Wednesday, 31 August 2016 12:09
- በ ፀጋው መላኩ
- ድርቅ፣ ግጭት የህዝብ ቁጥር እድገትና የኢኮኖሚው ፈተና
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ነው። የኤክስፖርት ምርቱ በከፍተኛ ደረጃ ወርዷል። ሀገሪቱ የውጭ ብድር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በመጀመሪው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የታቀዱት እቅዶች በሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን እንኳን የሚሳኩ አይመስሉም። የህዝቡ ቁጥር በ25 ዓመታት ውስጥ ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል። በሀገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተቀሰቀሱ ያሉት ግጭቶች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን እየገቱት ነው። የገቢ የወጪ ንግድ ክፍተቱ በከፍተኛ ደረጃ ሰፍቷል። እነዚህንና መሰል ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በማያያዝ በተወሰነ ደረጃ ተመልክተናቸዋል።
*** *** ***
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት አሁንም ድረስ ግብርናው ነው። ይህ ከቀደመው የሀገሪቱ ታሪክ ጀምሮ እስከ ዛሬም ድረስ መለወጥ ያልቻለ እውነታ ነው። በርካታ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት በግብርና የኢኮኖሚ መሰረት ውስጥ ቢያልፉም የእድገታቸው ማረፊያ ያደረጉት ኢንዱስትሪውን ነው። ግብርናው በምርምር የታገዘ እንዲሆን በማድረግ በጥቂት ሰዎችና በሰፋፊ እርሻ ከራሳቸው ተርፎ ሌሎችን ለመቀለብ የሚያስችል ብሎም ለአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ግብአት የሚሆን ምርትን በገፍ ያመርታሉ።
በእነዚህ ያደጉ ሀገራት ከአጠቃላይ ህዝባቸው ቁጥር አንፃር በግብርናው ዘርፍ የተሰማራው የህዝብ ቁጥር ከ3 በመቶ አይበልጥም። የሚበዛው ህዝብ በኢንዱስትሪውና በአገልግሎት ዘርፉ የተሰማራ ነው። ይህን ወደ ኢትዮጵያ ስንመልሰው ከ85 በመቶ ያላነሰው በግብርና ስራ የህይወት መሰረቱን የመሰረተ ነው። በአውሮፓና በአሜሪካ ከ3 በመቶ የማይበልጠው የግብርናው ዘርፍ ሀይል ለራሱ ቀለብ፣ ለኢንዱስትሪው ግብአት፣ ብሎም ለውጭ ገበያ በስፋት ሲያመርት፤ በኢትዮጵያ ከጠቅላላ ህዝብ ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ የሆነው የግብርናው ዘርፍ የሰው ሀይል ግን ለሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን የምርት መጠን እንኳን ማምረት የቻለበት ሁኔታ እስከዛሬም ድረስ ሊፈጠር አልቻለም።
ይህ ብቻ ሳይሆን የሚበዛው አርሶ አደር ምርቱን ለገበያ ማቅረብ ይቅርና አመቱን ሙሉ ቤተሰቡን ሊቀልብ የሚያስችል በቂ ምርትን እንኳን የሚያመርትበት ሁኔታ የለም። ከዘመናት ጀምሮ እስከዛሬም ድረስ የዝናብ ጥገኛ የግብርና ስራን የሚያከናውን በመሆኑ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆነው የአርሶ አደር ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። ትልልቅና አነስተኛ የመስኖ ግድቦች የሉም። በተወሰነ አካባቢ የተጀማመሩትም ቢሆኑ በግንባታ ሂደት ከተጠበቀው በላይ ጊዜን በመውሰድ ከፍተኛ ገንዘብ የበሉ ናቸው። በአነስተኛና ከፍተኛ የመስኖ ግድቦች ላይ በስፋት ባለመሰራቱ የዝናብ ጥገኛ የሆነው አርሶ አደር የአንድ የዝናብ ወቅት የአየር ንብረት መዛባት ሲያገጥመው፣ ለራሱ ቀለብ፣ ለከብቶቹም መኖ ማገኘት የሚችልበት ሁኔታ የለም።
የህዝቡ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ባለበት ሁኔታ የእርሻ መሬትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ በመሄድ ላይ ነው። ይህም በተበጣጠሰ መሬት የሚሰበሰበው ሰብል ለቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ሆነ ከእጅ ወደ አፍ አልፎ የእለት ኑሮ ለኢንዱስትሪ ግብአት ሊያገለግል የማይችል በመሆኑ በነፍስ ወከፍ ያለው የግብርና ምርት ተገቢው የእድገት ለውጥ አይታይበትም። ግብርና ሲባል ንብ ማነብ፣የአሳ ሀብት ልማት፣የእንስሳት ሀብት ልማት እንደዚሁም የደን ልማትንና የመሳሰሉትን ዘርፎችን የሚያካትት ዘርፍ ቢሆንም በኢትዮጵያ ዛሬም ድረስ እየተሰራበት ያለው በሰብል ምርት ላይ የተመሰረተው የግብርና ዘርፍ ነው።
