ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም እንድ ጊዜ ኢህድሪ የሚባለውን መንግስታቸውን ካቋቋሙ በኋላ “ዕውን አሁን ደርግ አለ?” ብለው አገሩን በሳቅ ሊፈጁት ነበር። ይዘቱ ያው የሆነ ነገር በቅርጹ ስለተለየ በውጤቱ የተለየ ይሆናል ብለን እንድናመን ፈልገው ነበር መሰለኝ። አሁን ደግሞ የህወሀት መሪዎች ተራ በተራ ካላንዳች ተከራካሪ በሞኖፖል በያዙት ቴሌቪዝን ላይ እየወጡ “ዕውን አሁን የትግራይና የህወሀት የበላይነት ኢትዮጵያ ውስጥ አለ”? የሚል ተጨፈኑልኝ ላሞኛችሁ ዘፈን መሰል ነገር በኦርኬስትራ መልክ እየተቀባበሉ እየደለቁት ነው። (ከብዙ ጥቂቱን እዚህ ይመልከቱ)። ተከራክረው እንደማይረቱ ሰለሚያውቁ ራሳቸው ጎን ለጎን ተኮልኩለው እየተቀባበሉ ይነጋገራሉ እንጂ ሞጋች አያስቀርቡም። ጥያቄ አቅራቢውም መልስ ሰጭውም እነሱ ናቸው። ዲሞክራሲ ማለት ያንድ አቅጣጫ መንገድ ነው ወያኔዎች ቤት። እነሱ ከተናገሩት ዕውነት ነው። አለቀ። ክርክርና ትችት እንደጦር ሲፈሩ ይገርሙኛል። ተቺ ጠቃሚ አስተካካይ ሳይሆን አሸባሪ ነው። ተቃዋሚ ጠላት ነው ብለው ያምናሉ። ይህ ባህሪያቸው እነሱንም ሃገራችንንም አብሮ እያጠፋና ሊያጠፋ የተቃረበ መሆኑ ፈጽሞ የገባቸው አልመሰለኝም።
የመንግስት ባለስልጣን አይዋሽም አይባልም። ውሸቱ ግን ወይ ለከት ወይ የማስመሰል ቅንብር (nuance) እንዲኖረው ይጠበቃል። ውሸት ብዙ አይነት ነው። አንዳንድ ውሸት ያስቃል። ዕውነት ከመሰለ የሚጠቅም ውሸትም አይጠፋም። አንዳንዱ ውሸት ያሳዝን ይሆናል። ውሸት እየዋሹ ሰው የሚያዝናኑ ሰዎችም አውቃለሁ። እንዳንዱ ውሸት ግን የአድማጩን የመገንዘብ ችሎታ (intelligence) የሚሳደብ ይሆንና ያናድዳል። ሰሞኑን የሰማሁት የአቶ ስዩም መስፍንና የሌሎች ህወሀት ባለስልጣኖች አይነቱ ከኋለኛው አይነት የሚመደብ ነው። አቶ ስዩም መስፍን ከዚህ ቀደም በማግስቱ የተጋለጠ አገር ጉድ ያለው ውሸት ሲዋሹ ያየሁዋቸው ሰው ሰለሆኑ ውሸት ካፋቸው እንዴት ወጣ ብዬ የምሞግታቸው ስው አይደሉም። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የግልግል (arbitration) ውሳኔ ማግስት ባድሜም ሁሉም ነገር ለኛ ተወሰነልን ደስ ይበላችሁ ያሉንንና በማግስቱ ጭልጥ ያለ ውሸት ሆኖ መገኘቱን ያልሰማ ኢትዮጵያዊ አይኖርም። እንደዚያ የቀናት አድሜ የሌለው ውሸት በሚሊዩኖች ፊት ለምን እንደዋሹ እስከዛሬ ይገርመኛል። ያሁኑን የትግራይና የህወሀት የበላይነት በኢትዮጵያ ምድር የለም የሚለውን ሌላ ቆሞ የሚሄድ ውሸት ምን እንደምንለው አላውቅም። ሳይኮሎጂስቶች አንዳንድ ሰዎችን እንዲህ ጸባየ ውሸታም (habitual liar) የሚያደርግ የሚገፋና የሚወተውት በሽታ (Compulsive Obsessive Disorder) የሚባል ህመም አለ የሚሉትን ነገር እንጠርጥር ይሆን?
