mola-asgidomዛሬ ሞላ አስገዶም የተባለው የቀድሞ የዴምህት ሊቀመንበር አየሁት። አሪፍ መኪና ይዟል። መኪና፣ ለቤት መስርያ የሚሆን መሬትና ገንዘብ እንደተሰጠው ሰማሁ። ላገኘው አስቤ አልተሳካም። የኢትዮጵያ ደህንነት እንደሚከታተለውና ከኔ ጋር እንዲገናኝ እንደማይፈቀድለት ሰማሁና ተውኩት። ዛሬ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሞላ አስገዶምን ያየሁበት ቀን ብቻ አይደለም። ባለፈው ዓመት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ቀን የአዲስ ዓመት ዋዜማ ነበር። በዚች ቀን ስለሱ ለመፃፍ ወደድኩ። የዴምህት ሊቀመንበር ሞላ አስገዶም እንደሚባል የሰማሁት ታስሬ ማእከላዊ ምርመራ በነበርኩበት ግዜ ኩርፊል ጅማ የተባለው የቤንሻንጉል ነፃ አውጪ ግንባር ወታደራዊ መሪ ነግሮኝ ነው።

ሞላ አስገዶም የቀድሞ የህወሓት ታጋይ የነበረ ሲሆን ከህወሓቶች ጋር ተጣልቶ ኤርትራ ገባ። ህወሓትን ለማስወገድ ትጥቅ ትግል ጀመረ። በህወሓት አገዛዝ የተማረሩ ብዙ የትግራይ ወጣቶች ፀረ ህወሓት በሚደረግ ትግል ለመሳተፍ ኤርትራ በረኻ ገቡ። በዴምህት አመራሮች ትእዛዝ ብዙ ትግል አካሄዱ። ብዙዎቹም በኢህአዴግ ወታደር ተይዘው በሽብር ተከሰው እስከ 22 ዓመት ተፍርዶባቸው በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ። ብዙዎቹም በምርመራ አካላቸው ጎድሏል።

አሁን በሆነ ይሁን ምክንያት ሞላ አስገዶም ወደ ሀገሩ ገብቷል። ለማንም ዜጋ ሊሰጥ የማይችል የክብር አቀባበል ተድርጎለታል። ለማንም የማይሰጥ መኪና አግኝቷል። ለማንም የማይሰጥ ገንዘብና መሬት ተሰጥቶታል። አሁን በአገልግሎት ደረጃ ከሰው በላይ ነው። ሞላ አኩርፎ ብረት ባያነሳ ኖሮ ይህንን ክብር ሳያገኝ ይጣል ነበር፣ ማንንም ከተጣለበት አያነሳውም ነበር። ብረት በማንሳቱ ምክንያት ራሱ ሰው አረገ። በነፃነት ደረጃ ግን ከሰው ሁሉ በታች ነው። ነፃ ሆኖ መንቀሳቀስ እንኳ አይችልም። ሁሌ በተግባሩ እንዳፈረ ነው። ገንዘብና መኪና ክብር አይገዛም። ክብር ስብዕና ነው። ለሆዱ የሚኖር አህያ ነው። አህያም ክብር የለውም። የሆነ ሁኖ ሞላ አልታሰረም።

ለመጥፎ ይሁን ለጥሩ ነገር ሞላ አስገዶም የላካቸው አባላቱ ግን ታስረው ይሰቃያሉ፣ ይገደላሉ። ለምን ታሰሩ? ለምን ተሰቃዩ? ህዝብን ሊያሽብሩ ነበር ተብለው ነው። የሞላ አስገዶም ወታደሮች ህዝብን ሊያሸብሩ ተብለው ከተከሰሱ ሞላስ ምን እያደረገ ነበር? እነሱ ታሰሩ፤ እሱ ግን ተሸለመ። እሱ ሳይከሰስ የህዝብ ልጆች ግን አሸባሪ ተብለው ታስረው ይማቅቃሉ።