ቅጥርን የማያበረታታ የክፍያ ሁኔታ
በኢትዮጵያ ስራ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለሰሩት ስራ ተገቢውን ክፍያ የማግኘቱ ጉዳይ ሌላኛው ፈተና ነው። በርካታ ሀገራት ዝቅተኛ የወለል ክፍያን የሚደነግግ ህግ (Minimum Wage rate) አላቸው። ይህ ህግም ሆነ አሰራሩ በኢትዮጵያ የለም። ሰዎች በመደበኛ ቅጥር እንኳን ዝቅተኛ የክፍያ ወለል የላቸውም። ቀጣሪዎች ከፍተኛ ገንዘብን ሲያገኙ ለእድገቱ ምክንያት የሆኑት ሰራተኞች ግን የእለት ኑሯቸውን የሚያሸንፉበት ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ እንኳን የለም። ይህም በሀገሪቱ የተፈጠረው ሀብት ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለዜጎች የሚዳረስበትን ስርአት ዝግ አድርጎታል።
የቅጥሩ ሁኔታ በገበያ የሚመራበት ሁኔታ እንዳይፈጠር እንኳን በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የቀጣሪ መጠንና የስራ ፈላጊው መጠን ፈፅሞ የተመጣጠነ አይደለም። ይህም አጋጣሚ ቀጣሪዎች በቀላል ዋጋ ርካሽ ጉልበትን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። ፍትሀዊ ካልሆነ ክፍያ ጋር በተያያዘ ኑሯቸውን በአገር ውስጥ መምራት ያቃታቸው በርካታ ዜጎች ስራቸውን እየለቀቁ ስደትን መርጠዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የቅጥር ክፍያ አነስተኛነት እና የተመጣጠነ አለመሆን በቅጥር ላይ ያሉ ሰዎች የቅሬታ ህይወትን እንዲመሩ እያደረጋቸው ነው። የአንዱ እድገት ሌላው እድገት ምክንያት መሆን አለመቻል አገራዊ እድገቱ ሁለንተናዊ ገፅታ እንዳይኖረው አድርጓል።
ድርቁና የኢኮኖሚው ፈተና
በኢትዮጵያ ድርቅ ብሎም ርሀብ አዲስ አይደለም። ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ በየአስር ዓመቱ እያሰለሰ ሲመጣ የቆየው ድርቅ ባለፈው በጀት ዓመትም 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን ለከፋ የምግብ እህል ውሃ እጥረት ዳርጓል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለተረጂ ዜጎች እህልን ለማቅረብ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር አስፈልጓል። መንግስት ይህንን ያህል ገንዘብ ወጪ በማድረግ ለዜጎች የምግብ እህል ለማቅረብ አቅሙ እንደሌለው በመግለፅ ለለጋሽ አካላት የእርዳታ ጥያቄን ቢያቀርብም የተገኘው ምለሽ ግን የታሰበውንና የተጠየቀውን ያህል አመርቂ አልነበረም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም መንግስት እስከ 360 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ የእህል ግዢን ለማከናወን ተገዷል። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከለጋሾች የተገኘውን እርዳታ ጨምሮ መንግስት በመደበው ገንዘብ የበርካታ ዜጎችን ህይወት ከህልፈተ ህይወት መታደግ ተችሏል።
ሆኖም የክረምቱን መግባት ተከትሎ በተለይ ከመጠጥ ውሀና ከከብቶች መኖ ጋር በተያያዘ የነበሩት ችግሮች ተቃለዋል። ሆኖም ተረጂዎችን እንደዚሁም ያለውን የድርቅ ደረጃ በተመለከተ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙም የሚለቀቁ መረጃዎች አይታዩም። ከድርቁ ጋር በተያያዘ መንግስት በቀጥታ ከካዝናው ካወጣው በመቶ ሚለዮኖች ከሚቆጠር ዶላር በሻገር የግብርና ምርት መቀነስንም እንደዚሁም የመንግስት ትኩረት አቅጣጫ መቀየርንም አስከትሏል። ድርቁ በቀጥታ በኢኮኖሚው ላይ ካስለተለው ጉዳት ባሻገር በቀጣይ አድርሶት የሚያልፈውም አሉታዊ ተፅዕኖም በቀጣይ ፍተሻ የሚያስፈልገው ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ በከተማም ሆነ በገጠር በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፎ የእለት ጉርሱን የሚጠብቅ ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነው። እነዚህ ሁሉ የኢኮኖሚው ፈተናዎች ዛሬም ድረስ መልስ ያላገኙ ናቸው።
