
2008 ዓ.ም. በገባ በሦስተኛው ወር በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ እየተቀጣጠለ በርካታ የክልሉን አካባቢዎች አዳረሰ፡፡ በተለያዩ የክልሉ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች በሰላማዊ መንገድ የተጀመረው ተቃውሞ መልኩን በመቀየር ወደ ደም መፋሰስ፣ የበርካታ ነዋሪዎችንና የፀጥታ ኃይሎችን ሕይወት እስከ መቅጠፍ ተሸጋገረ፡፡ በተመሳሳይ ወቅት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ለዓመታት ሲንከባለል በቆየው የቅማንት ብሔረሰብ የማንነት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ማጣት ከሰላማዊ መንገድ እንዲወጣ በመገደዱ፣ ደም አፋሳሽ ግጭትን አስከተለ፡፡ የበርካቶችንም ሕይወት ቀጠፈ፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሱት የሕዝብ ጥያቄዎች ለተወሰኑ ወራት ጋብ ያሉ ቢመስልም ተዳፍነው ሲግሉ ቆይተው መልካቸውን ቀይረው በድጋሚ ገነፈሉ፡፡ በኦሮሚያ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ ፖለቲካዊ ይዘትን ተላበሰ፡፡ በትግራይ ክልል በወልቃይት ማንነት ጋር የተገናኘ የወሰን ጥያቄ፣ በተለያዩ ተፅዕኖዎች ከትግራይ ክልል ተገፍቶ ወጥቶ በሰሜን ጎንደር በመክተም ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ማቅረቡን ቀጠለ፡፡ በአዲስ አበባ አዲስ የትራፊክ ሥነ ሥርዓት ደንብ ፀድቆ ወደ ተግባር መግባቱና ደንቡ የያዛቸው ተደራራቢና ጥብቅ ቅጣቶችን በመቃወም የታክሲ አሽከርካሪዎች የአንድ ቀን የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ በመንግሥት ላይ ጫናቸውን አሳረፉ፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሱት ተቃውሞዎች ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ይዘትን ተላብሰው መንግሥትና ገዥው ፓርቲን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በግራ መጋባት ውስጥ እየተቀበሉት ይገኛሉ፡፡ ተቃውሞ ወደ ገነፈለበትና በአገሪቱ በስፋት የተስፋፋበትን የ2008 ዓ.ም. ሕዝባዊ የተቃውሞ ክስተቶችን ዮሐንስ አንበርብር እንደሚከተለው ቃኝቷቸዋል፡፡
ቅድመ 2008 ዓ.ም.
በ2007 ዓ.ም. በኅዳር ወር ውስጥ የአዲስ አበባና የዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ለውይይት ይፋ መሆኑን ተከትሎ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ማስተር ፕላኑን በመቃወም የጀመሩት እንቅስቃሴ ወደ ኅብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ እንደገባ ይታወሳል፡፡ ለተወሰኑ ወራት የቀጠለው ተቃውሞ በፀጥታ ኃይሎች በአጭሩ ለመግታት በመቻሉ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ዕፎይታን አገኙ፡፡ የተቃውሞው መነሻ የሆነው የአዲስ አበባና የዙሪያው የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን የአዲስ አበባ ይዞታ ወደ ኦሮሚያ ክልል ድንበሮች ለማስፋፋት ያቀደ ነው የሚለው የተማሪዎችና የክልሉ ነዋሪዎች ተቃውሞ፣ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ውስጥ ቢወድቅም ጥያቄው ግን ሙሉ ምላሽን ወይም መግባባትን አላገኘም፡፡
በዚህ ጊዜያዊ መረጋጋት ፋታ ያገኙት ገዥው ፓርቲና መንግሥት አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. ውስጥ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲካሄድ አስቻላቸው፡፡ በውጤቱም ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላለፉት ዓመታት የመንግሥትን ሥልጣን ከያዘበት ውጤት የተለየና መነጋገሪያ ያደረገውን መቶ በመቶ ውጤት ማግኘቱ ይፋ ሆነ፡፡ ገዥው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች በሙሉ ማሸነፋቸው በአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ይፋ ሆነ፡፡
ገዥው ፓርቲ በውጤቱ ግራ የተጋባ ቢመስልም የሕዝብ ፍላጎት የተገለጸበት ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ በመቀበል አሥረኛውን አጠቃላይ ጉባዔውን በመቀሌ ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ የዚህ ጉባዔ ዋነኛ ማጠንጠኛም መልካም አስተዳደርን በማስፈን ሕዝቡ ለፓርቲው ያሸከመውን ትልቅ ኃላፊነት መወጣት ትልቁና ቀዳሚው ዕርምጃ መሆኑን ፓርቲው ይፋ አደረገ፡፡
2008 ዓ.ም.
