እኔ የዓረና-መድረክ ኣባል ከመሆኔ የተነሳ በምርጫ 2007 ዓ/ም ለፌደራል ወይም ለክልል ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ እንደምሆን የራሴ እቅድ ይዤ ነበር፤ እናንተም በተመሳሳይ ግምት እንደምትጠብቁ እገምታለው።

ኣሁን እየሆነ ያለው ግን “…ለምሳ ያሰቡን ለቁርስ ኣደረግናቸው..” ዓይነቱ የጓድ ሊቀ መንበር መንግስቱ ዓይነት ተግባር ህወሓት መራሹ የትግራይ መንግስት እጩ “ሽብርተኛ” ኣድርጎው ኣጭተውኛል።

እም በኣቅሚቲ “..የኣሸባሪነት..” ካባ ለብሼ ቅሊንጦ ወይም ሌላ ወህኒ ቤት እንደምላክ ዛሬ ጥዋት 02:00 ሰዓት ኣከባቢ በ የመቐለ ፖሊስ ኮማንደር ገብረሂወት፣ የመቐለ ዞን የፀጥታ ሃላፊ ኣቶ ወልዳይ ፣ የሓወልቲ ክፍለ ከተማ የፀጥታ ሃላፊ ኣቶ ኣዲሱና የሓወልቲ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ኮማንደር ገብረዝግኣብሄር ኣለማዮ በሓወልቲ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ወስደው ነግረውኛል።

“..የኣሸባሪነት..” እጩ እንደሆንኩ የተነገረኝ ሂደት ባጭሩ ልተርክላቹ።

ጥዋት 02:00 ሰዓት ኣከባቢ ዓዲ ሹምድሑን ከሚገኘው ቤቴ(ክራይ) ኣገር ሰላም ነው ብየ ስወጣ ሁለት ፖሊሶች እየጠበቁኝ ከነበሩበት ጥግ በመምጣት “..መታወቅያ ኣሳየኝ..” ብሎ ወጣት ፖሊስ ጠየቀኝ።

እኔም የራስዋ ታሪክ ያላት የቀበሌ መታወቅያዬ ሰጠሁት። ወጣቱ ፖሊስም “..በፅህፈት ቤት ለስራ ትፈለጋለህ..” ብሎ ወሰደኝ። የመያዣ መጥርያ ኣለህ ወይ ብየ ስጠይቀው “..ዩኒፎርም ለብሼ እያየኸኝ እንደት መጥርያ ብለህ ትጠይቀኛለህ?..” ብሎ እንደ መቆጣት ኣሰኘው።

ሰፈሬ ፖሊስ ጣብያው ቅርብ ነውና በሁለት ፖሊሶች ታጅቤ ወደ ፖሊስ ፅህፈት ቤቱ ሄድኩኝ። ሶስት ሰዓት ኣከባቢ ላይ ስማቸው የተጠቀሱት ሃላፊዎች ወዳለሁበት ክፍል ገቡ። ሞባይሌና መታወቅያዬ ከኮማንደር ገብረዝግኣብሄር የተያዘ ሲሆን ሃላፊዎችም ማንኛውም ድምፅ መቅረፅ የሚችል ኤለክትሮኒክስ እቃ እንዳይኖረኝ በመጠየቅ የያዙት ኣጀንዳ ነገሩኝ።

ኮማንደር ገብረሂወት “…ዛሬ በቁጥጥር ስር ያዋልንህ በዓረና ፓርቲ ኣባልነትህ ሳይሆን በኣገር ደህንነትና ፀጥታ ጉዳይ ነው..” በማለት ኣያያዜ ከፖለቲካዊ ኣሽጥር ነፃ እንደሆነ ነገረኝ። ይሁን ብየ ማድመጠ ቀጠልኩ።

በተመሳሳይ ኣነጋገር የፃጥታ ሃላፊውም የመያዜ ምክንያት ምንም ፖለቲካዊ ተልእኮ እንደሌለው ለማሳመን ደከመ። ያድርገው ብየ እሺታዬ ገለፅኩ።

