ ሰአትና ይልቁንም የሃገሪቱን መንግስታዊ ስልጣን ይዣለሁ የሚለውና የህወሃት እንዳሻው የሚዘውረው አሻንጉሊቱ ኢህአዴግ አንዴ “በስብሻለሁ” ሌላ ጊዜ “እየታደስኩነኝ” ሲያሻው “የአንድ ወር ጊዜ ይሰጠኝ” እያለ ጠራርጎ ሊውጠው ከመጣው የህዝብ ቁጣ ለማምለጥ ሰማይን እየቧጠጠ በሚገኝበት በዚህ ታሪካዊ የአብዮት ዋዜማ “የትግራይ ህዝብ በአማራ ህዝብ የዘር ማጽዳት ተፈፅሞበታል” እያሉ በማፌዝ የህዝብን ቁጣ ለማባባስና ይበልጥ ለማቀጣጠል መትጋት ህወሃት ያመጣው ጦስ ውስጥ ገብተው መውጫው ጠፍቷቸው ለሚዳክሩት “ኢህአዴግ” የሚባሉ አሻንጉሊቶቹ ያለውን ንቀት ከማሳየትና የህዝባዊ መንግስት ምስረታን ለጠየቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመናቅ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
በአጠቃላይ ድርጅታችን ልሳነግፉዓን ለአለፉት 19 ዓመታት የታገለለትን የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ ከህወሃት የዘር ማፅዳትና በትግሪያዊነት የመተካት ወንጀል ለመታደግና ከህወሃት የተስፋፊነት ጥቃት ለማዳን ያደረጋቸውን ተጋድሎዎች በመገምገም፤ በቆራጥና ጀግኖች ልጆቻችን ብርቱ ተጋድሎ “የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ” የድል ችቦ እስከ ተቀጣጠለበት እለት ድረስ ህዝባዊ ትግሉ የደረሰበትን ተጨባጭ የእድገት ደረጃ በመመዘን፤ ይልቁንም የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ያነሳውን ስርነቀል የለውጥ ጥያቄና በህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ላይ ባነሳው የአንገዛም ባይነት ህዝባዊ እምቢተኝነት በመነሳት፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ዳር እስከዳር ከሚያነሳው የዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ መንግስት ምስረታ ጥያቄ በመመርኮዝ የሚከተለውን ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
1ኛ. የወልቃይት ህዝብ “የአማራ ማንነቱን” የማስከበር ጥያቄ ከወልቃይት ህዝብ እጅ በክብር ለጎንደር ህዝብ ያቀበለ ሲሆን፣ የህዝባችን የዘመናት ጥያቄ የጎንደር ህዝብ ጥያቄ የመሆን እድገቱን ጨርሶ የመላው አማራ ህዝብ ጥያቄ ሆኗል። ስለዚህ የወልቃይት ህዝብ ወደ ጎንደር የመካለልና የአማራ ህዝብ አካል የመሆን ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው። የህዝባችን ጥያቄም የጊዜ ጉዳይ እንጂ የአማራ ህዝብ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን በመቻሉ ትልቁንና አስተማማኙን መልስ ከአማራ ህዝብ አግኝቷል። ስለዚህ ህወሃት መራሹ መንግስት ወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን ተጨማሪ ደም ሳይፈስ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ አማራ ክልል በክበር እንዲመልሱ አበክረን እንጠይቃልን!
2ኛ. ህወሃት የትግራይን ህዝብ በመያዣነት በመጠቀም “የስልጣን እድሜየን ማራዘም” የሚለው ያረጀ ሴራ ትልቅ ኪሳራ ላይ ነው። ህዝባዊ እንቢተኝነቱ ተጨማሪ ጊዜ ባገኘ ቁጥር የትግራይ ህዝብ ከህወሃት እየተነጠለና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን የመቆም እድሉን እያሰፋው ስለሚሄድ ህወሃት መራሹ መንግስት ለህዝብ ጥያቄ መልስ ያለመስጠቱን ግትርነትና ድንቁርና እየገፋበት በሄደ ቁጥር የተቃውሞ ጎራው እየሰፋ እንደሚሄድ እንረዳለን። በዚህም ድል እንደምንጎናፀፍ ጥርጥር የለንም። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ሆይ! የትግሉ መራዘም ጥቅሙ ለአንተ ነውና የተገኘውን እድል ሳታበላሽ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን በህወሃት ፋሽስትና ተስፋፊ ቡድን ላይ ተነስ!
