September 8, 2016
(ኢ.ኤም.ኤፍ) ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ሃሳቡን በነጻነት ስለገለጸ “አሸባሪ” ተብሎ በዝዋይ እስር ቤት ውስጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው። ዛሬ ቤተሰቦቹ ተመስገንን ለመጠየቅ ዝዋይ እስር ቤት ቢሄዱም፤ ሊያገኙት አልቻሉም። ታሪኩ ደሳለኝ፤ የጋዜጠኛ ተመስገን ወንድ እንዲህ በማለት ስለሁኔታው ገልጿል።
“ዛሬ ጳጉሜ 3/08 ዝዋይ እስር ቤት ብንገኝም፤ ተመስገን ከዚህ በፊት የነበረበት ደቡብ ክልል ተብሎ የሚታወቀው ቦታ የለም ብለውናል፤ በአሁን ሰዓት የእስር ቤቱ ተረኛ መኮንን ‘ተመስገን እዚህ አለ፤ ግን እዚህ የት እንዳለ አናውቅም።’ የሚል መልስ ሰጥቶናል፡፡
“ ከ3 ቀናት በፊት ተመስገንን ስናገኘው በዚህ 2 ወር ውስጥ አድርገውት በማያውቁት መልኩ በወታደር ተከቦ ነበር የመጣው። ከዛም ለ10 ደቂቃ ብቻ እንድናናግረው ፈቅደው፤ እሱም ወደ እስር ቤቱ፤ እኛም ወደ ቤታችን በስጋት ተመልሰን፡፡ ዛሬ ደግሞ እዚህ አለ ግን የት እንዳለ አናውቅም ብለውን የዝዋይ እሰር ቤት ግቢ በር ላይ በጭንቀት ቆመናል፡፡” በማለት የጋዜጠኛ ተመስገንን ጉዳይ አብራርቷል።
አሁን መንግስት ተሎ ስልጣን ላይ የተቀመጠው አካል፤ ተቃዋሚ የሆኑ ሰላማዊ ሰዎችን፤ “አሸባሪ” በሚል ሰበብ ማሰሩ ሳያንስ፤ እስር ቤት ድረስ በመሄድ የማዋከብ እና የመደብደብ ስራ እየሰራ ነው። በቅርቡ እንዳየነውም በቅሊንጦ እስር ቤት በመገኘት እስረኞችን በመረሸን እና እስር ቤቱን በማቃጠል፤ በደርግም ሆነ በፋሽስት ጣሊያን ዘመን ታይቶ የማይታወቅ ግፍ እየፈጸመ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም… ይህንኑም ድርጊት አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች፣ የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪቃ አንድነት እና አሜሪካ ያወገዙት መሆኑ ይታወቃል።