ኮማንደር ገብረሂወት “..ዛሬ የመያዣህ ምክንያት ከተለያዩ ህገ መንግስቱ በሃይል ለመናድ የሚታገሉና ኣሸባሪዎች ግንኙነት እንዳለህ መረጃ በእጃችን ስላለ በዚህ ጉዳይ ልናነጋግርህ ፈልገን ነው። በዚህ መሰረት ከነማን እንደምትገናኝ ራስህ ብትገልፅልን.?..” የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ።

እኔ” .. ኣሸባሪ..’ ከሚባል ማንኛውም ኣካል ግንኙነት እንደሌለኝና እኔም ኣባል የሆንኩበት ዓረና ፓርቲም በሰለማዊ ትግል የምናምንና የምንመራ መሆናችን ኣስረግጨ ገለፅኩኝ።

ኮማንደር ገብረሂወት “..ጎይተኦም በርኸ ታውቀዋለህ ወይ..?.” ሲል ጥየቀኝ። ኣዎ በ2003 የዓረና ሁለተኛ ጉባኤ ማእከላይ ኮሚቴ ኣባል ሁኖ ተመርጦ ነበር። ከተወሰኑ ቀናት በሗላ ግን በኤርትራ ሚድያ ኣስመራ እንደገባ መዘገቡን ሰንቻለው። ከዛ በሗላ ግን ስለ ልጁ የማውቀው ነገር እንደሌለ ገለፅኩ።

ኮማንደር “..በ2006 ዓ/ም በስልክ ግንኙነት ነበራቹ..? “ብሎ ተናገረ። ጎይተኦም ከሚባል ሰው ኣልተደዋወልኩም።

“..ኣብራሃ ደስታ ጓደኛህ ነው። ኬንያ ደርሶ እንደተመለሰ ታውቃለህ፣ ኣብራሃ ከተለያዩ “ኣሸባሪዎች” ግንኙነት እንደነበረው፣ ኣንተም ከኣብራሃ የቀረበ ግንኙነት ስለነበርህ ኣብራቹ እየሰራቹ ነበር..” የሚል ክስ ቀረበብኝ።

“…ኣብራሃ ደስታ ጓደኛየ ነው፣ የትግል ጓዴም ነው። ኣብረን በሰለማዊ መንገድ የዓረና ፖሊሲና ስትራተጂ በመላው ትግራይ ኣስተምረናል፣ ቀስቅሰናል። “ሽብር” የሚባል ጉዳይ እኔ የማውቀው ነገር የለኝም፣ ኬንያ መሄዱም ኣለመሄዱም ኣላውቅም። እኔ እንደማውቀው ኣብራሃ ሰለማዊ ታጋይ መሆኑ ብቻ ነው።..” ኣልኩኝ።
“ኣብራሃ ደስታ በምን እንደተከሰሰ ኣታውቅም..?” በሚድያ የተገለፀውንና ፍርድቤት ከቀረበው ክስ ውጭ የማውቀው ነገር የለኝም።

“..ኣንተ ከኣሸባሪዎች ካልተደዋወልክ እኛ ስልክህ እንዴት ልናገኘው እንችላለን..?”
የኔ ሰልክ ከዓረና በራሪ ፅሁፍ ተፅፎ ስላለ ማንኛውም የትግራይ ኑዋሪ ያገኘዋል።

ሰለ ኣያያዜ የበለጠ ለማስረዳት የፈለጉት ኣቶ ወልዳይ “..እኛ በፖለቲካ ማሰር ከፈልግን የዓረና መሪ ኣቶ ብርሃኑ በርኸ ነው ማሰር የነበረብን እናንተ እያሰርን ያለነው ግን ማስረጃ ስላለብን ነው..’ በማለት ገለፀ።(“..ኣቶ ብርሃኑ በርኸን ማሰር ይቀለን…” የምትለዋን ኣነጋገር የትግራይ ክልል ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ኣቶ ሓዱሽ ዘነበም ደጋግመው ይናገሯታል)።
እኔም ኣቶ ብርሃኑ በርኸን ያላሰራቹበት ምክንያት ይኖባቹሃል። ኣቶ ብርሃኑ ኣልታሰሩም ብሎ ያለ ሰው የለም። እኔ የማውቀው ግን ወጣቶች በብዛት ማሰራቹ ነው። ወጣቱ ደግሞ የማንኛውም ማህበረሰብ የለውጥ ሃይል መሆኑ የታወቀ ነው።

