“ትግላችንን ከዘላቂ ግብ ለማድረስና ሀገር አቀፋዊ ቅኝት እንዲኖረው ለማድረግ ሁሉም የዴሞኪራሲ ኃይሎች በአንድነት መቆምና ትግላቸውን ማቀናጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ኢህአዴግም የሕዝቡን ውሳኔ ሊቀበል ይገባል፡፡ “
(ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞኪራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ)
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለዘመናት ተጭኖባቸው የኖሩትን አምባገነናዊ አገዛዞች ለማስወገድና ፍትሕና እኩልነት የተረጋገጠበት ዴሞኪራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን ለመገንባት ከፍተኛ መስዋዕትነት የጠየቁ በርካታ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችንና ትግሎችን ሲያካሄዱ ቆይተዋል፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣን በያዘበት ጊዜ በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ የቆየባቸው የሰብአዊና ዴሞኪራሲያዊ መብቶች መከበር ጉዳይ ህዝባችንን ለመሸንገል የሚጠቀምባቸዉ ብቻ ስለነበረ ሕዝባችን ለዘመናት ሲታገልላቸው ለቆየባቸው ለእነዚህ መሰረታዊ አላማዎች ፈጽሞ ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት ሀገራችንን በአምባገነንነት እየገዛ የቆየውን የኢህአዴግ የአፈና አገዛዝ በማስወገድ በፍትሐዊና ዴሞኪራሲያዊ ሥርዓት ለመተካትም ያልተቋረጠ ትግል በማካሄድ ላይ ይገኛሉ ፡፡
ይህ በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ሕዝባችን በሰላማዊ አግባብ ሲያካሄድ የቆየው ፍትሐዊ ትግል ሰሚ በማጣቱና ምላሹም የኃይል እርምጃ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በብዙ አከባቢዎች ትግሉ ወደ ሰላማዊ እምቢተኝነት እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
ስለዚህም ከቀደምቶቹ አምባገነኖች የወረሳቸውን አምባገነናዊ ባሕሪያት በማን አለብኝነት እያንጸባረቀ ሕዝባችንን አፍኖ ለመግዛት የሚፈጽማቸው በደሎች የሕዝባችንን ትዕግሥት እያስጨረሱ ስለመጡ ሕዝባዊ ትግሉ በአገዛዙ ዘመንም ብዙ መስዋዕትነት እየተከፈለበት ቀጥሎአል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኢህአዴግን የከፋፍሎ መግዣ ሰንሰለቶች እየበጣጠሰ በመስፋፋትና በመፋፋም ላይ ይገኛል፡፡
በተለይም ባለፉት 10 ወራት በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴና ባለፉት 2 ወራት በአማራ ክልል ሲካሄድ የቆየው ሕዝባዊ እምብተኝነት ገዥው ፓርቲ ለሕዝቦች ሰላማዊ ጥያቄ ባለፉት 25 ዓመታት ሲሰጥ የቆየው የኃይልና የአፈና እርምጃዎች ውጤቶች ናቸው፡፡
ከጥፋት መንገዱ ለመመለስና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ ለመሻት መንገዱ የጠፋበት ኢህአዴግም በተቃዋሚዎቹ ላይ የኃይልና የአፈና እርምጃዎቹን በማባባስ በብዙ መቶዎች በሚቆጠሩት ላይ ግዲያ በመፈጸሙና በሺዎች በማሰር ሕዝባዊ ትግሉን ለማፈን እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡
በዚህም ምክንያት ሕዝባዊ ትግሉ የሰላማዊ እምብተኝነት መልክ ይዞ የበለጠ እየተጠናከረ ይገኛል፡፡
በመድረክ ግንዛቤ በአሁኑ ወቅት በሕዝባዊ ትግላችን ከሚታዩት ጠንካራ ጎኖች ውስጥ የሚከተሉት በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡
እነርሱም፡-
1ኛ፡- ኢህአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት በዘረጋቸው የአፈና መዋቅሮች አማካይነት በመላ ሀገሪቱ ላይ ጭኖ የቆየውን የፍርሃት ድባብ ሕዝባችን በቆራጥነት ገፎ በመጣልና የአፈና እርምጃዎቹን በቆራጥነት በመቋቋም በፍትሐዊ ትግሉ ወደፊት መቀጠል መቻሉ፣
