ክፍል አንድ
መቅድም

lalibela[ማሳሰቢያ፦ በዚህ ጽሑፍ ዉስጥ የዉጭ አገር ቋንቋዎች በጽሑፉ ዉስጥ አልፎ አልፎ ተካተዋል፤ ይህም የሆነበት ምክናያት የሥነ መለኮትን ምርምር በዉጭ አገር ቃላት ስለነበር ተዋህዶ የተባለዉን ሥረ ቃል ከየት እንደመጣ ለአንባቢ ለማሳወቅ ነው። ለምሳሌ የተዋህዶ ሥረ ቃል የመጣዉ ክግሪክ ሆሙሲየስ (homoouisious, born, and being begotten) ከሚለው ከግሪክ ቃላት ነው። በተጨማሪ ዉህደትን የሚያመለክቱ የግሪክ ቃላት አሰካክን እንመልከት (“essence” [ousia], “substance” [hppostasis], “nature” [physis], “person” [proson] እነዚህ ቃላት በመጀመሪያዉና በሁለተኛው ጉባኤ በ325 እና በ425 ዓመተ ምህረት በተደነገገው ሕግ መሰረት (canon ይህንንም “ቀነኖ ወይም ቀኖና እየተባለ በአሁኑ ግዜ ይጠራል) ነው። ቀኖና ወይም ቀነኖ ከማለት አፂ ዘርዓ ያዕቆብ እነደደነገገው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ቢባል መልካም ነበር። እነዚህ ቃላት የተጠቀሱበት ዋና ምክናያቱ አንባቢ የቃላቱን አመጣጥ በቅጡ እንዲያውቅ ለማድረግ ተብሎ ነው]።

ከዚህ በፊት ስለ ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብና ስለ ንጉሡ ዘርዓ ያዕቆብ  ሰፋ ያለ ጽሑፍ አቅርቤ  ስለነበር ብዙ አንብቤዎች ከላይ በተጠቀሰው አርዕስት ላይ እንድጽፍ ስለጠየቁኝ ለሁለተኛ ግዜ ከአንባቢያን ጋር  ለመወያየት ብቅ ብያለሁ። እንደገባኝ ከሆነ የተጠየቅሁበት ምክንያት የድቁና ትምህርት አለኝ ብዬ ስለነበር ምናልባት የቤተክርስቴያኑን ታሪክ ሳያውቅ አይቀርም በማለት ሳይሆን አይቀርም ብዮ እገምታለሁ። ግን አንድ ሰው ስለዳቆነ የቤተክርስቲያኑን ታሪክና ሥር ዓት ያውቃል ማለት ይቻላል? መልሱ ቀላል ነው፤ አንኳንስ ድቁና ጵጵስና የተቀበሉ አባቶች ም ታሪኩንም ሆነ ሥርዓቱን  በሚገባ አያውቁቱም፤ የአገራችን የቤተክርስቲያን አባቶች የተወሰኑ መጻሕፍትን እየመላለሱ ከመድገም በላይ ስለቤተክርስቲያን ያላቸው ዕውቀት እጅግ በጣም ዉስን ነው፤ ሃይማኖታችን ከባሕላችን ጋር ስለተጣመረ በቅጡ ለይቶ ለማወቅ ያስቸግራል። በዚህ ምክንያት እኛ የተዋህዶ እምነት ተከታዮች እምነታችንን በምኪገባ አናውቀውም። ይህም ታላቅ ጉዳት አድርሶብናል፤ አንባቢ በተረጋጋ መንፈስ ሆኖ ይህንን ጉዳይ መመርመር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ይህንን  ክአልኩ በኋላ ምን ያህል ዕውቀት ቢኖረው ነው በዜህ አርዕስት ላይ ሊጽፍ የተነሳው ? የሚል ጥያቄ ስለሚነሳ በቅድሚያ ለአንባቤዎቼ ያልኝን ችሎታ በአጭሩ አቀርባለሁ። ከላይ እንደጠቀስኩት ድቁናዬን በተወለድኩ በአስራ ስምንት ወሬ [18 ወራት] በበዕታ ቤተክርስቴያን በበፁዕ አቡነ ቄርሎስ ተቀብቼአለሁ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት እንደዚህ ነው፤ አባቴ ሥራቸው ግብርና ስለነበር ማፉድ ከሚባል ቆላማ ገጠር ውስጥ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ተከለው ስለነበር በዜያ እንዳገለግል ነበር። ግን ለአቅመ አዳም ሳልደርስ አባቴ ስለአረፉ ምኞታቸው ሳይሳካ ቀረ። ሆኖም እስከ ዳዊት ድረስ ትምህርቴን ስለአጠናቀኩ ከሞላ ጎደል የቤተክርስቲያኑን ሥር ዓት ለመመልከት ችያለሁ፤ ይህም ማለት ሥርዓቱን ጠንቅቄ አውቃለሁ ሳይሆን አጠቃላይ ሂደቱን የማወቅ ዕድል አግኝቻለሁ ለማለት እችላለሁ። ከቅዳሴና ክጾም ከጸሎት ሌላ ቤተክርስቲናችን አያሌ ሥርዓት አሏት፤ እሱ ዝርዝር ውስጥ አሁን አልገባም። በመጀመሬያ ክርስትና ወደ አገራችን እንዴት እነደመጣ ማወቅ ግዴታ ነው፤ በዜህ ላይ ብዙ በተለምዶ የሜነገር አፈ ታሪክ አለ፤ ይህም አፈ ታሪክ ከወሬ አልፎ በመጽሐፍ ተጽፎ እንደታሪክ እየተነበበ መሆኑን ማወቅ ለተዋህዶ እምነት ተከታዮች እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ምክናያቱም ይህ አፈ ታሪክ ከባሕላችን ጋር ስለተጣመረ ሃይማኖቱንና ባሕሉን ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፤ ወደዋናው ታሪኩ ውስጥ ከመግባታችን በፊት በዚህ መቅድም ላይ መወያየቱ ታሪኩንና ሥርዓቱን በሜገባ እንድናውቀው ይረዳናል ብዬ እገምታለሁ።

ይህ ከተባለ በኋላ ለዜህ ጽሑፍ መነሻ የሆነውን ለአንባቢ አጠር አድርጌ አቀርባለሁ። ከዚህ በፊት በጻፍኩት ላይ ከ20 ዓመት በላይ ለፍተን ግረን ያቋቋምነውን ቤተክርስቴቲን አንድ ጎበዝ  “እኛ ከሕግ በላይ ነን፤ ሕግ እናወጣለን፤ ደግሞ ስንፈልግ እንሽረዋለን፤ ይህንን የሚያስቆም ሃይል አይኖርም “ በማለት ማሕሌት አስቁሞ  ከበሮ አስመትቶ፤ እልል አስኝቶ፤ አስጨብጭቦ፤ ማዕበል አስነስቶ፤ ሲነጥቀን የጀግኖች ጀግና ያላለው ሰው የለም። ይህንኑ የጀግንነት ስራ ለማጠናከርና  በምን አይነት ዘዴ ቤተክርስቲያናትን ከቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚቻል ለማስተማር የመጣው ካድሬ መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሰ ከሰሜን፤ ከምዕራብ፤ ከደቡብ፤ ከምስራቅ፤ የተንሳውን ማዕበል የሚያስቆመው  የለም በማለት ነባያቱን  በሙሉ ፡ ትንቢተ ኢሳይያስ፤ ትንቢተ ኤርምያስ፤ ትንቢተ ሕዝቅኤል፤ ትንቢተ ዳንኤል፤ ትንቢተ ሆሴዕ፤ ትንቢተ አምጽ፤ ትንቢተ ሚክያስ፤ ትንቢተ ዳንኤል፤ ትንቢተ አብድዮ፤ ትንቢተ ዮናስ፤ ትንቢተ ናሆም፤ ትንቢተ ዕንባቆም ፤ ትንቢተ ሶፍንያስ፤ ትንቢተ ሐጌ፤ ትንቢተ ዘካርያስ፤ ትንቢተ ሚልክያስ፤ እየጠቀሰ በቅርቡ በአጠቃላይ የኤትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት ተጠቃላ በእኛ ሥር መሆኗ አያጠራጥርም እያለ ትንቢቱን ሴያወራ ምዕመን በከበሮ ፤ በዕልልታ፤ በጭብጨባና በደስታ ነበር የተቀበለው። ብዙዎቻችን የዚህን ማዕበል መነሻውን ስለማናውቅ እንዴት እንደዜህ  ሊሆን ቻለ?  እያልን ራሳችንን እንጠይቃለን። ለዚህ መልስ መስጠት ከባድ ነው። የከበደበተም ምክንያት ስለ ኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ታሪክ ያለን ዕውቀት ዉስን ስለሆነ ነው። እንግዲህ ለዚህ መፍተሔ የሚሆነው ታሪኩን በሚገባ መርምሮ ማወቅ ብቻ ነው፤ ለዚህ ሌላ አማራጭ የለውም። ከታሪኩ ምዕራፍ በፊት ያለማወቅ ምን ያህል ደፋር እንደሚያደርግ ማሳየት ጠቃሚ ነው ብዬ እገምታለሁ። ካድሬው ነበያቱን እየጠቀሰ ያላሉቱን አሉ እያለ ሲያወራ በማያዉቁት ምዕመን ላይ የፈጠረው ድፍረት ይህ ነው ሊባል አይቻልም፤ ከዚህ በላይ የሚገርመው ነገር ቢኖር በትንቢተ ዘካርያስ ላይ ምዕራፍ 14 ቁጥር 1-2 ድረስ ላይ የተጻፈዉን ትንቢት ያለማወቁን ነው፤ “እነሆ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፤ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይከፈላሉ። አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ ለሰልፍ እሰበስባለሁ ከተማያቱም ትያዛለች፤ ቤቶቹም ይበዘበዛሉ፤ ሴቶቹም ይነወራሉ፤ የከተማይቱም እኵሌታ ለምርኮ ይወጣል።” ይህ ትንቢት በኢትዮጵያ አገራችን  ላይ ደርሶ ወያኔ በአጋዚ[በናዚ ጦር ኅይሉ] ወንዱን ሴቱን ሕፃናቱን በጥይት ሲያስደበድብ፤ ካህናቱንና እና ዲያቆናቱን ካድሬ አድርጎ ለአሕዛብ መንግሥት ተገዙ ብሎ እንዲያስተምር በተገደደበት ስዓት ገለልተኛ ቤተክርስቲያናትን በውድ ሳይሆን በግድ በአሕዛብ በሜመራው መንግሥት ሥር ሁኑ ማለት የዘካርያስ ትንቤት እዉን ሆነ ማለት ነው። የሚያሳዝነው ግን አስተማሪውም ሆነ ምዕመን ነባያቱ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ የተነበዩቱን ትንቤት ያለማወቃቸው ነው። ይህ ማዕበል የተነሳው በሁሉ አቅጣጫ ሆኖ ሂደቱ አንድ ነው፤ ይህም የሚያሳየው ገለልተኛና ነፃ የሆኑቱን ቤተክርስቲያናት በመንግሥት ስር ጥገኛ እንዲሆኑ በሚያስተባብር ግብረ ኅይል መመሬያ መሰረት እንደሚመራ ነው። በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ የተፈጠረው ሁኔታ የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ምንም የማያዉቁ ወጣቶች በካድሬዎች ተመልምለው አጋዝያን ኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሱቱን ግድያ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸዉን የካድሬዎቹ መሪ በየጊዚው የሚሰጠው የደም ማፍሰስ ትዕዛዝ ነው። እንግዲህ እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት አልባነት የመጣው ከየት ነው ብሎ መጠየቁ አግባብ ነው፤ የቤተክርስቲያንን በር መቆለፍ፤ የቤተክርስቲያን በር መስበር ሥርዓተ አልባነት ነው፤ ከዚያም አልፎ ከቅድስት ቤተክርስቲያን ሥርዓት ዉጭ ነው።

