“ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚቅበዘበዙ ሁሉ እነሱ ይጠፋሉ እንጂ ኢትዮጵያ አትጠፋም” ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ
ዛሬ ላለፉት 25 አመታት በኢትዮጵያ አገራችን ላይ በወያኔ የትግሬ ነጻ አውጪ ግንባር አማካኝነት የተጫነው የባርነት ቀንበር ፈጽሞ የሚወገደበትና የፈነጠቀውን የነጻነት ጮራ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበራበት የመጨረሻ ሰአት ላይ እንገኛለን። ሰለሆነም ሙሉ ድልን ለመቀናጀትና ለማረጋገጥ ከመቸውም ጊዜ በበለጥ አስፈላጊውን ሁሉ በቆራጥነትና በጀግንነት መፈጸም የመላ ኢትዮጵያውያን ግዴታና ታሪካዊ ሀላፊነት ነው። በአሁኑ ወቅት ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በተለይም በአማራው ህዝብ ላይ በይፋ ያወጀውን ጦርነትና የዘር ማጥፋት ዘመቻ የአለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት በጽኑ የምናወግዘው ብቻ ሳይሆን ከመግለጫ ባለፈ ደረጃ ማንኛውንም አስፈላጊ ትብብርና ሙሉ አስተዋጽኦ ለማድርግ ዝግጁና ፈቃደኝ መሆናችንን ስንገልጽ በታላቅ ክብርና በልበ ሙሉነት ስሜት ጭምር ነው። በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን መሰለፍና አጋርነትን በተግባር መግለጽ ታላቅ መንፈሳዊ ጸጋ ነውና ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ወያኔ ያመጣወን መከራና ችግር ገፈት ቀማሽ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለድል የሚያበቃ ቆራጥ ሚና እና ወሳኝ አስተዋጾ እናደርግ ዘንድ ወገናዊ ጥሪያችንን በአክብሮት እናስተላለፋለን።
ወያኔ ጸረ ኢትዮጵያ አላማውን ለማሳካት የአገራችንን ሉአላዊነት በመድፈር፤ የህዝብን አንድነት በጎሳ፤ በሃይማኖትና በቋንቋ በመከፋፋል፤ ብሔራዊ ሕልውናዋን ለማጥፋት ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ ከምንጊዜው በላይ ግልጽ ነው። ወያኔ/የትግሬ ነጻ አውጪ ግንባር በውስጥና በውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ማንበርከክና ብሎም በመበታተን ትንንሽ የጎሳ አገሮችን ለመፍጠር የሚያደርገወን ጥረት ለማገባደድ ዛሬ የመጨረሻወን መፈራገጥ እያደረገ ነው። ይህ መፈራገጥ ለመላላጥ ይሆን ዘንድ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ያነሳወን የነጻነት ትግል ግቡን እንዲመታና እንዳይቀለበስ በአንድነት መንፈስ፤ በተደራጀና በተቀናጀ የትግል ስልት ልንቋቋመው ይገባል። ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ወያኔና መሰሎቹ የህዝብን የህልውናና የነጻነት ትግል በተለያየ ዘዴ ለማኮላሸት፤ ማህበረ ሰብን በማፍረስና በሚፈጥረው ማህበራዊ ቀውስን ሽፋን በማድረግ ህዝብን ለማጥቃት ይሞክራል። እንዲሁም ለባእድን ሆነ ለጥቂት የጎሳ አቀንቃኞች አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና፤ በዕርስ በርስ ግጭት እንድንጠመድም ይሞክራል። ይህ ሙከራ ከንቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ በተደጋጋሚ ቢያስይም ትግሉ በበለጠ አገር አቀፍ መልክ እንዲይዝ፤ ዘለቄታዊነት ያለው የበሰለና የጠራ አገራዊ የፖለቲካ ስልትና አደረጃጀት ዋና የድል መሳሬያ መሆኑን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መገንዘብ ይገባል።
