በቅርቡ የሚካሄደውን የ2007 ምርጫን አስመልክቶ፣ ኢሕአዴግ፣ አንድነት እና ኢዴፓን የወከሉ ሰዎች በፋና ሬዲዮ ባለፈው እሁድ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ መኖሩ ትርጉም ስለአልነበረው ነው እንጂ ሌላም አንድ ፓርቲ ወክያለሁ ያለ ሰው እንደነበር ዘንግቼው አይደለም፡፡ የኢሕአዴጉ ወኪል በመጨረሻ ላይ ያቀረቡትን ሃሳብ ሳደምጥ የኢሕአዴግ ተወካዮች ከላይ የተሞሉትን ወደታች ከማስተጋባት ውጪ አንዳቸውም በራሳቸው መርምረው ሊደርሱበት የሚፈልጉት ሀቅ አለመኖሩ ነው፡፡ በፓርቲው ስብሰባ ከሚሰበካቸው በተጨማሪ ዋነኛ የመረጃ ምንጫቸው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ገፋ ሲል ደግሞ ፋና ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ ነጥብ ደግሞ የአንድነት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ የነበረው አንዱዓለም አራጌ እና ሌሎች የህሊና እስረኞች ላይ የተፈረደውን የፍርድ ቤት ውሳኔ መቀበልና አለመቀበል፤ ከፍርድ ቤት ነፃነትና ለፍርድ ቤት እውቅና ከመስጠት ጋር ማያያዛቸው ነው፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ባለመስማማት የምንይዘውን አቋም፤ መረጃ የሌለው ነው ብለው የሚያቀርቡት ጉንጭ አልፋ ክርክር እጅግ አስገራሚ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም “አንዱዓለም አራጌ ይፈታ” በሚል አንድ ፅሁፍ ፅፌ ነበር፡፡ የመጣጥፍ አንድምታ አንዱዓለም የታሰረው በ “አሸባሪነት” ነው የሚለውን አይን ያወጣ ውሸት አንቀበልም፡፡ የኢህአዴግ ጉምቱ ባለስልጣናት ከእቅዳቸው በፊት ከስልጣን የሚነቀንቃቸው ሰላማዊ ታጋይ መሆኑን በመጠርጠራቸው ነው የሚል ነበር፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙት ደግሞ በምርጫ 2002 ክርክር ወቅት ተናዳፊ ተከራካሪ ሆኖ በመቅረቡ ጭምር ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ አንዱዓለም ንቢቱን አስንቆ በስልጣን ሲናገሩ የነበሩትን በመረጃ አስደግፎ ስላጋለጣቸው፣ ቂም እንደተያዘበት ይታመናል፡፡ ይህን እንድንገምት ያደረገን ደግሞ አንዱዓለም በተከሰሰበት ወንጀል አይደለም ለዕድሜ ልክ እስር ለምክር የሚጋብዝ ጥፋት ማጥፋቱን የሚያስረዳ ማስረጃ አልቀረበበትም ምስክርም አልተሰማበትም፡፡ አዳፍኔ ምስክሮችም ቢሆኑ ከእስር ቤት ለመውጣት ቃል የሰጡ ቢሆንም፤ በፍርድ ቤት ገብተው ግን አንዱዓለም ለሽብር ተግባር ወጣት ሲያደራጅ ነበር ብለው ሊመሰክሩ አልቻሉም፡፡ የኢህአዴግ ሹሞች በቦታው ባይኖሩም፤ እኛ ግን በቦታው ነበርን፡፡

ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠበት መዝገብ ማንም ሰው ሊያገኘው እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ የኢህአዴግ አባላትና ሹማምንት ደግሞ ይህን መረጃ ለማግኘት ከማንኛችንም በላይ እድሉ አላቸው፡፡ እነዚህ የኢህአዴግ አባላትና ባለስልጣናት፣ የምናቀርበው ጩኽት ልክ መሆኑን ለማጣራት ለምን ይህን የፍርድ ቤት መዝገብ መርምረው አቋም አይዙም? የሚል ብርቱ ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ ሹሞች ከላይ እንደገለፅኩት በኢህአዴግ ስብሰባ ወቅት ከሚሰሙት ማብራሪያ እና በመንግስት ሚዲያ ከሚሰሙት ውጭ ሌላ ነገር አንብበው ለመረዳት ዝግጁ አይደሉም፡፡

የኢህአዴግ ደጋፊዎች ቢሆኑም ከዚህ ጭፍን መስመር ውጭ አይደሉም፡፡ “አንዱዓለም ይፈታ” በሚል በፃፍኩት ፅሁፍ እንዲህ ብዬ ነበር፤
“መደበቅ የሌለብኝ ዕውነት ግን ከአንዱዓለም ጋር ከምናደርገው የሠላማዊ ትግል ውይይት (አንዳንዴም ጭቅጭቅ የሚባል ቦታ ሊደርስ የሚችል) በተቃራኒ አንድ የሆነ ሠይጣን አሳስቶት – ይህ ሠይጣን ኢህአዴግ ሊሆን ይችላል፤ ማለትም የሠላማዊ መንገዱን ሁሉ እያጠበበ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ – አንዱዓለም ተገዶ ሌላ አማራጭ ፍለጋ ሄዶ ይሆን በሚል የመረጃ ፍለጋ ጉጉቴ አልጨመረም ልላችሁ አልችልም፡፡”

