24 DECEMBER 2014 ተጻፈ በ 

ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ

የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክትን ችግር ስንመለከት ከህንድ ኩባንያ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይህ የህንድ ኩባንያ ከቻይናዎች አቅም ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የአቅም ችግር እንዳለበት ነው የተገነዘብነው፡፡

ይህ በብዙ መልኩ ፕሮጀክቱን በማጓተት የራሱን ድርሻ ተጫውቷል፡፡ እንግዲህ ያ ፕሮጀክት በዚህ መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ ከዚያ ባሻገር የተያዙት አዳዲሶቹን ፕሮጀክቶች በምናይበት ጊዜ በዘንድሮ ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ልናከናውናቸው ያቀድናቸው የስኳር ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡ በለስ አንድና ሁለት የምንለውን ጨምሮ የፋብሪካ ግንባታቸው በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚገነባ ነው፡፡ እየወደቅንና እየተነሳን ነው የምንሠራው፡፡ ስለዚህ ነገ እንደ ቻይና የስኳር ፕሮጀክቶችን በራሳችን አቅም ገንብተን ማምረት እንድንችል የሚያስችል አቅም እንድንገነባ፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ አቅም መጎልበት ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህም የኩራዝ አንድ ፕሮጀክት በያዝነው ዓመት መጋቢት አካባቢ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡ እነዚህ ሦስት ፋብሪካዎች የመጀመሪያዎቹ ቢሆኑም ግንባታው አልጋ በአልጋ ሊሆን አይችልም፡፡ ዘላቂውን የአገራችንን የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ችግሮቹን ተቋቁመን ጊዜው ቢራዘምም እንደምናሳካው እርግጠኞች ነን፡፡ ሌላው የአርጆ ደዴሳ ስኳር ፕሮጀክት ከፓኪስታን ኩባንያ ጋር የምናካሂደው ነው፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ወደ ሥራ የሚገባበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የስኳር ፋብሪካዎቹ ፕሮጀክቶች መዘግየታቸው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በጠቀስናቸው ምክንያቶች የተነሳ በመሆኑ ጊዜያቸውን ጠብቀው መጠናቀቃቸው የማይቀር ነው፡፡

ሌላው ከማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ጋር ተያይዞ የተነሳው ጉዳይ ነው፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችንም ቢሆን የፋብሪካዎቹ ግንባታ በአገር ውስጥ ለማድረግ ነው ሐሳባችን፡፡ ሁሉም አገር እንደሚታወቀው እንዲህ ዓይነት ከባድ ውሳኔ በመወሰን ነው እዚህ የደረሰው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የፋብሪካዎቹ ግንባታ 25 በመቶ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ዓመት የሚያልቅ አይሆንም፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ሊገባደድ ይችላል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡

በሶቨሪን ቦንድ ላይ

ሌላው ኢትዮጵያ የሶቨሪን ቦንድ ለገበያ ማቅረቧ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት የምትጠቀምበት አንዱ መሣሪያ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ወደዚህ ዓይነቱ መንገድ ያልገባችበት ምክንያት የሂፒክ አገሮች የሚባሉት (የዕዳ ጫና) ያለባቸው አገሮች የእንዲህ ዓይነቱ ዕድል ተጠቃሚ ስላልነበሩ ነው፡፡ አቅማቸው ለዚያ የደረሰ ነው ተብሎ ስለማይወሰድ ማለት ነው፡፡ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት አገራችን ይህ ዕድል አልነበራትም፡፡ ከአምስት ዓመት ወዲህ ግን ተገምግማ ይህን ፈቃድ ወስዳለች፡፡ ይህን ደግሞ የሚገመግሙት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ይህን ፈቃድ በማግኘታችን ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ዕድል ይፈጥርልናል፡፡ ለምሳሌ የስኳር ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ብድር የተገኘው ከህንድ ነው፡፡ ይህ ብድርም ኮሜርሻል ብድር ነው፡፡ ለባቡር መንገድ ግንባታም ከቻይናና ከቱርክ ብድር ተገኝቷል፡፡ በአጭሩ ይህ ሁሉ የሚሆነው አገር ተገምግማ፣ ይህን ብድር መሸከም ትችላለች አትችልም በሚለው፣ የኢኮኖሚ ዕድገቷና የፀጥታው ሁኔታው ታይቶ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አገራችን ተገምግማ ‹‹B (+)››፣ ‹‹B›› ያገኘች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይኼ በታዳጊ አገሮች ደረጃ ትልቅ ውጤት በመሆኑ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ልትበደር ችላለች፡፡ በእነሱ በኩል ግን ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የመበደር አቅም እንዳለን ተሰልቶ ነበር፡፡ ይሁንና አሁን ያለን ፍላጎት ያን ያህል ባለመሆኑ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንድንበደር አስችሎናል፡፡ የብደር ጫናን በተመለከተ አምስት መለኪያዎች አሉ፡፡ አንዱ አገሪቱ ያለባት የብድር ጫና ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ጋር ያለው ምጣኔ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ካሉ እንደ ጋና፣ አይቮሪኮስት፣ ወዘተ. ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ወደ 21 በመቶ የሆነ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ምጣኔ እስከ 50 በመቶ እስኪደርስ ድረስ መበደር እንችላለን፡፡ ሌላው ኤክስፖርት የምናደርገው ከወጭ ብድራችን ጋር ሲለካ ያለው ምጣኔ ሲሆን ይህም ከብድሩ 20 በመቶ ያነሰ መሆን የለበትም፡፡ የታክስ ገቢውም የብድር ምጣኔውም እንዲሁ ተለክተው ሲታዩ አገራችን በብድር ክምችት፣ በአረንጓዴ ወይም ዝቅተኛ አደጋ (Risk) በሚባለው ደረጃ ውስጥ መሆኗን ማየት ይቻላል፡፡ ብድሩን እንድንወስድ ያስቻለንም ይህ ነው፡፡ ስለዚህ የብድር ክምችት ሥጋት ሊሆን አይችልም፡፡

