Wednesday, 14 September 2016 14:44

በይርጋ አበበ

             “የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት 25 ዓመታት ሀገራችንን በአምባገነንነት እየገዛ የቆየውን የኢህአዴግ የአፈና አገዛዝ በማስወገድ በፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመተካትም ያልተቋረጠ ትግል በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው በመግለጫ አያይዞም “በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ህዝባችን በሰላማዊ አግባብ ሲያካሂድ የቆየው ፍትሐዊ ትግል ሰሚ በማጣቱና ምላሹም የኃይል እርምጃ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በብዙ አካባቢዎች ትግሉ ወደ ሰላማዊ እምቢተኝነት ተሸጋግሯል” ብሏል።
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰትን በዜጎቹ ላይ ሲፈጽም እንደቆየ ያስታወሰው መድረክ፤ የኢህአዴግ ባህሪ የተቀዳው ከቀዳሚዎቹ አምባገነን ገዥዎች ነው ሲልም አክሏል። ባለፉት 25 ዓመታት የኢህአዴግ የስልጣን ዘመን “ህዝቡን በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሲገዛ ቆይቷል” ያለው የመድረክ መግለጫ “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ይህ የኢህአዴግ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን ህዝቡ በራሱ ጊዜ እየበጣጠሰ ጥሎታል። ትግሉንም በጋራ እና በተቀናጀ መልኩ እያካሄደ ይገኛል” ብሏል።
     በአንዳንድ አካባቢዎችና ድርጅቶች አሁን በህዝቡ የተነሳውን ተቃውሞ በተናጠል ከመምራት ተቆጥበው በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ ሊያካሂዱት እንደሚገባ ለፓርቲዎች ማሳሰቢያ የሚሰጠው የመድረክ መግለጫ “ትግላችን አምባገነኑን ስርዓት ከማስወገድ ባሻገር የህዝባችንን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት አጠናክሮ የጋራ እና ፍትሐዊ የሆነ ዕድገታችንን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ዓላማዎችና ግቦች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ይገባል” ብሏል። ያለፉት 25 ዓመታት በኢህአዴግ ስር የቆየችው ኢትዮጵያ በዜጎቿ መካከል እኩል ተጠቃሚነት እንዳልሰፈነ ያረጋገጠው መድረክ “የኢህአዴግ አገዛዝ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በፖለቲካ ወገንተኝነት ላይ የተመሰረተ እና ዜግነትን ትርጉም ያሳጣ ስርዓት ነው” በማለት አስታውቋል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስራ ለመያዝ ወጣቶች የኢህአዴግ አባልነት እና ደጋፊነታቸው ከዜግነታቸው በላይ ዋጋ ሲሰጠው መቆየቱን አስታውሷል።
    መድረክ በመግለጫው “ኢህአዴግ ያለ አግባብ ያሰራቸውን የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈታ” ሲል የጠየቀ ሲሆን በእስር ላይ የሚገኙት ታራሚዎችም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ከመግፈፍ እንዲታቀብ ጠይቋል። መድረክ አያይዞም ”የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዴግ አገዛዝ በአሁኑ ወቅት በሀገራችንና በህዝባችን ላይ እያመጣ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲገነዘብና መድረክ ያቀረበውን ወቅታዊና ዘላቂ የመፍትሔ ሀሳብ እንዲደግፍ” ሲል የጠየቀ ሲሆን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የተጀመሩት ህዝባዊ ተቃውሞዎችም “በሰላማዊ አግባብ፣ በጋራ እና በአንድነት አጠናክሮ በመቀጠል ኢህአዴግ የሰላማዊ መፍትሔውን እንዲቀበል ሊያደርግ የሚችለውንና ለችግሩም ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችለውን ወሳኝ ህዝባዊ ሚና እንዲጫወት” በማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ስንደቅ

Leave a Reply