2ኛ፡- የኢህአዴግን የከፋፍለህ ግዛ ስልት በማፍረስ በአንድ አከባቢ የሚፈጸመውን የመብት ጥሰትና ረገጣ በሌላ አከባቢ ያለው ሕዝብ ጭምር እያወገዘ የትግል አጋርነቱን ማረጋገጡና፣
3ኛ፡- የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውና በተለያዩ አከባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሁሉም አከባቢዎች የሚፈጸሙትን የአገዛዙን የአፈና እርምጃዎች ማውገዛቸውና ለተበዳዩ ሕዝብ ያላቸውን የትግል አጋሪነት ማረጋገጣቸው ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ሕዝባዊ ትግሉን ይበልጥ ለማፋፋምና ከግቡ እንዲደርስ ለማድረግ እንዲቻል ትግሉን በጋራ ዴሞክራሲያዊ ዓላማ ሥር በማሰባሰብና ሕዝባችንም በአንድነት ተነስቶ በጋራ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ረገድ በርካታ መከናወን የሚገባቸው ተግባራት እንዳሉ መድረክ ይገነዘባል፡፡
በዚሁ መሠረት ትግላችን አምባገነኑን ሥርዓት ከማስወገድ ባሻገር የሕዝባችንንና የዜጎቻችንን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት አጠናክሮ የጋራና ፍትሐዊ የሆነ ዕድገታችንን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ዓላማዎችና ግቦች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይገባናል፡፡
ስለሆነም ሕዝባዊ ትግሉ እንዲሳካ የምንፈልግ ዜጎች በሙሉ በዚህ ረገድ ያሉብንን ጉድለቶች በመገምገምና በማረም የሕዝባችን ትግል ሁሉንም የሀገራችንን ሕዝቦች በባለቤትነት ደረጃ የሚያሳትፍ እንዲሆን ማድረግ መቻል ይገባናል፡፡
ለዚህም ደግሞ የአሁኑን ሕዝባዊ ትግላችንን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን መለየትና ጠንካራዎቹን በማዳበር ድክመቶቹን በወቅቱ ማረም ይጠበቅብናል፡፡
የምንታገልላቸውን አጀንዳዎች ሀገር አቀፍ በማድረግ ረገድ በርካታ ክፍተቶች ስለሚታዩ እነዚህም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በትግሉ አስተባባሪዎች በኩል በወቅቱ መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡
ሁላችንም እንደምንረዳው በአገዛዙ አማካይነት በመላ ሀገሪቱ እየተፈጸሙ ያሉት በደሎችና ግፎች ከአንድ ማዕከል በሚተላለፉ የአፈና መመሪያ የሚፈጸሙና በአብዛኛው ተመሳሳይ ይዘትም ያላቸው ናቸው፡፡
የኢህአዴግ መሪዎች ምንም እንኳን በአንድ ወቅትና ሁኔታ ለአንድ የሕብረተሰብ ክፍል የሚቆሙ መስለው የተለያዩ ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ቢሆንም በሁሉም የሀገራችን አከባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የአፈና አገዛዛቸውን ተቀብለው እንዲኖሩ ስለሚፈልጉ ከዚህ ፍላጎታቸውና አመለካከታቸው የተለየ አቋም የሚይዙ ዜጎችን በሙሉ የዜግነት መብታቸውን እየገፈፉ ይገኛሉ፡፡
በዚሁ መሠረት በአገዛዙ ዘመን የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊ ያልሆኑ የሁሉም ብሔር ብሔረሰብ አባላት የሆኑ አርሶ አደሮች በእርሻ ይዞታቸው ላይ ለመቆየት ዋስትና እንዲያጡና በሰበብ አስባቡ እንዲፈናቀሉ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዕርዳታዎቸንና ከመንግስት የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዳያገኙና ከማሕበራዊ ኑሮም እንዲገለሉ ሲያደርጓቸው ቆይተዋል፡፡
የከተማ ነዋሪዎችም የቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘትም ሆነ የመንግሥት ቤት ተከራይተው ለመኖር የኢህአዴግ አባልነት ወይም ደጋፊነት የሚመዘኑበት ጉዳይ ሆኖባቸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ኢህአዴጎች ከሚያስፈልጋቸው በላይ የከተማ ቦታ እየተመሩ በውድ ዋጋ በመቸብቸብ ሲከብሩ ሌላው ዜጋ በመኖሪያ ቤት እጦት ለመንከራተት እየተገደደ ነው፡፡
የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅመው ቦታ በማግኘት ቤት ከሠሩም ቤታቸው በጭካኔ ፈርሶባቸው እንዲፈናቀሉና ለባሰ ችግርና ሥቃይ እንዲዳረጉ እየተደረገ ነው፡፡
መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ማናቸውም ተቋሞች የሚሠሩ ዜጎችም በዜግነታቸው የመሥራት መብት እንዲያጡና በሥራ ላይ ለመቆየትም ሆነ የዕድገትና የትምህርት ዕድል ለማግኘት ዋስትናው ዜግነትና ብቃት መሆኑ ቀርቶ ኢህአዴግነት እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶችም ወደሥራ ዓለም ለመሰማራት ችሎታቸውና ብቃታቸው ሳይሆን የኢህአዴግ አባል ለመሆን ያላቸው ፈቃደኝነት በቅድመሁኔታ እየቀረበ ለግድ ኢህአዴግነት እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡
ይህንን የኢህአዴግ ተጽኖ የተቃወሙ ሠራተኞችም ሆኑ ወጣት ተማሪዎች ደግሞ በሀገራቸው በሥራ አጥነት ለመንከራተት ወይም ለአስከፊ ስደት መዳረግ ግድ እየሆነባቸው ይገኛል፡፡
ነጋዴውም የንግድ ስራውን ለማከናወን የኢህአዴግ አባል ወይም ደጋፊ መሆኑን ለኢህአዴግ በሚለግሰው መዋጮና በሚያበረክተው የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያረጋግጥ ከፍተኛ ተጽኖ እየተደረገበት ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ የኢህአዴግ አገዛዝ በሁሉም የሀገራችን አከባቢዎች በፖለቲካ ወገንተኝነት ላይ የተመሠረተና ዜግነትን ትርጉም ያሳጣ ሥርዓት ዘርግቶ የጭቆና አገዛዙን አስፍኖአል፡፡
ኢህአዴግ ላለፉት 25 ዓመታት የሕዝባችንን የተቃውሞ እንቅስቃሴ አፍኖ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ያስቻለው ዋና ነገር የፀረ-አምባገነናዊ አገዛዙ ትግላችን የተበታተነና የተከፋፈለ ሆኖ መቆየቱ እንደሆነ መድረክ ይገነዘባል፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴም በተወሰነ ደረጃ መሻሻሎች ቢታዩበትም ትግሉን የጋራ በሆኑ ዘላቂ ዓላማዎች ላይ እንዲመሠረትና በጋራ ግቦች ላይ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ ረገድ መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ማወቅና በወቅቱ ማስተካከል ለትግላችን መሳካትና ውጤታማነት ወሳኝነት አላቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን የሕዝባዊ ትግላችንን ዓላማዎችና ግቦችን ለማሳካትና የትግላችን እንቅስቃሴም የላቀ ስፋትና ጥልቀት ያለው እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም ለችግሮቻችንም ዘላቂነት ያላቸው መፍትሔዎችን ለማስገኘት እንዲቻል የሚከተሉት እርምጃዎች በሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እንዲወሰዱ እንጠይቃለን፡፡
1ኛ፡- የኢህአዴግ አገዛዝ ከላይ እንደተገለጸው በርካታ ዜጎቻችንን በገፍ በየእስር ቤቱ አጉሮ የሚገኝ ሲሆን በተለያዩ መንገዶች ከሚፈጸሚባቸው ግፎችና በደሎች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በእስር ቤቶች በሰበብ አስባቡ በሚነሱ የእሳት አደጋዎች ለጉዳት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡
በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የቅልንጦ እስር ቤት፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው የአምቦ እስር ቤትና በአማራ ክልል በሚገኙት የጎንደርና የደብረታቦር እስር ቤቶች እሳት ተነስቶ በበርካታ ዜጎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከዚህም በላይ የሞቱትንና የቆሰሉትን ታሳሪዎች ማንነት ለቤተሰቦቻቸው በወቅቱ ባለማሳወቅ በእስረኞቹ ቤተሰቦችና ዘመዶች ላይ ከፍተኛ መጉላላትና ጭንቀት እንዲደርስባቸው እያደረገ ይገኛል፡፡