ሌላው ከግብርና ስትራቴጂው አኳያ የተነሳው ጉዳይ ነው፡፡ ግብርናው በአርሶ አደሮች ደረጃና በግል ባለሀብቶች ደረጃ የሚከናወን ነው፡፡ አገራችን ሰፊ የሚለማ መሬት ያላት በመሆኑ የግል ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ እንዲሰማሩ ይፈለጋል፡፡ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እያደገ ነው፡፡ መሬቱ በማንም ያልተያዘ፣ የአካባቢ እንክብካቤን ከግምት ያስገባና ልማቱ በተለያዩ ምዘናዎች ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ለባለሀብቶቹ የሊዝ ሥርዓት አዘጋጅተናል፡፡ ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂውን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የማይፈናቀሉበት መሆኑን በአገራችን ውስጥ ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያረጋገጡት ነው፡፡ ይሁንና ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ዘመቻ የሚያካሂዱት ለምንድነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ለዚህ ምላሻችን ‹‹ግመሉም ይሄዳል፣ ውሻውም ከኋላ እየተከተለ ይጮሃል፤›› ነው፡፡ ዋናው እነዚህ ኃይሎች የተቋቁሙበት ምክንያት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምዕራባውያን እንደፈለጉ የሚያሽከረክሩት መንግሥት ስለሌላት ነው፡፡ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ነው የምንመክረው፡፡ እኛም ይህንን በመዋጋት እንቀጥላለን፡፡ እነዚህ የኒዮ ሊበራል ኃይሎች ለተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ያወጧቸው መድኃኒቶች ብዙዎቹን ገድለዋል፡፡ ስለዚህ እኛ ይህን መድኃኒት መዋጥ አንፈልግም፡፡ የሚያዋጣንን የራሳችንን እንወስዳለን እንጂ፡፡ ከእነሱ ጋር ጥላቻ ስላለን ወይም እንካ ሰላንቲያ ስላማረንም አይደለም፡፡ ከዚህ ውጪ ፈጣን ዕድገት ልናስመዘግብ ስለማንችል ነው፡፡ እነሱም በአገራችን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ተቋማትን በማስነሳት ሊያንበረክኩን ይፈልጋሉ፡፡ ምርጫ 97 አንዱ ምሣሌ ነው፡፡ አሁንም ከምርጫው ጋር ተያይዞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን የሚያቀርቡት መግለጫም የዚህ አካል ተደርጎ የሚታይ ነው፡፡ ነገሮች ሲሟሟቁ እነሱም ይግላሉ፡፡ ነገሮች ሲቀዛቀዙ ደግሞ እነሱም ተቀዛቅዘው ቁጭ ይላሉ፡፡ ስለዚህ ይህ የተለመደ አካሄዳቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚወስነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት መሥራት ነው እንጂ ለእነዚህ ሁኔታዎች አንንበረከክም፡፡ በቤንሻንጉልና በጋምቤላ አካባቢ ያሉ ተፈናቀሉ የተባሉ ማኅበረሰቦች ‹‹እኛ አልተፈናቀልንም፣ አታውኩን›› ብለው ነግረዋቸዋል፡፡ እነሱ ኬንያና በጎረቤት አገሮች ያሉ ስደተኞችን ነው አናግረው የሚያቀርቡት፡፡