ለዚህ ትምሕርት እንዲረዳ በማለት ሥርዓተ አልባነት በአገራችን እንዴት እንደተስፋፋ ማሳወቁ ጠቃሚ ነው ብዬ እገምታለሁ፤ ይህ ጸሐፊ ሕጻን በነበረበት ወቅት በወቅቱ በሰፊው ይወራ የነበረ ታሪክ ነበር፤ ይኸዉም አንድ ወጣት ሴት ወይዘሪት እንግሊዝ አገር ትምህርቷን ስትክታተል አንድ ኢንግሊዛዊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ስንት ይሆናል? ብሎ ቢጠይቃት ይህች ከኦሮሞ መሳፍንት የተወለደች  ንጉሣዊ  ቤተሰብ እኛ ቁጥራችን አምስት መቶ ነው አለችው ይባላል። ጠያቂውም በመገረም  የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 20 ሚሊዮን ነው አልተባለም ነበር ወይ? ብሎ ቢጠይቃት፤ አይ እነሱ የሚሉት ግብስቡሱን ሁሉ ቆጥረው ነው አለችው ይባላል። በካህናቱና በቀሳዉስቱ አካባቢ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ የሚወራው ወሬ በንጉሠ ነገሥቱ አካል ላይ ነበር፤ የንጉሡ  አካል በእግዚአብሒር  የተቀባ ስለሆነ አይከሰስም አይገስጽም ክብሩ ታላቅ ነው ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም እድሜዉም እንደ ማቱ ሳላ ነው እየተባለ ይነገርለት ነበር። ዛሬ የቀድሞው የወያኔ አምባገነን አካል  በአንድ መነኩሴ ነኝ በሜል ሰባኪ “መለሰ ዜናዊ  ማለት ፍጹምና ሕያው” ነው ተባለ፤ ይህ ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማያውቅ  በቃሉ ተፀንሶ  ያልተወለደዉን የሰው ልጅ አምላክነት ነው፤ እግዚአብሔር የሰዉን ልጅ በአምሳሉ ፈጠረው እንጅ የሰዉን ልጅ ፍጡርን እንዲፈጥር አምላክ አድርጎ አልፈጠረውም። ከዚህም አልፈው እንደ ዮሐንስ ራእይ “የመለስ ራእይ” ተብሎ በደምቦስኮ ማእከል የተገመገሙቱን ካድሬዎች ለጥፋታቸው ቀኝ እጁን ግንባራቸው ላይ ጭኖ ምሕረት ሲያደርግላቸው እራሱን “ሕያው ነኝ “  በማለት ነበር፤ “የመለስ ራእይ ሕያው ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤” ወደፊትም እንደ ቁዱስ ዶምቦስኮ እሱም በራእዩ መሰረት “ቅዱስ ዜና መለስ” ተብሎ ሕያዉነቱን ይጎናጸፋል፤ እንግዲህ አንባቢ በአንክሮ መመልከት ያለበት በቅዱስ መጽሐፍ ላይ የተጻፈዉን “መጽሐፈ ምሳሌን” ነው፤ ይህ ምሳሌ የተጻፈው ለዳዊት ልጅ ለሰሎሞን ነው፤ እሱም እንዲህ ይላል፤

የእስራኢል ንጉሥ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሊዎች፤ ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፤ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፤ የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል ብልሃትን  ለአላዋቂዎች ይሰጥ ዘንድ  ለጎበዛትም እውቀትንና ጥንቃቄን፤ ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፤ አስተዋይም መልካም  ምክርን  ገንዘቡ ያደርጋል፤ ምሳሌንና ትርጓሜን  የጠቢባንን ቃልና የተሽገገዉን ነገር ለማስተዋል፤ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ፤ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ ለራስህ የሞገስ ዘውድ ላንገትህም ድሬ ይሆንሃልና። ልጄ ሆይ ኃጢአትኛ  ቢያባብሉህ እሺ አትበል። ደምን ለማፈሰስ  ክእኛ ጋር እናድባ ለንጹሕም ያለ ምክንያት ወጥመድን  እንሽምቀበት ቢሉ። [መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 1 ቁጥር 1-11].

