(EMF) በኢትዮጵያ ከሚከበሩት የሙስሊም በአላት መካከል አንደኛው የነብዩ መሃመድ የልደት በአል ወይም መውሊድ ነው:: ዘንድሮ የመውሊድ በአል አርብ ምሽቱን ተጀምሮ ቅዳሜ ቀኑን ሙሉ ተከብሮ ይውላል:: ታዲያ እኛ ተከብሮ ይውላል እንበል እንጂ; አሁን አሁን በተለይ በውጭ አገር በሚገኙ ኢትዮጵያዊ ሙሊሞች ዘንድ በአሉ ብዙም አይከበርም:: እናም እንደድሮው “እንኳን ለመውሊድ በአል አደረሳችሁ” ለማለት ብዙ እንሳቀቃለን::
የነገሩ መነሻ “የነብዩ መሀመድም ሆነ የሰው ልደት መከበር የለበትም” የሚለው አዲሱ የወሃቢዎች አመለካከት ነው:: ውሃቢዎች የራአቸውም ሆነ የልጆቻቸውን አልፎ ተርፎም የሌሎችን ልደት አያከብሩም:: በቤታቸው ውስጥ የራሳቸውም ሆነ የሌሎች ፎቶ አይሰቀልም:: አልፎ ተርፎ የመውሊድን በአል የሚያከብሩትን “አህባሽ” የሚል ስም ሲሰጧቸው ይደመጣል:: እኛም ከመውሊድ በአል በፊት በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ የሚሰጥ ሰው እያፈላለግን ሳለ; ታዋቂው ጸሃፍ አፈንዲ ሙተቂ ይህን አስመልክቶ መውሊድ፣ “አሕባሽ” እና እኛ” በሚል የጻፈውን ማስታወሻ አገኘን:: ከዚህ በመቀጤል አቅርበነዋል::

መውሊድ፣ “አሕባሽ” እና እኛ

(አፈንዲ ሙተቂ)
—–
እነሆ ከንዳዳማው የዐረቢያ በረሃ ተነስቶ የዓለምን ታሪክ ለመቀየር የቻለው ታላቁ ሰው የተወለደበትን ልደት በዓል ከምናከብርበት ዋዜማ ላይ ደርሰናል፡፡ የዚህን ብርቅና ድንቅ ሰው ክብርና ገድል በመንዙማ፣ በመዲህ፣ በቡርዳ እና በዚክሪ ልናወሳለት ተዘጋጅተናል፡፡ እስቲ ከያንዳንዱ ዘርፍ ለናሙና ያህል እናቅምሳችሁ፡፡

1. “ላዚም” መንዙማ (ዐረብኛ)
አላሁመ ሰልሊ ዐላ ሙሐመዲን
ዐደዳ ማ ጀርረል ቀለሙ
ሙከረም ዐለይከ-ስ-ሰላሙ፡፡
አላሁመ ሰልሊ ዐላ ሙሐመዲን
ሀዲና ነቢና ነቢና
ሰዪዲ ያ ሸምሰል መዲና
—-
2. ቀሲዳ (ቡርዳ)
ያ ረብቢ ሰልሊ ወሰሊም ዳኢመን አበዳ
ዐላ ረሱሊከ ኸይሪ በኸልቂ ኩልሊ ሂሚ
ሙሐመዱን ሰይዱል ከውነይነ ወሥቀለይን
ወልፈሪቀይኒ ሚን ኩልሊ ዑርቢን ወ-ዐጀሚን፡፡

3. ዐጀሚ መንዙማ (ኦሮምኛ)

Allahuma Salli Alaa Muhammdin
Rasululaah Yaa malkaa waraabaa (3)
Anbiyaaf Awliyaa jaalachuun waajibaa
Sheyxanni gamasii sumatti lallabaa
Yoo isa dhageesse niseenta azaabaa
Sheyxaanaa fi nafsiin walitti saahibaa
Nafsii jala deemtee hintakin kilaaba
Rasulallah yaa malkaa waraaba

4. ዐጀሚ መንዙማ (አማርኛ)
ሰላም ዐለይኩም ነቢ
ሰላም ዐለይኩም ነቢ
የጀሊል ቁድራ
በኩኑ የተሰራ
——
እኛ መውሊድን ከድሮ ጀምሮ እናከብረዋለን፡፡ ወደፊትም እናከብረዋለን (የማታከብሩ ሰዎችም መብታችሁ ነው)፡፡

