Wednesday, 20 May 2015 12:54

በሳምሶን ደሳለኝ

 

አምስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ይካሄዳል። የምርጫ ቦርድ መረጃ እንሚያሳያው 58 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበው ወደ ሀገር አቀፍ ምርጫ ውስጥ ገብተዋል። እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 5 ሺህ 783 ለፌዴራል ፓርላማ እና ለክልል ም/ቤቶች ተወዳዳሪ ዕጩዎችን አስመዝግበው ለእሁዱ ምርጫ የህዝቡን ውሳኔ በመጠባብቅ ላይ ናቸው። ከዘጠና ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል እድሚያቸው ለምርጫ ከደረሱ ዜጎች መካከል 36 ነጥብ 8 ሚሊየን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ድምጽ ለመስጠት የቀናት ጊዚያትን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

በምርጫ ቦርድ የተደለደለውን የመገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓቶች እና በሕትመት ውጤቶች ላይ የሚስተናገዱ ፅሁፎችን የፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃቀማቸው በጣም የተለያየ እንደነበር የኢትዮጵያ ፕሮድካስት ባለስልጣን በሳለፍነው ሳምንት ያስታወቀው። እንደባለስልጣኑ መረጃ ከሆነ ኢህአዴግ 98 በመቶ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድምር 51 በመቶ፣ አጋር ፓርቲ ተብለው የሚጠሩ ሆኖም ግን ራሳቸው ፖለቲካዊ ሕልውና ያላቸው ፓርቲዎች 63 በመቶ መጠቀማቸውን ይፋ አድርጓል። በአጠቃላይ ለቅስቀሳ የቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶች 98.31 በመቶ በምርጫ ቦርድ የጸደቀውን ሕጋዊ የቅስቀሳ ስርዓቶችን ያሟሉ መሆናቸውን ባለስልጣኑ ጨምሮ አስረድቷል።

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም የሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ቀጣዩን የኢትዮጵያ መንግስት ሥርዓተ-መንግስት የሚመሰርተውን የፖለቲካ ፓርቲ ይፋ የሚሆንበት እንደሚሆን ይጠበቃል። የቅድመ ምርጫው የነበረው ሂደት ከሞላ ጎደል በሰላም እየተጠናቀቀ ያለበት ሁኔታዎች ናቸው ያሉት። ቀሪው የድምጽ መስጠትና የድምጽ ቆጠራ እንዲሁም ድህረ ምርጫ በጉጉት ተጠባቂ አድርጓቸዋል።

በቅድመ ምርጫው በልዩነት ሊነሳ የሚችለው በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ተነስቶ የነበረው የፓርቲዎች የሕጋዊ ውክልና ጥያቄዎች ነበሩ። የውክልና ጥያቄ ያነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁለትና ከዚያ በላይ ተከፋፍለው እኔነኝ…እኔነኝ… የፓርቲው ሕጋዊ ወኪሉ እየተባባሉ ለበርካታ ወራት እሰጥ ገባ ውስጥ መክረማቸው የሚታወስ ነው። በመጨረሻም ምርጫ ቦርድ በሰበሰበውና በሰነድ በነበረው መረጃ መነሻ ሕጋዊ ውሳኔዎች አስተላልፎ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውሳኔ አግኝተው ውዝግቡ እንዲቆም ተደርጓል። የምርጫ ቦርድ ውሳኔን የተቃወሙ የፖለቲካ ሃይሎች ቢኖሩም የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ ምርጫ ቦርድ በመሆኑ የተሰጠው ውሳኔ ወደ ተግባር ተለውጦ ውዝግብ ውስጥ የነበሩ ፓርቲዎች ወደ ምርጫው ተቀላቅለዋል።

