ምንጮች እንደገለጹት በማረሚያ ቤቱ የአጣዳፊ ትውከትና ተቅማጥ (አተት) በሽታ በመግባቱ ሳቢያ፣ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ይህንን ክስተት አስመልክቶ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች የተቃውሞው መነሻ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ ከሚገኙ እስረኞች በተወሰኑት ላይ የአተት በሽታ ምልክቶች በመታየታቸው፣ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የእስረኞች ቤተሰቦች የሚያቀርቡት ምግብ ለበሽታው መንስዔ ነው በሚል ቤተሰቦች ምግብ ለታሳሪዎች እንዳያቀርቡ ማገዱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማረሚያ ቤቱ የሚያቀርበውን ምግብ ወትሮውንም ብዙ የማይዋጥላቸው እስረኞች፣ የቤተሰቦቻቸው የምግብ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ መታገዱ እንዳስቆጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህም የተነሳ ታራሚዎች ተቃውሟቸውን ማሰማት መጀመራቸውንና በኋላም የምግብ አለመብላት አድማ መጀመራቸው፣ ከዚህም አልፎ ከማደሪያ ቤታቸው ያለመውጣትና በየዕለቱ ለሚደረገው ቆጠራ ፈቃደኛ አለመሆን ውስጥ መግባታቸው ተመልክቷል፡፡ ይህንንም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በተገቢው መንገድ አለመያዙን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

በማረሚያ ቤቱ ከተነሳው የእሳት አደጋ አስቀድሞ የታራሚዎች ተቃውሞ እንደነበር ለሪፖርተር የተናገሩት ምንጮች፣ ይህ ተቃውሞ ከእሳት አደጋው ጋር ግንኙነት ይኑረው ወይም አይኑረው ለማወቅ እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን ከማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ለማጣራት ሪፖርተር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

በወቅቱ መንግሥት የገለጸው ግን እስረኞች በፈጠሩት ግርግር የእሳት አደጋው መነሳቱን ነው፡፡ ይህም ቢሆን እሳቱን የቀሰቀሱት እስረኞች ስለመሆናቸው መንግሥት የሰጠው መግለጫ በግልጽ አያሳይም፡፡ የእሳት አደጋው መንስዔና በአጠቃላይ የእስረኞች አያያዝን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ማጣራት እንደሚጀምር መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዚህ የእሳት አደጋ ምክንያትና ከአደጋው ጋር በተያያዘ ‹‹23 ሰዎች›› መሞታቸውን መንግሥት የገለጸ ሲሆን፣ እስካሁንም የስምንት እስረኞችን አስከሬን ለቤተሰቦች ማስረከቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሟች አስከሬኖችን ቤተሰቦች እንዳይመለከቱ የፀጥታ ኃይሎች መከልከላቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