ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ዜጎቿንም ሆነ አጋር ምዕራባውያን አገሮችን እያስጨነቀ ይገኛል፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ያነገቡ ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ ጥያቄያቸውን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ወደዚህ አጣብቂኝ ውስጥ እንዴት ገባ? የሕዝብ ተቃውሞ ገዢውን ፓርቲ ኢሕአዴግ ወዴት እየገፋው ነው? ከዚህ ለመውጣት መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ያሰቧቸው የለውጥ ዕቅዶችስ ምን ያህል ያዋጣሉ?

ምርጫ 97 እና 2002 እንደ መነሻ

በ1983 ዓ.ም. የተፈጠረውን የሥርዓት ለውጥ ተከትሎ የመንግሥት ሥልጣንን በሕዝብ ምርጫ ለማግኘት ላለፉት 20 ዓመታት ከተካሄዱት አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች፣ በ1997 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በአንፃራዊነት የተሻለ እንደነበር የውጭ ታዛቢዎችና በፖለቲካ ፉክክሩ ያለፉ ይመሰክሩለታል፡፡ ከምንጊዜውም የተሻለ የፖለቲካ ምኅዳር፣ ግልጽና የቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ያገኘ የፖለቲካ ክርክር፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት የመራጩን ንቃተ ህሊና በማጎልበት ረገድ በነፃነት ሚናቸውን የተጫወቱበት፣ እንዲሁም በገዢው ፓርቲ በኩልም አንፃራዊ ዴሞክራሲያዊነት የታየበት እንደነበር ያለ ልዩነት በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

በምርጫው ውድድር የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተበታትነው የሕዝብ ድምፅን እንዲበታተን ከማድረግ ይልቅ፣ በጥምረት በመሳተፋቸው ከአሥር ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ የቆየውን ገዢውን ፓርቲ ኢሕአዴግን አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱበት ወቅት ነበር፡፡ ምርጫውን በሚያስፈጽመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በይፋ የተገለጸው ውጤት በጥምረት ገዢውን ፓርቲ የተወዳደሩት ተቃዋሚዎች አስገራሚ ውጤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቢያገኙም፣ ፓርቲዎቹ እርግጠኛ በነበሩበት ውጤትና በይፋ በተገለጸው ውጤት መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት ለመቀበል በመቸገራቸው ከውጤቱ በኋላ መንግሥት በወሰዳቸው አንዳንድ ጤነኛ በማይመስሉ ዕርምጃዎች ምክንያት ፓርላማውን እንደማይቀላቀሉ መግለጻቸው ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ቀያይሯል፡፡

የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቱ እንደተጠናቀቀ የቀድሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማድረግ ለአንድ ወር መከልከሉን ገለጹ፡፡ በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ዕዝ ተቋቋመ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ላይ ወከባና ጫና ስለመድረሱ ሪፖርቶች መውጣት ጀመሩ፡፡ በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ ሙሉ በሙሉ ያሸነፈው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አዲስ አበባን መረከብ አለመረከቡ ሳይታወቅ፣ በአዲስ አበባ ሥር የነበሩ አንዳንድ ቢሮዎች ተጠሪነት ወደ ፌዴራል መንግሥት እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ በተደነገገው መሠረት ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም በሕግ እንዲወሰን እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ፡፡ በመቀጠልም ሕዝቡን ለአመፅ አነሳስተዋል እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ለእስር ተዳረጉ፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ መንግሥት መሥርቶ ሥልጣኑን ካረጋጋ በኋላም ቢሆን፣ ቀድሞ የፈቀደውን ዴሞክራሲ ያህል መክፈት እንዳልቻለ ይተቻል፡፡ የአባላት ቁጥሩን በአንድ ጊዜ በአራት ሚሊዮን እንዲጨምር በማድረግ የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ለፖለቲካና ማኅበራዊ ፋይዳዎች መጠቀም ጀመረ፡፡ የምርጫ አዋጁ ማሻሻያ አሁንም የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት ማስጠበቅ አልቻለም በሚል ትችት ተጠናክሮ ቀረበበት፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ በአገሪቱ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ጉልህ ሚና የነበራቸውን ሲቪክ ማኅበራት አንኮታኮተ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለፉት አምስት ዓመታት ተጠናቀው ምርጫ 2002 ዓ.ም. ገባ፡፡ በዚህ ወቅት የተሻለ ተፅዕኖ የነበረው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ የተባለው ፓርቲ ቢሆንም፣ የፓርቲው አመራር የነበሩት ወይዘሮ ብርቱካን ሚደቅሳ ቀደም ሲል የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በይቅርታ የተለቀቁበትን ሥርዓት ‹‹ይቅርታ አላልኩም ብለው ክደዋል›› በሚል ክስ በድጋሚ ወደ ወህኒ ተወረወሩ፡፡ ይህም በውጤቱ አንድነት ፓርቲ መሠረቱ እንዲፈራርስ እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተካሄደው የ2002 ዓ.ም. ምርጫን ኢሕአዴግ ከሁለት ወንበሮች ውጪ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረው፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የምርጫ 97 አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገባ እንጂ ምርጫ 2002 በዚህ ሁኔታ የማሸነፍ ዕቅድ እንዳልነበረው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት ዋና አዘጋጅ እንደነበሩ በሚነገርላቸው አቶ መለስ ዜናዊ እንደጻፉት የሚታመነው ጽሑፍ፣ ምርጫ 2002 ትልቅ ድል የተገኘበት እንደሆነ ይከራከራል፡፡ በአዲስ ራዕይ መጽሔት ላይ የታተመው ይኼው ትንታኔ በርካታ ሌሎች ነጥቦችንም ይዳስሳል፡፡

በምርጫ 2002 የተገኙት ድሎች ሁለት መሆናቸውን ይኼው ጽሑፍ ይገልጻል፡፡ አንደኛው በጥላቻና ቂም በቀል የተመሠረቱና ይህንኑ የሚያራምዱ ፓርቲዎች ለሕገ መንግሥቱ አደጋ የማይሆኑበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል የአውራ ፓርቲ ሥርዓትን አገሪቱ ውስጥ የፈጠረ በመሆኑ የተረጋጋ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አገሪቱ ውስጥ ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን እንዳበጀ ይተነትናል፡፡

ኢሕአዴግ ለአራት ተከታታይ ጊዜያት በምርጫ እንዳሸነፈ የሚያስታውሰው ይኼው ጽሑፍ፣ ኢሕአዴግ በምርጫ 2002 አስገራሚ ድል ያስገኙለትን መሠረታዊ ባህሪዎችን ጠብቆ ከቀጠለ የሚቀጥሉትን አንድ ሁለት ምርጫዎች ምናልባትም ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ሊያሸንፍ እንደሚችል ይተነብያል፡፡ ስለሆነም በተግባር በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ሥርዓት በስዊድንና በጃፓን ታይቶ እንደነበረው ዓይነት የአውራ ፓርቲ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ነው ብሎ መከራከር እንደሚቻል ይጠቅሳል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢሕአዴግ በምርጫ 2002 አስገራሚ ድል ቢያገኝም፣ ይህንን ድል ያረጋገጠበትን ጠንካራ ጎኖች ካጣ በሚቀጥለውም ምርጫ ሊዘረር እንደሚችል ጽሑፉ ያስረዳል፡፡ ‹‹ይልቁንም እነዚህን ጠንካራ ባህሪያቱን ካጣ ሕዝቡ አንቅሮ የተፋቸው ፀረ ሕገ መንግሥት ፓርቲዎች ሳይቀሩ ሊያንሠራሩና የምርጫ 97 ሁኔታ ሊደገም ይችላል፤›› ሲልም ያክላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከውድቀታቸው ተምረው ጉድለቶቻቸውን አስተካክለው ከመጡ፣ በአጭር ጊዜ ተጠናክረው ኢሕአዴግን ሊያሸንፉት ይችላሉ ብሎ መከራከር እንደሚቻልም በትንታኔው ተመልክቷል፡፡