መጪውን አገር አቀፍ ምርጫ በተመለከተ

ምርጫውን በተመለከተ ይህን ታዳጊ ዲሞክራሲ ለማጎልበት ሁላችንም የራሳችንን ሚና መጫወት አለብን ነው፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለዚህ መሥራት አለባቸው፡፡ ዲሞክራሲ እንዲያብብ ከተፈለገ ሁሉም ወገኖች ለመጫወቻ ሜዳው ፍትሐዊነት መታገል አለባቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ይህንን ከእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ጋር ያመሳስሉታል፡፡ ሁሉም ሰው ተቆጣጣሪ በሌለበት የእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ ገብተህ ተጫወት አይባልም፡፡ ሕግና ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት የምንጫወትበትን ሜዳ በአግባቡ ለመጫወት ያስችለናል ባልነው መሠረት የምርጫ ሕግ አውጥተናል፡፡ ከዚህ ውጪ እንጫወት ለሚሉ ቢጫ ካርድ ሲያልፉም ቀይ ካርድ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ እኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሦስት ነው የምንከፍለው፡፡ አንደኛ ሕጉን አክብረው የሚጫወቱ፣ ሁለተኛ ገባ ወጣ የሚሉና ሌሎቹ ደግሞ ከሕግ ውጪ የሆኑት ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በውጭ አገር ካሉ የተገለሉ ድርጅቶች ጋር የሚሠሩና ለአመፃና ትርምስ የሚሠሩ አሉ፡፡ የሕግ የበላይነትን ካልተቀበሉ መጫወት አይችሉም፡፡ መንግሥት ደግሞ ይህንን ማስከበር አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ‹‹መሪዎቻችን ታሰሩ ከማለት ይልቅ ለምን ታሰሩ?›› ብለው ነው መጠየቅ ያለባቸው፡፡ እኔም እንደማስበው ይህ ነው አግባብ ያለው አካሄድ፡፡ ከዚህ ውጪ ከተኬደና መንግሥትን ለመፈታተን የሚፈልግ ካለ፣ መንግሥትን መፈታተን አይቻልም ነው መልሱ፡፡ አንዳንዶች በልማት ቦታዎች ሰላማዊ ሠልፍ ማካሄድ አለብን ይላሉ፡፡ ይኼ መንግሥትን መፈታተን ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ በፓርላማ ‹‹አሸባሪ›› ተብለው ከተቦደኑ ጋር እየዶለቱ የሚውሉ አሉ፡፡ እነዚህ በሕግ እንዲጠየቁ ወደ ፍርድ ቤት እናቀርባቸዋለን፡፡ መንግሥት ሳይሆን ፍርድ ቤት ነው ይህንን የሚወስነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን መንግሥት ዝም ይላል ካሉ ተሳስተዋል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት የማያወላዳ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ይህ ካልሆነ በአፍሪካ ቀንድ እንደምናየው ቦምብ እዚህም እዚያም የሚፈነዳባት አገር እንድትሆን አንፈቅድም፡፡

ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ

ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ መንግሥታችን መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ተግቶ እየሠራ ነው፡፡ አሁን የተሻለ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ሁላችንም የድርሻችንን ስንወጣ ደግሞ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል፡፡ በቅርቡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል አባላት፣ ምሁራንን ጨምሮ በፖሊሲዎችና በስትራቴጂዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡ በመንግሥት ውስጥም እንዲሁ ተካሂዷል፡፡ ይህ ደግሞ መልካም አስተዳደርን ለማጎልበት የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይታሰባል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ሕዝቡ ያልረካባቸው ዘርፎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ይህን ደግሞ በሁለት መልኩ ከፍለን እናየዋለን፡፡ አንደኛው የሕዝባችን አገልግሎት የመጠቀም ሁኔታ ማደጉ ነው፡፡ ለምሣሌ የአዲስ አበባ ከተማ የመብራት አጠቃቀም ሥርዓት በሚታይበት ጊዜ፣ ሕዝቡ ከዚህ በፊት በጋዝ (ነጭ ጋዝ) የሚጠቀምበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን ሲጠና ስቶቮችን፣ ፍሪጆችንና ሌሎች የቤት ቁሳቁሶችን የሚጠቀሙ መሆናቸው ነው የሚታየው፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በራሳቸው ከ400 ሺሕ በላይ ሰዎች የሚኖሩባቸው ናቸው፡፡ ይህ በራሱ አንድ ከተማ ማለት ነው፡፡ ይህን ቀድመን ስላልተዘጋጀንበት በቀድሞው የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ጫና ይፈጥራል ማለት ነው፡፡