በዚህ ጽሁፍም ቀሪዎቹን የድምጽ መስጠትና የድምጽ ቆጠራ እንዲሁም ድህረ ምርጫ ሂደቶችን ሁላችንም አሸናፊዎች ሆነን እንዴት መውጣት እንችላለን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ይሞክራል። ሁላችንም አሸናፊ መሆን የሚጠበቅብን ዋነኛ ምክንያት በሁሉም ባለድርሻ አካለት ዘንድ ቅቡል የሆነ ሀገር አቀፍ ምርጫ ማድረግ ስለሚጠበቅብን ስለሚጠቅመንም ጭምር ነው። ቅቡልነት ሲባል “Governments have authority only if their power is legitimate. Legitimate power means power that is recognized and accepted by society as legally and morally correct.” ይህም ሲባል፣ ሥርዓተ መንግስታት የማስተዳደር ስልጣን የሚኖራቸው ስልጣናቸው ቅቡል ሲሆን ብቻ ነው። ቅቡል ስልጣን ማለት ስልጣኑ በሕብረተሰብ ውስጥ በሕግና በሞራል እውቅና እና ተቀባይነት ሲያገኝ ነው።

ይህን መሰል ቅቡልነት ባለቤትም ሰጪም ሕዝብ ብቻ ነው። ሆኖም ግን የሕዝብ አካል የሆኑ ባለድርሻም አካላትም በዚህ የቅቡልነት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የራሳቸው ሚና አላቸው። በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የጋዜጠኞች ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሌላው በሕግ ስልጣን የተሰጣቸው የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎችና አስፈፃሚዎችም ሚና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ስለዚህም ከማን ምን ይጠበቃል በመጪው ምርጫ የሚለውን መመልት አግባብነቱ አጠያያቂ አይደለም።

በመጪው ምርጫ ከጋዜጠኞች ምን ይጠበቃል?

በየትኛውም ዓለም የሚገኙ የምርጫ ዘጋቢዎች ጋዜጠኞች የምርጫ ዘገባ ሲያቀርቡ ቢያንስ አራት መሰረታዊ መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። እንዲሁም በመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚሰመራ ጋዜጠኞች። ይሄውም አንደኛ፣ ትክክለኛ የምርጫ ዘገባ መረጃ ማግኘት ማቅረብ (Accuracy)። የተጋነኑ በእውነት ላይ ያልተመሰረቱ ዘገባዎችን ከማቅረብ መቆጠብ። ሁለተኛ፤ ከወገንተኝነት የፀዳ መረጃ ማቅረብ (Impartiality (Fair Balance) ለሁሉም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ። በተለየ መልኩ ለአንድ ወይም ለተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ የምርጫ ዘገባ ሪፖርት አለማቅረብ። እንዲሁም ጋዜጠኛው የራሱን እምቅ ፍላጎት ከምርጫ ዘገባ ሪፖርቶች ጋር አያይዞ ከማቅረብ መቆጠብ አለበት። ሶስተኛ፣ጋዜጠኛው ለሚያቀርበው የምርጫ ሪፖርት ሃላፊነት ሊሰማውም (Responsibility) መውሰድም አለበት። ጋዜጠኛው በሚያቀርበው ሪፖርት የምርጫው ሂደት እንዳይዛባ እና የዜጎች ህይወትን ወደ አላስፈላጊ መስመር ሊከት በሚችል መልኩ እንዳይሆን ሃላፊነት መውሰድ አለበት። ጋዜጠኛው በሚያቀርበው ሪፖርት ቢያንስ ለራሱ ተማኝ መሆን ይጠበቅበታል።

