ጳጉሜን 2፣ 2008 ዓ. ም
ወያኔወች በተቃዋሚወች መካካል “ያሰረጓቸው” የኦህዲድ ሰወችና የወያኔ የጥገና ለውጥ ዕቅድ [አበራ ቱጂ]
ባለፈው ጽሁፌ ወያኔወች በተለያየ መንገድ ራሳቸው ያሰለጠኗቸውን ሰወች ለውጥ በሚፈልገው የኦሮሞ ህዝብ መሃል በማስረግ የህዝቡን ጥያቄ ግብ እንዳይመታ በተለያየ መንገድ ህዝቡን ለመከፋፈል እንደሚጥሩ ለማሳየት ሞክሪያለሁ። ወያኔወች ከምንም
ነገር በላይ የሚፈሩት የህዝቡን አንድነት ነው። በአንድነት የቆመ ህዝብ አሸናፊ መሆኑን የተገነዘቡት ህውሃቶች ሁሉንም አይነት የመከፋፈያ ዘዴ ይጠቀማሉ
አሁን የወያኔን ዕቅድ ቀድሞ በመግለጽ የሚታወቀው አይጋ ፎረም እንደገለጸልን፣ ወያኔወች ኦሮምኛን ሁለተኛ የስራ ቋንቋ በማድረግና ለኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም እንዲኖረው በማለት የማታላያ ሃሳብ በማቅረብ በተለመደው የከፋፍሎ መምታት ዘዴያቸው የህዝቡን ትግል ለማጨፍለቅ ሌት ተቀን እየሰሩ ነው።
ይህ የቀረበ ሃሳብ ብዙ ሰው የሚደግፈው ቢሆንም፣ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት፣ ወያኔ ሊያቀርብ ያሰበው ይህ የጥገና ለውጥ ሃሳብ ምንነት ሳይሆን፣ ይህ ሃሳብ በማን ተጠየቀ? መቼ? ለምን? ለምን ዓላማ? የሚለው ነው።
ይህን ጥያቄ ያነሱት ወያኔን ተቃዋሚ መስለው የቀረቡና ካለፈው ህዳር ጀምሮ በተለያየ የመገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ገጽ ሃሳባቸውን ሲገልጹን የነበሩ ሁለት ቀድሞ ከወያኔ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጋር በቅርብ ሲስሩ የነበሩ ግለሰቦችን ማንነት ማወቅ ይገባል። አንደኛው ዶ/ር (?) ብርሃነመስቀል አበበ ሰኚ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ ይባላሉ።
ዶ/ር ብርሃነመስቀል አበበ ሰኚ በወያኔ ተሹሞ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጲያ ኢምባሲ ተመድቦ ሲያገለግል የነበረ ዲፕሎማት ሲሆን፣ አሁን የወያኔ ተቃዋሚ መስሎ በመቅረብ ኦሮምኛ ኦፊሻል ቋንቋ መሆን አለበት ብሎ በድህረ ገጽ ዘመቻ ሲያደርግ የነበር ነው። ዶ/ር ፀጋዬ ደግሞ ወያኔወች ባለስልጣኖቻቸውንና ከፍተኛ ካድሬወቻቸውን ለማስልጠን በአቋቋሙት ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የነበረና የወያኔ ከፍተኛ ባለስልጣኖችን ሲያሰለጥን የነበረ ነው። ዶ/ር ፀጋዬ ለኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም እንዲኖረው የሚለውን ሃሳብ በተለያየ የመገናኛ ብዙሃን ሲገልጽ የነበረ ነው።