ለዚያ የሚመጥኑ ሰብ ስቴሽኖች ስለሌሉ በየጊዜው መቆራረጥ ይከሰታል ማለት ነው፡፡ ቀድመው የተተከሉት ትራንስፎርመሮች እየተቃጠሉ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ዕቅድ ትራንስፎርመሮቹን መቀየር ሲሆን ሌላው ሰብ ስቴሽኖችን ማደራጀት ነው፡፡ ይህን ለመሥራት ደግሞ እኛ ራሳችን እንግባ ብንል ጊዜ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ሌሎች የውጭ ድርጅቶች እንዲያከናውኑት ኮንትራት መስጠት ጀምረናል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ አካባቢ ከውጭ የሚገባው መስመር የራሱ ችግር አለው፡፡ ከዚህ ቀደም ተጀምሮ ለሰባት ዓመት የቆየው ሥራ እየተገባደደ በመሆኑ ይህን ችግር ይቀርፋል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ ፍጆታው አድጓል፡፡ ለጊዜው መፍትሔ ይሆናል ያልነውን ሁሉ እንሠራለን፡፡ ይህ ነው አንዱ የመልካም አስተዳደር ክፍተትን የፈጠረው፡፡ ውኃ ሌላው ችግር ነው፡፡ ይህንንም ለማቃለል ወደ አዲስ አበባ ከተማ ነባር የውኃ ማጣሪያ ወደ መቶ ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ እየገባ ነው፡፡ ያልተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች እስከመጪው መጋቢትና ሚያዚያ ድረስ ሲያልቁ፣ በአጠቃላይ ወደ 130 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ትልቅ መጠን ያለው ውኃ ሲገባ የአዲስ አበባን የውኃ ችግር የሚቀርፍ እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡ የስልኩ ጉዳይም እንደዚያው ነው፡፡ የኦፕሬሽንና ቴክኒካዊ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ የኔትወርክ ሥራውን በሚሠሩ ኩባንያዎች ሲስተም መካከል መደራረብ ነው ችግሩ፡፡ ብዙ የሚያሳስብ አይደለም፡፡ በቅርቡ ይስተካከላል፡፡ ሁዋዌ በሰሜን አዲስ አበባ ሥራውን ጀምሮታል፡፡ በቅርቡ ኤሪክሰንና ዜድቲኤም ሥራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ይህ እንደሚስተካከል ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ ስለተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ

ሰላማዊ ሠልፉን በተመለከተ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባዋል፡፡ የመንግሥት የጥበቃ ኃይሎች ብቻ ኃላፊነት አይደለም፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታት የፌዴራል ፖሊስ በዚህ ረገድ ሥልጠና ወስዷል፡፡ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ሠልፍ የተወሰነ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህ በማን እንደደረሰ በመጣራት ላይ ያለ ጉዳይ በመሆኑ ወደፊት ይገለጻል፡፡ በመንግሥት በኩል ሰላማዊ ሠልፉን በተመለከተ ፖሊስ በደንቡ መሠረት ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ይህ ደግሞ በሌላው አገርም የተለመደ ነው፡፡ ፖሊስ ተጠያቂ በሚሆንበት መንገድ ይጠየቃል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ይህ የሚጣራ ነው፡፡ የታጠቀ ኃይል ባዶ እጁን አይመጣም፡፡ መሣሪያውን ለመንጠቅ የሚሞክር ሠልፈኛ ካለ ጉዳት ይመጣል፡፡ ስለዚህ ሠልፈኛው ራሱ መጠንቀቅ አለበት፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ከሠልፈኛው ከራሱ የሚመጡ የጦር መሣሪያ ጥቃቶች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ አንዱ አንዱን ካጠቃ በኋላ መንግሥት እንዲህ አደረገ የሚል ሁኔታን ለመፍጠር የሚደረግ ነው፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የዘንድሮውን ምርጫ አለመታዘቡን በተመለከተ

