December 25th, 2014

መታሰር ክፉ ነው፡፡ የታሰረ ሰው ተስፋው ሁሉ ውጪ በቀረው ታጋይ ላይ ነው፡፡ የሀብታሙ አያሌው እና የየሺዋስ አሰፋ ልብ የሚነካ ተማፅኖ አእምሮዬን ሁሉ ተቆጣጥሮታል፡፡ ‹‹እባካችሁ ተባበሩ›› ‹‹እስቲ ቀረብ ብላችሁ ተነጋገሩ›› በየንግግራቸው መሀል እየደጋገሙ የሚያስተላልፉት መልዕክት ነው፡፡ ‹‹እኛ እኮ ከዛሬ ነገ ለውጥ መጥቶ ኑ ውጡ እንባላለን ብለን ነው የምንጠብቀው……በተናጠል ድርጅቶች ያላቸውን አቅም የምናውቀው ነው….እባካችሁ ተባበሩ›› ሀብታሙ አያሌው፡፡

አንድነት እና ሰማያዊ በትብብሩ ውስጥ አብረው መስራት ለምን አይችሉም???
አብረው መስራት የማይችሉበት ምንም ምክንያት ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ከሁለቱም በኩል በቀና እና ለውጥ ፈላጊ ልቦና ተቀራርቦ መነጋገር ከተቻለ የሚያግዳቸው ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ሀብታሙ አያሌው እና የሺዋስ አሰፋ ቂሊንጦ ሲገቡ ተግባብተዋል፡፡ እኛም ነገ ቂሊንጦ ከገባን መግባባታችን አይቀርም፡፡ ከዛም እንደ የሺዋስ እና ሀብታሙ ውጪ ያለውን ሰው ተባበሩ እያልን እንመክራለን፡፡ በተስፋ ምግብም መንፈሳችንን በሂወት ለማቆየት እንጥራለን…..ከንቱ ልፋት፡፡
ወህኒ ሳንወርድ አሁን ላይ መግባባት ስለምን ይሳነናል???
አሁን ባለው ነባራዊ እውነታ አንድነት እና ሰማያዊ በትግል ስልታቸው ላይ መጠነኛ ልዩነት ያላቸው ይመስላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነት መጠነኛ ልዩነት አይደልም በሁለት ፓርቲ መሀል ይቅርና በአንድ ፓርቲ ውስጥም ባሉ ግለሰቦች መሀል የሚከሰት ነው፡፡ አንድነት ያለምንም ቅድመ ሁናቴ ምርጫ ውስጥ እገባለሁ ብሏል፤ ሰማያዊ ደግሞ ቅድመሁናቴ አስቀጧል፡፡ ነገር ግን ከምርጫ ሂደት ውስጥ ወጥቻለሁ ያለ የለም፡፡ በመሆኑም ምርጫውን ያለቅድመ ሁናቴ የሚሳተፈውና ቅድመሁናቴ ያስቀመጠው አካል የምርጫ ምህዳሩን ለማስፋት፤ ምርጫው አልሆን ካለ ደግሞ ለህዝባዊ እምቢተኝነት ተባብረው የማይሰሩበት ምክንያት አይታየኝም፡፡
አንድነት ወደ ትብብሩ ያልመጣበት ምክንያት ከመድረክ ከወጣሁ በኋላ እንደገና ያለጥናት በፍጥነት ወደ ሌላ ትብብር ውስጥ መግባት የለብኝም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን አንድነት ፓርቲ ውህደት ከሆነ በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ ነኝ ይላል፡፡ ለመዋሀድ ዝግጁ የሆነ አካል ደግሞ ለመተባበር ይከብደዋል ብዬ ማሰብ ያቅተኛል፡፡ በመሆኑም ለመተባበር ዛሬ ነገ ሳይል ቢወስን ደስ ይለኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ትብብሩ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ግማሽ መንገድ ሄደው አንድነትን መቀበል አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድነት ካለው ድርጅታዊ አቅም አንፃር ታይቶ የትብብሩ ምክር ቤት አባል ብቻ ሳይሆን የትብብሩ ስራ አስፈፃሚም ውስጥ ተወካዩን እንዲያስገባ ሊፈቅዱለት ይገባል እላለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ለአረናም ሆነ ለኦፌኮ የሚሰራ ይመስለኛል፡፡
በዚህ መልኩ ተባብረው የሚሰሩ ከሆኑ ምናልባትም አሁንም ቢሆን ጊዜው አረፈደም እና ሁሉም ፓርቲዎች በስምምነት በአንዱ ፓርቲ የምርጫ ምልክት ሊወዳደሩ ይችላሉ፡፡ ይህ እንኳን ባይሆን በእጩ አቀራረብ ላይ እየተመካከሩ ድምፅ የማይነጣጠቁበትን መንገድ መፈለግ ይችላሉ፡፡ ምርጫው ነፃ እስካልሆነ ድረስ አላስፈላጊ ነው ብለው ካሰቡም በጋራ ህዝቡን ለህዝባዊ እምቢተኝነት የሚያነቁበትን እና የሚያደራጁበትን መንገድ መፈለግ ይችላሉ፡፡
በቅርቡ አንድነት ፓርቲ በተለያዩ ክፍለሀገሮች ሰልፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ትብብሩም ሁለተኛ ዙር መርሀግብሩን አውጥቷል፡፡ እነዚህን ሁለት እንቅስቃሴዎች ማቀናጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ከእንቅስቃሴዎቹ በፊት ፓርቲዎቹ አንዳች ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡
የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እኔም ሆንኩ ሌሎች ጓዶች መታሰራችን እንደማይቀር አውቀዋለሁ፡፡ እስር ቤት ከገባሁ በኋላ ግን ውጪ ያለውን አካል እንዲተባበር መለመንን አልሻም፡፡ ‹‹ቀን ሳለ ሩጥ›› እንዲሉ ዛሬ ውጪ እያለሁ ፓርቲዎቹ እንዲተባበሩ ሙሉ ጊዜየን ሰጥቼ እሰራለሁ፡፡ ሌሎችም እንዲሰሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡10653596_722906117794325_2186365328621114192_n

Leave a Reply