ለነገሩ አሁን የምንሰማው “እውን የትግራይና የህወሀት የበላይነት አለ?” ዘመቻ የተቀነባበረ (orchestrated) ይመስላል። ባለስልጣናቱ ተራ በተራ እየደጋገሙት ነው። አቶ አባይ ጸሐዬ፣ አቶ ደብረ ጽዮን ፣ አቶ በረከት ስምኦንና ሌሎችም ይህንኑ አይኔን ግምባር ያርገው ከማለት ያልተናነሰ ነገር ሲናገሩ ሰምተናል።
ሁሉም ሹማምንት ባንድ ሀገር ውስጥ ያንድ ብሔረሰብ የበላይነት አለ ሲባል ምን ማለት ነው የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ለመተርጎም ምንም ሙከራ አላደረጉም። እራሴው ልጽደቅባቸውና ከተለያዩ ምንጮች ያገኘሁትን ትርጉም አሳጥሬ ለሁሉም በሚገባና በሚያስማማ መልክ ተርጉሜ ልጀምር። ያንድ ብሄረሰብ ወይም ቡድን የበላይነት ማለት በቡድኑ ወይም በብሔረሰቡ ስም የተሰበሰበው ስብስብ በግልጽና ግልጽ ባልሆነ መንገድ የሌላ ሕዝብ ስብስብን ወይም ስብሰቦችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ህልውና በበላይነት የሚቆጣጠርበትና ሌሎቹን በመጫን ራሱንና የራሱን ስብስብ ወይም ወገን ለመጥቀምና በበላይነት ለማስቀመጥ የሚሰራበት ስርዓት ነው። (Political domination is an explicit or tacit measures taken which put a group or groups of people under the political, and sometimes, economic control of another group or groups በማለት Emefiena Ezeani የሚባል “In Biafra Africa Died” ና ሌሎችንም መጽሀፍ የጻፈ አፍሪካዊ ምሁር ከሰጠው አጭር ትርጉም ጋር ይቀራረባል)። የህወሀት መሪዎችን ዕምነትና ክህደት የምንመረምረው ከዚህ ቀላልና ብዙ ሰው ከማያጣላ ትርጉም ተነስተን ቢሆን ይሻላል ብዬ ነው ስለትርጉሙ የተጨነኩት።
አቶ ስዩም መስፍን ትግሬ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን 25 ዓመት ሙሉ ደጋግመው በመዋሸት የትግራይና የህወሀት የበላይነት እውነት ያለ እንዲመስል አድርገዋል ፣ “ፕርሴፕሺን” ፈጥረዋል ይላሉ። በሳቸው ቤት ያለው ዕውነታ ሳይሆን ፐርሴፕሺን (ዕውነት የሚመስል ቅዠት) ነው። “ትግራይ እስክትለማ ኢትዮጵያ ትድማ” ብለው ተርተዋል ፣ የትግራይ መሬት በልማት ሊሰምጥ ነው ብለው ተሳልቀዋል ፣ ትግራይ ፋብሪካ በፋብሪካ ሆነች ፣ መንገድ በመንገድ ሆነች ብለው ዋሽተዋል እያሉ ይከሳሉ። ይህን ሲሉ የኢትዮጵያውያንን የመገንዘብ ችሎታ የሰደቡም አልመስላቸውም። አቶ ስዩም ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የዘረጉለትን ሥርዓት አፓርታይድ ብሎ ስላልጠራው ባያመሰግኑት እንኳን የፈጠራ ወሬ የሚያወራ ውሸታም ብለው ሊሰድቡት አይገባም ነበር።
እስኪ ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ አገር ስለሚያውቃቸው ነገሮች ከብዙ በጥቂቱ እንነጋገርና ይህን ውሽልሽል ውሸት እንየው። በደርግ ጊዜ የነበሩትን የመንግስት እርሻ ተቋማት ንብረት መሳሪያዎች ትራክተሮች መኪኖች ጄኔሬተሮች (ለምሳሌ ያህል ጣና በለስ የነበረውን) ከዚያ በተጨማሪ ያውራ ጎዳና መስሪያ ዶዘር ኤክስካቬተርና ያ ሁሉ ማሽኒነሪ በጠራራ ጸሀይ ከየቦታው እየተጋዘ ይሄድ የነበረው ወደቱርክ ነበር እንዴ አቶ ስዩም? ያንን ባይኑ በብረቱ የሚያይ ሰው ምን እንዲል ትጠብቁ ነበር? የትግራይ መሬት ሊሰምጥ ነው ማለት ብዙ ንብረት ወደዚያ መጋዙን ለመናገር የቀረበ ዘይቤያዊ እነጋገር እንጂ መቼም ተፈጥሮ መሬቱ ይሰምጣል ማለቱ ነው ብለው ሕዝቡን የሚከራከሩት አይመስለኝም። እስቲ ሌላው ሁሉ ይቅርና አቶ ስዩምን እንድ ቀላል ጥያቄ እንጠይቅ። ለመሆኑ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሁሉ ጉልሕና ዋና የሆነውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በርስትነት ለብዙ አመታት ይዘው ቁጭ እንዲሉና ዛሬም ከትግሬ እጅ ያልወጣው እንዲሁም አቶ መለስ እስኪሞት ድረስ 21 አመት ሙሉ በያዘው ስልጣን ላይ የተቀመጠው በብሔረሰብና ድርጅታዊ የበላይነታችሁ ነው ወይስ በብሔረሰብ ቁጥራችሁ ተመዝኖ ባገኛችሁት ድምጽ? ነው ወይስ የናንተን ያህል ችሎታ ያለው ሰው ካገር ስለጠፋ? መልሱ ቀላል ነው። ሕወሀትና እናንተ የትግራዩ ልሒቃን ጠያቂና ተቆጣጣሪ የሌለበት የበላይነት ስላላችሁ ነው። የሌሎቹ ብሄረሰብ ድርጅት አባሎችና ድርጅቶች የናንተ የበታች ፓርትነሮች ስለሆኑ አንዳንዶቹም የናንተ ፍጡራን በመሆናቸው ስለሚፈሯችሁ መሆኑን ድፍን አገር ያውቀዋል። እነሱም ይናገራሉ። ከስር ቤታችሁ አውጥታችሁ የፓርቲ መሪ ያደረጋችኋቸው እነ አባዱላና እነኩማ የበላይ ወይም እኩል እንሁን ብለው ይፎካከሩናል ብለው በሳቅ እንዳይገሉን ብቻ። ይህን ገብስ ገብሱን ቀለል ስለሚል እነሳሁ እንጂ በብሔረሰብ ስብጥር ከሐይለስላሴና ከደርግ መንግስት ቀርቶ ከሚኒሊክ መንግስት ጋር ስለማይወዳደረው የሀገሪቱ ሰራዊት አመራር አላነሳሁም። ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን ቁልፍ የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራሎችና የሰራዊት አዛዦች የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጆች የያዙበትን ሁኔታ ምን ብለን እንጥራው? በሌላ ሀገር እንዲህ አይነቱን ስርዓት አፓርታይድ ነው እኮ የሚሉት። ዶክተር ደብረ ጽዮን መካድ ስለከበደውና ብልጥ የሆነ መልስ የሰጠ መስሎት የመከላከያ ተቋሙ ምን ይሰራል ብላችሁ ጠይቁ እንጂ ብሔረሰቡን አትዩ። መታየት ያለበት የሰራዊቱ አመራር ብሔረሰብ ሳይሆን ሚሺኑ ነው። ስራው ደግሞ ያገር ሰላም መጠበቅ ነው የሚል ደረቅ ሳቅ የሚያስቅ ድሪቶ ነገር ነገረን። የሰራዊቱ ተቋማዊ ስራ የሰራዊቱ መሪዎች ትግሬዎች ብቻ ይሁኑ ብሎ ያስገደደ አስመስሎት አረፈ። የድፍረቱ ብዛት ደግሞ ያስተሳሰብ ቀረጻ ስላልሰራን ነው ህዝቡ እንዲህ የሚያስበው ይላል። የህዝቡን ጭንቅላት ማጠብ ነበረብን ማለቱ ነው። የአቶ በረከት ስምዖን ቅብዥር (bizzare) አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይነበባል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራል የሚባል ህዝብ የለም፤ ክልላዊ ህዝብ ነው ያለው።አማራ በራሱ ክልል ነው ያለው። ኦሮሞ በራሱ ክልል ነው ያለው። ትግራይም በራሱ ክልል ውስጥ ነው ያለው። ትግራይ ልማቱም ውድቀቱም በራሱ ልጆች እጅ ነው ያለው። አማራ ልማቱም ውድቀቱም በራሱ ልጆች እጅ ነው ያለው። ኦሮምያ ልማቱም ውድቀቱም በራሱ ልጆች እጅ ነው ያለው። እያንዳንዱ ክልል ከለማ የራሱ ልጆቹ እየመሩት ነው የሚለማው። እያንዳንዱ ክልል ካለማ ልጆቹ ፌል (fail) ስላደረጉ ነው የማይለማው። ስለዚህ ሌላ ክልልን ሰበብ ማድረግ አይቻልም። አዲስቱን ኢትዮጵያ ባህሪዋ ይህን ነው። ሌላ ክልልን ሰበብ ማድረግ አይቻልም። ሌላ ክልልን ሰበብ ማደረግ የሚመጣው መቼ ነው? እያንዳንዱን ክልል ራሱን የማልማት ተልእኮ ሳይፈፅም ይቀርና ህዝቡን ሊጠይቀው ይጀምራል። የክልል የወረዳ አመራር ‘ለምን አላለማህኝም’ ብሎ ሲጠይቀው ‘እኔ እኮ ሞክሬ ነበር ግን እከሌ አደናቀፈኝ’ የሚል አመራር ሲኖር………”