ምርጫን በተመለከተ የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው መግለጫ የዘንድሮውን ምርጫ መታዘብ አንችልም፡፡ የሎጂስቲክስና የበጀት እጥረት ስላለብንና በሌሎች ቦታዎችም ትልልቅ ምርጫዎች ስላሉ የዘንድሮው ምርጫ ይለፈን ሲሉ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቀዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ ምርጫው በዋነኝነት የእኛ በመሆኑ ቢታዘቡም ባይታዘቡም እኛ ሥራችንን እንሠራለን፡፡ ከዚህ ውጪ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ወኪሎች ምርጫውን ይታዘባሉ፡፡ ምርጫው በዋነኝነት የእኛ በመሆኑ ቢታዘቡም ባይታዘቡም እኛ ሥራችንን ሥራ እንሠራለን፡፡ በዋናነት ራሳችን ምርጫውን ተዓማኒነትና ፍትሐዊነት ያለው እንዲሆን እንሠራለን፡፡

በሸቀጦች ላይ እየታየ ስላለው የአቅርቦት ችግርና የዋጋ ንረት

የ2015 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ በዓለማችን ፈጣን ዕድገት ከሚያሳዩ ሦስት አገሮች አንዱ ኢትዮጵያን አድርጓል፡፡ ይህንን በተመለከተ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን እንሠራለን፡፡ በዚህ ረገድ በሸቀጦች አቅርቦትና ዋጋ ንረት ላይ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ስኳርን በተመለከተም ይህን መሰል ሁኔታ በቅርቡ ታይቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ወደ ምርት አለመግባቱ ነው፡፡ አንድ የህንድ ኩባንያ ፍተሻ ሲያደርግ አንድ ዕቃ መሰበሩን ነው ያስታወቀው፡፡ ይህ ዕቃ ሲሰበር ወደ ህንድ ተልኮ መጠገን ነበረበት፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ለሁለት ወራት መዘግየት ተፈጠረ፡፡ ይህ ዕቃ ይሰበራል ብለን አልጠበቅንም፡፡ አሁን ግን ይህ ዕቃ ተጠግኖ ሥራ በመጀመሩ ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ችግር አይገጥመንም ብለን እናምናለን፡፡ የነዳጅ ችግሩን በተመለከተ ችግሩ የነዳጅ ድርጅቶች ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋው ዝቅ በማለቱ የነዳጅ ድርጅቶች ይህንን ጊዜ ሸውደው ለማለፍ የፈጠሩት ዘዴ ነው፡፡ አሁን ግን ከነዳጅ ዴፖዎች መንግሥት ነዳጅ እያቀረበ በመሆኑ ይህ ችግር ይቀረፋል፡፡ ወደፊት ግን በእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራን ነው፡፡ ለምሣሌ በየወሩ የሚደረግ የነዳጅ ዋጋ ክለሳን በየወሩ ይሁን ወይስ ረዘም ባለ ጊዜ የሚለውን ከሌሎች አገሮች ልምድ አንፃር እያየነው ነው፡፡

በግብፅ ተልዕኮውን ፈጽሞ ስለተመለሰው ሕዝባዊ ልዑካን ቡድን

በግብፅ ተልዕኮውን ፈጽሞ የመጣው ቡድን ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ አገራችን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ሰላምንና መግባባትን እናስፋፋ ነው የምትለው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለመላው ኢትዮጵያዊ ዋናው ጠላት ግብፅ ሳይሆን ድህነት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ግብፆች የተለያዩ የፀብ አጫሪነት ሁኔታዎችን ፈጥረው ነበር፡፡ ይህ ግን አሁን እኛ ባለን ድህነትን የማሸነፍ ዓላማ ተቀይሯል፡፡ የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነቱ የተሻለ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡ ይህን ደግሞ ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ደረጃ ማውረድ ስላለብን የተለያዩ የእምነት አባቶችን፣ ምሁራንና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ግብፅ ተጉዟል፡፡ በጣም ጥሩ አቀባባል ነበር የተደረገላቸው፡፡ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ጥሩ የሚባል ሥራ ተሠርቷል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ግን የተፈጠሩትን ጥርጣሬዎች ያጠፋል ማለት አይደለም፡፡ እነሱም በተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ይህ በሒደት የሚታይ ይሆናል፡፡

በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ

የሕገወጥ የሰዎች ዝውውሩ በተለይ ወጣቶች የተሳሳተ መረጃ በመውሰድ የለመለመ መስክ በመጠበቅ እዚያ ላይ ተሰማርቼ ማጨድ አለብኝ በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ የሚካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ርብርብ የለመለመ መስክ እንደሌለ ማስገንዘብ አለብን፡፡ ይህ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ ምን ያህል ብሷል፣ ወይስ ቀንሷል የሚለው በጥናት የሚታይ ነው፡፡ አሁንም ግን ፍልሰቱ አለ፡፡ ሌላው የዚህ ጉዞ መነሻ ምንድነው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ወጣቶች በአገር ቤት ሥራ የሚፈጥሩበት ሁኔታን መፍጠር አለብን፡፡ አሁን በአገራችን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ሥራ አጡ የኅብረተሰብ ክፍል 17 በመቶ ይሆናል፡፡ ከበፊቱ ቢቀንስም ይህም በራሱ ቀላል ቁጥር ባለመሆኑ መቀነስ አለበት፡፡ የሥራ ባህሉም መቀየር ይገባዋል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በጉልበትም ቢሆን ሠርቶ ነገን የተሻለ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሁሉም የተማረ ኃይል የጉልበት ሥራን የሚሸሽ ከሆነ ኢትዮጵያ የጉልበት ሠራተኛ አይኖራትም ማለት ነው፡፡ እነዚህ ተሰደው የሚሄዱትስ ምንድነው የሚጠብቃቸው ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ያ የለመለመ መስክ የጉልበት ሥራ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህ ፍልሰት የበዛው ወደ አንዳንድ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚደረገው ጉዞ በመከልከሉ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ ይህም በጥናት መረጋገጥ አለበት፡፡ እኔ በበኩሌ ይኼም በአውሮፕላን ሆነ እንጂ ከዚያኛው የሕገወጥ ጉዞ አይሻልም፡፡ ከደላሎች ጋር  ሳይሆን ከመንግሥታት ጋር ስምምነት ሲኖረን ብቻ ነው የምንፈቅደው፡፡

ስለውጭ ብድር ፖሊሲው

ቀደም ሲል በቅድሚያ የኢትዮጵያ የብድር ፖሊሲ በቀጥታ አንድ አገር ወይም ከለላ አገር ብድር ማግኘት አለብን ብሎ የሚደነግገው ነገር የለም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በቅርቡ የሶቨሪን ቦንዱን ጨምሮ ከሌሎች ምንጮች ኮሜርሽያል ብድር ማግኘት የጀመረችበት ምክንያት ቀደም ሲል ወደዚህ ካታጐሪ የሚያስገባ አቅም ስላልነበረን ነው፡፡ እንደገለጽኩት የምናገኘው የውጭ ብድር፣ ቦንዱን ጨምሮ ከእኛ አቅም ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአፍሪካ አገሮች ወደ ኮሜርሻል ብድር መግባት አለባቸው ብለው ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ወደ ካፒታል ገበያ የሚያበቁ መሥፈርቶችን በማሟላት ነው የቦንድ ሽያጩ የተከናወነው፡፡ የካፒታል ገበያው በተፈጥሮው በምዕራብ አገሮች ላይ ነው፡፡ በብዛት የሚገኘው ወደ ቻይናና ሌሎች የምሥራቅ አገሮች ያየን እንደሆነ በብዛት የካፒታል ገበያው አይገኝም፡፡ ሊገኝ የሚችለው የፕሮጀክት ብድር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የኮሜርሽያል ብድር በብዛት ከምዕራብ አገሮች ገበያ ነው የሚወሰደው፡፡

ሌላው ጉዳይ ብድር አወሳሰድ ነው፡፡ ብዙ አገሮች በዚህ ምክንያት ዕዳ ገብተዋል፡፡ ይህም ብድሩን ለፍጆታ ማለትም ለደመወዝና ለመሳሰሉ ክፍያዎች አውለውት ነው፡፡ እኛ ግን አምስት ሳንቲሙን ከመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ውጪ አናውልም፡፡ ጎረቤቶቻችን ይህን ማድረግ አይችሉም፡፡ የኃይል አቅርቦታቸውን ለውጭ ኩባንያዎች ሰጥተዋል፡፡ የልማታዊ መንግሥት ውጤት ይኼ ነው፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ  

ከደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በኢጋድ ሊቀመንበርነቷ ለደቡብ ሱዳን ሰላም የራሷን ሚና ተጫውታለች፡፡ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በመካከላቸው የሕዝቡን መብትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕድሉን በተመለከተም ድርሻዋ የተለየ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ሱዳን ቅርንጫፉን እንዲከፍት አስችሏል፡፡ እርግጥ ነው እንደሌሎች ጐረቤት አገሮች ለምሳሌ እንደ ኡጋንዳ እንዳሉ አገሮች አይደለም፡፡ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን የበለጠ የኢኮኖሚ ትስስሩን ያጠናከሩት ስላለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ግን ምንም እንኳ በእኛ በኩል ያለው የመንገድ መሠረተ ልማት ተሠርቶ ቢያልቅም፣ በደቡብ ሱዳን ወገን ያለው ግን አልተሠራም፡፡ ወደፊት እኛም ያንን መንገድ እንከተላለን፡፡