ኢትዮጵያውያን 2008 ዓ.ም. በተቀበሉበት በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት፣ ኢሕአዴግና አጋሮቹ በፓርላማው 547 ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን የሚመራውን መንግሥት መሠረቱ፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን እንዲያስተዳድሩ በድጋሚ ተሾሙ፡፡
በጥቅምት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ የመንግሥትን የ2008 ዓ.ም. ዕቅድ ለመግለጽ በፓርላማ ተገኝተው የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ የዓመቱ ቁልፍ ተግባር እንደሚሆን አወጁ፡፡
ይህ የመልካም አስተዳደር አገር አቀፍ ንቅናቄ ከውጥን አልፎ መሬት ከመንካቱ በፊት፣ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. የኦሮሚያ ተቃውሞ በድጋሚ ፈነዳ፡፡
በምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ ከተማ የምትገኝ አንድ ትምህርት ቤት ይዞታ ያለ አግባብ ለባሀብት ተሰጠ በሚል በተማሪዎች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ የተዳፈነውን ‹‹የአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ መስፋፋት›› ጉዳይ በድጋሚ እንዲቀጣጠል አደረገ፡፡ ተቃውሞው ከሰላማዊ መንገድ በመውጣት ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የንግድ ተቋማትንና የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ወደማውደም ተሸጋገረ፡፡ በርካታ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት መዋቅር ቢሮዎች በተቃዋሚዎቹ እንዲወድሙ ተደረገ፡፡
በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ከሰላማዊ መንገድ እንዲወጣ ያደረገው መንግሥት ለሕዝቡ ጥያቄ ወቅታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ ነው የሚል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ትችታቸውን በስፋት ሰነዘሩ፡፡
ተቃውሞው ወደ ግጭት ተቀይሮ የበርካቶችን ሕይወት ከቀጠፈ በኋላ፣ የኦሮሚያ ክልል የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን በሕዝብ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አሳወቀ፡፡
መንግሥት በራሱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በግጭቱ የሞቱን ሰዎች በአጠቃላይ 173 መሆናቸውን ቢገልጽም፣ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ሒውማን ራይትስ ዎች በኦሮሚያ ግጭት ከ400 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄን የክልሉ መንግሥት በፍጥነት መመለስ ባለመቻሉ ወደ ግጭት አመራ፡፡ በዚህም የበርካታ ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡ በመንግሥት መረጃ መሠረት የ95 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በሁለቱም ክልሎች የተቀሰቀሱት ደም አፋሳሽ ግጭቶችና ተቃውሞዎች ከተረጋጉ በኋላ በአካባቢዎቹ መርማሪዎችን በመላክ መረጃ የሰበሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፀጥታ ኃይሎች በአማራ ክልል ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀማቸውን ሲገልጽ፣ በኦሮሚያ ግን ተመጣጣኝ ኃይል እንደተጠቀሙ ሪፖርት አደረገ፡፡ ነገር ግን ሪፖርቱን በርካቶች አልተቀበሉትም፡፡ አጠቃላይ የሪፖርቱ ይዘትም እስካሁን ለሕዝብ ይፋ አልሆነም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በመጋቢት ወር
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመንግሥታቸውን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሳው ግጭት መንስዔና ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የተመለከተ ይገኝበታል፡፡
በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹ጣታችንን በሌላ አካል ላይ ከመቀሰር ችግሩ የራሳችን እንደሆነ አስምረን መሄድ አለብን፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ባለፉት 12 ዓመታት የአገሪቱ አርሶ አደሮችም ሆነ የከተማ ነዋሪዎች ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት አገር እንደሆነች ቢገነዘቡም፣ የሕዝቡን ጥያቄ በፍጥነት መንግሥትና ገዥው ፓርቲ መመለስ ባለመቻሉ ምክንያት ከሕዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