ኣቶ ወልዳይ “…ኣንተ ገና ወጣት ነህ፣ የሰራኸው ወንጀል ከፍተኛና ወህኒ ሊያስወርድህ የሚችል ነው። እኛ የምንመክርህ ግን የሰራኸው ጥፋት ኣምነህ ህዝብ ፊት ቀርበህ በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅና ምህረት እንድታግኝ ነው..” ሲሉ ነገሩኝ።

እኔ ለሃገርና ለወገን ደህንነት ኣደጋ ሊሆን የሚችል ስራ በፍፁም ኣልሰራም። በሰለማዊ መንገድ ህገ መንግስቱ በሚያዘው ኣግባብ ሰለማዊ ትግል መርጬ የምታገለው ከውስጤ ስለማምንበት ነው። ያላቹት ዓይነት በደል በሃገሬ ላይ ኣልመኩረውም።
እደምትሉት ፈፅሜው ብሆን ንሮ ለህዝብ ይቅርታ ለማለት ምንም ኣላቅማማም ነበር። እኔ ንኳን ሃገርን የምታኽል ታላቅ ነገር ኣንድ ግለ ሰው ብበድል ይቅርታ የማለት ልምድ ኣለኝ።
ይሁን እንጂ የምትሉኝ ጥፋት ስላላጠፋው ይቅርታ የምልበት ምክንያት የለኝም። እኔ የመረጥኩት ሰለማዊ ትግል ህብረተሰቡ የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ ነገር እንዳለው ኣይታየኝም። በማለት ኣሳወቅኩኝ።

እነ ኮማንደር መጨረሻ ያስተላለፉብኝ ትእዛዝ, ማስጠንቀቅያ “..የተወሰነ ግዜ እንድታስብበት ሰጥተናኻል። ኣስበህ ይቅርታ ብለህ ከኣደጋ ራስህን ኣውጣ እንለሃለን። በፈለግነው ሰዓት ኣስጠርተን ውሳኔኽ እናውቃለን..” ብለው ለቀቁኝ።

ኣዎ..! እኔም ከምርጫ ተወዳዳሪ እጩ ወደ “የሽብር” ታሳሪ እጩ ሽግግር ኣድርግያለው። ይህ ማለት ለኣቅመ መታሰር ደርሻለው ማልት ነው።

“..ይህ ሳናውቅ ፖሊስ ኣልተቀጠርንም..” ኣለ ፖሊሱ፤ እኛም በኣሁኑ ሰዓት ኣሳርያችንና ኣሳሳርያችን ቀድመን ኣውቀናል።

ኣሁን ከፍተኛ ውድድር የሚደረገው በዓረና-መድረክ ለምርጫ 2007 ዓም እኔን እጩ ኣድርጎ ማቅረብና የኢህወዴግ መንግስት ፀረ ሽብር ኣዋጀ ምክንያት ከእጩ ኣሸባሪነት ወደ ሙሉ ኣሸባሪ ለማሸጋገርና ከምርጫው ማስወጣት የሚደረግ ፉክክር ነው።

እቺ በፀረ ሽርብ ኣዋጅ ኣስታክኮ ዓረናን የማዳከም ዕቅድ ተግባራዊ እየተደረግች ትገኛለች።
ኣዎ..! መጪው ምርጫ ሰለማዊ፣ ፍትሃዊ ፣ ነፃ ከሆነ ዓረና ጠራርጎ እንዳያሸንፋቸው የሚደረግ ጥረት በሽብር ክስ ስም በርካታ የዓረና ኣባላት በማሰር ውጤቱን ለመቀየር ይሰሩበታል።

ህወሃቶች “..የኣሸባሪነት እጩ ኣድርገው ያቀረቡኝ ሂደት ይህ ይመስላል።

ወገን ህልም ተፈርቶ ሳተኙ ኣይታደርም ትግላችን ኣሁንም ይቀጥላል።

ነፃነታችን በእጃችን ነው..!

Leave a Reply