31 DECEMBER 2014 ተጻፈ በ 

ሙጃ በጅማና አካባቢዋ የሚታወቅ ተራራ ነው፡፡ ከከተማውም ከ7 ኪሎ ሜትር በላይ ይርቃል፡፡ የተስተካከለ መንገድ ስለሌለውም የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት ዘበት ነው፡፡

በአካባቢው የሚኖሩ አንዳንድ ግለሰቦችም የሚያስፈልጓቸውን ግልጋሎቶች ለመሸመት በተወሰነ ጊዜ ወደ ከተማ እንደሚወጡ ይናገራሉ፡፡ አንዴ ምክንያቱም የትራንስፖርቱ ችግር እንደፈለጉ የሚያወላደ አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ የከተማው ነዋሪዎች በዓመት አንዴ ተራራውን፣ ደኑን፣ ቋጥኙንና ወንዙን ተሻግረው ከሙጃ ተራራ ይመጣሉ፡፡ ማረፊያቸውንም ከተራራው በስተጀርባ በሚገኘው መስጊድ ያደርጋሉ፡፡ መስጊዱ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ‹‹ቁባ አባረቡ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ስያሜውንም ያገኘው ከሊቢያ እንደመጡ በሚገነርላቸው አባረቡ በተባሉ የሃይማት አባት ስም እንደሆነ ይነገራል፡፡

እኚህ የሃይማኖት አባት ኑሯቸውን በተራራው ላይ መሥርተው ስለ እስልምና አስተምህሮቶች ለከተማው ነዋሪዎች አስተምረዋል፡፡ ብዙ ተአምራትንም እንደሠሩና  ለእስልምና መስፋፋትም ትልቁን ድርሻ እንዳበረከቱ ይነገርላቸዋል፡፡ እንደ ወልይ (ፈጣሪ የወደደውና ትንቢተኛ) ተደርገው ይታያሉ፡፡ የመረቁትም የረገሙትም ይደርሳል ተብሎ ስለሚታመን ጥቂት በማይባሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜም ሰዎች በአባረቡ ስም  ስለት ተስለው ሲሞላላቸው ስለታቸውን ለመስጊዱ ያስገባሉ፡፡

የሁለት መቶ ዓመት ታሪክ እንዳለው የሚነገርለት ቁባ አባረቡ፣ የመውሊድ በዓልን የሚያከብሩ ሙስሊሞች በየዓመቱ ብቅ ይሉበታል፡፡ ‹‹መውሊድ አልነቢ›› የነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) የልደት ቀን ሲሆን፣ ‹‹የተቀደሰው ልደት›› እንደማለት ነው፡፡ በዓሉ ከሰዓውዲ ዓረቢያ በስተቀር በሁሉም የሙስሊም አገሮች ብሔራዊ ክብረ በዓል ነው፡፡

መውሊድ እንዳሁኑ በብዙ አገሮች መከበር ከመጀመሩ በፊት፣ አቅሙ ያላቸው ሰዎች ነብዩ ሙሐመድ ወደ ተወለዱበት ቤት በመሄድ ፀሎት ያደርሱ ነበር፡፡ በኋላም ቤቱ መስጊድ ተገንብቶበት ብዙ ሰዎች ፀሎት የሚያደርሱበት መስጊድ ሆኗል፡፡

የዚህን ቅዱስ ልደት ክብረ በዓል በተመለከተ ሁለት ዓይነት ሐሳቦች ይሰነዝራሉ፡፡ የነብዩ መሐመድን ልደት ማክበር አያስፈልግም የሚሉና አቅም በፈቀደ ሁሉ ማክበሩ የእሳቸውን ትልቅነት ማውሳት በመሆኑ መከበር አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ‹‹የነብዩን ልደት በማክበር የሚከሰት ምንም ዓይነት ችግር የለም፡፡ ስለዚህም ስለምንወዳቸውና ስለምናከብራቸው ልደታቸውን እናከብረዋለን›› የሚሉ ሱፊዎች ናቸው፡፡ ከሰለፍ ወገን የሆኑት ደግሞ ‹‹እኛ በቁርዓን እንመራለን፡፡ ቁራዓን ደግሞ የነብዩን ልደት አክብሩ የሚል ትዕዛዝ አልያዘም›› በሚል የመውሊድን ክብረ በዓል ይቃወማሉ፡፡