እንደዚሁም በሀዲያ ዞን በሆሳእና ከተማ ፖሊስ በእስረኛው ላይ በፈጸመው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት አድርሶአል፡፡ ስለዚህም ኢህአዴግ ያለአግባብ አስሮ የሚያሰቃያቸውን የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈታቸውና በእስር ላይ የሚገኙትም ዜጎች ሁሉ ሰብአዊና ሕገመንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር እንዲያደርግ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
2ኛ፡- በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የሚደረጉ የትብብር እንቅስቃሴዎች አምባገነኑን አገዛዝ በጋራ ለመጣል የሚደረጉ ጊዜያዊ ትብብሮች ብቻ ሳይሆኑ የጋራ ጨቋኛችንን ወደ ሰላማዊ የድርድር መድረክ እንዲመጣ ለማድረግና እንደ እስከ አሁኑ በእምተኝነቱ አቋም ፀንቶ ለሰላማዊ መፍትሔ የማይተባበር ከሆነም በጋራ ትግላችን በማስወገድ ከዚያም በኋላ የሀገራችንና የሕዝባችንን አንድነት በማስጠበቅ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ሁላችንም በዕኩልነት ተጠቃሚ የምንሆንበትን ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት በጋራ የምንገነባበት ትብብር እንዲሆን በትግሉ ሂደት የሚሳተፉ ኃይሎች ሁሉ የበኩላቸውን አሰተዋጾ እንዲያበረክቱ እንጠይቃለን፡፡
3ኛ፡- የገዥው ፓርቲ አባልና ደጋፊ ያልሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢህአዴግ የጭቆና አገዛዝ ሰላባ ስለሆነ በአከባቢ ወይም በብሔር ብሔረሰብ ሳይለያይና ለኢህአዴግ የከፋፍለህ ግዛ ዘዴው በር ሳይከፍት የአገዛዙን የጭቆና ቀንበር ከላዩ ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል ትግሉን እንዲያስተባብርና በጋራ እንዲቆም መድረክ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
4ኛ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕዝባዊ ትግሉ አስተባባሪ የሆኑ ዜጎች ሁሉ የሕዝባችንን አንድነት ከሚጎዱ ማናቸውም ተግባራት እንዲቆጠቡና አምባገነኑን ሥራዓት በማስወገድ የሀገራችንና የሕዝባችን አንድነት የተረጋገጠበትን ትክክለኛ ዴሞክራሲዊና ፌዴራላዊ የሆነ ሥርዓት ለመገንባት በጋራ በሚናከሄደው ትግል የድርሻቸውን እንዲወጡ መድረክ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃንም የሕብረተሰባችንን የጋራ ትግል ሊጎዱ የሚችሉ መልዕከቶች እያስተላለፉ የሚገኙ ግለሰቦችና ኃይሎች ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲታረሙ መድረክ ያሳስባል፡፡
5ኛ፡- ገዥው ፓርቲ በከፋፍለህ ግዛ ስልቱ ባለፉት የአገዛዝ ዘመኑ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች ሕዝባችንን እርሰበርሱ እያጋጨ ለመፈናቀልና ለተለያዩ ችግሮች ሲያጋልጥ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሕዝባዊ ትግሉ ተጠናክሮ እየተካሄደ ካለባቸው አንዳንድ አከባቢዎች ለምሳሌም በአማራ ክልል መተማ ከተማና አከባቢው ከ6000 በላይ የትግራይ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ዜጎቻችንን ለመፈናቀል ያበቃ አስነዋሪ ሁኔታ መከሰቱ መድረክን አሳስቦታል፡፡
ስለዚህም ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሚኖሩባቸው አከባቢዎች ሁሉ በአንድነት ቆመው በፀረ-ጨቋኝ አገዘዝ ትግል መተባበር እንጂ እርስበርስ መጋጨት ፈጽሞ የማይገባ ተግባር መሆኑን ሊናሰምርበት እንወዳለን፡፡
እንዲህ አይነት ክስተት ጥቅሙ ከፋፍሎ ሊገዛን ለሚፈልገው አምባገነን ኃይል ብቻ ስለሆነ በአስቸኳይ መታረምና አብሮ በመቆምና በመታገል ሊተካ ይገባል እንላለን፡፡
በዚህ ተገቢ ያልሆነ ክስተት የተጎዱ ወገኖቻችን ተመልሰው እንዲቋቋሙና ለሕጋዊ መብታቸው ከሚታገሉት ወገኖቻችን ጋር እንዲቆሙ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፆ እንዲያበረክትም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
