ታኀሳስ ፲፬(አስራ አራት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-መድረክ ባወጣው መግለጫ  በሀገራችን የምርጫ ሂደት የነበሩ ጉድለቶችንና በተለይም በ2002 የሀገራችን የምርጫ ሂደት የወረደበትን አዘቅት በሚገባ በጥልቀት ገምግሞ እነዚህን ቀደም ባሉት ምርጫዎች የነበሩ ጉድለቶችን ማረምና ማሰተካከል ለ2007 ምርጫ ነፃ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን የምኖረውን ወሳኝ ሚና በግልጽ ቢያስቀምጥም፣ ይህንን እውነታ በአግባቡ መገንዘብ ያልቻሉና ከ1997 እና ከ2002 ምርጫዎች ደካማ ጎኖች ተገቢውን ትምህርት ለመቅሰም ያልቻሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመሠረታዊ የምርጫ ችግሮች ላይ የመደራደሩን ጉዳይ ወደጎን ትተው በምርጫው ለመሳተፍ ወስነናል የሚል መግለጫ አሰቀድመው መስጠታቸው ልክ ቅንጅት በ1997 ተቻኩሎ ለኢህአዴግ የለገሰውን አይነት ድጋፍና እፎይታ እየቸሩለት ይገኛሉ ብሎአል፡፡

የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ልብ ያገኘው ኢህአዴግ፣  መድረክ ያቀረበውን የድርድር ጥያቄ ወደ ጎን ትቶ በ1997 ሳይፈቱ የቀሩ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን በ2002 የጨመራቸውን እንደ 1ለ5 የጠርናፊና ተጠርናፊ የምርጫ ሠራዊት መዋቅሩን አጠናክሮና የሕዝብ የምርጫ ታዛቢ ጉዳይንም በአስቅኝ ድራማው እያጠናቀቀ ይገኛል ብሎአል፡፡

መድረክ በመግለጫው  ኢህአዴግ  በድርጅታዊ መዋቅሩ አማካይነት በስውር በጠራቸው ጥቂት አባሎቹ አማካይነት ቀደም ብሎ የተዘጋጁ ምልምሎቹን የሕዝብ ታዛቢዎችን አስመረጥኩ እያለ ለትዝብት ያጋለጠውን ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል ሲልም አክሏል።

ኢህአዴግ በሕዝብ መብት ላይ መቀለዱን ትቶ ሕገ መንግሥቱንና ሕግን አክብሮ ምርጫን ማካሄድ ስለሚቻልበት ሁኔታ ጊዜ ሳያባክንና ሳይረፍድ ከመድረክና ሌሎችም ለዚህ ዓላማ ዝግጁ ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር በመወያየትና በመደራደር የሀገራችን የምርጫ መሠረታዊ ችግሮች የሚፈቱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች እንጠይቃለን ብሎአል።

መድረክ በባሕርዳር ከተማ በሰላማዊ አግባብ ተቃውሞ ባሰሙ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የአምባገነናዊ አገዛዝ ባሕሪይ ነጸብራቅ በሚል አውግዞታል።

አገዛዙ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሕይወት ማጥፋትና የአካል መጉደልን ጨምሮ የወሰደው  የኃይል እርምጃ ቀደም ሲልም የሌሎች ሀይማኖቶች ተከታይ በሆኑትና በተለያዩ አከባቢዎች በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየ በመሆኑ የሥርዓቱን ኃላፊነት የጎደለው አምባገነናዊ ባሕሪይ ገላጭና በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተባብሮ ሊታገለው ይገባል ብሎአል።

የኢህአዴግ አገዛዝ ኃላፍነቱን ወስዶ በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን በአስቸኳይ ካሳ እንዲከፍልና ጥቃቱን የፈጸሙ ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ መድረክ ጠይቋል።

Leave a Reply