በእነዚህ ሁለት የሐሳብ ልዩነቶች ላይ ተመሥርቶም ከፊሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ መውሊድን በደመቀ መልኩ ያከብራል፡፡ ከፊሉ ደግሞ እንደማንኛውም ቀን ያሳልፋል፡፡ በዓሉ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከበር ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በተለያዩ ቦታዎው እንዲሁ ተከብሮ ይውላል፡፡ ዘንድሮ ታኅሣሥ 25 ቀን በሒጅራ አቆጣጠር በ12 ረቢአል አወል የሚውል ሲሆን፣ በዓሉ በድምቀት ከሚከበሩባቸው ቦታዎች መካከል በትግራይ ነጃሺና በሆጂራ ፎቂሳ፣ በደቡብ ወሎ በጀማ ንጉሥ፣ በባሌ ድሬ ሼሕ ሁሴን፣ በጅማ ደግሞ በቁባ አባረቡ ይከበራል፡፡

በጅማ ቁባ አባረቡ የሚከበረው የመውሊድ በዓል እንደ ድሬ ሼክ ሁሴንና በሌሎች ቦታዎች እንደሚከበረው ገኖ የወጣ ስም የለውም፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎች ውጭ እምብዛም የሚታወቅ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ስለ አባረቡ ተአምራት የሰሙ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ምእመናኖች በየዓመቱ እየመጡ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡ ራቅ ካለ አካባቢ የሚመጡ ምእመናኖችም በዓሉ ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ ወደ ቁባ ይተማሉ፡፡

በእነዚህ ቀናት ባለባላ በትር፣ ቅል፣ ሙስባህ (መቁጠሪያ) የያዙና በለበሱት ነጭ ጀለቢያ ላይ ሽርጥ ያገለደሙ፣ ውኃ በጀሪካን የያዙና ሌሎች ስንቅ ቋጥረው የሚጓዙ ሰዎች በየጎዳናው ይታያሉ፡፡ ምንም እኳን እርስ በርስ የማይተዋወቁ ቢሆንም ‹‹አሰላም አለይኩም›› በማለት እየተዘያየሩ ረዥሙን ጉዞ አብረው ይሄዳሉ፡፡ አልፎ አልፎም ሰዎቹ ባላቸው መረዋ ድምፅ ፈጣሪንና አባረቡን በመንዙማ እያወደሱ መንገዳቸውን ያቀናሉ፡፡

የዕለቱ ዕለትም የሙጃን ተራራ አልፈው ከበስተጀርባው ወደ ሚገኘው ቁባ አባረቡ የሚተሙ ሰዎች ከሌሎቹ ቀናት በተለየ መልኩ ቁጥራቸው ይበዛል፡፡ ጉልበታቸውን ለማበርታት ውኃ ከኮዳቸው ፉት እያሉና ከያዙት ምግብ እየበሉ ይጓዛሉ፡፡

ወደ መስጊዱ ሲቃረቡም እናቶች ቡና የሚያፈሉበትንና ሌሎች ምግቦች የሚያበስሉበትን እንጨት ከየመንገዱ እየለቀሙ አልፎ አልፎም ስለት ያለባቸው ሰዎች የተሳሉትን (በብዛት በግ) እየነዱ ወደ ሥፍራው ያዘግማሉ፡፡ በስለት የወለዱ እናቶችም አራስ ልጃቸውን ተሸክመው ወደ ሥፍራው ይሄዳሉ፡፡

በብዙ ልፋት ቁባ አካባቢ ሲደርሱ ከአካባቢው በተለየ መልኩ ጠባብና ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሽር ጉድ የሚሉ ሰዎች ከቅርብ ርቀት ይታያሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቀድመው ቦታው የደረሱ ነጋዴዎች ሲሆኑ፣ ልዩ ልዩ ምግቦች፣ አልባሳትና የመሳሰሉትን ይዘው ብቅ የሚሉ ናቸው፡፡ ከከፍተኛው ሥፍራ ግርጌ ሲደረስም ወደ መስጊዱ ለመግባት ሁለት መቶ ሜትር ያህል ርቀት ላይ የዘምዘም ውኃ (ፀበል) ይገኛል፡፡ ይህ ፀበል ሰዎች ካለባቸው ሕመም የሚፈወሱበት ሲሆን፣ በዕለቱ ለመጠጥ ውኃነትና ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች ይጠቀሙበታል፡፡ ምዕመናኖቹ ወደ መስጊዱ ከመግባታቸው በፊት  የያዙትን ውኃ ከኮዳቸው ደፍተው በምትኩ ከዘምዘም ይጨልፋሉ፡፡ የመስጊዱ ቅጥር ውስጥ እንደገቡም የሚያደርሱትን ስለት ወዲያው ያስረክባሉ፡፡