በአቶ በረከት ሎጂክ ኦሮሚያ ወይም አማራ ክልል ውስጥ የሚኖር ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ እኖራለሁ ማለት አይችልም። ክልላዊ ነዋ። ክልላዊ ሰው እንጂ ኢትዮጵያዊ ሰው የለም። ክልሎቹን ራሳቸውን ነፃ ሀገር አስመሰላቸው። በሱ ቤት የፌዴራል መንግስቱ ውሳኔዎች ክልሉን አይነኩትም። ሕይወቱ ውስጥ አይገቡም። ጉዳያቸውን በጋራ የሚወስን ፓርላማም የላቸውም። ያለው ክልላዊ ሕዝብ ነው። የፌዴራል ህዝብ የለም። ክልሉ ውስጥ የፌደራል መንግስት አይገባም። የጋምቤላን መሬት ነዋሪ እያፈናቀለ ለህንድና ላረብ የሚቸበችበው የፌዴራል መንግስት አይደለም። ባሁኑ ሰዓት በኦሮሚያና ባማራ ግዛቶች ውስጥ ተሰማርቶ ህዝቡን እየፈጀ ያለው ሰራዊት ሁሉ የፌዴራል መንግስቱ አይደለም። በጣም የሚገርም ነው። ሰው ያውም ትልቅ ባለስልጣን ጭልጥ ያለ ውሸት ሲዋሽና ሲቀዣብር ትንሽ እኳን ትዝብት አይፈራም?
ዛሬ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ሁለት ሶስተኛው ኤፈርት የሚባል ባሰራሩ ከህጋዊነት ይልቅ ወደማፊያ ኦፐሬሺንነት የሚቀርብ የውሸት ኢንዳውመንት የሚቆጣጠረው መሆኑ የታወቀ ነው። ይህ ኩባንያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢንቨስትሜንት ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክለው ህግ ተጥሶ በህወሀት ባለቤትነት እየሰራ ያለ ኩባንያ መሆኑ ሚስጥር አይደለም። ይህን ማድረግ ካለበላይነት ይቻላል? ይህ የበላይነት ማረጋገጫ ካልሆነስ የበታችነት ትርጉሙ ምንድን ነው? የኛን ኢንቨስትመንት ያህል በኢትዮጵያ የሚወዳደር የለም ብለው በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የነገሩን እኮ አቶ ስብሐት ናቸው። ዋሸተዋል? ኢንዳውመንት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቢያውቁስ ባያውቁስ ምናባታቸው ያደርጉናል ብላችሁ ያቋቋማችሁት የፓርቲ ኩባንያ ያስተዳደር ቦርዱ ቤተመንግስት ውስጥ እየተሰበሰበ ይሰራ እንደነበር እኮ በኋላ ከመሀላችሁ የወጡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎች መጽሀፋቸው ላይ ጽፈው ነገሩን።
ስልጣን የወጣችሁ ሰሞን ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚል ውሳኔ አሳልፋችሁ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በዚያ ክፉ ጦርነት ያልተጎዳ ይመስል ለትግራይ ለይታችሁ ትደጉሙ አልነበረም እንዴ! የትግራይ ህዝብ እንደህዝብ ከዚህ ምን ያህሉ እንደተጠቀመ የሚያውቀው እግዜር ነው። ይህ ግን ባደባባይ ካለፍረት ያወጃችሁት አዋጅ ነው። እኔ እንኳን ባቅሜ ባጋጣሚ የማውቀው እኤአ በ1993 ዐመተ ምህረት ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ባጋጣሚ ባገኘሁት መረጃ አንድ ትግራይ ውስጥ ላለ የመምህራን ማሰልጠኛ ተማሪ የቦርዲንግ ወጭ 180 ብር ሲከፈል በሌላው የሀገራችን ክፍል በሙሉ ላሉት 30 ብር መሆኑን ማወቅ ችዬ ነበር። ይህን ምን አይነት እኩልነት እንበለው? ለመሆኑ አሁን ትግራይ ውስጥ የተሰሩትን አልሜዳ ጨርቃጨርቅ መስፍን ኢንጂነሪንግ መሶቦ ሲሚንቶ የኬሚካልና የማዕደን ፋብሪካዎችና ያገልግሎት ተቋሞች በብዙ ሰው መቅጠርም ይሁን በዘመናዊነት የሚወዳደራቸው ፋብሪካ የትኛው ሌላ ክልል ውስጥ ነው ያለው? ከህዝብ ባንክ ለኤፈርት ኢንቨስትመንት የተበደራችሁትን ብድር ከሰረ ብላችሁ ስትሰርዙና የኢትዮጵያ ሕዝብ ባዶ ከረጢት ይዞ እንዲቆም ማድረግ የቻላችሁት የናንተ የበላይነት ስላልነበር ነው? ይህን ለሌላ ለማን ፈቅዳችኋል? የኦሮሚያን ቡና የውጭ ንግድ የሚነግደው የናንተ ኩባንያ አይደለም እንዴ? እስኪ ሀገሪቱን የሚቀልበው ዋናው የሀብት ምንጭ ኦሮሚያና ትግራይ ውስጥ ባለፈው 25 ዓመት የተገነባው ዘመናዊ ፋብሪካ ልዩነት ይወዳደር። መስፍን እንጂኔሪንግስ የገጣጠማችኋቸውን ካሚዎኖች ለመሸጥ ገበያ የምትፈጥሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ገብታችሁ ለገዥ ብድር በማመቻቸት (በማዘዝ ማለት ይቀላል) መሆኑን ያላየንና ያልሰማን መሰላችሁ? በመንግስት በኩል ኮንትራት ሰጭ በኤፈርት በኩል ኮንትራት ተቀባይ ሁናችሁ ኮንትራት በመዋዋል የምትሰበስቡት ገንዘብስ ካለማናለብኝ የበላይነት የሚቻል ነው? በህዝብ መዋጮ ለሚሰራው ያባይ ግድብ ሲሚንቶና ሌላ ዕቃ ካላጨረታ የሚያቀርቡት የናንተ ኩባንዮች አይደሉም? አንድ ነገር ያንድ ብሔር ልሒቃንና ድርጅት ዝርፊያ ነው የሚባለው ምን ሲሆን ነው አቶ ስዩም? ሜቴክ የሚባለው የናንተ ሰዎች በበላይነት የሚመሩት ጉደኛ ድርጅት ጋ ከገባሁ ስላማልወጣ ባላነሳው ይሻላል። ጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚካሄደው የመሬት ዝርፊያ ውስጥ ሰባ በመቶ የሚሆኑት ተካፋዮች የትግራይ ተወላጆች ናቸው ማለት የምን ምልክት ነው? ለልሂቃኖቻችሁ ቅርበት (access) የበላይነታችሁን መከታ በማድረግ አመቻችታችኋል ማለት ነው። ሌላ ምን ትርጉም አለው። ርግጥ ነው ይህ ማለት መላው የትግራይ ህዝብ የዚህ ተግባራችሁ ተጠቃሚ ነው ማለት አይደለም። መምህራችሁ ቭላዲሚር ሌኒን ራሱ እንደሚለው እኮ አንድ ሌሎችን የሚጨቁን ብሔር የራሱንም ብሔር አባላት አይምርም። አሁን ተጠቂ እያስመሰላችሁ የትግራይን ህዝብ በመናጆነት ባታሰልፉት ይበልጥ ትጠቅሙታላችሁ። የትግራይ ህዝብም ረጋ ብሎ ሲያስብና ሲገባው ዝም ብሎ የሚከተላችሁ አይመስለኝም። የምናወራው በስልጣን ላይ ያላችሁትና ተባባሪያችሁ ልሒቅ ሆናችሁ ሀገራችን ላይ ስላሰፈናችሁት የበላይነት ነው ፣ ስለህወሀት ስለሚባል የትግሬዎች ድርጅት ሰራሽ የበላይነት። ይህን ዶሮ ጭራ የምታወጣውን ነገር በጥልቅ የተቀበረ ሚስጥር ማስመሰል ለናንተም ለማንም አይበጅም።
በመጀመሪያዎቹ ጥቂት አመታት የህወሀትም የበላይነት ሆነ የሀገሪቱ ጦር ባብዛኛው በትግሬ አዛዦች መመራቱ ብዙ ነውርነት አልነበረውም። በትግሉ ውስጥ የህወሀት ሚናና ተሳትፎ ትልቁ በመሆኑ ይህ አላስገረመንም። አሁን ግን ሩብ ምዕተ ዓመት አለፈው። ይሉኝታ ይዟችሁ ታሻሽሱታላችሁ ብለን ስንጠብቅ አባሳችሁት። ከሚገባ በላይ ትዕግስት ጠየቃችሁኝ ነው የሚለው አሁን ህዝቡ። ይህን በጩኸት የሚወጣ ድምጽ ሰው እንዴት መስማት ያቅተዋል?