በመጽሐፈ ምሳሌ የተጻፈው ለዳዊት ልጅ ለሰሎሞን ነው። ንጉሥ ሰሎሞን ታዋቂ ጠቢባን የሆነበት ምክናያት ከትውልድ ትውልድ የተላለፈውን በተግባር የተፈጸሙትን ተግባሮች ጥሩዉንና መጥፎዉን ለይቶ እንዲያውቅ ስለተደረገ ነው። ንጉሥ ሰሎሞን እንደማንኛውም ሰው ፍጡር ነው፤ ከሌላው ሊለይ የቻለው በምሳሌ የተጻፉቱን በአንክሮ ስለተገነዘበ ነው፤ ሰሎሞን “ጥበብ በጎዳና ትጮዃለች” የተባለዉን ሰምቶ በተረጋጋ መንፈሱ አዳመጣት፤ ጥበብም በሰሎሞን ላይ አደረች፤ ጥበብን የማወቅ ሚስጥሩ ይህ ነው። በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ የተሰጠው ተግሣጽ ከፍተኛ ነው፤ “እናንት አላዋቂዎች  እስክ መቼ አላዋቂነት ትወዳላችሁ?”  ተብሎ ምሳሌ ላይ እንደተጻፈው የኛ አላዋቂነት ልክ የሌሽ ነው፤ ያለማወቅ ደፋር ያደርጋል የተባለበትም ምክናያት ይህ ነው፤ ደፍረን ሌላዉንም ደፋር እናደርጋለን፤ የደፋር ደፋር ነን፤ በአምሳሉ የፈጠረዉን ሰው አምላክ ነው እንላለን፤ መለሰን ደግሞ እናዋርደዋለን፤ እንሰድባዋለን፤ እንገድለዋለን፤ ምሳሌ ላይ እንደተጻፈው “ፌዘኞችም” ነን፤ “እውቀትንም” አጥብቀን እንጠላለን፤ እውቀት ከማንበብ ነው የሚገኝው፤ ስንቶቻችን ነን መጽሐፈ ምሳሌን ያነበብነው? በወሬ የምንነዳ እንስሳ መሆን አይሆንብንም?

አርዕስቱ ላይ ከተሰጠው ታሪክ ከመግባቴ በፊት “ገለልተኛ “ ነን በሚሉ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተከፈተዉን ዘመቻ በአጭሩ ማቅረብ የኢትዮጵያን ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ታሪክ ለመርመርና ለማወቅ ይረዳል ብዬ እገምታለሁ። በቤተክርስቲያናችን ረጅም ዘመን ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ “ገለልትኛ” በሚል ሥም ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያመልኩቱን ቤተክርስቲያናት  በያሉበት ማቋቋም ጀመሩ፤  እዚህ ላይ “ገለልተኛ” የተባለዉን ቃል ምን እንደሆነ ማስረዳት አስፈላጊ ነው፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከመጀመሪያው ጀምሮ የምትተዳደረው በአገሩ መሪ በላይ ጠባቂነት ነው፤ ለ1600 ዓመት የራሷ ጳጳስ ሳይኖራት በግብፅ በሚላክላት ጳጳስ ነበር የምትስተዳደረው፤ ይህም ማለት ቅስናውም ድቁናዉም የሚሰጠው በሊቀ ጳጳሱ ነው፤ ከዚህ በላይ የቤተክህነቱን አስተዳደር የሚመራው ዕጨጊ ከበላይ ጠባቂው ከንጉሠ ነገሥቱ በሚስጠው መምሪያ መሰረት የቤተክርስቲያኑን ጉዳይ ያስፈጽማል። በአጭሩ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አወቃቀር ይህንን ይመስላል። አሁን የተለወጠ ነገር ቢኖር ክ 1952 ጀምሮ ኢትዮጵያ በራሷ ሲኖድ [የጳጳሳት ጉባኤ] እንድትስተዳደር ስለተደረገ ከግብፅ ግዞት ነፃ ሆነች፤ ነገር ግን በአገር ዉስጥ የነበረው ሥርዓት ስለአልተለወጠ አሁንም የቤተክርስቲያኗ የበላይ ጠባቂ የአገሩ ገዥ ነው፤ስለዚህ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከፖለቲካ ነፃ የሆነችበት ዘመን የለም፤ የፖለቲካው ክፍል አካል ነች፤ ገዥው ከየትም ይምጣ ተቀብላ ታስተናግዳለች፤ የገዥውንም ክፍል ማወደስ ዋና ተግባሯ ስለሆነ በቅዳሴ የገዥውን ተቃዋሚን በጠላትነት ፈርጃ በፍጥነት አስገዛላት እያለች ትማለዳለች፤ የኢትዮጵያ ገዥዎች በየግዚው ይለዋወጣሉ የቤተክርስቲያኗ አቋም ግን አንድ ነው፤ አዲሱን ገዥ ማወደስ የወደቀዉን መኮነን ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያናችንን እንዴት አድርገን ነው ነፃ የምናወጣት በማለት በውጭ የምንገኝ ትውልደ ኢትዮጵያ ጥሩ አጋጣሚ ስለአገኝን የቤተክርስቲኒያችን አባቶች አንድ ሆነው ከፖለቲካ  ነፃ የሆነች [autocephalous] ራሷን በቅዱስ ሲኖዶስ የምታስተዳድር እናድርጋት በማለት “ገለልተኛ” በሚል መዋቅር መገልገል ጀመርን። ሁኔታዎች አመቺ ስለነበር በርካታ አቢያተ ክርስቲያናት “ገለልተኛ” በሚለው መዋቅር የመተዳደሪያ ደንባቸውን ጽፈው ሰበካ ጉባኤውን መርጠው በሚያመልኩበት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሁካታ በመክፈት በካድሬዎች አማካይነት ወደነበረችበት ፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እንድትገባ እየጣሩ ነው። በአጭሩ “ገለልተኛ” ማለት ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ማለት ነው፤ አንዳንድ ምዕመናን ከሁለቱ ሲኖዶሶች ያልወገነ ማለት ነው እያሉ ይተረጉሙታል፤ የሁለቱ ሲኖዶስ ጉዳይ ፈጽሞ ከዚህ ጋር መገናኝት የለበትም፤ የእነሱ ትግል በመንበሩ ላይ ነው። መንበሩ የኔ ስለሆነ በተጠሪነት ማገልገል የሚገባኝ እኔ ነኝ ነው፤ እርቅም ተጀምሮ ተመልሰው ለመግባትና ሥርዓቱን ለማገልገል ፈቃደኛ ነበሩ፤ አግልግሎታቸውን አስፈላጊ ሆኖ ያላገኘው ወያኔ ነው። በውነት ጥሩ አባቶች ቢሆኑ ኖሮ ሲኖዶስ የሚባለውን ትተው ትክክለኛውን የሃይማኖት ትግል አድርገው ቤተክርስቲያናችንን ከፖለቲካ ነፃ ማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።

