(ኢ.ኤም.ኤፍ) ዛሬ በየቀበሌው ምርጫ ሲካሄድ ነው የዋለው:: የምርጫው ዋና አላማ በመጪው 2007 በኢትዮጵያ የሚደረገውን የምርጫ ሂደት ለመታዘብ የሚችሉ ገለልተኛ ሰዎችን መምረጥ ነው:: ይህን አመልክቶ ሁኔታዎችን ስንከታተል ነበር:: በቅድሚያ ይህን አስመልክቶ ዘጋባውን ያሰፈረው ፍኖተ ነጻነት ነው:: በመቀጠል ደግሞ አቶ ተክሌ በቀለ በግል የታዘቡትን አስተያየት ልናቀርብላችሁ ወደድን:: በቅድሚያ ፍኖተ ነጻነት እንዲህ ይላል::

የህዝብ ታዛቢ በመሆን ሊያገለግሉ የሚችሉ ሰዎችን ለመምረጥ በየቀበሌው በተደረገው ታዛቢዎችን የማስመረጥ ሂደት ላይ የገዢው ፓርቲ አባላት በታዛቢነት መመረጣቸውን በምርጫው ሂደት ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች ለፍኖተ-ነፃነት ገለፁ፡፡

በዛሬው እለት ታዛቢዎችን በማስመረጥ ሂደት ላይ “የገዢው ፓርቲ አባላት ህዝቡን በማግለል እርስ በእርስ በመመራረጥና የምርጫ ሂደቱን በድብቅ እያካሄዱ” መሆኑን የገለፁት የፍኖተ-ነፃነት ምንጮች “ይህ አካሄድ ህገ-ወጥ እና የምርጫውን ደንብ የጣሰ” መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በደንቡ መሠረት የየትኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል የሆነ ሰው ታዛቢ መሆን እንደማይችል የተገለፀ ቢሆንም ይህ ደንብ ተጥሶ የገዢው ፓርቲ አባላት በታዛቢነት እየተመረጡ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተያያዘ ዜና የህዝብ ታዛቢ ምርጫውን ለመታዘብ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ወረዳ የተገኙ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባላት በተመረጡት የህዝብ ታዛቢዎች ላይ ባነሱት ቅሬታ የተነሳ ለእስር መዳረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከታሰሩት የአንድነት ፓርቲ አባላት ውስጥ የወረዳ 12/13 ሰብሳቢ የሆነው አቶ ብሩክ አየለ ይገኝበታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ከሄዱት መሃል የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆኑት እየሩሳሌም ተስፋው እና እመቤት ግርማ የታሰሩ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል::

በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ተክሌ በቀለ የዛሬውን ምርጫ በስፍራው ተገኝተው ታዝበው ተመልሰዋል:: እንዲህ ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጡ::

በዛሬው እለት የህዝብ ታዛቢ በመሆን ሊያገለግሉ የሚችሉ ሰዎችን ለማስመረጥ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት/አካላት፤ አመራሮችም ጭምር በተለያዩ የምርጫ ጣብያዎች እንደተገኙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የታዘቡትን እያካፈሉን ሲሆን እኔም ያየሁትን ላካፍል ወደድኩ፡፡ የታዘብኩት የየካ ክ/ከተማ ወረዳ ዘጠኝን ነዉ፡፡ መቐለ ከተማ ወረዳ ሓዉልቲ ያለሁ ነበር የመሰለኝ፡፡ አስተባበሪዎቹ፤ የወረዳዉ ካድሬዎች፤ የአንድ ላምስት አስተባባሪዎች፤ በሰፈሩ የማዉቃቸዉ ደህንነት ነን ባዮች ወዘተ ከተጠራዉ ህዝብ በቁጥር አያንሱም፡፡ የሚሉትን በሙሉ እኔና ታዛቢ አድርጌ የወሰድኩት የማይጨዉ ሰዉ እንሰማለን፡፡ አደራጅተዋቸዉ ለቀሩባቸዉ ስልክ ይደዉላሉ፤ ግርግር በሌለበት ይጨነቃሉ፤ የላኩዋቸዉን ለማስደስት መልእክቱንም በሸፍጥ ለመፈጸም ሽልጉድ ይላሉ፤ ከዉጭ ሆነዉ ይሰልላሉ፤ የማያዉቁትን ያሰተውላሉ::
ኢህኣዴግን ምርጫ እያስጨነቀዉ መሆኑንና ምርጫ ቦርድም ከጭንቀቱ ሊገላግለዉ ከልኡካኖቹ አንዱ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ታዝቧል፡፡ …በመላ አገሪቱ የተመረጡቱ የዛሬዎቹ የህዝብ ታዛቢዎች ሁሉም በኢህኣድግ ደም የሚሰሩ ፍጡራን ናቸዉ በማለት መደምደም በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ መቁረጥ አይገባም፡፡ በምርጫዉ ሰበብ ብቻ ህዝቡን ለማደራጀት የሚያስችሉ ቀጣይ ስራዎችና እድሎች አሉን፡፡ እንጠቀምባቸዉ፡፡

እንግዲህ በዛሬው እለት ምርጫውን የሚታዘቡ ሰዎች በየቀበሌው ተመርጠዋል:: ሁሉም ተመራጮች ኢህአዴጎች ናቸው የሚል ተስፋ አቆራጭ መላምት የለንም:: ቢሆንም ግን የዛሬውን የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫ በመጠኑ የታዘብነውን አቅርበንላችኋል::

Leave a Reply