September 22, 2016
ገና እንደተመሰረተ ኢሳት የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሚልክለትን መግለጫዎች ሁሉ ወደጎን በመግፋት የሚታወቅ ነዉ ሲሉ የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ም/ሀላፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። መኢአድ የሚልክለትን መግለጫዎች ሁሉ እያፈነ ወደ ቅርጫት ሲወረውር ከርሟል አሁንም ያንኑ ድርጊቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ም/ሀላፊ አቶ ለገሰ ወ/ሃና በምሬት ኢሳትን ወቅሰዋል።
በሚያሳዝን እና በሚያሳፍር ሁኔታም የአማራ ህዝብ ተጋድሎ በመላዉ ጎጃም እና ጎንደር ሲቀጣጠል ደግሞ ወያኔ በዋናነት አሳዶ ለማጥፋት የተነሳዉ መኢአድን ነዉ። እናም ኢሳት አሁን በመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ላይ ወያኔ ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ የድርጅቱን ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረን: የድርጅቱን የህዝብ ግንኙነት ም/ሀላፊ አቶ ለገሰን : እንዲሁም በርካታ አመራሮችን ወያኔ እያሳደዳቸዉ እንዳለ መግለጫ ሲላክለት አፍኖ የሚያስቀረዉ የመኢአድ ህልዉና መጥፋት እና መክሰም አለበት የሚል ዉሳኔ ላይ በመድረሱ ይመስላል ሲሉ አቶ ለገሰ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በቅርቡም ስለ ደራሲ ያሬድ ግርማ ሀይሌ (የመኢአድ የሠሜን ጎንደር አመራር) እንዲሁም ስለ አቶ አለምነህ ዋሴ (ከመአሕድ ጀምሮ የሠሜን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ሰብሳቢ) መታፈን መግለጫ ሲላክላቸዉ መግለጫዉን አፍነዉታል ሲሉ ገልጸዋል። ወያኔ የመኢአድን አባላት እና አመራሮች ሲያፍን ኢሳት ደግሞ መኢአድ ላይ የሚደርሰዉን የግፍ በደል ያፍናል።በመላዉ አለም እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለዉ ህዝብ ስለ መኢአድ ተጋድሎ መረጃ እንዳያገኝ ሆን ብሎ የምንልክለትን መረጃ ሁሉ ወደ ቅርጫት ይወረውረዋል ሲሉ አብራርተዋል።
ኢሳት ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰዎች ምንነቱ በማይገባ ምክንያት መኢአድ ከስሟል: መኢአድ መንግስት ዘግቶታል የሚል ወሬ መንዛት እንደሚመርጡ የገለጹት የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ም/ሀላፊ አቶ ለገሰ መኢአድ ሱቅ በደረቴ አይደለም። ወያኔ ሲፈልግ የሚዘጋዉ ወይም የሚከፍተዉ ድርጅት አይደለም። መኢአድ ሲመሰረትም ወያኔ ስለፈቀደ አይደለም የተመሰረተዉ። ኢትዮጵያዉያንን ከወያኔ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ነጻ ለማዉጣት የተቋቋመ ድርጅት ነዉ ሲሉ አብራርተዋል።
መኢአድ በደም እና በአላማ ተላቁጦ የተፈጠረ ድርጅት ነዉ። መኢአድ በወጀብ እና በመከራ መሃከል ማለልፍ የለመደ: በደም ታሪክ ከሚጽፉ አባቶች አብራክ በተወለዱ ልጆች በጥልቅ መሰረት ላይ የቆመ ድርጅት መሆኑን ወያኔም ሆነ ኢሳት ይወቀዉ ሲሉ መራራ ብስጭታቸዉን ገልጸዋል።
መኢአድ ኢትዮጵያን ነጻ ሳያወጣ ማንም ሊያከስመዉ የሚችል ድርጅት አይደለም ሲሉም አብራርተዋል። በተያያዥም በመኢአድ ላይ በኢሳት ዙሪያ ያሉ ሰዎች መኢአድ የአማራ ድርጅት ነዉ ስለዚህ መክሰም ያለበት ድርጅት ነዉ የሚል ወንጀለኛ ክስ እንደሚያቀርቡበት አቶ ለገሰ አብራርተዋል። መኢአድ የመላዉ ኢትዮጵያዉያን ድርጅት መሆኑን የሚያረጋግጠዉ ግን መኢአድ በደቡብ ክልል ብቻ ከሶስት መቶ ሽህ አባላት በላይ አባላት ያፈራ ድርጅት መሆኑን ኢሳትም ሆነ ወያኔ ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። ሌላዉ ቀርቶ መኢአድ የአማራ ድርጅት ነዉ ቢባል እንኳን ፍትሃዊ የሚዲያ ሽፋን እንዳናገኝ ኢሳት በኛ ላይ የመረረ ጥላቻ ለምን ሊኖረዉ እንደቻለ አናዉቅም ሲሉ በኢሳት አቋም ግራ መጋባታቸዉን ተናግረዋል። ይሄን የተሳሳተ አቋማቸዉንም እንዲያርሙ ለኢሳት አመራሮች ጥሪያቸዉን አቅርበዋል።
አቶ ለገሰ አያይዘዉ ሲገልጹ “..,ትላንትና ጀምሮ አዲስ አበባ የሚገኙት አባሎቻችን ቤታቸው እየተከበበ ነው። ለጊዜው ያላወቅናቸው አባላት ሣይታሰሩ አልቀሩም። በርካታ የመኢአድ አባላት በመላ ሀገሪቱ እየታሰሩ ነዉ። ከላይ እንዳልኩትም አቶ ማሙሸት አማረንም አገዛዙ ሊያስረው እየፈለገው ነው። እኔም ስራየን ጥየ ተደብቄ ነው ያለሁት። ይህንን እና የመሣሠሉ በደሎች እየደረሱብን መግለጫ እና መረጃ ስንልክላቸዉ ገና መኢአድ የሚል ቃል ሲያዩ መረጃዉን ወደ ቅርጫት ዉስጥ ይወረውሩታል ሲሉ አብራርተዋል።
ከኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰበሰብ ገንዘብ ከተቋቋሙት ሚዲያዎች ማለትም ከእነ ኢሳት የሚዲያ ሽፋን ተነፍጎን: ወያኔም ልዩ መኢአድን የማጥፋት ወንጀል እየሰራብን ቢሆንም መኢአድ የነጻነት: የአንድነት እና የድል መንፈስን የታጠቀ ሀይል ነዉና ከህዝባችን ጎን ቆመን መራራ ተጋድሎ እያደረግን ነዉ ሲሉ አብራርተዋል። መኢአድ መንፈስ መሆኑን ከጠላት እስከ ወዳጅ ይወቅ ሲሉም ቁርጥ ያለ አቋማቸዉን አስተላልፈዋል።
በተያያዥም የኢትዮጵያዉያን ተጋድሎ እስከ ነጻነትን የሚያስተባብሩ አመራሮችም ኢሳት የሚላክለትን ዜናዎች ወደ ጎን የመግፋት አባዜ እንደተጠናወተዉ አብራርተዋል። እንዲሁም እንደ አቶ ለገሰ ሁሉ በምሬት ኢሳትን ወቅሰዋል።
ምንጭ ወልቃይት