ዜና መድረክ
>
> የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ /መድረክ/ #ነፃ፣ ፍትሐዊና ታአማንነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ
> በሀገራችን እውን እንዲሆን እንጠይቃለን$ በሚል መሪ መፈክር ያዘጋጀው ሰላማዊ ሰልፍ ታህሳስ 5 ቀን
> 2007 ዓ ም በአዲስ አበባ ከተማ እጅግ ደማቅ በሆነ ሁኔታ ተካሄዷል፡፡
>
> በሰላማዊ ሰልፉ ከ10000 እስከ 15000 የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት ሲሆን ከአራት ኪሎ በስተምሥራቅ ከሚገኘው
> የግንፍሌ ወንዝ ድልደይ ተነስቶ ሰልፈኛው ሲያስተጋባቸው በነበሩ ወቅታዊ መፈክሮች ደምቆ ወደ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8
> ኳስ ሜዳ ድረስ ተካሄዳል፡፡
>
> በወቅቱ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ሲያስተጋቡ ከነበሩት መፈክሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡
>
> 1-  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንጂ በአስመሳይ ፕሮፓጋንዳ፣ በኃይልና በተጽኖ  አይገነባም!!
>
> 2-  የሀገራችን ችግሮች በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በሚገለጽ የሕዝብ ውሳኔ እንጂ በኃይል እርምጃ አይፈቱም!!
>
> 3-  ከምርጫ በፊት የምርጫ ውድድር ሜዳው የሚስተካከልበት ውይይትና ድርድር እንዲካሄድ አጥብቀን እንጠይቃለን!!
>
> 4-  በማስመሰያ ምርጫ በየአምስት አመቱ ሕዝብን ማታለልና ሀብቱን ማባከን ይቁም!!
>
> 5-  የማስመሰያ ምርጫ ለማካሄድ ለሚባክነው የሀገርና የሕዝብ ሀብት ኢህአዴግ ተጠያቂ ነው!!
>
> 6-  ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በሌለበት ሁኔታ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት እውን ሊሆን አይችልም!!
>
> 7-  ሕዝባችን በ1ለ5 መረብ አፈናና ቁጥጥር ከሚካሄድ የምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ነፃ እንዲሆን እንጠይቃለን!!
>
> 8-  ያለገለልተኛ የምርጫ አስተዳደርና ያለገለልተኛ የምርጫ ታዛቢ ታአማንነት ያለው ምርጫ ሊኖር አይችልም!!
>
> 9-  ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ይቋቋም!!
>
> 10-  በካድሬዎች የሚከናወን የምርጫ አስፈጻሚነትና ታዛቢነትን አንቀበልም፣ እናወግዛለን!!
>
> 11-  ነፃ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ታዛቢዎች ምርጫውን በነፃነት የሚከታተሉበትና የሚታዘቡበት ሁኔታ እንዲመቻች
> እንጠይቃለን!!
>
> 12-  በምርጫ ወቅት በታጠቀ ኃይል በሕዝባችን ላይ የሚፈጸም ማስፈራሪያና ወከባን እናወግዛለን!!
>
> 13-  በሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ የሚካሄድ እስራትና ወከባ በአስቸኳይ ይቁም!!
>
> 14-  ኢህአዴግ በመንግሥት ሀብትና ንብረት የሚያከሄደውን ሕገወጥ የምርጫ ዘመቻ እናወግዛለን!!
>
> 15-  የጸጥታ ኃይሎች የሕዝብ አገልጋዮች እንጂ ሕዝብን ማስፈራሪያና ማሸማቀቂያ መሆን የለባቸውም!!
>
> 16-  ያልተሟላ የምርጫ ሥነምግባር ኮድ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም!!
>
> 17-  ከድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎችን ማባረር የሕዝብን ድምጽ ለመስረቅ ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲቆም
> እንጠይቃለን!!
>
> 18-  የሕዝብን ድምጽ መዝረፍ ዴሞክራሲን መገንባት ሳይሆን መቅበር ነው!!
>
> 19-  የምርጫ ጣቢያዎች ከአስተዳደር አካላትና ከታጣቂ ሠራዊት ተጽኖና አፈና ነፃ ይሁኑ!!
>
> 20-  በምርጫ ወቅት በምርጫ ጉዳዮች ፈጣን ውሳኔ የሚሰጡ ነፃና ገለልተኛ ዳኞች በየደረጃው እንዲኖሩ እንጠይቃለን!!
>
> 21- ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና መግደል ሕዝባችን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሥልጣን ባለቤት ለመሆን
> የሚያካሄደውን ትግል አይገታም!!
>
> 22-  ሀሳብን የመግለጽ ሕገመንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው የታሰሩ የሕልና እስረኞች በሙሉ በአስቸኳይ ይፈቱ!!
>
> 23-  በግፍ የታሰሩ ሰላማዊ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ ጋዜጠኞችና የሙስሊሙ ማሕበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊዎች በአስቸኳይ
> ይፈቱ!!
>
> 24-  የፀረ-ሽብር ሕጉን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀሚያ ማድረግን እናወግዛልን!! ሕገ-መንግሥታዊ መብትን በማይጥስ ሁኔታ
> በአስቸኳይ እንዲሻሻልም እንጠይቃለን!!
>
> 25-  የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ለገዥው ፓርቲ የሚያሳዩትን ወገንተኝነት በአስቸኳይ  ያቁሙ!!
>
> 26- ሁሉም ፓርቲዎች በሕጋዊና ፍትሐዊ አግባብ ከመንግሥት በጀት ድጋፍ የሚያገኙበት ሥርዓት እንዲኖር አጥብቀን
> እንጠይቃለን!