ሁለቱም መከራከሪያዎች ጠንካራ ጎን እንዳላቸው የሚጠቅሰው ይህ ጽሑፍ ዞሮ ዞሮ ልዩነቱ የሚያጠነጥነው በሁለት ጉዳዮች ላይ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ጠንካራ ጎኖቹን ጠብቆ ማቆየት ይችላል ወይስ አይችልም በሚለው ጉዳይ ላይና ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ከጥላቻና ከቂም በቀል ፖለቲካ ነፃ አውጥተው በምን ያህል ፍጥነት ተጠናክረው ይወጣሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ነው ልዩነቱ፤›› የሚለው ይኼው ጽሑፍ፣ ‹‹ሁለቱም አስተያየቶች ስለመጪው ሁኔታ መላምት የሚያስቀምጡ ስለሆኑ ወደፊት የሚሆነውን ማንም ሰው በእርግጠኝነት ማወቅና ያ ነው ትክክል ያ ደግሞ ስህተት ነው ማለት አስቸጋሪ ይሆናል፤›› በማለት ይገልጻል፡፡ የሚኖረው አማራጭ እስካሁን ድረስ ያሉት አዝማሚያዎች ላይ በመመሥረት የተሻለ የሚመስለውን መላምት ማስቀመጥ የሚበጅ መሆኑን በማስረገጥ አዝማሚያዎቹን ወደ መገምገም ይሻገራል፡፡

‹‹ከዚህ በመነሳት ስንገመግመው ምንም እንኳን ኢሕአዴግ ጠንካራ ጎኖቹን ጠብቆ እንዲቀጥል ምንም ዓይነት ዋስትና የሌለው ቢሆንም፣ አዝማሚያው ባህሪውን ጠብቆ ለመቀጠልና ይበልጥም ለማጠናከር ከፍተኛ ትግል እንደሚያካሂድ የሚያመለክት ነው፡፡ ስለሆነም ኢሕአዴግ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን ሊገመት በማይችል መልኩ ይበላሻል ብሎ ከመተንበይ ይልቅ፣ በተፃራሪ ረዘም ላለ ጊዜ ባህሪውን እንደጠበቀ ይቆያል ብሎ መተንበይ ይበልጥ አሳማኝ ይሆናል፤›› በማለት ጽሑፉ ይደመድማል፡፡ በተመሳሳይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጥላቻና ከቂም በቀል ፖለቲካ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አፅድተው ኢሕአዴግ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘባቸውን መስመሮችና ስትራቴጂዎች የራሳቸው አድርገው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናክረው፣ ከኢሕአዴግ ከራሱ የበለጡ ኢሕአዴጎች ሆነው ይወጣሉ ብሎ ከመተንበይ ይልቅ ይህ ሒደት በተነፃፃሪ ረዘም ያለ ጊዜ ይጠይቃል ብሎ መተንበይ ይበልጥ አሳማኝ እንደሚሆን በአዝማሚያ ትንተና የደረሰበት ሁለተኛው ነጥብ ነው፡፡ ‹‹በመሆኑም ኢሕአዴግ በቀጣዮቹ የተወሰኑ ምርጫዎችም አሸናፊ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው ማለት ይቻላል፤›› በማለት የወደፊት ሁኔታዎችን ለመመልከት ሞክሯል፡፡

ምርጫ 2007ን ተከትሎ

ከምርጫ 2002 በኋላም ቢሆን ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የቀጣይ ዓመታት ሥልጣኑንና የልማታዊ ዴሞክራሲን እንጂ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ፍላጎት የማረጋገጥ ፍላጎት እንደሌለው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተለያዩ ጊዜያት ገልጸዋል፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያትም በርካታ ጋዜጠኞች ሥራቸውን በመሥራታቸው ብቻ በፀረ ሽብር ሕጉ አዋጅ ወደ ወህኒ ቤት መወርወራቸውን፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም የወጣቶች ስብሰብ እንደሆነ የሚነገርለት ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ በነፃነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻሉ በተለያዩ ሁኔታዎች ተገልጿል፡፡

በዚህ ሁኔታ የተካሄደው ምርጫ 2007 በዓለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አስገራሚ ሊሆን የሚችለውን የመቶ በመቶ ድል አስመዘገበ፡፡ ኢሕአዴግ 547 መቀጫዎች ያሉትን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ፡፡ ይሁን እንጂ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በ2007 ምርጫ ያገኘውን ውጤት ይዞ መንግሥት ቢመሠርትም በወሩ በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎች የሕዝብ ተቃውሞ ገነፈለ፡፡ የዚህ ተቃውሞ መነሻ የአዲስ አበባና የዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ የማስፋፋት ውጥን አለው በሚል የተቀሰቀሰ ነው፡፡ ተቃውሞው ወደ ደም መፋሰስ ሲያመራና የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ማስተር ፕላኑን መሰረዙን ገለጸ፡፡ ሁኔታዎች ለተወሰነ ጊዜ በረድ ያሉ ቢመስልም በአማራ ክልል ከወልቃይት የወሰን ጥያቄ ጋር ተያይዞ ከተነሳው ተቃውሞ ጋር ተገናኝቶ የኦሮሚያ ተቃውሞው ዳግም ፈነዳ፡፡