አደገኛው የውሸት መደምደሚያ
ውሸቱ ምንም ሶፍስቲኬሽን የሌለበት ሌጣ ውሸት ስለሆነ ከላይ ያነሳሁዋቸው አይነት ጥቂት ዉሸቶችና ጥቂት አገር የሚያውቃቸው ምሳሌዎች ብቻ ጠጥቶ ርቃኑን ማስኬድ ይቻላል። እኔን ያሳሰበኝና ከማሳሰብም አልፎ ያስፈራኝ ባለስልጣናቱ ከዚህ ውሸት ላይ ተንደርድረው የሚሰጡት ትንታኔና ሀላፊነት የጎደለው መደምደሚያቸው ነው። ለዚህ ጽሁፍ ዋነኛ መነሻ የሆነኝም ከዚህ ያገጠጠ ውሸት በኋላ እነ አቶ ስዩም መስፍን የሚሰጡት ትንታኔና ሊከተል ይችላል የሚሉት “የሰይጣን ጆሮ አይስማው” የሚያሰኝና በነሱ ቤት ሕዝብ ማስፈራሪያ ይሆናል ብለው የሚጠቅሱት ዘግናኝ የታሪክ ምስስል (analogy) ነው። አቶ አባይ ጸሐዬ ይህንኑ ውሸት ከተናገረ በኋላ የጠቀሰልን ምሳሌ የሩዋንዳ እልቂት ጉዳይ ነው። እንደሩዋንዳ ልንሆን እንችላለን እያለ ነው የሚያስፈራራን። አቶ ስዩም መስፍን ደግሞ ስለ አይሁዶች ሆሎከስትና የናዚዎች ጭካኔ በሰፊው ነገረን። የመንግስት ቃል አቀባዩ ቢሮ ደግሞ ድረ ገጽ ላይ የሶሪያን የፈራረሱ ከተሞች ፎቶግራፍ እየለጠፈ ያስፈራራናል። ትግሬ ያልሆነውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በጅምላ የትግሬ የበላይነት አለ ይላል ብለው ከከሰሱ በኋላ ሩዋንዳ የሆነውንና የጀርመን ናዚዎች ያደረሱትን ጥፋት ሊያደርሱ የተዘጋጁ ኢትዮጵያውያን አሉ ነው የሚሉን ባጭሩ። ለዚህ ሰለባ የሚሆነው ደግሞ እነሱ እንደሚሉት የትግራይ ህዝብ ነው። የፈረደበትን የትግራይ ህዝብም አደጋ መጥቶብሀልና ሌሎች ወገኖችህን ፍራ ከሁዋላችን ሆነህ ለመዋጋትም ወይም ሌሎች ወገኖችህን ለመፍጀት ተዘጋጅ ነው የሚሉት። ሊከሱ የፈለጉት ደግሞ አሁን ራሳቸው እየቀጠቀጡት ያለውን የኦሮሞና ያማራ ህዝብ መሆኑ ነገሩን አሳዛኝ ስላቅ ያደርገዋል። ለመሆኑ ዛሬ በኢትዮጵያ ናዚ ናዚ የሚሸተው ማነው?
