ፎቶ በሪፖርተር/ታምራት ጌታቸው
ፎቶ በሪፖርተር/ታምራት ጌታቸውዋና ዜና
24 MAY 2015 

የምርጫ 2007 ዜናዎች – አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ

እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ አገሪቱ ድምፅ የመስጠት ሥነ ሥርዓት ተጀምሯል፡፡ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ከተማና ከተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ዘገባዎችን ያስተላልፋል፡፡ በዚህም መሠረት አንባቢያን ድረ ገጹን እንዲጎበኙ እናሳስባለን፡፡

ድምፅ የመስጠቱ ሥነ ሥርዓት ተጠናቀቀ

እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከንጋቱ 12 ሰዓት የተጀመረው ድምፅ የመስጠት ሥነ ሥርዓት በአብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች ተጠናቋል፡፡ የሚቀጥለው ተግባር የድምፅ ቆጠራ ነው፡፡
አንባቢያን እስካሁን አብራችሁን ስለቆያችሁ እያመሰገንን፣ የድምፅ ቆጠራ ውጤቱ ይፋ መደረግ ሲጀመር ዘገባዎቻችን ከሰኞ ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ይቀጥላሉ፡፡

መቐለ 

በትግራይ ክልል ተወዳዳሪ የሆነውና የመድረክ አባል የሆነው የዓረና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ በህንጣሎ፣ በሃገረ ሰላም፣ በሽሬ፣ በሃውዜን፣ በኢሮብና በሌሎችም አካባቢዎች የፓርቲው ታዛቢዎች እየተባረሩ እንደሆነ ቀደም ሲል ገልጸዋል፡፡

ይህን አስመልክቶ የትግራይ ክልል የምርጫ አስተባባሪ አቶ ወልደጊዮርጊስ በላይ በጉዳዩ ላይ ቅሬታ እንዳልቀረበላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር በመቐለ ተዘዋውሮ ካያቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በሁለቱ ብቻ የዓረና ታዛቢዎችን ተመልክቷል፡፡

አቶ ወልደጊዮርጊስ ታዛቢዎች ተለይተው መታወቅና መቅረብ የነበረባቸው ከአሥር ቀናት በፊት ቢሆንም፣ የምርጫ ሒደቱን የተሻለ ለማድረግ ከዚያም በኋላ መቀበላቸውን አመልክተዋል፡፡

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ድምፅ እየሰጡ ሲሆን፣ ከሰዓት በኋላ የወረቀት እጥረት አጋጥሟል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በሚገኙ 3 ካምፓሶች ውስጥ 31 የምርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን፣ 17,500 ተማሪዎች ካርድ መውሰዳቸው ታውቋል፡፡

የወረቀት እጥረቱ ያጋጠመው በአዲሃቂ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ካምፓስ ባሉ 9 የምርጫ ጣቢያዎች ነው፡፡ የወረቀት እጥረቱ ከ6 ሰዓት በኋላ ማጋጠሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ነቀምት 

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) በምሥራቅ ወለጋ ዞን ያሰማራቸውን 77 ታዛቢዎች ከመለመለ በኋላ፣ በጀት ባለመኖሩ ማሰማራት አለመቻሉ ተገለጸ፡፡ የኢዴፓ የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተባባሪና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ አቶ ኃይለየሱስ ፊጤ በጀቱ ከሦስት ቀናት በፊት መድረስ የነበረበት ቢሆንም፣ በጀት ባለመለቀቁ ታዛቢ ማሰማራት አለመቻሉን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በነቀምት ከተማ የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ 99 ታዛቢዎች፣ መድረክ ደግሞ 36 ታዛቢዎች አሰማርተዋል፡፡ ከነቀምት ውጪ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች መድረክም ታዛቢዎች እንደሌሉት ታውቋል፡፡

ሰሜን ሸዋ 

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን 835,585 መራጮች ተመዝግበው፣ በዞኑ አሥር የፖለቲካ ፓርቲዎች ያወዳድራሉ፡፡ ብአዴን/ኢሕአዴግ (17 ለፓርላማ፣ 36 ለክልል ምክር ቤት)፣ ሰማያዊ (6/16)፣ መኢአድ (7/14) ኢዴኦ (4/0)፣ ቅንጅት (5/1)፣ መኢብን (1/2)፣ አትፓ (1/0)፣ አንድነት (4/4)፣ አርጎን አብዲን (1/0) ኦሕዴድ (1/0) ናቸው፡፡