3ኛ. ኢህአዴግ የተባለው የህወሃት አሻንጉሊት ስብስብ የወልቃይትን ህዝብ ጥያቄ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የህዝብ ወኪል የሆኑ “የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ አቀራቢ” ኮሚቴ መሪዎችና አባላትን ጭምር በትግራይ የማሰቃያ ጉድጓዶች፣ በማእካላዊ፣ በጎንደርና … ወዘተ የማሰቃያ እስር ቤቶች አፍኖ እያሰቃየ “ጥያቄያችሁን ለትግራይ ክልል መንግስት አቅርቡና በዚያ መልስ ታገኛላችሁ” ማለት አንድም ህዝብን መናቅ አልያም ከጥጋብ የሚመነጭ መታበይ እንደሆነ እንረዳለን። ስለዚህ የከፋው ጊዜ ሳይመጣ በየቦታው ያሰራችኋቸውንና አድራሻቸውን ሰውራችሁ የምታሰቃዩቸውን የህዝብ ልጆች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ዛሬውኑ ልቀቁ!
4ኛ. አስተዳድረዋለሁ በሚለው ህዝብ ላይ ጦርነት ያወጀ መንግስት በምንም የቅድስና ህይወት ውስጥ ቢያልፍ የህዝቡን ልብ ማሸነፍ እንደማይችል በእርግጠኝነት ለመናገር ኢትዮጵያዊ መሆን በቂ ነው። ወደ ህዝብ የተኮሰ መንግስት ውድቀቱን እንደሚያፋጥን ደግሞ የሟች ሃየሎም አርአያን ፎቶግራፍ ግርጌ የፃፋችሁትን ዘወር ብላችሁ ማንበብ ነው። ስለዚህ በጠለቀው ጀምበራችሁ ላይ ጨርሶ ሳይጨልም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለህዝባዊ መንግስት ምስረታ ሁኔታውን ለሚያመቻች ከህዝብ ለተወጣጣ ጊዜያዊ ባለአደራ መንግስት ስልጣናችሁን እንድታስረክቡ አበክረን እንጠይቃልን!
5ኛ. በህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ የተጠራውን ብሄራዊ የሃዘን ሳምንት፣ ሃገራዊ እርቅም ሆነ የህዝባዊ መንግስት ምስረታ እንዲሁም በመግለጫው ውስጥ የተካተቱትን መልዕክቶችና ተግባራዊ እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ የምንቀበለው መሆኑንና ለተግባራዊነቱም አቅማችን በፈቀደው ሁሉ የምንሳተፍ መሆኑን መግለፅ እንወዳለን። አባላቶቻችንና፣ ደጋፊዎቻችንና፣ መላው የሃገራችን ህዝብ ለሲኖዶሱ ጥሪ በጎ ምላሽ እንዲሰጡ አበክረን እንጠይቃለን። የሌሎችም እምነቶች አባቶች ከህዝብ ጎን በመቆም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን!
6ኛ. በቂሊንጦ እስር ቤት ህወሃት ሆን ብሎ ባስነሳው ቃጠሎ 23 እስረኞች መግደሉን በጀብደኝነት ነግሮናል። በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ፈሪው ህወሃት ደፍሮ አንድም ጀግና ላይ እንደማይተኩስ እናውቃለን። ይሁን እንጂ የሟቾቹ ማንነት ባለመገለጹ ምክንያት የሁሉም እስረኞች ቤተሰቦችና መላው ህዝባችን በከፍተኛ ሃዘንና ጭንቀት ውስጥ ወድቋል። ይህ እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ አላማው የህዝብን አመፅ አቅጣጫ ለማስቀየር የተደረገ የእኩዩ ህወሃት ሴራ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ለአፍታም ሳንዘናጋ ህወሃትን የማስወገድ ትግሉን አጥናክረን በመቀጠል ይህን በወገኖቻችን ህይወትና በወላጆች ሰቆቃ ላይ የሚያላግጥ ጭራቅ ታሪክ እንድናደርገው እናሳስባለን!
7ኛ. በመጨረሻም ከላይ ከተራ ቁ. 1 – 4 በዝርዝር ያስቀመጥናቸው ቅድመ ሁኔታዎች በአፋጣኝ ተግባር ላይ ባለመዋላቸው ለሚደርሰው ሃገራዊ ቀውስ ተጠያቂው ህወሃትና በህወሃት ዙሪያ ተከማችታችሁ ንጽሃን የምትገሉና የምታስገድሉ፣ ሃገር የምትዘርፉና የምታዘርፉ “….ማህበረ ተጋሩ…” ና “አይጋ ፎረም”ን መሰል ተቋማት መሆናችሁን በአንክሮ ማሳሰብ እንወዳለን።
ህዝብ ሁሌም ያሸንፋል!
ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
ጳጉሜ 1, 2008