በአሁኑ ወቅት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በደቡብ ክልል የኮንሶ ሕዝብ ከሰገን ሕዝብ በመነጠል ራሱን ችሎ የመተዳደር ጥያቄ አንስቷል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ዓይታ የማታውቀው ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ የተቃውሞ መነሻ የሆኑ ምክንያቶች እየጠፉ የኢሕአዴግ አገዛዝ ‹‹በቃኝ›› ወደሚል ጥያቄ ተሸጋግሯል፡፡

የሕዝብ ተቃውሞ ኢሕአዴግን ወዴት እየገፋ ነው?

ከላይ የተገለጸውና አቶ መለስ ዜናዊ እንደጻፉት የሚታመነው ጽሑፍ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት ማግሥት የተጻፈ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የአውራ ፓርቲ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየተመሠረተ መሆኑንና ይህም ለተተኪ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ምቹ ሁኔታን እንዳበጀ ገምቷል፡፡ ኢሕአዴግ በወቅቱ የነበሩትን ጥንካሬዎችን ይዞ ሊቀጥል የሚችል እንደሆነ ከአዝማሚያዎች በመነሳት የደመደመው ይህ ጽሑፍ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከጉድለታቸው ተምረውና ከቂም በቀል ፖለቲካ ፀድተው ኢሕአዴግን ይጥሉታል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን በመጠቆም፣ ኢሕአዴግ ረዘም ላለ ጊዜ ሥልጣን ላይ እንደሚቆይ አዝማሚያን መሠረት ያደረገ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ትንታኔ በሕዝብ ውስጥ ያለን አዝማሚያ መመልከት እንዳልቻለ መረዳት ይቻላል፡፡

በዚህ ወቅት ከሰሜን እስከ ደቡብ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ የተፈተነው ኢሕአዴግና የኢሕአዴግ መንግሥት የተቃውሞው መነሻ ምክንያትና ተገቢ ናቸው ያላቸውን ምላሾች መመለስ ጀምሯል፡፡ በኢሕአዴግ ትንተኔ መሠረት የተቃውሞው መነሻ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም አመራሩ ሥልጣንን ለግል ጥቅምና ብልፅግና ማዋል የሚሉት ምክንያቶች ናቸው፡፡

ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተይዞ የተነሳውን የወሰን ለውጥ ጥያቄም የአማራና የትግራይ ክልል አመራሮች በወቅቱ መመለስ ባለመቻላቸው የፈነዳ እንደሆነ የፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ማሻሻያ እንደሚያደርግም በይፋ አስታውቋል፡፡ አንደኛው የአገሪቱን የምርጫ ሕግ ማሻሻል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከገዢው ፓርቲ ነፃ የሆኑ ልሂቃን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ጥቅም መመለስ ነው፡፡

