Wednesday, 07 September 2016 13:52
 –    በጉዳዩ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት ተወካዮችና የአፍሪካ ህብረት

ውይይት አካሂደዋል

 

የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ያልተመጣጠነ ኃይል መጠቀሙን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ገለፁ። ዘገባውን ያሰራጨው አሶሼትድ ፕሬስ እንዳመለከተው ከሆነ በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ መንግስት በሰልፈኞች ላይ ያልተመጣጠነ ኃይልን የመጠቀሙ ጉዳይ ሀገራቸውን ያሳሰባት መሆኑን አመልክተዋል። እንደዘገባው ከሆነ አምባሳደሯ፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ጉዳዩ ገለልተኛ በሆነ አካል በግልፅነት ሊጣራ ይገባዋል በማለት አሳስበዋል። ሀገራቸውም ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ሰልፍ ማካሄድ እንዲችሉ መንግስት እንዲፈቅድ የኢትዮጵያን መንግስት የጠየቀች መሆኗን አምባሳደሯ ጨምረው የገለፁ መሆኑን ይኸው ዘገባ አመልክቷል።

ከሰሞኑ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተወካዮች ከደቡብ ሱዳን የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በዚያው በደቡብ ሱዳን ቆይታ ያደረጉ ሲሆን፤ በዚሁም በኢትዮጵያ ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ለመወያየት ወደ አዲስ አበባ ያመሩ መሆኑን የአሶሼትድ ዘገባ ጨምሮ አመልክቷል። አምባሳደሯም ይህንኑ ማብራሪያ የሰጡት ልዑካን ቡድኑ የደቡብ ሱዳን ጉብኝቱን አጠናቆ የመጨረሻውን ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠ በነበረበት ወቅት ነው።

ዘገባው የአፍሪካ ህብረትም ጉዳዩ ያሳሰበው መሆኑን ከሳምንት በፊት የገለፀ መሆኑን አስታውሷል። የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተወካዮችና የአፍሪካ ህብረት የተወያዩበትን ጭብጥ በተመለከተ ግን እስከ አሁን ይፋ የሆነ መረጃ የለም።

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተወካዮች በደቡብ ሱዳን የሶስት ቀን ቆይታ በማድረግ ባለፈው እሁድ ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል። የጉብኝቱም ዋነኛ ዓላማ በደቡብ ሱዳን አለም አቀፍ ሠላም አስከባሪ ኃይል ከሚጠናከርበት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ነው።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በመንግሥት በኩል በቂ የሆነ ምላሽ ባለመሰጠቱ ቅር የተሰኙ ወገኖች እንደቀሰቀሱት የሚገመተው ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻውን ጎንደር አድርጎ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች መስፋፋቱን፣ ይህንን አመፅ ለመቆጣጠርም የፀጥታ ኃይላት በወሰዱት እርምጃ ንፁሃን ዜጎች ለሞትና ለጉዳት መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው። በተመሣሣይ ሁኔታ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የጋራ ማስተር ፕላን የቀሰቀሰው ተቃውሞ በኦሮሚያ ክልል ከአስር ወራት በላይ የተራዘመ ሕዝባዊ ተቃውሞን ማስከተሉ አይዘነጋም።

Leave a Reply