እነዚህ ሰዎች ለነዚህ ዋና ጥያቄዎች ምን መልስ ይሰጡ ይሆን። ለመሆኑ ዛሬ በኢትዮጵያ የናዚዎቹን የሚመስል ቁመና ላይ ያለው ማነው? ማለትም በኢትዮጵያ ዛሬ እንደ ናዚዎቹ ባለጠማንጃው ባለስልጣኑና ወታደር የሚያዘው ማነው? እየገደላችሁት ያለው ኦሮሞና አማራ ናዚዎቹን ይመስላል ወይስ ስለባዎቹን አይሁዶች? በየክፍለ ሀገሩ የሠራችኋቸው ኦሮሞና አማራ ያጎራችሁባቸው አውችዊትዝን (Auschwitz) የመሳሰሉ የሰው ማሰቃያ ኮንሴንትሬሽን ካምፖች ከማን ሥራ ጋር ይመሳሰላሉ? አማሮችና ኦሮሞ እስረኞቻችሁ የታጎሩባቸውን የብር ሸለቆና የሁርሶ ካምፖችን የመሳሰሉትን ማለቴ ነው። የናዚዎቹ ወይስ ያለቁት አይሁዶች መታጎሪያ ነው የሚመስሉት? ተብለው ቢጠየቁ አቶ ስዩም መስፍን ምን እንደሚሉ አላውቅም። ልጇን ገድሎ እናትዮዋን ልጅሽ ሬሳ ላይ ተቀመጭ ብሎ የሚቀጠቅጠው ነው ናዚ የሚመስለው ወይስ የልጇን ሬሳ ታቅፋ ሰውነቴ እስኪሰባበር ደበደቡኝ የምትለው እናት? መሀል አራዳ አዲስ አበባ ያለው ማዕከላዊ የተባለውን የሰው መጥበሻ የሰቆቃ ማዕከል የትኛው ብሔረሰብ ሰዎች ናቸው የሚያስተዳድሩት? እዚያ ተቁዋም ውስጥ ዋናው የሹሞቹ ቋናቋ ትግሪኛ መሆኑን አገር እንደሚያውቅ እነ አቶ ስዩም መስፍን የሚያውቁም አይመስሉም። ከዚያ የወጡ ሰዎችን አቶ ስዩም ቢጠይቁ ማን ናዚ እንደሚመስልና በቀላሉም መሆን እንደሚችል በቅጡ ይረዱት ነበር። እነ አቶ ስዩም መስፍንና እነደብረጽዮን ለምን እንድ ጊዜ ቃሊቲ ወይም ቂሊንጦ ብቅ አይሉም። የወህኒ ቤቱ ሀላፊዎች ከየትኛው ብሔረሰብ ናቸው? ታሳሪዎቹስ? ይትኛው ብሔረሰብና የፖለቲካ ድርጅት ሰዎች ናቸው ወደ ናዚዎቹ የተግባር ስምሪት የሚቀርቡት? ለመሆኑ ከዚህ የተለየ ያንድ ጎሳ ድርጅት የበላይነትንስ የሚያሳይ ምን ልታመጡ ነው ተብለው ቢጠየቁ ምን ሊሉን ነው?
የትግራይ ህዝብ ላይ የተነጣተረ ጥላቻ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ያለቀለት መረጃ አላየንም። ዉሱንም ቢሆን አለ ከተባለ ግን ህወሀት ሁሉንም ቦታ ለመቆጣጠር ሲል በፈጠረው ስራ የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። የፖሊስ ጣቢያው አዛዦች ትግሬዎች፣ የወህኒ ቤቱ አዛዞች ትግሬዎች፣ የግርፊያው መስሪያ ቤት አዛዦች ትግሬዎች ሆነው መታየታቸው የሚፈጥረው መጥፎ ስዕል (Image) አለ። ይህ ኢሜጅ በራሱ ቁጣ (resentment) ቢፈጥር የሚያስገርም አይመስለኝም። እኔ ከሀገር ከወጣሁ ስለቆየሁ ባይኔ ያላየሁት ነገር ግን በተደጋጋሚ ከብዙ ሰዎች የምሰማው ብዙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ከመጠኑ በላይ (Disproportionate) የሆነ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር አለ ሲባል እሰማለሁ። ከተለያዩና ከብዙ ሰዎች ስለምሰማው ውሸት ነው ለማለት አልችልም። አየር መንገድ፣ ኢሚግሬሺን መስሪያ ቤት፣ ጉምሩክ ወዘተ ያላቸው ከሌላው የላቀ ቁጥር ሌሎች ብሔረሰቦች ላይ ጥሩ ስሜት እንደማይፈጥር ለማወቅ ብዙ መማር አያስፈልግም። ችግሩን ማስወገድ የፈለገ ሰው ይህንን ማስተካከል ነው። ሕዝቡ እኮ ዛሬ ባመጸባቸው ቦታዎች ሁለተኛ ዜግነት መረረኝ እያለ ነው። ይህን በተግባር እንጂ በውሸት መቀየር አይቻልም። የትግራይ ህዝብ በጅምላ የዚህ መድሎ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ከሌሎቹ ብሔረሰቦች ግን ለመንግስት የተሻለ ቀረቤታ (access) አለው ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን አሉ። የወያኔዎቹ ሹሞች የሚክዱት የበላይነት ትርጉምም ይህ ነው። ድህነት በበዛበት ሀገር ውስጥ ባለው የስራ እድል ሽሚያ ያንድ ብሔረሰብ አባላት እድሉን በማግኘት በልጠው ከታዩ ሌላው ከንፈሩን ይነክሳል። ይህ ይህን ያህል ለሁላችንም ሊገባን ይገባል። ሰብዓዊ ስሜት ነው። የህወሀት ሰዎች የአማራ ለማኝ ባማርኛ በመለመኑ ምክንያት የትግሬውን ለማኝ ይጨቁነዋል እያሉ አልነበር ስታሊኒዝምና ማርክሲዝም ሲያስተምሩ የነበሩት። ነገሩ እኮ ለማያውቅሽ ታጠኝ ነው። የዚያ ሁሉ የህወሀት ጸረ አማራ ዘፈንና ስነጽሁፍ መሰርቱስ ይህ አይደል። ግዙፉ ዕውነት ይህ ነው።