‹‹ይህ ቅራኔ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ወደ ግጭት አምርቷል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ግጭት ስላለ ሌላ ቦታ ይኼ ግጭት የለም ማለት አይደለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ከትግራይ ጀምሮ እስከ ደቡብ ጫፍ ይኼ ችግር ያውና ተመሳሳይ ነው፤›› በማለት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
አገሪቱ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገቧ ምክንያት የአገሪቱ ሕዝቦች ዓይን መከፈቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ እንዲቀጥል ኅብረተሰቡ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ በሚፈልገው ፍጥነት ገዥው ፓርቲ መፍጠን ባለመቻሉ የተፈጠረው ቅራኔ እየተስፋፋ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
‹‹ከፊት ለፊት ደንቃራ ስንሆንበት ዞር በሉ ብሎ መግፋቱ አይቀርም፡፡ ዞር በሉ ሲል አንዳንዴ በእጁ ይላል አንዳንዴ በቃሉ ይላል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አሁን በእጁ ነው ዞር በሉ ያለው፤›› ሲሉ ችግሩ ከመልካም አስተዳደርና ከኢኮኖሚ ጥያቄዎች ጋር የተገናኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአማራ ከቅማንት ጋር በተገናኘ ለተፈጠረው ችግርም የክልሉ መንግሥት ጥያቄውን በፍጥነት ባለመመለሱ ወደ ግጭት እንዳመራ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ሊመለስ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የማንነት ጥያቄ ግጭት ሊያስከትል የሚገባ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህንን ጉድለት የክልሉ መንግሥትና ፓርቲ ተገንዝቦ ጥያቄው ዕውቅና እንዲያገኝ መደረጉን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከዚህ በኋላ ጥያቄው ከቀጠለ ሌላ ጉዳይ እንደሚሆን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በማከልም በኢትዮጵያ ውስጥ የማንነት ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ እየተተረጐመ እንጂ ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
በአንድ ብሔር ውስጥ የሚኖር ጐሳ ተነጥሎ ራሱን የቻለ ብሔር ይሁን የሚል የተሳሳተ ጥያቄ እየተነሳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
‹‹ከአሁን በኋላ የማንነት ጥያቄ ተመልሶ አልቋል የሚል ምላሽ መሰጠት አለበት፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሕዝቡን የባህል ልብስ እያስለበሱና እያሠለፉ የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ጥገኞችም ማረፍ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
ወልቃይት
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የማንነት ጥያቄ በኢትዮጵያ ተመልሶ አልቋል ቢሉም በትግራይ ክልል ከወልቃይት ማንነት ጋር የተያያዘ የወሰን ለውጥ ጥያቄውን ይዞ የተነሳው በዚያው ወር ውስጥ ነበር፡፡
የወልቃይት የማንነት ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጥያቄውን ለትግራይ ክልል ምክር ቤት ሳያስገባ የጥያቄ አቀራረብ አካሄዱን በመዝለል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ የሰጠው ምላሽ በመጀመሪያ ለትግራይ ክልል እንዲቀርብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ከወልቃይት ማንነት ጋር የተያያዘ የወሰን ለውጥ ጥያቄ በሐምሌ ወር መጀመሪያ በሰሜን ጎንደር ጐዳናዎች ላይ ይዞ ወጥቷል፡፡
ኮሚቴው ጥያቄውን በትግራይ ክልል ለማቅረብ ወይም ጥያቄውን በወልቃይት ጐዳናዎች ይዞ እንዳይወጣ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሊወስዱት የሚችሉት ዕርምጃን ምክንያት በማድረግ ወደ አጐራባች ሰሜን ጎንደር እንዲሄድ መገደዱን የሚገልጹ አሉ፡፡