ባለሀብቶቻችንን በተመለከተ ግን የምንመክረው ከመንግሥት ጋር ሳይሆን ከሕዝቡ ጋር የሚፈጠር ሽርክናን እንዲመሠርቱ ነው፡፡ ዘላቂ የሚሆነው ኢንቨስትመንት መንግሥት ከመንግሥት ጋር ሳይሆን ሕዝብ ከሕዝብ ጋር የሚፈጥረው ነው፡፡ ሶማሊያን በተመለከተ 65 በመቶ የሚሆነውን አካባቢ የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ ሌሎቹ ቁጥራቸው ትልቅ ቢሆንም የሚቆጣጠሩት ቦታ ትንሽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ስትራቴጂ ሌሎችን ተክቶ ማውራት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከጊዜ በኋላ ከዚያ መውጣቱ ስለማይቀር ነው፡፡ ያ ማለት ሶማሊያውያንን አሠልጥነንና አብቅተን፣ እኛ ጥቂቶች እኛ ብዙዎች ሆነን በርካታ ቦታዎችን እንዲይዙ በማድረግ አልሸባብን መምታት ይሆናል ዓላማችን፡፡ ሶማሊያውያን ወታደሮችን በእኛ ቅርጽና ዲሲፕሊን አሠልጥነን አልሸባብን እንዲዋጉ የማብቃት ግብ አለን፡፡ ይህ በመሆኑም ዛሬ አልሸባብ 65 በመቶ ከሚሆነው አካባቢ እንዲለቅ ነው የተደረገው፡፡ ነገር ግን በዚህ መሀል በፕሬዚዳንቱና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል የተከሰተው ሽኩቻ ጉዳት ቢኖረውም ያን ያህል አልነበረም፡፡ ችግራቸውን በውል ስለምናውቅ ከኢጋድና ከምዕራባውያን ጋር ተመካክረን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራውን እንዲቀጥል አድርገናል፡፡

ከጂቡቲ ጋር ያለው የኢኮኖሚ ትስስርና የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋበሩ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡ ለጂቡቲ ዜጎች የተሰጠ የተለየ ዕድል አለ፡፡ ለምሣሌ አንድ የጂቡቲ ዜጋ በኢትዮጵያ ቤት መሥራት ይችላል፡፡ ይኼ ደግሞ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ለማጠናከር ታስቦ ነው፡፡ በአፍሪካ ኅብረት 2063 አጀንዳ የአፍሪካን አንድነት ለማሳካት በተወጠነው መሠረት የክልላዊ ድርጅቶች ቅድሚያውን መውሰድ ስላለባቸው በኢጋድ ሥር የሚከናወን ዕቅድ ነው፡፡ ለጊዜው ግን ለኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ቅድሚያ ሰጥተናል፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና ይዞታ ላይ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችና የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር

የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ መንግሥት ቤቶቹን የሚያስተላልፍበት ግልጽ መመርያ አለው፡፡ ከተተኪ ቤቶች በስተቀር ሌሎች በዕጣ ነው የሚደርሳቸው፡፡ ለሰባት ዓመት ይመስለኛል በቀጥታ ሽያጭና ዝውውር ማስተላለፉ ሕገወጥ ነው፡፡ ይህን አጣርተን ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ ሕጉን ተከትሎ የተፈጸመ ከሆነ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ በግለሰቦች የብድር ውልና ስምምነት እጃችንን አናስገባም፡፡ የቤት ኪራይን በተመለከተ ግን የሚፈቀድ አይደለም፡፡ በአደጉ አገሮች ጭምር የቤት ኪራይን ዋጋ ማናር አይቻልም፡፡ ነፃ ገበያም ቢሆን በሕግና በሥርዓት የሚመራ ነው፡፡ በዚህ  ረገድ እየተሠራበት ነው፡፡