በመጪው ምርጫ የሚሰማራ ጋዜጠኛ ራሱን ከምን መቆጠብ አለበት? አንደኛ፣ በተሳሳቱ መረጃ መነሻ ሃሰተኛ ክሶችን (Defamatory) በተወዳደሪ እጩዎች ላይ ሆነ ምርጫውን በሚያስፈጽመው ተቋም ላይ ከመዘገብ መቆጠብ አለበት። ሁለተኛ፣ በምንም መልኩ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የቀረቡ ዘገባዎችን የማጣራት የማረጋገጥ ስራዎችን ሳይሰራ (Derivative) የምርጫ ዘገቢ ጋዜጠኛ ዘገባዎችን ደግሞ ከማቅረብ መቆጠብ አለበት። ሶስተኛ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወይም ተወዳደሪ ፖለቲከኞችን ግለሰባዊ ሆነ ተቋማዊ ገጽታቸውን የሚያጠልሽ ሪፖርት (Malicious) ከመዘገብ መቆጠብ አለበት። የጋዜጠኝነት ሙያውን ተገን በማድረግ መረጃዎችን በማዛባት መራጭ ሕዝቡን ሆን ብሎ ወደ ግጭት እንዲያመራ ከሚያደርጉ ዘገባዎች ራሱን ማራቅ ይጠበቅበታል። አራተኛ፣ በምን አይነት መልኩ የሚቀርብ የገንዘብ ሆነ ሌላ የማባበያ ስጦታዎችን ተቀብሎ ከመሞሰን ራሱን መቆጠብ አለበት። ሙያውን ከመሸጥ መቆጠብ አለበት። በተለይ ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመወሰን ሕጋዊ ሆነ ሞራላዊ መብት ከሌላቸው ሶስተኛ ወገኖች አጀንዳ ራሱን በብዙ ርቀት ነጥሎ ማስቀመጥ እና አጀንዳቸውን ከመቀበል መቆጠብ አለበት።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል?

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቆጠራ ተጠናቋ የምርጫ ውጤቱ ሲገለፅ የሚሰጡት አስተያየት በምርጫው ውጤት ላይ የተቀባይነት ወይም የጥርጣሬ መንፈስ ሊረጩበት ይችላሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ውጤት ላይ ትክክለኛ ምልከታና አስተያየት እንዲኖራቸው ቢያንስ የሚከተሉትን ከግምት መውሳድ ይኖርባቸዋል።

የፓርቲን ጥቅም፤ ከሕዝብ ሰላም በላይ አለመመልከት

በሀገር አቀፍ ምርጫ ለመሳተፍ ወደ ውድድር ውስጥ የገባ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያገኘው የምርጫ ውጤት ምንም ይሁን ምንም ከሕብረተሰቡ ሰላም በላይ ሊሆን እንደማይችል ግንዛቤ ሊወስድ ይገባል። ሕዝቡ የሚሰጠው የምርጫ ድምፅ ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ አድርጎ ለመቀበል የፖለቲካ ፓርቲዎች ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸው። ከሕዝቡ ውሳኔ ውጪ በማኛውም ዋጋ የፖለቲካ ስልጣን ይገባኛል የሚል የፖለቲካ ፓርቲ፣ በሰነቀው የፓርቲ ጥቅም መጠንና ደረጃ ለሚፈጠረው ማንኛውም አይነት ሁኔታ ሃላፊነትንም ለመውሰድ መዘጋጀት ይጠበቅበታል።

ለምርጫ በቀረቡት ተወዳዳሪ ልክ፤ የፖለቲካ ስልጣን መሻት

የኢትዮጵያ ሥርአተ መንግስትን ለመመስረት የሚያስችሉ 547 የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫ ወንበሮች መካከል ሃምሳ ሲደመር አንድ ማግኘት የቻለ የፖለቲካ ፓርቲ የራሱን ሥርአተ መንግስት ይመሰርታል። በመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻቸውን ወይም የጥምር መንግስት በሚያገኙት የምርጫ ውጤት መሰረት ቀጣዩን ሥርአተ መንግስት ለመመስረት ይችላሉ።

ሆኖም ግን ለውድድር ያቀረቡት የተወዳዳሪ መጠን ሃምሳ ሲደመር አንድ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከወዲሁ እስከምን እርቀት መጓዝ እንደሚችሉ ይገነዘቡታል። ይህም ማለት ብቻቸውን ሥርዓተ መንግስት መመስረት አይችሉም። ስለዚህ ከምርጫው የሚያገኙትን ውጤት ተከትሎ ከየትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ብጣመር የተሻለ ይሆናል የሚለውን አሁን መመለስ አለባቸው። ስለዚህም ከምርጫው የሚጠብቁት ውጤት መሆኑ ያለበት ለመወዳደር ካዝመዘገቧቸው እጭዎቻቸው ቁጥር ጋር እኩል መሆን አለበት። ከዚህ ውጪ የፖለቲካ ስልጣን በመጪው ምርጫ መፈለግ ከሌላ እምቅ ፍላጎት ጋር ሕብረተሰቡም ሆነ ሕግ አስፈፃሚው ሊመለከተው ይችላል።