ግጭቶችና የኢኮኖሚው ፈተና
ብዙም መረጋጋት በማይታይበት አፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ በአንፃራዊ ሰላም ውስጥ የምትገኝ ሀገር ሆና ቆይታለች። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በየአቅጣጫው የሰላም መደፍረስ ሁኔታዎች ይታያሉ። ቀደም ብሎ በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ግጭት በርካታ ኢኮኖሚያዊ አውታሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት የውጭ ባለሀብቶችን ንብረት ሳይቀር ሰለባ አድርጓል። በዚህ መልኩ የደረሱት ጉዳቶች የኢትዮጵያን የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰትን እንደሚጎዳው ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል በየቦታው የተቀሰቀሱት ግጭቶችና ስራ አቁሞ ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማው በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የቱሪስት መዳረሻ የሆነችው ጎንደር ብሎም ባህርዳር ሰላም ከራቃቸው ሰነባብተዋል።
በአካባቢው ከተከሰተው ግጭትና ውጥረት ጋር በተያያዘ በተለይ የጎንደር ከተማ በከፍተኛ የኢኮኖሚ መዳከም ውስጥ መግባቷን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሰሞኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል። የትራንስፖርት መስመሮች አስተማማኝነት አይታይባቸውም። በአዲስ አበባ ከተማ ሳይቀር የእህል ዋጋ በተለይም የጤፍ ዋጋ እንደዚሁም የደረቅ እንጀራ ዋጋ ጭምር የዋጋ ጭማሪ ሁኔታ ታይቶበታል። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በድምሩ ሲታዩ ኢኮኖሚው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ የሚያመላክቱ ናቸው።
ከግጭቶች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ የኢኮኖሚ መንሸራተትና መዳከሞች መልሶ ለማገገም ረዘም ያለ ጊዜን የሚወስዱ ናቸው። በአረብ አብዮት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ግብፅ እስከዛሬም ድረስ ኢኮኖሚዋ ሊያገግም አልቻለም። በሳዑዲና በተባበሩት አረብ ኤሜሬት የተደረገው ከፍተኛ የገንዘብ እገዛ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ማምጣት አልቻለም። ሀገሪቱ ከገባችበት የኢኮኖሚ ድቀት ለመውጣት ቀላል በማይባል የብድር እዳ ጫና ውስጥ መግባት ግድ ብሏታል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የግብፅን ያህል ግጭቶችን ተሸክሞ የመቆየት አቅም የለውም።
የመንግስት የትኩረት አቅጣጫና ኢኮኖሚው
በተለያዩ ጊዜያት የተነሱት ግጭቶች አሁንም ድረስ ሊበርዱ አልቻሉም። የግጭቶቹ መባባስ የመንግስት ወቅታዊ ትኩረት ግጭቱን ማረጋጋት ላይ እንዲጠመድ አድርጎታል። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከስራ አስፈፃሚ ጀምሮ እስከ ፓርቲው ምክር ቤት ድረስ ለተከታታይ ቀናት ለመምከር አስገዳጅ ሁኔታን የፈጠረበት ይሄው የሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ነው። ይህም የመንግስት ሙሉ የትኩረት አቅጣጫ ወዴት እንደሆነ ግልፅ ማመላከቻ ነው። የማህበራዊ ድረገፆች እንደዚሁም የግል ሚዲያዎች የመረጃ ትኩረትም ሆነ የመንግስት ሚዲያዎች የዘገባ አቅጣጫ በየአቅጣጫው ከተነሱት ግጭቶች ጋር የሚያያዝ ሆኗል።
እነዚህም ሁኔታዎች ሲታዩ የህዝቡና የመንግስት የትኩረት ሚዛን አቅጣጫ ወቅታዊው የሀገሪቱ ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ማሳያ ናቸው። ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ ሁኔታዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የሰላምና መረጋጋት ስራን ለመስራት በራሱ ተጨማሪ ጊዜን ይጠይቃል። ተጨማሪ የትኩረት አቅጣጨንም የሚሻ ነው። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ጥርጥር የለውም።
የህዝብ ቁጥር ማሻቀብና ኢኮኖሚው