“ገለልተኛ” በተባለው ንጥረ ሃሳብ ላይ በመጠኑ መዋያየት ጠቃሚነው። ትክክለኛ ሃሳቡ ቤተክርስቲያኗ ከፖለቲካ ተገላ ፍጹም ነፃ [autocephalous] የምትሆንበትን ሁኔታ ለማመቻት ነበር። ሆኖም አባቶች አብረው ሥርዓቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በእኛ ስር ከአልሆናችሁ አንባርካችሁም ስለአሉና ይህንን ሁኔታ የሚለዉጥልን አባት ስለአጣን ክፖለቲካ ገለልተኛ መሆን አልተቻለም። ለምሳሌ በገለልተኛነት ለተቋቋሙ ቤተክርስቲያናት የእምነት አቋም ተግባራዌዊ እንዳይሆን በተቀነባበረ መንገድ ተሰንኩሏል።

ከፖለቲካ ነፃ የሆነ የተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእምነት አቋም

እኛ በዉጭ አገር የምንገኝ የኢትዮጵያ  ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  አማኞች  ፍጹም  ነፃ የሆነ የካህናት ጉባኤ  ለማቋቋም  ዓላማችን በማድረግ  ይህንኑ ጉባኤ በቤተክርስቲያናችን  ለመመስረት አስፈላጊውን  ጥረት እያደረግን ነው፤ ይኸውም  ፍጹም ነፃ  [autocephalous] የሆነ ጉባኤ የሚመሰረተው በቁዱስ አባቶች ትምህርትና ቡራኬ  ከዚያም  ከጥንት ጀምሮ ቤተክርስቲያናችን  የምትመራበትን ቀኖና መሰረት በማድረግ ነው። በተጨማሪ ቅዱስ ቁርባን በሚያዘው ትዕዛዝ  መሰረት አባቶች  በአጃቸው  ዳሰው  የቅስና  እና የዱቁና  ሥልጣን በሚሰጡት አካል እነደምንገለገል ፍጹም  እምነታችን ነው።  ከሁለም በላይ  ደግሞ  የኢትዮጵያ  ተዋህዶ  ቤተክርስቲያናችን  የቁዱስ  ተክለሃይማኖትን  መንበር  አክብራ  አንድ መንበር  አንድ ሲኖድ  አንድ  ቀኖና  ብላ ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓለም  በላይ  የቆመች  ቤተክርስቲያን  መሆኗን  እናምናለን። ሰክለዚህ ቤተክርስቲያናችንን  ከፖለቲካ ውጭ  እንድትሆን  በአገር ም ሆነ በውጭ  አገር ያሉ  ምዕመናን  አስፈላጊውን መሷዋዕትነት  እንድንከፍል ክርስቲያናዊ ጥሪአችንን  እናደርጋለን።

