September 8, 2016
(ኢ.ኤም.ኤፍ – የዳዊት ከበደ ወየሳ አጭር ዘገባ) በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር 2ኛ የወጣው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፤ በአሜሪካ መንግስት ተቀባይነት በማግኘት ወደ አሜሪካ የሚገባበት ቪዛ ተሰጥቶታል። ምሽቱን ዘግይቶ የደረሰን ዜና እንዳመለከተው ደግሞ፤ አሁን አሜሪካ የሚገኝ መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮች በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ ገልጸዋል።
አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የሪዮ ኦሎምፒክን 2ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ ሁለት እጆቹን አቀናጅቶ፤ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን በመንግስት ድጋፍ የሚደረገውን ጥቁር ሽብር ማውገዙ ይታወሳል። አትሌቱ በዚህ የጀግና ስራው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ አክብሮትን ተቀዳጅቷል። ሌሎች አትሌቶች የሩጫ ውድድር ሲያሸንፉ በተመሳሳይ መልኩ እጃቸውን በማቀናጀት ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረዋል።
ለአትሌት ፈይሳ… ግጥሞች ተጽፈውለታል። በቅኔ ተወድሷል፤ ዘፈን ተዘፍኖለታል። ሲ.ኤን.ኤን እና ቢቢሲን ጨምሮ የአለም ታላላቅ የዜና አውታሮች፤ እጁን ያቀናጀበትን ምክንያት በመዘርዘራቸው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ለማጋለጥ ልዩ ምክንያት ሆኗል።በአጭሩ… ኢትዮጵያውያን ለ25 አመታት የጮሁለትን እውነት፤ የ25 አመቱ ወጣት አትሌት… 25 ደቂቃ ባልሞላ ግዜ ውስጥ የ25ቱን ግፍ አለም እንዲያውቀው አድርጎታል።
አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፤ ቤተሰቡን ኢትዮጵያ ትቶ ትልቅ መስዋዕትነት በመክፈል ለፈጸመው አኩሪ ተግባር እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን ሲገልጹ፤ የኢህአዴግ ደጋፊዎች በድርጊቱ ተቆጭተው፤ “ሜዳሊያውን መቀማት አለበት” እስከማለት ደርሰው ነበር። ያሰቡት ግን አልተሳካም። ይልቁንም የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የብር ሜዳልያ ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ለወደቁት እና ለሚሞቱት ዜጎች ዘላለማዊ መታሰቢያ ሆኗል። ሌላም ነገር እንጨምር። በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፤ 2ሺህ 852 ሰዎች በ18 ቀናት ውስጥ ከ160 ሺህ ዶላር በላይ በኢንተርኔት መዋጮ አድርገውለታል።
በዚህ የኦሎምፒክ ማራቶን ውድድር የአሜሪካ አትሌት ጌለን ራፕ 3ኛ መውጣቱ ይታወቃል። ይህም በዚህ ክፍለ ዘመን 5ኛው የማራቶን ሜዳሊያ ነው – ለአሜሪካ። በቀጣይ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ለአሜሪካ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን እንደሚሮጥ ይጠበቃል። በሚቀጥለው የኦሎምፒክ ማራቶን ካሸነፈ ደግሞ ለአሜሪካ የክፍለዘመኑ 6ኛውን ሜዳሊያ ያስገኛል ማለት ነው።
አዲሱን ቪዲዮ
በመጨረሻም ለፈይሳ ሌሊሳ መታሰቢያ የተዘጋጀ አዲስ ነጠላ ቪዲዮ ተለቋል። የግጥሙን ድርሰት ያዘጋጀው የአትላንታው ንጉሤ ስመወርቅ ነው። ድምጻዊ መስፍን የተሻ ጥሩ አድርጎ ተጫውቶታል። የሙዚቃ ቅንብሩን ደግሞ ታዋቂው ሄኖክ ነጋሽ ነው የሰራው። በቅርብ ያገኘነውን በዘፈን ግጥሞቹ ታዋቂ የሆነውን ንጉሤ ስመወርቅን ነው። “ይህን ግጥም ለመጻፍ ምን አነሳሳህ?” የሚል ጥያቄ አቅርበንለት፤ ጠቅለል አድርጎ እንዲህ በማለት ምላሽ ሰጥቶናል።
“ግጥሙን የጻፍኩት የማራቶን ውድድሩን ያየሁ እለት ነው። በደስታ ተውጬ ነው የጻፍኩት። የሁላችንንም ጩኸት፤ የህዝቡንም ለቅሶ፤ እጁን ከፍ አድርጎ በማጣመር ለአለም ህዝብ ትርጉም የሚሰጥ መልዕክት አስተላልፏል። ይህ ልዩ ደስታ የሚሰጥ ነው። እናም ግጥሙን ከጻፍኩት በኋላ፤ ለጓደኛዬ ለድምጻዊ መስፍን የተሻ እንዲዲጫወተው ሰጠሁት። ቀጣዩ ስራ የሙዚቃ ቅንብሩ ነው። ሄኖክ ነጋሽ ባለው የተጣበበ ግዜ፤ ዜማውን አዘጋጅቶ ሙዚቃውን አቀናብሮታል።
“ስራው ካለቀ በኋላ ብዙ ሰዎች ስራውን እንደወደዱት ገልጸውልኛል። ከኔ የበለጠ ግን ሌሎቹ ብዙ ግዜ ወስደው ስለሰሩት ሁሉም ሊመሰገኑ ይገባል።” በማለት ሃሳቡን በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ ገልጾልናል።
ገጣሚ ንጉሤ ስመወርቅ በብዙ ስራዎቹ የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይም በምርጫ 97 ወቅት… “የሩዋንዳን ታሪክ አንደግመውም እኛ” በሚለው ስራ እጅጉን ይታወቃል።