አንዱዓለም የትግል ጓዴ ቢሆንም ሊሳሳት ይችላል ብዬ መጠራጠሬ አልቀረም ነበር፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትርም ክምር ማስረጃ አለ ብለውን ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ከቀረበው ማስረጃ እና ከቀረቡት ምስክሮች ግን ክምር ቀርቶ አንድ ገፅ ወረቀት ሲጠፋ፣ ፍርድ ቤት ወስኗል ብለን ከህሊናችን ጋር ተጋጭተን እንደ ኢሕአዴጎቹ ‹አንዱዓለም አሽባሪ ነው!› እንድንል መፈለጋቸው አስገራሚ ነው፡፡

ኢሕአዴግን ወክሎ የቀረበው የውይይት ተሳታፊ፤ “በእስር ቤት የሚገኙትን አመራሮችና አባሎች ጀግኖቻችን ማለታችሁ አሁንም በሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ህጋዊና ህገ-ወጥ መስመር እያጣቀሳችሁ ለመሄድ ያላችሁን ዝግጅት የሚያሳይ ነው፡፡” የሚል አስተያየት ሲሰጡ መስማቴ ነው፡፡ የሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ሰላማዊ ሊሆን የሚችለው ሀቅን በመደፍጠጥ እና ፍርደ ገምድል ውሳኔን አሜን ብሎ በመቀበል ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ በስልጣኑ የመጡበትን ያለምንም ይሉኝታ እድሜ ልክም ቢሆን እስር ቤት ለመወርወር ደንታ የሌለው መሆኑን በማጋለጥ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ለመመርመር ድፍረት ያገኙ የኢህአዴግ አባላትም ሆኑ ሹሞች፣ በዚህ አይነት ስርዓት ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ለመረዳት አይቸገሩም፡፡ ይህን ስርዓት በመለወጥ የሚገኘው ትንሳኤ፣ ማንም በግፍ እና በፍርደ-ገምድል ውሳኔ ስጋት ላይ እንዳይወድቅ የሚያድርግ ነው፡፡ የዚህ ትሩፋት ደግሞ ለኢህአዴግ አባላትም የሚደርስ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ሹሞች፣ በዚህ ዓይነት ውይይት ወቅት ከፓርቲያቸው በተቃራኒ መስመር ይቁሙ የምል የዋህ አይደለሁም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ነጥቦች መከራከሪያ ሆነው ቢመጡ እንኳ ችላ ብለው በማለፍ ከትዝብት ሊተርፉ ይችላሉ የሚል እምነት ስለአለኝ ነው፡፡ በሀገራችን ያሉትን ተቋማት የምናከብራቸው፣ በህንፃቸው ግዝፈት ወይም በቀጠሩት የሰው ሀይል ብዛት ሊሆን አይችልም፡፡ ፍርድ ቤቶች ሊከበሩ የሚችሉት በሚያሰፍኑት ፍትህ ነው፡፡ ዜጎች መብቴን ፍርድ ቤት ሄጄ አስከብራለሁ የሚል ደረጃ ላይ ሲደርሱ ነው፡፡ በሀገራችን ያለው የፍትህ ስርዓት፣ ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን፣ በቤተስብ ውርስ ጉዳይ እንኳ አፋጣኝ መፍትሄ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በፍትሃ-ብሔር ጉዳይም ቢሆን በዓለም-አቀፍ መለኪየ የሚሰጠው ደረጃ የወረደ ነው፡፡ ይህ እንዲሻሻል ማሳሰብ እና መታገል፣ ፍርድ ቤቶችን እውቅና እንደመንፈግ መቁጠሩ ተገቢ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ፍርደ-ገምድል ውሳኔዎችን እንድንቀበል መገደድም የለብንም፤ ብንገደድም ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ የህሊና እስረኞች ጀግኖቻችን ናቸው የምንለው ለዚህ ነው ፡፡

እኔም እላለሁ፤ የአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ እየተለጠፈ ያለው “የአሸባሪነት” ታፔላ በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ደግመን ደጋግመን ማሳሰብ እንፈልጋለን፤ መፍትሔውም ፖለቲካዊ ውሳኔ በመስጠት መፍታት እና ለሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል መድረኩ በጠበበ ቁጥር ደግሞ ዜጎች አማራጭ የትግል ስልት መፈለጋቸው የግድ ነው፡፡ በጠረጴዛ ላይ ያለው ሌላኛው አማራጭ፣ አገርን ህዝብን ከመጉዳት ውጭ ገዢዎችንም ሊጠቅማቸው የሚችልበት አንድም መንገድ አይታይም፡፡ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት ስርዓት መዘርጋት፣ ለፍትህ ስርዓቱም ትንሳኤ ስለሚሆን ጀግኖቻችንን በመፍታት ለፍትህ ስርዓቱ ትንሳኤ በጋራ እንድንቆም መንግስት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

ምርጫ ሁለት ሺ ሰባት ለለውጥ!!!

ቸር ይግጠመን

Leave a Reply