በሰሜን ጎንደር እጅግ ሰፊ የሆነ ሕዝብ የወልቃይት ጥያቄን በማንሳት ሰላማዊ ሠልፎችን በሰላማዊ መንገድ አከናወነ፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ወልቃይትን የሚጠይቁ ሰላማዊ ሠልፎች የተካሄዱት በሕገወጥ መንገድ ነው ቢልም ሠልፉ ሰላማዊ በመሆኑ በማንም ላይ ዕርምጃ አልወሰደም፡፡ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የወልቃይት መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በሽብር ወንጀል እንደሚፈልጋቸው በመግለጽ፣ በሰሜን ጎንደር አባላቱ የሚገኙበትን አካባቢ በመክበብ ለመያዝ ያደረገው እንቅስቃሴ ደም መፋሰስን ብሎም የሕይወት መጥፋትን አስከተለ፡፡
የፌዴራል መንግሥት የወልቃይትን ጥያቄ ለማፈን አይደለም ቢልም ተዓማኒነትን ማግኘት አልቻለም፡፡
ከዚህ በኋላ የወልቃይት ጉዳይ መነሻ እንጂ የተቃውሞው መስፋፋት ምክንያት አልሆነም፡፡
ከሰሜን ጎንደር ወደ ባህር ዳርና የተያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተንሰራፋ፡፡ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የንብረት ማውደም እንቅስቃሴም የተቃውሞው መገለጫ ሆነ፡፡
በአማራ ክልል በተደረጉ ሠልፎች ላይም የኦሮሞ ሕዝብ መብት እንዲከበር የሚጠይቁ መፈክሮች ተስተጋቡ፡፡
በሰላማዊ ሠልፍ የተጀመው ተቃውሞ በቤት ውስጥ መቀመጥ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሀብቶችንና የሕዝብ መገልገያዎችን በማውደም ከመስፋፋቱ በተጨማሪ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ ዳግም እንዲነሳ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን አጠቃላይ ሕዝብ 60 በመቶ በሚወክሉት ሁለቱ ክልሎች የተነሳው ተቃውሞ ተመሳሳይ የተቃውሞ ቴክኒክ በመጠቀም፣ አንዴ በሰላማዊ ሠልፍ አንዴ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ አገልግሎት በማቋረጥና መንገድ በመዝጋት የፖለቲካ ሥርዓቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከተውታል፡፡
በእነዚህ ተቃውሞዎች መሀል በየካቲት ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ለአንድ ቀን የታክሲዎች የሥራ ማቆም አድማ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ በከተማዋ አዲስ የትራፊክ ሥነ ሥርዓት ደንብ ተግባራዊ መደረጉን በመቃወም ነበር የታክሲ አሽከርካሪዎች የሥራ ማቆም አድማውን ያካሄዱት፡፡
ይህ ክስተት ገዥውን ፓርቲና መንግሥትን የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ በመሆኑ፣ የትራፊክ ሥነ ሥርዓት ደንቡ በአስቸኳይ እንዲነሳ በመደረጉ በተለያዩ ክልሎች የተነሳው ተቃውሞ አዲስ አበባን መያዝ አልቻለም፡፡ የተለያዩ የሠልፍ ጥሪዎች ለአዲስ አበባ ቢተላለፉም ውጤታማ አልነበሩም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እየተቀጣጠሉ ያሉት ተቃውሞዎች ማንነት ተኮር በመሆናቸው አዲስ አበባን መያዝ እንዳልቻሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
ይህንን ትንታኔ የማይቀበሉት ደግሞ የፀጥታ ኃይሉ የአዲስ አበባ ሕዝብ እንዳይነሳ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ መሆኑን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡
ኢሕአዴግ
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አሁን ያለውን ሁኔታ በቀድሞው ዕይታው እየተመለከተ ይገኛል፡፡ በነሐሴ ወር መገባደጃ አካባቢ የተሰበሰበው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም ማዕከላዊ ኮሚቴው ተቃውሞውን ከመልካም አስተዳደርና ከኢኮኖሚ ጥያቄ ጋር አሁንም አያይዞታል፡፡
ሥልጣንን ለግል ጥቅም መገልገያ የሚል አዲስ አገላለጽ ከመጨመሩ ውጪ፣ ለሕዝብ የተገለጸው ግምገማ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው፡፡
በ2007 ዓ.ም. በኦሮሚያ የተጀመረው ተቃውሞ በ2008 ዓመቱን ሙሉ ተቀጣጥሎና ከአማራ የሕዝብ ተቃውሞ ጋር አብሮ 2009 ዓ.ም. እየተቀበለ ይገኛል፡፡
አዲሱ 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ምን ይዞ ይመጣል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡
- ዮሐንስ አንበርብር’s blog
- 943 reads