ህወሓት ለስልጣኑ እንጂ ለህዝብ አስቦ አያውቅም። የዴምህት ወታደሮች በሽብር ተጠርጥረው ሞላ አስገዶም ግን ሊሸለም አይችልም ነበር። ግን የሞላን ሀገር መግባት ለህወሓት ፖለቲካ ስለሚጠቅም ብቻ የህዝብንና የሀገርን ሃብት አሳልፋ ሰጠችው። ለሞላ አስገዶም የተሰጠው ገንዘብ ይሁን መሬት የመንግስት ሃብት ነው። የመንግስትን ሃብት በግብር መልክ ከህዝብ የተሰበሰበ ነው። ነጋዴዎች ንግዳቸውን እየዘጉ የከፈሉትን ግብር ለሞላ ተሰጠ። ምንስላደረገ? ብረት ስላነሳና ወደ ሀገር ስለገባ። አንድምታው ምንድነው? በህጋዊ መንገድ ከመነገድ ብረት አንስቶ መመለስ እንደሚሻል ለማሳየት ይመስላል።

ሞላ አስገዶም ብዙ ሰው መልምሎ ብዙ ወታደሮቹን ትቶ ነው የገባው። ህወሓቶች የሸለሙትም ሌሎች ተቃዋሚዎችን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ለማማለል ይመስላል። ግን አብዛኛው ታጋይ ብረት ያነሳው ጭቆናን ጠልቶ እንጂ ሞላ አስገዶምን ተከትሎ አይመስለኝም። አብዛኛው ወጣት ወደ ኤርትራ የሚሄደው ሞላ አስገዶም ኤርትራ ዉስጥ ስለነበረ ወይም ሻዕብያ ስለሚመለምለው አይደለም። የህወሓትን አገዛዝ አንገሽግሾት እንጂ። ታጣቂዎች ወደ ኤርትራ እንዳይሄዱና ከኤርትራም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ከተፈለገ ጭቆናን ማስቀረት እንጂ ብረት አንስቶ ብረት ለሚጥል መሸለም አይደለም። ሞላ አስገዶም ቢመጣም ጭቆናው እስካለ ድረስ ብዙ ወጣቶች ይሄዳሉ፤ ጫካ ይገባሉ። ስለዚህ ብረት የሚያነሱ ታጣቂዎችን ለመቀነስ ሰላማዊ ታጋዮችን አለመጨፍለቅ እንጂ ከትጥቅ ትግል ለሚመለሱ ገንዘብና መኪና መስጠት አይደለም።

አብዛኞቹ ትጥቅ ትግልን የመረጡ (የግንቦት 7ቱ ደ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ) በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ ናቸው። በሰላማዊ መንገድ ታግለው የህዝብ ድጋፍ አግኝተው ተመርጠው በገዥው ስርዓት ታስረው ሰላማዊው መንገድ ሲዘጋባቸው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ናቸው። ሰላማዊ ትግል ቢፈቀድ ኖሮ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ግንቦት 7 ብረት አንስቶ ባላየን ነበር። ስለዚህ ትጥቅ ትግልን የማንደግፍ ከሆነ ሰላማዊ ትግልን ማበረታት አለብን። ሰላማዊ ትግልን በመጨፍለቅ ትጥቅ ትግልን እያበረታታን ከትጥቅ ትግል የሚመለሱን ግለሰቦች የህዝብን ሃብት ማስረከብ ኪሳራ ነው፤ በዴሞክራሲም በገንዘብም።

ስለዚህ ትጥቅ ትግልን ማስወገድ የምንችለው ጭቆናን አስወግደን ሰላማዊ ትግልን ስናበረታታ ብቻ ነው። ጭቆና ካለ ትጥቅ ትግል አይቀርም። ሰላማዊ ትግል ከተዘጋ ትጥቅ ትግል መጀመሩ አይቀርም። የዚህ ዓይነቱ የፖለቲካ ችግር መፍትሔ ስልጣንን ለህዝብ አስረክቦ ዴሞክራሲን ማስፈን ነው። ይህንን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ትጥቅ ትግልን በገንዘብና መኪና ሽልማት አይቆምም። ጭቆናን አለማስቀረት የራስ መቃብርን መቆፈር ነው።

Leave a Reply