ስለዚህም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍለ አገራት የሚካሄደውን ህዝባዊ ትግል ለህዝብ ደህንነትና አንድነት፣ አገራዊ ህልውናን እና ሉዓላዊነትን ያማከለ ኢትዮጵያዊ ንቅናቄ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አስፈላጊ ግዳጅ ነው፤ አንድን የጎሳ ፖለቲካ በሌላ የጎሳ አስተሳሰብ መተካት ፍትህና ርትእ የሚያጎናጽፍ ብሄራዊ መፍትሄ አለመሆኑን ማስተዋል ከወዲሁ ተገቢ ነውና። በተጨማሬም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ትግሉን የሚያንቀሳቀሱ ሃይሎች ሁሉ፣ሊከሰቱ የሚችሉትን አሰከፊ ሁኔታዎችን ለመከላከል የወያኔን የጎሳ የማንነት ካርድን በመቅደድ እምቢ ማለትና፤ ሁለንተናዊ ማእቀብ በወያኔና በተባባሬዎቹ ላይ ማድረግ ቁልፍ የትግል ዘዴ መሆኑን በመገንዘብ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምን የሚያስጠብቅ፣ ኢትዮጵያዊ ትንሳኤን የሚያመጣ አቅጣቻ መተለም ወቅቱ የሚጠይቀው ፖለቲካዊ ተግባር ነው። ለዚህም ኢትዮጵያዊ ጥብብን ያነገበ፣ የተቃና ህዝባዊ ድልን የሚያጎናጽፍ የትግል መንገድ ለመከተል ያስችለን ዘንድ አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት ለአገር ወዳድ ምሁራንና ለአንድነት የፖለቲካ ሃይሎች ይህን ታሪካዊ ሃላፊነት ይወጡ ዘንድ በዚህ ልዩ ጥሪ እናሳሰባለን።
የኢትዮጵያ ህዝብ ትግልን የሚመሩ የፖለቲካ ድርጂቶች በየጊዜው በአገራችን ውስጥ የሚፈጠረውን አመቺ አጋጣሚ በተገቢው ሁኔታና ጊዜ ባለመጠቀም ትግላችን ከሚገባው በላይ ሲራዘም ኖሯል፤ ካለፈው በመማር በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ የድል ባላቤት ሊሆን እንደሚችል በማወቅ፣ በራሱ በመተማመን፣ በቁርጠኝነት እንድንነሳ እንጥራለን። በዚህ ፈታኝ ወቅት እስከዛሬ ከወያኔ ጎን የተሰለፉትን የውስጥ ሆነ የውጭ ኃይሎች አቋማቸውን አስተካከለው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲሰለፉ እያሳሰብን፣ በተለይም ወያኔ የህዝብን ትግል ለማፈን የሚያካሂደውን ግድያ፣እስራትና ማሳደድን አጥብቀን እያወገዝን ፣ ለዚህ ተግባር መሳሪያ የሆነው የወታደሩን ክፍል በወገኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መሳሪያውን እንዳያነሳና በአስቸኳይ ከህዝብ ጎን እንዲቆም አጥብቀን እንመክራለን።
በድጋሚ የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ለመብታቸው፣ ለአንድነታቸውና ለብሔራዊ ህልውናቸው ለሚያደርጉት ትግል አጋር ነን ስንል የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ያንበረከኩ በርካታ ጀግኖች ኢትዮጵያውያ ሴቶችን ታሪክ በማስታወስና የነሱን የጀግንነት መንፈስ የሀይላችን ምንጭ በማድረግም ጭምር ነው። ዛሬም ኢትዮጵያ አገራችንና ህዝቧን ከወያኔ ጥቃት እንድንከላከልና እናድናት ዘንድ ለመላ ኢትዮጵያውያን በተለይም ለሴቶች ልዩ የነጻነት ትግል ጥሪ እናቀርባለን።
የመጭው አዲስ አመት የኢትዮጵያ ህዝብ ድልን የሚጎናጸፍበት የወያኔ ስርአት የሚወገድበት አመት ይሆንልን ዘንድ ምኞታችንና እምነታችን ነው።
ስራ የጀግና ድል የእግዚአብሄር ነው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት
ጳጉሜ 3 2008