እንደሚሻሻሉ የተገለጹት ነጥቦች ከምርጫ 97 በኋላ ፓርቲው ከመጣበት መንገድ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የምርጫ ሕጉ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ማሻሻያ የተደረገለት ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ 30 የሚሆኑ የማሻሻያ ሐሳቦችን አቅርቦ ነበረ፡፡ መሠረታዊ የመሻሻያ ነጥቦቹ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትን ጨምሮ ቢያቀርቡም ተቀባይነትን አላገኙም፡፡ የምርጫ 97 ውጤት አዲስ አበባ ላይ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉን ተከትሎ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅምን የመመለስ ጥያቄ በሕግ ለመመለስ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለአሥር ዓመታት አዳፍኖ የቆየው ገዢው ፓርቲ፣ አሁን ጥያቄውን ለመመለስ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥት መዋቅሮች የግድ በኢሕአዴግ ፖለቲከኞች ብቻ መሞላት የለባቸውም የሚሉ የተቃዋሚዎችም ሆነ የምሁራን ምክርን ወደ ጎን ሲል እስከ መጋቢት 2008 ዓ.ም. ድረስ ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት ይኸው ጥያቄ ተነስቶላቸው፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ዝግጁ አይደለንም፤›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ተንታኞችም ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ የመጣበትን የተበላሸ መንገድ እያረመ ይመስላል ብለዋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኝና የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ለመለወጥ መሞከር ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን ላለው ተቃውሞ ምን ፋይዳ አለው? የሕዝቡ ጥያቄ ምንድነው? በሚለው ላይ መግባባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ ላለው ችግር ራሳቸው ትርጉም ሰጥተው መልሱንም ራሳቸው ለመመለስ እየሞከሩ ነው፤›› የሚሉት አቶ ሙሼ፣ ‹‹በዚህ መንገድ ፋታ ሊገኝ ቢችል እንኳ እንደገና እንደማይገነፍል ማረጋገጫ የለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ወደ መንግሥት መዋቅር ይገባሉ የሚባሉት ከፖለቲካ ነፃ የሆኑ ግለሰቦች እነማን ናቸው?›› ብለው የሚጠይቁት አቶ ሙሼ፣ ምርጫ 97ን ተከትሎ ኢሕአዴግ ያቋቋመው ባለአደራ አስተዳደር ውስጥ እነማን እንደተካተቱ ይታወቃል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላው የገቨርናንስና ዴቨሎፕመንት መምህር በበኩላቸው፣ የችግሩ ምንጭ ይኼ ነው ብሎ አንጥሮ መለየት እንደሚያስፈልግ በተመሳሳይ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በእኔ እምነት በዚህ መንገድ የሚገለሉ የገዢው ፓርቲ ልሂቃንን ያስቆጣል፡፡ በቡድን ተደራጅተው ሥርዓቱን ወደ መገዝገዝ እንዳይገቡ ሥጋት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

የምርጫ ሕጉን ማሻሻል ጥሩ ቢሆንም አሁን ላለው ተቃውሞ መፍትሔ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ የገለጹት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ምርጫ የሚደረገው በሚቀጥለው ዓመት ቢሆን ኖሮ ያስኬዳል፡፡ ነገር ግን ገና አራት ዓመታት ለሚቀሩት ምርጫ አዋጁን ማሻሻልና አሁን ካለው ተቃውሞ ጋር የማገናኘት ተገቢነቱ አይታየኝም፤›› ብለዋል፡፡

በሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ዶ/ር ፀጋዬ ረጋሳ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ንቅናቄ አቀንቃኝ ሲሆኑ፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም አስመልክተው፣ “The Special Interest: The Affirmation of Denial” በሚል ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ አዲስ አበባ ኦሮሚያ ውስጥ ብትሆንም የኦሮሚያ እንዳትሆን ተደርጋለች የሚል መሠረታዊ ነጥብ በማንሳት ይከራከራሉ፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) መሠረት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም የማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚነት፣ የጋራ አስተዳደርና ሌሎች በሕግ የሚወሰኑ ተብለው ነው የተቀመጡት፡፡

ማኅበራዊ አገልግሎትን በተመለከተ በኦሮሚያ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ አበባ እንዲቋቋሙ ማድረግ፣ የኦሮሞ ባህልን በአዲስ አበባ ማጎልበት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንደሚገባ፣ የኦሮሚኛ ቋንቋ በአዲስ አበባ የአማርኛ አቻ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ማድረግና ሌሎችንም መመለስ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

ሌላኛው መሠረታዊ ጥያቄ የጋራ አስተዳደርን የተመለከተ ፖለቲካዊ መብት በመሆኑ፣ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ጥያቄውን ለመመለስ የጋራ የመሬት አስተዳደር እንዲኖር መፍቀድ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ተጠሪነት ለፌዴራል መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ተጠሪ እንዲሆን ማድረግና ሌሎቹንም ነጥቦች ያነሳሉ፡፡

ነገር ግን የፕሬስና የኢንፎርሜሽን ነፃነትን ለማጎልበት የወጣው ሕግ እንዴት የፕሬስ ነፃነት ላይ ገደብ እንዳደረገ፣ የምርጫ መብቶችን ለማስፋት በሚል የወጣው ሕግ እንዴት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫን በኢትዮጵያ እንዳቀጨጨ፣ የሲቪክ ማኅበራት እንዴት በሕግ እንዲንኮታኮቱ እንደተደረጉ የተመለከተ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በሕግ ይመለሳል ብሎ ተስፋ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

Leave a Reply