አቶ ተሰማ ከበደ የዞን የምርጫ ቦርድ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምርጫው ከተጀመረ ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ፣ ከተቃዋሚም ሆነ ከገዢው ፓርቲ የቀረበላቸው አቤቱታ የለም ብለዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎቻቸውን በየምርጫ ጣቢያው አልመደቡም፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ ሰማያዊ ፓርቲ በሦስት ምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች አስቀምጧል፡፡

ወ/ሮ ሰርካለም ከበደ በሰሜን ሸዋ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ አስተባባሪና ለተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪም ናቸው፡፡ በደብረ ብርሃን በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎችና በዞኑ በሚገኙ ከአብዛኛው ወረዳዎች ፓርቲያቸው ታዛቢ እንደላከ ገልጸው፣ ሆኖም ተዘዋውረው ሲመለከቱ ታዛቢዎች የሉም ብለዋል፡፡ ‹‹ምክንያቱም ምን ምን እንደሆነ መረጃ አልደረሰኝም፡፡ ቀደም ሲል በአግባቡ ለታዛቢዎች አበል አለመቅረቡ ግን አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን የመኢአድ ምርጫ አስተባባሪ ሻምበል ባሻ አበበ በቀለ፣ ከምርጫ ዋዜማ ጀምሮ በደጋፊዎቻቸውና በታዛቢዎቻቸው ላይ ደረሰ ባሉት ወከባ ምክንያት ታዛቢ መመደብ አልተቻለውም ብለዋል፡፡

በዞኑ በቀይት ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት መኢአድን በመወከል የሚወዳደሩትን አቶ ተረፈ በረደድ እስካሁን በስልክም ማግኘት እንዳልቻሉ ሻምበል ባሻ አበበ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ታዛቢዎችን በተመለከተ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያነሱዋቸውን ቅሬታዎች አስመልክቶ ከየትኛውም ፓርቲ ምንም ዓይነት አቤቱታ እንዳልቀረበላቸው፣ የዞኑ ምርጫ አስተባባሪ አቶ ተሰማ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ የመኢአድ አስተባባሪ ግን ለዞኑ የምርጫ ወረዳም ሆነ ለሲቪክ ማኅበራት እየደረሰ ነው ያሉትን ወከባ በተመለከተ ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች የሚመርጡበት ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተዘጋጅቷል፡፡ ነገር ግን ተወዳዳሪዎቹ ማን እንደሆኑ የምርጫ ወረቀቱ ባለመድረሱ ምክንያት አልታወቀም፡፡ ስለዚህም ምርጫው በተሟላ ሁኔት እየተካሄደ አይደለም፡፡ እስከ ቀኑ አሥር ሰዓት ይደርሳል ተብለው እየተጠባበቁ ነው፡፡ ይህንንም አቶ ተሰማ አረጋግጠዋል፡፡

የሐረሪ መራጮች በአዲስ አበባ 

ከብሔራዊ ሎተሪ

በአዲስ አበባ ከተማ በዞን 5 የምርጫ ክልል በወረዳ 2 እና 14 ምርጫ ጣቢያ በብሔራዊ ሎተሪ ግቢ ድምፅ መስጫ የተዘጋጀላቸው የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ድምፅ እየሰጡ ነው፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሦስት ቢሆኑም፣ ለውድድሩ ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበው ሐብሊ (የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ) መሆኑን አስተባባሪው አቶ አደም አቡበከር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ነዋሪ ለሆኑት ሐረሪዎች ክልላቸውን የሚመሩላቸው 14፣ በፓርላማ የሚወክሏቸውን አንድ ዕጩ ለመምረጥ በአዲስ አበባ በተለያዩ አምስት ጣቢያዎች እየመረጡ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ለፓርላማ ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ወ/ሮ ኑሪያ አብዱራህማን ኡመር ናቸው፡፡ በብሔራዊ ሎተሪ የዞን 5 ምርጫ ጣቢያ 362 መራጮች መመዝገባቸውንና እስከ እኩለ ቀን ድረስ 140 መምረጣቸውንም አቶ አደም አውስተዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሐረሪዎች ለሚኖሩበት ወረዳ በፓርላማ የሚወክላቸውን፣ በሐረሪነታቸውም ከሐረር በፓርላማ ለሚወክላቸው ድምፆች ይሰጣሉ፡፡