አትዮጵያ ህዝብ ቁጥር የእድገት ፍጥነት ከፍተኛ ነው። ዓመታዊ እድገቱ እስከ 3 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዓመታት በፊት በአፍሪካ ከናይጄሪያና ከግብፅ በመቀጠል በህዝብ ብዛቷ የሶስተኝነትን ደረጃ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ በአሁኑ ሰአት ግብፅን በማለፍ ናይጄሪያን ተከትላ በአህጉሩ የሁለተኝነት ደረጃን ይዛ ትገኛለች። የደርግ መንግስት የስልጣን ዘመኑ ባከተመበት ወቅት ኤርትራን ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 48 ሚሊዮን አካባቢ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ማለትም በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ መቶ ሚሊዮን መጠጋቱን የእድገት ፍጥነቱን መሰረት በማድረግ የሚሰሩ ስሌቶች ያመለክታሉ። ይህም በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የሚያመለክት ነው።
ኢኮኖሚና የህዝብ ብዛት ያላቸው ግንኙነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ነው። አንድ ኢኮኖሚ ምንም ያህል በፍጥነት ቢያድግም የህዝብ ቁጥር እድገቱ ባልተመጠነ መልኩ እድገትን የሚያሳይ ከሆነ እድገቱ ዜሮ ድምር ተደርጎ ነው የሚታየው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ድሃ አገር የለማ የሰው ሀብትን መፍጠር የሚቻልበት አቅም ውስን በመሆኑ አብዛሀኛው ህዝብ በኢኮኖሚው ላይ እሴትን ከመጨመር ይልቅ የተፈጠረውን ውስን ኢኮኖሚ ተቀራማች እንዲሆን ያደርገዋል። የአንድ አገር ኢኮኖሚ የሚለካው በአጠቃላይ ዓመታዊ ጥቅል ምርቱ ብቻ ሳይሆን (GDP) ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የምርቱን መጠን ለጠቅላላ የህዝቡ ቁጥር (GDP per Capital) በማካፈል ነው። ይህ የኢኮኖሚ ስሌት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ማን ምን ደረሰው የሚለውን የኢኮኖሚ ድርሻ በመጠኑም ቢሆን ያመለክታል። ቻይናን የመሰሉ ሀገራት ምንም ያህል የኢኮኖሚ እድገትን ቢያስመዘግቡ እስከዛሬም ድረስ በታዳጊ አገርነት ደረጃ ውስጥ ያሉት አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት መጠናቸው ለህዝባቸው ሲካፈል አነስተኛ በመሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚ ማስመዝገቧ በነገርም የህዝቧ ቁጥር በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ማደጉ የኢኮኖሚ እድገቱን ከህዝቡ ቁጥር ምጣኔ ጋር ያልተመጣጠነ እንዲሆን ያደርገዋል።
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በግልም ሆነ በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረተው የሰው ኃይል እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነው። ኢኮኖሚው ለዚህ ትውልድ የሥራ እድልን መፍጠር የሚችለው አንድም በስራ ፈጠራ አለበለዚያም በቅጥር ነው። ሆኖም የኢኮኖሚ እድገቱ ከህዝቡ ቁጥር እድገት አንፃር ፈጥኖ መሄድ ካልቻለ ቀጣይ ፈተናውም ቢሆን ከባድ ነው።
በአሁኑ ሰዓት እየታየ ያለውም ችግር ይህ ነው። በዚህ ዓመት ብቻ ከ180 ሺህ ያላነሱ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚቀላቀል መሆኑ ታውቋል። ከዚህም ባለፈ በቴክኒክና ሙያ የስልጠና ዘርፍ ትምህርት ለመውሰድ የተዘጋጁም በርካቶች ናቸው። በዚሁ መጠን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን አጠናቀው የስራውን ዘርፍ ለመቀላለቀል የሚጠባበቀው የሰው ኃይል ቁጥርም ከፍተኛ ነው። የኢህአዴግ መንግስት የህዝብ ቁጥር እድገትን በስነ ህዝብ ፖሊሲው በመቆጣጠሩ ረገድ ደካማ አካሄድ እንዳለው አሁን እየታየ ያለው ከቁጥጥር ውጪ የወጣ የህዝብ ቁጥር እድገት ያሳያል። ይህንን የህዝብ ቁጥር እድገት የሚመጥን ሰፊ የኢኮኖሚ መሰረትን መፍጠር ካለተቻለ ሀገሪቱን ለሚያስተዳድረው መንግስት ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ በአጠቃላይ ከባድ ፈተናን እንደሚደቅን ከወዲሁ የሚታዩት አመላካች ምልክቶች እየጠቆሙ ነው።¾
Source – Sendek NewsPaper.