ይህ ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የእነት አቋም የተወሰደው በገለልተኛነት ሲመራ ከቆዬ ቤተክርስቲያን ነው። ነገር ግን ምእመን በወያኔ አምስት ለአንድ ተጠንፍረው በነፃነት ሲስተዳደር የኖረዉን ቤተከርስቲያን በመንግሥት የፖለቲካል ሥርዓት ስር እንዲሆን ተገዷል፤ ቤተክርስቲያኑን የሰሩ ምዕመን ተገፍተው ወጥተዋል። እንግዲህ አንባቢ በታላቅ ትኩረት መመልከት ያለበት ይህንን ሁኔታ ማመቻቸት የሚችሉ አባቶች ብቻ መሆናቸውን ነው፤ ምዕመን ሥልጣን የለዉም፤ ልጅም አባትም ሊሆን አይችልም፤ ሆኖም አባቶችን ፖለቲካን ከመቅደሱ ከአሶጣችሁ  ወደ ቤተክርስቲያን አንመጣም ማለት  የምዕመን መብት ስለሆነ ሁኔታን የመለወጥ አቅም አለው፤ ነገር ግን ይህ አቅም በፖለቲካ ኃይል ስለተያዘ ቤተክርስቲያኗን ነፃ የሚያወጣው ኃይል የፖለቲካ ሰው ተብሎ ከቤተክርስቲያን እንዲገለል ተደርጓል፤ ከሁሉ በላይ የሚያስገርመው ደግሞ አባቶች ብቻ ሳይሆን ምዕመናን በፖለቲካ ተደራጅተው ቤተክርስታያኑ የአባዮ እና የጋሼ ቤት ማድረጋቸው ነው። አንጋፋ የሆነችው  የዲሲ ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን የአባዬ እና የጋሼ ቤት ሆናለች፤ የፖለቲካ ካድሬዎች ወንጌላዊ ሆነው ዓለም ልትለማ ነው ዓለም ልትጠፋ ነው እያሉ ምዕመኑን እያዋከቡት ነው፤ ሥርዓት አልባነት ነግሶ የቤተክርስቲያን በር ተሰብሮ ቤተክርስቲያኑን የሰሩትን አባላት አባረው ምንም የሚያቁቱን የሰንበት ተማሪዎች እንደ አጋዚ ዘበኛ አቁመው ደም እናፈሳለን በማለት የውንብድና ተግባራቸዉን እየሰሩ ነው። ከቤተክርስቲያን ደጀ ሰላም ላይ ቆሞ አትገቡም ማለት የተሐድሶ ዋና መገለጫ ነው፤ ከዚህ በላይ ተሐድሶነት አይኖርም።  እንደዚህ አይነቱ ሕግ ወጥነት ሊመጣ የቻለው የቢተክርስቲያኑን ታሪክ በአለማወቅ የተነሳ ነው።

ታሪኩ ከመተረኩ በፊት ግን ስለታሪክ አጻጻፍ በአጭሩ መወያየት ያስፈልጋል። ታሪክ ጸሐፊዎች አንድ አይነተኛ የሆነ የአጻጻፍ ዘዴ አይጠቀሙም፤ በተለምዶ የሚጽፉ ታሪክ ጸሐፊዎች ድርጊቱ በተደረገበት ተደርጓል የተባለዉን ድርጊት በመረጃ ተደግፈው ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ ለምን ድርጊቱ ሆነ ብለው ሳይመረምሩ በቀጥታ ይጽፋሉ። ለምሳሊ ገድል፤ዉዳሲ፤ተአምር የአገር መሪ ያደረጓቸውን ድርጊት በጽሑፍ ያስቀምጣሉ። የታሪክ አጻጻፍ ስልት በትምህርት ገበታ ተቀምጠው የሰለጠኑ ጸሐፊዎች ደግሞ ለምን ድርጊቱ እንደተረገ አመላካች ምክንያቶችን እየፈለጉና ትርጉም እየሰጡና እያመሳከሩ ይጽፋሉ፤ መላ ምታቸዉም ያ ነገር ባይኖር ኖሮ ድርጊቱ አይሆንም ነበር እያሉ ይጽፋሉ፤ ይህም ማለት ለሁሉ ነገር መነሻ አለው ያለመነሻ ምንም ነገር ሊሆን አይችልም፤ በተጨባጭነት ያለዉን ሁኔታ ለመለወጥ ለዋጭ ሃይል ያስፈልጋል ይላሉ፤ ይህም ሆኖ ሁሉንም የሚያስማማ አንድ አይነተኛ ዘዴ እስከአሁን ድረስ አልተገኝለትም፤ ከሁሉ በላይ አስቸጋሪ ሆኖ የተገኝው በዋቢነት የሚሰበሰቡ መረጃዎች ናቸው፤ ታሪክ ድርጊቱ በሚሰራበት ወቅት ሊጻፍ አይችልም፤ ምክንያቱም ገና ታሪክ አልሆነም፤ ቢያንስ ሶወስት ትውልድ [90 ዓመት] ማለፍ ይኖርበታል፤ በግዚው የሚጻፈው ታሪክ ሳይሆን መረጃ ነው፤ ከሶወስት ትውልድ በኋሏ መረጃው እንዳለ ቢጻፍ ታሪክ መሆኑ ቀርቶ ንግርት ይሆናል፤ ንግርት ማለት የሆነ የአልሆነዉን በማጋነን ለዕለት ጥቅም ማግኛ የሚነገር ትዕይንታዊ አነጋገር ነው፤ በአሁኑ ዘመን ወንጌላዊ ነን ብለው የሚሰብኩ ሰባኬዎች የሚሰጡት ትምህርት ንግርት ነው፤ ከመጻሕፍ ቅዱስ ዉጭና ከሃይማኖት ጋር ፈጽሞ የማይገኛን ዓለማዊ ሆኖ አላማው የፖለቴካ ሥርፃቱን ማጠናከር ነው፤ ለምሳሌ ከዚህ የሚከተሉቱን የሁለት ወዶ ገባ ካድሬዎችን ትምህርት በአንክሮ እንመልከት፤ “ካድሬ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ከቤተክርስቲያን ሥርአትና ደንብ ውጭ የሆነ ትምህርት ለማስተማር ተብሎ “መምሕር” የሚባል የቤተክርስቲያን ማዕረግ በመጠቀም ቤተክርስቲያናትን የፖለቲካ ሥርዓትን እንድትከተል ለማድረግ “የካድሬ” ስራዎችን ስለሚሰሩ ነው። ትምህርቱም የሚያመለክተው “የካድሬን” ባሕርይ ነው። በአንክሮ እንመልከተው።0