የትራንስፖርት ችግሩን በተመለከተ ግልጽ ነው፡፡ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ይሁንና መሻሻል እየታየ ነው፡፡ ከመጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ውጪ የትራፊክ ፍሰቱም ችግር ነው፡፡ አውቶብሱም፣ ታክሲውም ሁሉም አንድ ላይ ይጓዛል፡፡ የሕዝብ መጓጓዣዎች የተለየ መስመርና ዕድል ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የመጓጓዣዎች ቁጥር በመጨመርና የትራፊክ ፍሰቱን አስተዳደር በማስተካከል ሊቃለል ይችላል፡፡ የከተማ ነዋሪዎች መጓጓዣ ባደጉት አገሮችም ጭምር ለግል ባለሀብቶች አዋጭ ባለመሆናቸው በመንግሥት ነው የሚተዳደሩት፡፡ የባቡር መስመር ግንባታን በተመለከተ እንደ አዲስ አበባ ቀላል ባቡር በፍጥነት የተገባደደ ግንባታ የለም፡፡ በሦስት ዓመት ውስጥ ከ37 ኪሎ ሜትር በላይ ተገንብቷል፡፡ በቀጣይ የካቲት ወር ላይ የሙከራ ሥራውን ይጀምራል፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር በዚህ መቅረፍ አይቻልም፡፡ ተጨማሪ የባቡር መስመርና አማራጭ የትራንስፖርት አቅርቦቶችን እንገነባለን፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ የትራፊክ ፍሰቱም በዘመናዊነት መቀጠል አለበት፡፡ በርካታ ተቋማት ጽሕፈት ቤቶችን አዲስ አበባ ውስጥ እየተከፈቱ በመሆናቸው የመንገድ የትራፊክ ሥርዓቱም መሻሻል አለበት፡፡

የአዕምሮ ፈጠራን በተመለከተ

በመንግሥት የኢኖቬሽን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ውስጥ የተቀመጡ ግልጽ መመርያዎችና ፖሊሲዎች አሉ፡፡ ይህን ለማስፈጸም የተቋቋመ ካውንስል አለ፡፡ በተጨማሪ የመምህራን ማኅበራት በካውንስሉ ውስጥ መግባት ካለባቸው የሚታይ ይሆናል፡፡ ሌላው አገራችን ከፍተኛ እመርታን ልታመጣበት የምትችልበት ዘርፍ የባዮ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚህ ረገድም የተዘጋጁ መመርያዎች አሉ፡፡ በወጣቶች የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የሚሠሩ አምራቾችም ማበረታቻ ይደረግላቸዋል፡፡ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መመሥረትም አንዱ ለዚህ በመሆኑ ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ግብዓት እንዲሆኑ ይበረታታሉ፡፡ በመለዋወጫ ማምረቻ ረገድ አሁን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ማምረት በሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ሁሉም ክልሎች ማለት ይቻላል፡፡ የመለዋወጫ ፋብሪካዎች አላቸው፡፡ በስፋት እየተሠራበት ያለ ዘርፍ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማትን በተመለከተም ተመሳሳይ ነው፡፡ በየሥርቻው የቀሩ የምርምር ውጤቶችን ለመደገፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ሥራውን እየሠራ ይገኛል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የአምራች ተቋማት ክትትልና ደረጃ አሰጣጥ ካውንስል አለ፡፡ ካውንስሉንም የምመራው ራሴ ነኝ፡፡ በዚህ ረገድ ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የፋይናንስ እክል ገጥሞታል ስለመባሉ ጉዳይ

መንግሥት የሶቨሪን ቦንድን ሸጦ በሚያገኘው ገቢ ለፈለገው ዓይነት የመሠረተ ልማት ማዋል ይችላል፡፡ ለህዳሴው ግድብ ግን የፋይናንስ እክል ስላልገጠመን እዚያ ላይ አይውልም፡፡ ገንዘቡ የመንግሥት ኪስ ውስጥ ቢገባም ለጊዜው በህዳሴ ግድቡ ላይ አይውልም፡፡ በዋናነት ይህ ገንዘብ በስኳር ልማቱና በኢንዱስትሪ ማኑፋክቸሪንግና የኤክስፖርት ዘርፉን ማሳደግ ላይ ነው የሚመደበው፡፡

ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ስለሚደረግ የጋራ ምክክር መድረክ

እኛ ሁልጊዜም በራችን ክፍት ነው፡፡ ‹‹ይኼ ፓርቲ ካለ አልሰበስብም›› የሚሉ አሉ፡፡ ከ91 ፓርቲዎች ጋር በዚህ መልኩ የሚደረግ የተናጠል ውይይት አይኖርም፡፡ ለጋራ አገራችን በጋራ እንወያይ የሚል ጥሪ ማቅረብ ግን እፈልጋለሁ፡፡

Leave a Reply