>
> 27-  በነፃነት የመሰብሰብና የመደራጀት መብታችን ይከበር!!
>
> 28-  የአንድ አምባገነን ፓርቲ ሳይሆን ትክክለኛ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንሻለን!!
>
> 29-  ኢህአዴግ ለሕገመንግሥትና ለሕግ ተገዥ በመሆን ለነፃ ምርጫ እራሱን እንዲያዘጋጅ እንጠይቃለን!!
>
> 30-  የሕግ የበላይነት ባልተከበረበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት አይቻልም!!
>
> 31-  የኑሮ ውድነቱና የተጎሳቆለው የሕዝባችን ሕይወት የኢህአዴግ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው!!
>
> 32-  በወገንተኝነትና በአድልኦ በሕዝባችን ላይ የሚጫን ግብር በአስቸኳይ ይስተካከል!!
>
> 33-  በልማት ስም በሕገወጥና ግብታዊ በሆነ መንገድ ሕዝብን ማፈናቀልና ለችግር ማጋለጥ  እንቃወማለን!!
>
> 34-  የመሬት ወረራ ይቁም!!
>
> 35-  በሙስና የተዘረፈው የሕዝብ ሀብት ለሕዝቡ ይመለስ!! ሙሰኞችም ለፍርድ ይቅረቡ!!
>
> 36-  የውኃ፣ የማብራት፣ የትራንስፖርትና የስልክ አገልግሎቶች ችግሮቻችን በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው
> እንጠይቃለን!!
>
> 37- የአህአዴግ አገዛዝ በሐይማኖቶች የውስጥ ጉዳዮች የሚፈጽማቸውን ጣልቃ ገብነቶች እናወግዛለን!!
>
>
>
> ሰልፈኛው በውረዳ 8 ኳስ ሜዳ /ታቦት ማደሪያ/ ከደረሰ በኃላ የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው
> የኢህአዴግ አገዛዝ በሀገራችን ሕዝብ ላይ የጫነው የግፍ አገዛዝ ሰለባዎች ሆነው ለስደት የተዳረጉትና በቅርቡ በየመን የቀይ
> ባሕር ዳርቻ በደረሰባቸው አደጋ ሕይወታቸውን ላጡት ወገኖቻችን መድረክ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በግንባሩ የሥራ አስፈጻሚ
> ኮሚቴ ስም ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተላልፈዋል፡፡ በመቀጠልም የሀገር ሸማግለዎች፣ የወጣቶችና የሴቶች
> ተወካዮችና የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር በየተራ  ንግግር አድርገዋል፡፡
>
>
>
> የሀገር ሸማግሌዎችን በመወከል ንግግር ያደረጉት የቀድሞ የኦፌዴን ሊቀመንበርና የፓርላማ አባል ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ
> ሲሆኑ እርሳቸውም ባደረጉት ንግግር ኢህአዴግ በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እገነባለሁ እያለ ለረጅም ጊዜ ሲያታልለን
> የቆየ ቢሆንም ቃሉን በተግባር ላይ ስላላዋለ የኢትዮጵያ ሕዝብ #በቃህ$ ሊለውና በራሱ ነፃ ምርጫ በሚመርጠው ፓርቲ ሊመራ
> ይገባል ብለዋል፡፡ የመድረክ የወጣቶች ክንፍ ተወካይ የሆኑት አቶ ደስታ ዲንቃ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ
> ወጣቶች በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የከፈሉት መስዋዕትነት ከፍተኛ ቢሆንም የምንፈልገው ሥርዓት እስከ አሁን
> ተግባራዊ ስላልሆነ ትግላችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ በመድረክ አባል ሆነው እየታገሉ ያሉትን ሴቶች በመወከል
> ወ/ሪት ኤልሳቤጥ ሊማሳ ባደረጉት ንግግር ትግላችን አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝን ለማስወገድና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት
> ለመገንባት ስለሆነ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አመካይነት ይህ እውን ሆኖ እስከገኝ ድረስ በፆታም ሆነ በሌላ ነገር ሳንለያይ
> ጠንክረን መታገል ይገባናል ብለዋል፡፡
>
>
>
> በመጨረሻም ክቡር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ለሰልፈኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት መድረክ የተለያዩ
> የሀገራችን ችግሮች በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውይይትና ድርድር እንዲፈቱና ነፃ፣ ፍትሐዊና ታአማንነት ያለውን ምርጫ ተግባራዊ
> ለማድረግ እንዲቻል በተደጋጋሚ ለገዥው ፓርቲ የውይይትና የድርድር ጥያቄዎችን ሲያቀርብ የቆየ ቢሆንም በኢህአዴግ አሻፈረኝ
> ባይነት እስከ አሁን ሥራ ላይ ለማዋል አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም
> በ2007 በሚካሄደው ምርጫ ሂደት ውስጥ ከመገባቱ በፊት እስከአሁን በተካሄዱት ምርጫዎች የተፈጸሙት ሕገወጥ ተግባራት
> የሚወገዱበትን ሁኔታ በውይይትና በድርድር ለማምጣት ያቀረብነው ጥያቄ ችላ ተብሎ ወደ ምርጫው ውስጥ እየተገባ ስለሆነ
> የዛሬውን የተቃውሞ ሰልፍ ለመጥራት መድረክ እንደተገደደ ገልጸው የኢትዮጵያ ሕዝብም ብቸኛ የሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ
> መሣሪያው የሆነውን ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እውን ለማድረግ ወሳኝ ድርሻውን እንዲየበረክት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
>
>

Leave a Reply