ስለ ቅዱስ ሲኖድ የተሰጠ ትምህርት፡

ገለልተኛ ቤተክርስቲያናትን ጠቅልሎ በመንግሥት ስር ለማድረግ ካድሬው በጥያቄ መልክ ስለሲኖድ ሲያስተምር እንዲህ ይላል፤ ጥያቄ፡ [ካድሬ] ሲኖድ ስንት ነው? መልስ፡ [ምዕመናን] አንድ ነው፤  [ካድሬ] የሲኖድ መንበር በማን ሥም ነው የተሰየመው? [ምዕመናን] በተክለሃማኖት፤ [ካድሬ] ሲኖድ ከሃገር ዉጭ ይሰደዳል? [ምዕመናን] አይሰደድም፤ [ካድሬ] የኛ የኢትዮጵያ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ስንት ሲኖድ አለን? [ምዕመናን] አንድ ነው፤ [ካድሬ] ይህ ሲኖድ የትነው ያለው? [ምዕመናን] ኢትዮጵያ፤ [ካድሬ] ስለዚህ ይህ  የናንተ ቤተክርስቲያን በማን ስር መሆን አለብት? [ምዕመናን] በታላቅ ጭብጨባ፤ በከበሮ፤ በዕልልታ በመዝሙር፤ በዋዜማ፤ በሽብሽባ፤ በማዕበል ታጅቦ ኢትዮጵያ በአለው ሲኖድ ስር እያለ ሲጨፍር ካድሬው እዚያ ላይ አላቆመም፤ ገና ምን አይታችሁ? አንድ ገለልተኛ [ከፖለቲካ ነፃ የሆነ] የሚባል ቤተክርስቲያን አይኖርም፤ ወደዛች ቅድስት በሆነች ምድር ለመመለስ ሁላችንንም ተዘጋጅተናል፤ በቅርብ ግዜ ሁሉም ቤተክርስቲያን ተጠቃለው ይገባሉ [በመንግሥት ስር ይሆናሉ]፤ የእግዚአብሒር ስም የተመሰገነ ይሁን፤ ወስብሐት ለእግዚአብሒር።

ስለ ካህናት የበላይነት የተሰጠ ትምህርት

ይህ ትምህርት ከዚህ በፊት ከተሰጡት ትምህርት የሚለይበት ምክንያት በአዲስ መምሪያ ተዘጋጅቶ ምዕመናኑን በአንድ አገዛዝ ስር ሆኖ የፖለቲካዉን ሥርዓት ሳይቃወም አቤት ብሎ እንዲገዛ ተቀነባብሮ የቀረበ ነው። ካድሬውም ስሜትን በሚያነቃቃ መንፈሳዊ መዝሙር ትምህርቱን ይጀምራል። የሚገርመው ደግሞ ትምህርቱና መንፈሳዊ መዝምሩ አይጣጣሙም፤ መዝሙሩ መንፈሳዊ፤ ትምህርቱ ፖለቲካዊ ሆኑ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ምዕመኑን በመንፈሳዊ ዜማ ስነ ልቦነዉን ይዘው ሳያስበው  በደመ ክልብ ያለዉን የፖለቲካ ሥርዓት  ከሃይማኖቱ ጋር አዋህዶ እንዲቀበለው ነው። ካድሬው ስለ ካህናቱ የበላይነት ሲፈላሰፍ እንዲህ ይላል፤ እግዚአብሒር ካህናቱን “ቀብቷችዋል” [ቅባት]፤ ደግሞም የተለየ “ጸጋ” አልብሷችዋል [ጸጋ] ከመላእክትም በላይ ናቸው፤ እሚቤተኞችና አፈንጋጭችን በስይፍ [ካራ] የመቅጣት ኃይል ተስጥቷችዋል። ይህ ከተባለ በኋሏ ዉዳሴው ይቀጥላል፤ [ካድሬ] ቤተክርስቲያን አላችሁ ወይስ የላችሁም? [ምዕመናን] አለን፤ [ካድሬ] ቤተክርሲቲያኑ ዉስጥ ታቦት አለ ወይስ የለም? [ምዕመናን] አለ፤ [ካድሬ] ቅዳሴ ይቀደሳል? [ምዕመናን] ይቀደሳል፤ [ካድሬ] ቅዳሴዉን ማነው የሚቀድሰው? [ምዕመናን] ቄሶች (ቀሳዉስት]፤ [ካድሬ] ካህናቶች (ካህናት) ቀድሰው ያቆርባሉ? [ምዕመናን] ያቆርቡናል፤ [ካድሬ] ቤተክርስቲያን፤ቅዳሴ፤ቁርባን ያለ ካህኖች (ካህናት) ሊኖር ይችላል? [ምዕመናን] አይችልም፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያንና ምዕመናን ያለ ካህኖች (ካህናት) ሊኖሩ አይችሉም፤ ምዕመናን የካህናቱ ተገዝዎች [ለፖለቲካ ሥርዓቱ?] መሆን አለባችሁ።