ሠልፍ በማይታይበትና በድንኳን ውስጥ ድምፅ በሚሰጥበት የሐረሪ ምርጫ ጣቢያ የተገኙት የአዲስ አበባው ነዋሪው አቶ አቡበከር ራሕመት፣ በአዲስ አበባና በሐረር ለፓርላማ ለሚወዳደሩት ሁለት ድምፅ መስጠታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የሐረሪ ተወላጆች ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከ1987 ዓ.ም. የመጀመሪያው ዙር ጀምሮ ይመርጣሉ፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ 17 የምርጫ ጣቢያዎች በመምረጥ ላይ ከሚገኙ የክልል ተወላጆች፣ ለአንዳንዶቹ የመምረጫ ሰነድ ተሟል0ቶ አለመቅረቡ ተገለጸ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሥር በሚገኙ 15 ካምፓሶች የሚማሩ 7,029 የክልል ተወላጆች ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚካሄደው የክልልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለመሳተፍ ካርድ የወሰዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከትግራይ አክሱም፣ ከጋምቤላ አንዳንድ አካባቢዎች፣ ከአማራ አምባሰል፣ ከሐረሪ አንዳንድ አካባቢ ለመጡ ተማሪዎች በምርጫው ሙሉ ለሙሉ ለመሳተፍ የሚያስችላቸው ሰነድ ተሟልቶ አልቀረበም፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ጫኔ እንደሚሉት፣ ችግሩ የተፈጠረው በዩኒቨርሲቲው ሳይሆን በምርጫ ቦርድ ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለምርጫ ቦርድ አሳውቀው የጐደሉትን የመምረጫ ወረቀቶች በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡

የምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምርጫ ሒደት ላይ ለተፈጠረው ክፍተት ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አንድም ተማሪ ሳይመርጥ እንደማይቀርና ችግሩም እንደሚፈታ አሳውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢሾፍቱና በፍቼ የሚገኙትን ካምፓሶች ጨምሮ በ17 የምርጫ ጣቢያዎች የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የትግራይ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የሐረሪና የጋምቤላ ተወላጅ ተማሪዎች ድምፅ እየሰጡ ነው፡፡

ባህር ዳር 

በአማራ ክልል ዘንድሮ ለሚካሄደው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ከ7.7 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መመዝገቡ ሲታወቅ፣ በባህር ዳር ምርጫ ክልል ብቻ 92,379 መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአማራ ክልል ከሚገኙት 137 መደበኛ የምርጫ ክልሎች (የአርጎባ ብሔረሰብ ባለው ሕገ መንግሥታዊ ልዩ መብት ሳቢያ 38ኛው የምርጫ ክልል ነው)፣ በባህር ዳር የምርጫ ክልል 115 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን የሚጠቁመው የምርጫ ቦርድ መረጃ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢዴፓ፣ አንድነት፣ ቅንጅትና ብአዴን/ኢሕአዴግ ከሚወዳደሩት ፓርቲዎች መካከል እንደሚገኙበት ያመለክታል፡፡

በባህር ዳር ምርጫ ክልል የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን ማዘጋጀት የተጀመረው ዓርብ ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ሲሆን፣ ይህ የሆነውም በባህር ዳር ከተማ አልፎ አልፎ እየጣለ የሚገኘው ዝናብ ሒደቱን እንዳያስተጓጉል ተሰግቶ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች ይገልጻሉ፡፡ መሪ ጌታ ነትወሪ ጌቱ 10-1ለ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚገልጹት፣ ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ የምርጫ ሒደቱ ዝግጅቶች ተጠናቀው፣ የምርጫ ቁሳቁሶችም በጣቢያው ደርሰዋል፡፡

በየምርጫ ጣቢያዎቹ አምስት የሕዝብ ታዛቢዎች ሲገኙ፣ ከሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ 2,575 ታዘባዎች ባህር ዳርን ጨምሮ በ51 የተመረጡ የምርጫ ክልሎች ተመድበዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች ቡድንም በባህር ዳር ተዘዋውረው እየታዘቡ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ግን ባህር ዳር ከተማ ከወትሮው በተለየ የሕዝቡ እንቅስቃሴ የቀነሰ ሲሆን፣ የንግድ ተቋማትም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በአብዛኛው ተዘግተው ይገኛሉ፡፡ ወደ አጎራባች ወረዳዎች የሚደረጉ የተጓዞች እንቅስቃሴዎችም በምርጫው ሒደት ሳቢያ ደካማ ሆነዋል፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎች በብዛት በሚታዩባት ባህር ዳር ቁጥጥርና ጥበቃ እየተደረገ ነው፡፡

