14 Sep, 2016
ለ1437ኛ ጊዜ መስከረም 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በተከበረው የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል ላይ፣ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ተቃውሞዎች ታዩ፡፡ ይሁንና በሰውና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት አለመፈጠሩን የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሪፖርተር ዓይን እማኞች እንደገለጹት፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በዓሉን ያለምንም ተቃውሞና ረብሻ እንዳከበረ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን የገለጹ ቢሆንም፣ ጀሞ ቁጥር ሦስት ፉሪ አካባቢ ቀይ ካርድ የያዙና ያለምንም ድምፅ እጃቸውን በማጣመር ተቃውሞአቸውን ያሳዩ ነበሩ፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲዬም ተሰባስበው በዓሉን በሰላም ያከበሩ የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር እንደወትሮው ያልነበረ ቢሆንም፣ በምልክትም ሆነ በሌላ ነገር የታየ ተቃውሞ አልነበረም፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ባሉ የክልል ከተሞች በተለይ በአሰላና በሻሸመኔ አካባቢዎች የሚኖሩ የተወሰኑ የእምነቱ ተከታዮች፣ እጃቸውን በማጣመርና የተለያዩ መዝሙሮች በማሰማት ተቃውሞአቸውን ማሰማታቸውን የዓይን እማኞች አስረድተዋል፡፡
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የእምነቱ ተከታዮች በመስጅድ ውስጥና ከመስጅድ ውጪ ተቃውሞአቸውን እጃቸውን በማጣመር፣ መፈክሮችን በአንድ ድምፅ በማስተጋባትና ዝማሬዎችን በማሰማት ከሌሎቹ አካባቢዎች ለየት ያለና ጠንከር ያለ ተቃውሞ ማሰማታቸውንም የአካባቢው የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የበዓሉን አከባበር ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ ያቀረቡና ለማቅረብ የሞከሩ ቢኖሩም፣ በሁሉም አካባቢ ተመድበው የነበሩ የፀጥታ አስከባሪዎች በትዕግሥትና በዝምታ በማለፋቸው፣ ያለምንም ግጭትና ረብሻ በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን የዓይን እማኞች አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ከዓመታት በፊት ከእስር እንዲፈታቸው የእምነቱ ተከታዮች አበክረው ሲጠይቁላቸው የነበሩትን ‹‹የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ›› አባላት መካከል ዘጠኙ፣ አዲስ ዓመትን በማስመልከት በምሕረት መለቀቃቸው እንዳስደሰታቸው የእምነቱ ተከታዮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በምሕረት የተለቀቁት የኮሚቴ አባላት አቡበከር አህመድ፣ ካሚል ሸምሱ፣ በድሩ ሁሴን፣ ሼህ መከተ ሙሔ፣ ሰዒድ ዓሊ፣ ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው፣ ሙባረክ አደም፣ ኑሩ ቱርኪና ሙራድ ሽኩር መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ያልተፈቱትት የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የሚባሉት ፍርደኞች አህመዲን ጀማል፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ መሐመድ አባተና ካሊድ ኢብራሒም ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት ዘመን መለወጫ በምሕረት የተፈቱት ያሲን ኑሩ፣ ሳቢር ይርጉ፣ አቡበከር ዓለሙ፣ ባህሩ ዑመር፣ ሙኒር ሁሴንና አብዱራዛቅ አክመል መሆናቸው ይታወሳል፡፡
- ታምሩ ጽጌ’s blog
- 2294 reads