ኦሮምኛ ተጨማሪ የፈደራል ወይም የስራ ቋንቋ ቢሆን የአገራችንን አንድነትና የህዝብ መግባባትና መተሳሰር ያጠነክራል እንጂ ጉዳት የለውም። አማርኛ ተናጋሪው ኦሮምኛ ቢማር፣ ኦሮምኛ ተናጋሪው አማርኛ ቢማር አገራችን የበለጥ ትጠቀማለች ህዝባችን የበለጠ ይተሳሰራል ባህላችንም ይዳብራል። ወያኔ ግን እስከአሁን የሰራው ህዝብን የሚያቀራርብ ሳይሆን፣ ህዝብን የሚለያይ የዘር ጥላቻ ስራ ብቻ ነው። እንደዚሁም ለኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም እንዲኖረው የተነሳው ጉዳይ ባግባቡ ታስቦበትና ህዝብ ተውያይቶበት መፍትሄ የሚፈለግለት ጥያቄ ነው።
ወያኔወች አሁን ይህን ጉዳይ በዚህ በተወጠሩበት ወቅት እንደማታለያ፣ ከፋፍሎ የመምቻና፣ ስልጣናቸው ላይ ለመቆያ ዘዴ መጠቀማቸው፣ ከዳር እስከዳር የተነሳባቸውን የህዝብ አንድነት አመጽ አያበርደውም። የኦሮሞና የአማራ ህዝብ እንደማይለያይና በጋራ ተነስቶ ወያኔን እንደሚታገል በዚህ ፈታኝ ወቅት በህይወቱ ዋጋ እየከፈለ አስመስክሯል። የወያኔ የሃያ አምስት ዓመታት የዘር ጥላቻ ዘመቻ አልሰራም። አሁንም ለነጻነት የሚታገሉ ኢትዮጲያዊያን፣ በይበልጥ የአማራና የኦሮም ህዝብ፣ በዚህ አይነት መሰሪና ከፋፋይ ዘዴ ሳይታለሉ፣ በአንድ ላይ ተያይዘው ይህን ዘረኛና ጨካኝ የወያኔ አገዛዝ ማስወገድ አለበቸው።
ወያኔ የሚፈጽመው ግፍና ሰቆቃ ገደብ የለውም። በደምቢ ዶሎ እንደፈጸሙት፣ ወጣትን ልጅ ገድሎ የተገደለውን ወጣት እናት ከልጃቸው አስከሬን ላይ እንዲቀመጡ የሚያስገዲዱ አረመኔወች ናቸው። እስረኞችን በእሳት አቃጥሎ የሟቾችን አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መስጠት ያልፈለገ ቤተሰቦቻቸውን የደበደበ ያሰረ ስይጣናዊ ስራ የሚሰራ መንግስት ነው። በኦሮሚያና አማራ አካባቢ በግፍ እየተጨፈጨፈ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለውን ወጣት የምንዘከረው፣ ይህን ለሃያ አምስት ዓመታት ከፈፍሎና ረግጦ የገዛንን ጨካኝ የወያኔ አገዛዝ ባንድ ላይ ቆመን አሽቅንጥረን ስንጥል ነው። የሚፈሰው ደም የሁላችንም ደም ነው። በወያኔ የጊዜ መግዣና የጥገና ለውጥ እንዳንታለል። ከላይ የተገለጹት ግለሰቦች በእውነት በግፍ ለሚፈጀው ኢትዮጲያው የሚቆሙ ከሆነ አቋማቸውን ግልጽ አድርገው ማሳወቅ አለባቸው። በኢትዮጲያ አሁን ያለው ስርወ ችግር ህዉሃት ወያኔ የፈጠረው ህግ አልባ ዘረኛና ብልሹ ስርዓት ነው። የሰወች መቀያየር የትንንሽ የህዝብ ሃብት ሌቦችን ማሰር ወይንም ጥቃቅን የፖሊሲ ለውጥ ማምጣት፣ የወያኔን እድሜ ያራዝማል እንጂ ስርወ ችግሩን አይፈታውም። ችግሩ ከስር መሰረቱ የሚፈታው ዘረኛው ወያኔ ተውግዶ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ስልጣን ሲይዝና የህግ የበላይነት በኢትዮጲያ ሲኖር ነው። አሁንም ያለን አመራጭ በዘር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳንለያይ በአንድ ላይ ቆመን መታገል ነው። ምንም የጥገና ለውጥ ስርወ ችግሩን ከማስወገድ ሊያግደን አይገባም።
አንድነት ሃይል ነው!
አበራ ቱጂ
SOURCE – SATENAW