ከሶስተኛ ወገኖች አጀንዳ ሁሉም ጽዱ መሆን አለባቸው

ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ከሶስተኛ ወገኖች አጀንዳ የጸዳ መሆን አለበት። የሶስተኛ ወገኖች አጀንዳ የሚባለው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከምዕራቡ ሆነ ከምስራቁ ዓለም የሚሰጡ አጀንዳዎች ፈጻሚ አለመሆን ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሃይል መንግስት ለመመስረት ጦር መሳሪያ ካነገቡ ወገኖች አጀንዳ የፖለቲካ ፓርተዎች ራሳቸውን ማራቅ አለባቸው። ምክንያቱም ለፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ የሚሰጠውም የያዙትንም አጀንዳ የሚያጸድቀው በመጪው እሁድ ድምጽን ለመስጠት የሚውጣው ሕዝብ ብቻ ነው። ከዚህ ሕዝብ ፍላጎት ውጪ መንቀሳቀስ የሶስተኛ ወገኖች አጀንዳ በአደባባይ ከማራመድ ተለይቶ የሚታይ ተግባር አይደለም።

ቀጣይ ምርጫ ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ

አምስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ በመጪው እሁድ 16 ቀን 2007 ዓ.ም ይደረጋል። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም በተሰጠው ስልጣን መሰረት በየአምስት አመቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ ያከናውናል። ስለዚህም ቀጣዩ ምርጫ በ2012 ዓ.ም ይካሄዳል ማለት ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም እሁድ በሚደረገው ምርጫ የሚፈልጉትን ያህል ውጤት ማግኘት ባይችሉ በቀጣይ በ2012 በሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ አሁንላይ ያለባቸውን ድክመቶች አርመው አሸናፊ ፓርቲ ሆነው ሊመጡ ይችላሉ። በሌላ መልኩም የተወሰነ የሕዝብ ተወካዮች የምርጫ ወንበር የሚያገኙ ፓርቲዎችም በበኩላቸው በቀጣይ ምርጫ የበለጠ ወንበር ለማግኘት መስራት እንዳለባቸው ግንዛቤ በመውሰድ በመጪው ምርጫ የሚያገኙትን የፓርላማ መቀመጫ በተገቢው መንገድ እንዴት እንደሚጠቀሙ ከወዲሁ ሊዘጋጁበት ይገባል።

በሃምሳ ሲደመር አንድ የኢትዮጵያን ሥርአተ መንግስት ለመመስረት የሚበቃ ፓርቲም በበኩሉ አንድም ሆነ ከዚያ በላይ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት ከቻሉም ሆነ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት ካልቻሉትም ጋር በጋራ በመሆን ለመስራት መዘጋጀት ይጠበቅበታል። ምክንያቱም በአብላጫ ድምጽ ማሸነፍ ማለት የሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ውክልና ማግኘት ባለመሆኑ ነው። ለጊዜው ያለውም ብቸኛ የተሻለ አመራጭ ምርጫ ብቻ በመሆኑም የተገኘ ውጤት መሆኑን አሸናፊው ፓርቲ ሊረዳው ይገባል።

ምርጫው በሰላም ካለቀ፣ ተሸናፊ ፓርቲ የለም

እሁድ የሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሰላም ከተፈጸመ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርም። ምክንያቱም፣ በሕግ የበላይነት መከበር ውስጥ ተሸናፊም አሸናፊም አይኖርም፤ የሚኖረው የሕግ የበላይነት ብቻ ነው።

Leave a Reply