እኛ ከአሕባሽ ጋር የተጣላነው መውሊድን አከብራለሁ ስላለ አይደለም፡፡ አንጃው በጸረ-እስላም ሀይሎች የሚገፋ ስውር የጥፋት ቡድን መሆኑን ስለምናውቅ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ትምህርቱንና ርዕዮቱን ለራሱ ጀመዓ ብቻ በራሱ ማዕከሎችና መድረሳዎች ቢያስተላልፍ መብቱን እናከብርለት ነበር፡፡ ነገር ግን እኔን የሚቃወም ሁሉ ካፊር ነው ይለናል፡፡ በዚያ ላይ መጅሊሱን ተቆጣጥሮ ወሃቢያን በማጥፋት ስም አመለካከቱን በግዴታ ሊጭንብን መነሳቱ ነው ያበገነን፡፡ ሰው በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የኔን እምነት በግዴታ ተከተል ይባላል እንዴ?…. ይህ አንጃ በጽንፈኝነቱ በኢራቅ ከምንሰማው ISIL እና ከሶማሊያው አል-ሸባብ በምንም መልኩ አይሻልም፡፡ ልዩነቱ አሕባሽ በ“ህጋዊ”ነት ሽፋን የሚንቀሳቀስና መሳሪያ ያልታጠቀ ጽንፈኛ መሆኑ ብቻ ነው (መሳሪያ ያልታጠቀ ነው ያልኩት፤ ሆኖም ለራሱ መሳሪያ ባይታጠቅም መሳሪያ በታጠቁ ሃይሎች ተጠቅሞ ሌሎችን በማስመታት አንደኛ ነው)፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም ይስማን፡፡ የ“አሕባሽ” እምነት በግዴታ በህዝቡ ላይ እንዲጫን መፈቀድ የለበትም፡፡ ሼኾቻችንና ኡስታዞቻችን ስንቱን ስቃይና ችግር አይተው የገነቧቸው መስጂዶችና መድረሳዎች ለዚህ አንጃ ተላልፈው መሰጠት የለባቸውም፡፡ ከዚህ በተረፈ አሕባሽና ጀሌዎቹ እንደሚሉት “መውሊድን እንከለክላለን፤ የቅዱሳትና የመሻኢኾችን የቀብር ስፍራዎች እናፈርሳለን” ብለን አናውቅም፡፡ እንደዚህ የሚያስብ ሰው ካለ መጀመሪያ የሚታገለው ሰው እኔ አፈንዲ ነኝ፡፡ የአያቶቻችን “ደሪህ”፣ ዛዊያ እና ኸልዋዎች የታሪክ ቅርሶቻችን በመሆናቸው ሁልጊዜም ቢሆን እንከባከባቸዋለን፡፡
—–
እኔ የገለምሶ ልጅ ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ታላቁ የመውሊድ ማክበሪያ ስፍራ የሚገኘው እኔ በተወለድኩባት ከተማ ነው፡፡ በኛ ከተማ መውሊድ የሚከበረው ጥብቅ በሆነ እስላማዊ ባህል ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ሴትና ወንድ በጭራሽ ተቀላቅለው አያውቁም፡፡
(ዝርዝሩን ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ በተሰኘው መጽሐፌ ላይ የገለጽኩት ስለሆነ ከዚያ ማንበብ ይቻላል)፡፡

ከገለምሶው የሼኽ ዑመር አሊዬ ሐድራ በተጨማሪ በአያቴ (ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ ሼኽ ቢላል) እና በቅድመ አያቴ (ሼኽ ዓሊ ጃሚ ጉቶ) የተገነቡ ሁለት ታላላቅ ሀድራዎችን ጨምሮ በርካታ እስላማዊ ማዕከሎች፣ ኸልዋዎች፣ ደሪሆችና ዛዊያዎች ከገለምሶ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ በምሥራቅ ኢትዮጵያና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክልሎች ጥንታዊ መስጊዶች፣ ሀድራዎች፣ መርከዞች፣ መድረሳዎች፣ ወዘተ አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ጠብቀን ለተከታዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት አለብን፡፡ ትናንት የመጣው የአሕባሽ ጀመዓ ከኛ በበለጠ መልኩ ለነርሱ ተቆርቋሪ የሚሆንበት ምክንያት የለም፡፡
——-
ዐላሁመ ሰልሊ ዐላ ሰይዲና ሙሐመዲን ወዐላ ኩልሊ ወሊዪን
ወሰልሊ ዐላ አቢበክሪን ወዐላ ኩልሊ ወሊዪን
ወሰልሊ ዐላ ጂብሪለን ወዐላ ኩልሊ መለክ
——-
እንኳን ተወለድክልን አንተ የጠይባው ሙሽራ!! ከነፍሳችን አስበልጠን እንወድሃለን፡፡ (ሰ.ዐ.ወ)
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 2007

Leave a Reply