ቀጥለውም በአራት ማዕዘን በሰንደል ተከቦ ከሚታየው የአባረቡ መቃብር ጎን  ፀሎት ያደርሳሉ፡፡ ከዚያም ከመስጊዱ ቅጥር ውስጥ ከሚገኝ ክፍት ቦታ ላይ ቅጠል አንጥፈው በመቀመጥ በድጋሚ ፀሎት ያደርሳሉ፡፡ ስለት የገቡ በግ፣ ፍየልና የመሳሰሉት እንደ ስለታቸው ዕርዳቸው ይከናወናል፡፡

በየመልኩ ተደርጎ ከበሰለ በኋላ በሼሆቹ ምርቃት እየተቆጠረ ይታደላል፡፡ ቀስ በቀስም ሀድራው፣ ፀሎቱ፣ ዚያራው ሞቅ እያለ ይመጣል፡፡ በቄንጠኛ ሁኔታ ድቤ እየተመታ ሼኮቹ ባለባላ በትራቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ እየጠቆሙና በአመልካች ጣታቸው ጆሯቸውን ይዘው በመረዋ ድምፅ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡ ቡናውም በላይ በላይ ይፈላል፡፡ እጣኑም እንደዚሁ ሞቅ ተደርጎ እንዲጨስ ይደረጋል፡፡

በዚህ ሁኔታ እስከ ምሽት ይዘልቃሉ፡፡ ከሩቅ አካባቢ የመጡት በመስጊዱ ውስጥና አካባቢ ቅጠል አንጥፈው ጎናቸውን ያሳርፋሉ፡፡ ከከተማው ብቅ ያሉ ሰዎች ግን የሚጠበቅባቸውን ካደረጉ በኋላ ወደየቤታቸው በመመለስ የበዓሉን ቀሪ ጊዜ ከቤተሰባቸውና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያሳልፋሉ፡፡

አቶ ከማል አባዱራ የ35 ዓመት ጎልማሳና የሦስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ የአካባቢው ተወላጅ ሲሆኑ ከልጅነታቸው ጀምሮ መውሊድን የሚያከብሩት በቁባ አባረቡ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቤተሰብ ከመሠረቱ በኋላም መውሊድን ከመላው ቤተሰባቸው በቁባ አባረቡ ማክበር ልምዳቸው ነው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ለበዓሉ የሚዘጋጁ ልዩ ልዩ ምግቦች ዳቦ፣ ቃሪቦ፣ ቡናና የመሳሰሉት ወደ ቁባ አባረቡ ከመኬዱ በፊት ቀደም ተብለው ሊበሉ ይችላሉ፡፡ ካልሆነም ከመስጊድ መልስ በቤት ውስጥ በሚደረግ ተጨማሪ አከባበር ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ‹‹በበነጋታው የግድ ሥራ መግባት አለብኝ፤›› የሚሉት አቶ ከማል ግን ጠዋት ወደ ቁባ አባረቡ ሄደው ከሰዓት መመለስ ግድ ይላቸዋል፡፡ ስለዚህም በቤታቸው ዝግጅት የሚደረገው በዕለቱለት ከከሰዓት በኋላ ይሆናል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በሥፍራው የሌሎች እምነት ተከታዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ገንዘብ የሚልኩም ጥቂት አይደሉም፡፡

ከአካባባቢው ርቀትና የትራንስፖርት ችግር አንፃር በቁባ አባረቡ ከማክበር ይልቅ በቅርባቸው ባለ መድረሳ (መስጊድ) የሚያከብሩ ምእመናኖችም አሉ፡፡ አቶ መሐመድ አሊ አንዱ ሲሆኑ፣ እንደ እሳቸው ገለጻ ወጣት ሳሉ ይሄዱ ነበር፡፡ ነገር ግን ዕድሜአቸው እየገፉ ሲሄድ በመንደራቸው ውስጥ በሚገኝ መስጊድ ለማክበር ተገደዋል፡፡ ድፎ ዳቦና ቃሪቦ ለክብረ በዓሉ እንዳዘጋጁ የሚናገሩት አቶ መሐመድ በመድረሳ ውስጥ በጀመአ (በጋራ) ፀሎት ካደረሱ በኋላ ቀሪውን ክብረ በዓል በቤት ውስጥ ከመላው ቤተሰባቸው ጋር እንደሚያከብሩት ይናገራሉ፡፡

Leave a Reply