በቅርቡ ከትግራይ ማህበረሰቦች ጋር ተደረጉ የተባሉትን ግጭቶች እያጋነኑ ለመጠቀም መሞከር ለዘለቄታው ሀገር የሚጎዳ ነገር ነው። በተለይ በህዝብ መገናኛ ይህን ወሬ የሚነዙት ባለስልጣኖች ሀላፊነት የጎደለው ስራ እየሰሩ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። መኖር የሌለበት ግጭት ለመፍጠር የሚደረግ የከይሲ ሙከራ ነው። ቢያንስ ከአማራ ክልል ባለስልጣኖች የምንሰማው ህዝቡ ቁጣውን የገለጠው ከመንግስት ጋር ሆነው አጠቁኝ ባላቸው በርካታ አማሮችና ጥቂት ትግሬዎች ላይ እንጂ ትግሬዎችን በዘር እየለየ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘር ተጣልቶ ለመጋደል የሚያስችል የተፈጥሮም የታሪክም መሰረት የለውም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሩዋንዳም ሆነ የሌላ ሀገር አይነት የዘር ግጭት የሚመጣው ባለስልጣኖች የራሳቸውን ስልጣን ለመጠበቅና የዘረፉትን ሀብት ለመንከባከብ ሲሉ ሊፈጥሩ በሚችሉት እኩይ ተግባር ምክንያት ብቻ ነው።
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሀትና የትግራይ ልሂቃን የበላይነት ያንፈራጠጠበት ሁኔታ አለ። ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዛሬ የተደራጀ ለአፓርታይድ የቀረበ (Instituionalized and systematic) ብሔረሰብ ጭቆና አይታ አታውቅም። ይህ የትም ቦታ ቢሄዱ አግጦ የሚታይ ሊደብቁት የማይቻል እውነት ነው። ይህን በትልልቅ ስልጣን ላይ የተቀመጡት ሰዎች እነ አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ መሆናቸው አይቀይረውም። በከፍተኛ ስልጣን ላይ ካሉት ሰዎች በቁጥር የሚበልጡት ትግሬ ያልሆኑ ሰዎች ናቸው የሚለው አባባል ዕውነታውን አይቀይረውም። የሀገሪቱ የምር የሀይል ማዕከል የት እንዳለ ትንንሽ ልጆች ሳይቀሩ ያውቁታል። ሰራዊቱን ኢኮኖሚውንና ደህንነቱን ማን እንደሚቆጣጠረውና በሌላው ብሔረሰብ ተወላጅ ጉያ ቁጭ ብለው ሐይለማሪያምን የመሳሰሉትን ሹማምንት የሚቆጣጠሩት እነማን እንደሆኑ አገር ያውቃል። ችግርና ጥፋት የሚያስወግደው ይህንን ነገር እያፍረጠረጡ በመወያየትና በማረም እንጂ በመሸምጠጥ አይደለም።
ህዝባችን በራሱ በመሀሉ ለጠብ የሚሆን እንደሩዋንዳ የሚያጫርስ ምንም ምክንያት የሌለው ድሀ ህዝብ ነው። አብሮ መኖር ያውቅበታል። ዛሬ በየቤተሰባችን ካንድ በላይ ብሔረሰብ ያለን ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ሚሊዮኖች ነን። ስልጣን ላይ ያላችሁት ሰዎች በተለይ የህወሀት መሪዎች ይህን ለራሳችሁ ስትሉ የፈጠራችሁትን “ርዋንዳ መጣባችሁ ሂትለር መጣባችሁ” ማስፈራሪያ ይዛችሁ ሂዱልን። በሰላም ከተዋችሁን በዝርፊያ ጭምር ያገኛችሁትን ንብረት መርቀን ልንተዋችሁ የምንፈልግ ኢትዮጵያውያን ብዙ ነን። ለሰላማዊ ለውጥ ከተመቻችሁን ይህን እንከፍላለን። ሕዝቡን ልቀቁት። የትግራይ ህዝብንም ልቀቁት። ከወገኖቹ ጋር በሰላም ይኑርበት።
Fekadeshewakena@yaho
SOURCE – WELKAIT.COM
?>