አዲስ አበባ

ምርጫ ክልል 28

በአዲስ አበባ በዞን 3 ምርጫ ክልል 28 ውስጥ በሚገኙት 86 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ከመገናኛ ኮተቤ በሚወስደው ጐዳና ሀና ማርያም አካባቢ በሚገኘው ሀና ማርያም የምርጫ ጣቢያ 1,422 መራጮች ድምፅ ለመስጠት መመዝገባቸውን የጣቢያው ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ይገዙ ገልጸዋል፡፡ በብሎኬት ማምረቻ ግቢ ውስጥ በተመሠረተው የምርጫ ጣቢያ ከሕዝብ ታዛቢዎች በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲና የኢሕአዴግ ታዛቢዎች የድምፅ አሰጣጡን ሒደት ሲከታተሉ ነበር፡፡ በምርጫ ክልል 28፣ 108,103 መራጮች ተመዝግበው ከሌሊቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር አያሌው ዘለቀ ከኢሕአዴግ፣ አቶ አምሳሉ ፍስሐ ከሰማያዊ፣ አቶ ኪዳኔ ደምሰው ከመድረክ፣ አቶ ጌታሁን ብሬ ከኢዴፓ ከ12 ዕጩዎች መካከል ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በዚሁ ክልል ዓድዋ ምርጫ ጣቢያ (ኮተቤ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ) 1,401 መራጮች ድምፅ ለመስጠት መመዝገባቸውን የጣቢያው ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተሾመ ገልጸዋል፡፡ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የምርጫ ክልል 28 የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተክለ ወልድ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

ምርጫ ክልል 16

ከ35,800 በላይ መራጭ የተመዘገበበት ምርጫ ክልል 16 (የቀድሞው ከፍተኛ 16 ሾላና መገናኛ አካባቢ) በ46ቱም ጣቢያዎች ድምፅ እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ምርጫ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ሲሆን፣ ወ/ሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ ከኢሕአዴግ፣ አቶ ዓለሙ በየነ ከመድረክ፣ አቶ አሸናፊ ታደሰ ከኢዴፓ፣ አቶ ወንድሙ ካሳሁን ከሰማያዊ ፓርቲ ይገኙበታል፡፡ በአስቸጋሪ ሥፍራ ላይ በተተከለ ድንኳን ውስጥ የተቋቋመው የወረዳ 5 ምርጫ ጣቢያ 4፣ ከ1,308 በላይ መራጮች ድምፅ ለመስጠት እንደተመዘገቡበት የምርጫ ጣቢያው አስተባባሪ አቶ ሰለሞን አሞኘ ገልጸዋል፡፡ የምርጫ ጣቢያው መገናኛ የካ ተራራ ቶፕ ቪው ሆቴል አካባቢ አቀበቱ ላይ በመቋቋሙ ለመራጮች አስቸጋሪ ነበር፡፡ አቶ ሰለሞን ግን በአካባቢው ካሉት የተሻለ ቦታ ተመርጦ ጣቢያው መቋቋሙን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ጣቢያ ምንም እንኳን 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢወዳደሩም፣ የሁለት ፖለቲካ ፓርቲዎች የኢሕአዴግንና የሰማያዊ ፓርቲን ታዛቢዎች ብቻ ለማየት ተችሏል፡፡ እነዚህ ታዛቢዎች በምርጫው ሒደት ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ

ምርጫ ክልል 15

ካዛንቺስ መተባበር ሆቴል አካባቢ በሚገኘው ድምፅ መስጫ ጣቢያ 444 መራጮች ለመምረጥ የተመዘገቡ ሲሆን፣ በዕለቱ ከ12 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ ፓርቲና የሲቪክ ማኅበራት ታዛቢዎችን አይተናል፡፡ ለመልሶ ማልማት እየፈረሰ ያለውን የካዛንቺስ አካባቢን የሚያጠቃልለው የምርጫ ክልል 15 ከሦስት ክፍለ ከተሞች ውስጥ በተካተቱ 38 የምርጫ ጣቢያዎች ሲኖሩት፣ 31,399 መራጮች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል፡፡ ኢሕአዴግ የአዲስ አበባ ሕፃናት ወጣቶችና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊን አቶ ዳኛቸው ቸርነትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፣ መድረክ አቶ ሽመልስ ተመስገንን፣ ሰማያዊ አቶ ተገኔ ታደሰን፣ ኢዴፓ አቶ ጥላሁን ሱፋን አቅርበዋል፡፡ በዚሁ ምርጫ ክልል ኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው ሁለት 31/1 እና 31/2 ጣቢያዎች ከ1,694 ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡ ሲሆን፣ በእነዚህ ጣቢያዎች የሕዝብ ተወካዮች የመድረክ፣ የሰማያዊ ፓርቲና የኢሕአዴግ ታዛቢዎች ምርጫውን ሲከታተሉ ተመልክተናል፡፡ በሒደቱም ላይ ምንም ችግር እንዳላጋጠማቸው የ31/1 ምርጫ ጣቢያ (8) አስተባባሪ ወ/ሮ ስመኝ አሰፋ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ የጣቢያ 9 (31/2) ኃላፊ አቶ ወርቁ ወልዴ የምርጫው ሒደት ችግር እንደሌለበትና ምንም ቅሬታ እንዳልቀረበበት አስረድተዋል፡፡ ይህንንም በጣቢያው የተገኙ የኢሕአዴግ፣ የሰማያዊና የመድረክ ታዛቢዎች አረጋግጠዋል፡፡