6ኛ፡- የኢህአዴግ አገዛዝ በሩብ ክፍለ ዘመን አገዛዙ የሀገራችንን ችግሮች ይበልጥ ከማወሳሰቡና ከማባባሱ በስተቀር አንዳችም ተጨባጭ መፍትሔ ያላስገኘና የመፍትሔ አቅጣጫም እየተከተላ ካለመሆኑም በላይ በአሁኑ ወቅት የሕዝባችንን ትዕግሥት በማስጨረሱ ምክንያት የተነሳበትን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለማፈን ዘግናኝ የሆኑ የጭካኔ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡
በዚህም የተሳሳተ እርምጃው ሀገራችንንና የሕዝባችንን ሕልውናና ደህንነት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከቶት ይገኛል፡፡
ትናንት በተጭበረበረ ምርጫ ከሕዝቡ መቶ በመቶ ድጋፍ አግኝቼ ተመረጥኩ ያለበትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የህዝባችን ጠንካራ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እርቃኑን ስላስቀረበትም ተቃውሞውን በኃይል ለማፈን በአሁኑ ወቅት እያደረጋቸው ያሉት እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሀገራችንን ወደ ባሰ ችግር የሚከቱ ስለሆኑ ሰላማዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን እየተወሰዱ ያሉት የኃይል እርምጃዎች በአሰቸኳይ እንዲቆሙ እንጠይቃለን፡፡
ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻልም በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 3 መሠረት ከሕዝባችን እምነትና ይሁንታ ውጭ በ2007 ዓ/ም በተካሄደው በተጭበረበረ ምርጫ ላይ ተመሥርቶ የተቋቋመው (የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት) እና ይህንን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያስፈጸመው የምርጫ ቦርድ ፈርሰው ገለልተኛነቱ በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕብረተሰብ ክፍሎች በጋራ የሚታመንበት የምርጫ አስፈጻሚ አካል ተቋቁሞ ነፃ፣ ፍትሐዊና ታአማኒነት ያለው ዴሞክራሲዊ ምርጫ በሀገራችን በአስቸኳይ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ኢህአዴግ ከመድረክና ሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአስቸኳይ ወደ ድርድር እንዲገባ እንጠይቃለን፡፡
በምርጫው የሕዝብ ድጋፍ በሚያገኙት ፓርቲዎች አማካይነትም የሽግግር ይዘት ያለውና ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችና የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የብሔራዊ አንድነት መንግስት በአሰቸኳይ ተቋቁሞ ሀገራችን ወደ ትክክለኛ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚትሸጋገርበት ሂደት እንዲያመቻችና ሂደቱንም እንዲመራው እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
7ኛ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብም የኢህአዴግ አገዛዝ በአሁኑ ወቅት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ እያመጣ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲገነዘብና መድረክ ያቀረበውን ወቅታዊና ዘላቂ የሆነ የመፍትሔ ሀሳብ በመደገፍ ሕገመንገሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ በማካሄድ ላይ ያለውን የሰላማዊ እምብተኝነት ትግል በሰላማዊ አግባብ ፣ በጋራና በአንድነት አጠናክሮ በመቀጠል ኢህአዴግ የሰላማዊ መፍትሔውን እንዲቀበል ሊያደርግ የሚችለውንና ለችግሩም ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችለውን ወሳኝ ሕዝባዊ ሚናውን እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ
መስከረም 2 ቀን 2009 ዓ/ም
አዲስ አበባ ”
ነፃነታችን በእጃችን ነው !