ውይይትና ትንተና

እዚህ ላይ የሚደረገው ውይይት ስም ተጠቅሶ አንዱ ሌላዉን ለመወቀስ ሳይሆን “ሁኔታ” እንዴት አድርጎ የስዉን ልጅ ታሪካዌ ሂደት እንደሚቆጣጠረው ለመረዳት የሚያስችል ግንዛቤ እንዲኖረን ነው። ካድሬ ተብለው የተጠቀሱት ከኢትዬጵያ አብራክ የወጡ ወጣት ልጆች ናቸው፤ ያለፈው ትውልድ በፈጠረው “ሁኔታ” ዉስጥ ያሉ አሁን ከሚያውቁት በላይ የማያውቁ ናቸው። ለማወቅ ያለመፈለግ ሳይሆን እንዲያውቁ አልተደርገም። ለምሳሌ የመጀመሪያዉን ትምህርት እንመልከት፤ በአርግጥ ሲኖድ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር እቃ አይደለም፤ መንበሩም ለተወሰነ አገር ሲኖድ የሚሰጥ ስም ነው፤ መንበረ ማርቆስ፤መንበረ ጴጥሮስ፤ መንበረ ቶማስ፤ መንበረ ተክለሃይማኖት እየተባሉ ለተመረጠው ፓትርያርክ መቀመጫ ነው። ፓትሪያርኩ ቢሰደድ መንበሩ ከሱ ጋር አይሰደድም፤ በታሪክም ተደርጎም ተሰምቶም አያውቅም፤ ፓትሪያርኩ የፈለገዉን ሊያደርግ ይችላል፤ ከአልተመቸው ወደገዳም ይሄዳል።  መንበሩን ከለቀቀ በኋላ  ግን መልሶ ይገባኛል የማለት መብት የለዉም፤ የቤተክርስቲያኑ ሥርዓት ያግደዋል። እዚህ ላይ ካድሪው ያልገባው ነገር ቢኖር የቤተክርስቲያናችንን ታሪክ ነው፤ ቤተክርስቲያኑን የሚያዝ ከፓትሪያርኩ በላይ ያለ አካል ነው፤ ሲኖዱን ተቀበል ማለት የፖለቲካውን ሥርአት ተቀበል ማለት ነው፤ በዚሁ አይነት ለካህናቱ ታዘዙ ማለት የፖለቲካውን ሥርዓት አክብሩ ማለት ነው፤ ይህ ትዕዛዝ ተግባራዊ ከአልሆነ ግን ካህኑ በቅዳሴ ጊዚ ጠላቶቿን [የፖለቲካ ተቋዋሚ ኅይሎችን ማለት ነው] በፍጥነት አስገዛላት ማለት ቋዋሚ ሥራው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ካድሪው ያልገባው ነገር ቢኖር “ቅባት” “ጸጋ” “”ካራ” የተባሉት የፕሮቶስታንት እምነቶች ናቸው፤ ይኸዉም የክርስቶስን ባሕርይ የሚገልጹ ስነ መለኮትን የሚፃረሩ እምነቶች ናቸው፤  ተዋህዶ ይህንን አይቀበልም። ታሪኩ ውስጥ ስንገባ በሰፊው ይዘረዘራሉ። እነዚህ ካድሪዎች መንግስት ባዋቀረው “ተሐድሶ” ሳያውቁት ተጠልፈው ገብተዋል፤ ስለዚህ ነው አንዱ ሌላዉን “ተሐድሶ” እያሉ በማያውቁት ነገረ መለኮት ውስጥ ገብተው የተሳሰሩት፤ እውር እውሩን ቢመራ ተያይዘው የሚሄዱት ገደል ነው፤ ግን ከሁሉ በላይ የሚገርመው ሰው ገደል ሲገባ ዕልል እያለ፤እያጨበጨበ፤ እየጨፈረ መሆኑ ነው። እንግዲህ ይህ ከተባለ በኋላ መፍትሄው የቤተክርስቲያኑን ታሪክና ነገረ መለኮትን በቅጡ ማወቅ ግዲታ ነው። በክፍል ሁለት የኢትዬጵያን ቢተክርስቲያንን አጭር ታሪክ እንመለከታለን ። ይቀጥላል፤ መልካም ንባብ።

tarikuw@gmail.com

ምንጭ      _      ሳተናው

Leave a Reply