ሐዋሳ 

በደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሐዋሳ በ26 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የቦሪቻ ምርጫ ጣቢያ ሰማያዊ ፓርቲ ካሰማራቸው ታዛቢዎች ሦስት-አራተኛው ቅዳሜ ምሽትና እሑድ ጠዋት መታሰራቸውን ገለጸ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች በመሆናቸው ብቻ ነው የታሰሩት ብሏል፡፡ መታወቂያ ተቀምተው የተባረሩም እንዳሉም ገልጿል፡፡ የሲዳማና የሐዋሳ ምርጫ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዱካሞ፣ ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚለው ሳይሆን የታሰሩት ሁለት ናቸው ብለዋል፡፡ ታሳሪዎቹም እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለመታሰራቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ እሳቸው አሁን እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ቀደም ሲል የታሰሩ ሁለት ታዛቢዎች መለቀቃቸውንም ገልጸዋል፡፡ መድረክን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት ዶ/ር አየለ አሊቶ፣ የመድረክ 60 በመቶ ታዛቢዎች እንደታሰሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እስካሁን ድምፅ አለመስጠታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ ግን ሁሉም ታሳሪዎች እንደሚፈቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ባህር ዳር

በባህር ዳር የምርጫ ክልል ውስጥ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የኢዴፓና የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎችና ታዛቢዎች፣ በድምፅ መስጫ ጣቢዎች የተመለከቷቸው ስህተቶች መኖራቸውን ገለጹ፡፡

በባህር ዳር ምርጫ ክልል ካሉት 115 ምርጫ ጣቢዎች፣ 663 መራጮች የተመዘገቡበት የሰፈረ ሰላም 04-2ለ ምርጫ ጣቢያ የብአዴን፣ የኢዴፓና የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ታዛቢዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢዴፓና የሰማያዊ ዕጩ ተወዳዳሪ ታዛቢዎች ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ምንም እንኳ በድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ላይ የጎላ ችግር ባያስተውሉም፣ በዕድሜ የገፉ መራጮች የሚስተናገዱበት አግባብ ቅር አሰኝቷቸዋል፡፡ ከምርጫ ሕጉ ጋር የማይጣጣም ሆኖ እንዳገኙትም ገልጸዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ አቶ እንደሻው አቤ፣ ‹‹እስካሁን ያየነው ሒደት ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም ችግሮች አይከሰቱም አይባልም፡፡ ጥቃቅን ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ለምሳሌ ለአረጋውያን በድምፅ መስጫ ጣቢያ ውስጥ የድምፅ አሰጣጥ ገለጻ መስጠት ተገቢ ባለመሆኑ፣ ይህ ሒደት ከድምፅ መስጫው ውጪ እንዲደረግ ከብአዴን፣ ከሕዝብ ታዛቢዎችና ከሲቪክ ማኅበራት ታዛቢዎች ጋር ተነጋግረን እየተስተካከለ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ደረጄ ተሾመ የኢዴፓ ዕጩ ተዋወዳዳሪ ናቸው፡፡ ድምፅ አሰጣጡ በተገቢው ሰዓት መጀመሩንና በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ሆኖም አረጋውያንን በተመለከተ ከሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ምርጫው በተገቢው መንገድ እየተካሄደ መሆኑን የምርጫ ጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚ አቶ ገረመው ጌትነት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ 

ምርጫ ክልል 4

በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 4 መራጮች በማለዳ ነበር የወጡት፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል አራት በተለምዶ አብነት ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የነበረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፡፡

በዚህ የምርጫ ክልል ከሚገኙ 16 የምርጫ ጣቢያዎች በአንዱ ከ100 ያላነሱ መራጮች ጣቢያው ከሚከፈትበት ከማለዳው 12 ሰዓት አስቀድመው ነበር ሠልፍ የያዙት፡፡ ይኼም የተወሰነ መጨናነቅ ፈጥሮ እንደነበር፣ አቶ ነስረዲን ጁሃር የምርጫ ክልሉ የምርጫ አስፈጻሚና አስተባባሪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ማልደው ከመጡት መራጮችም ውስጥ የምርጫ ካርዳቸው የጠፋባቸው መራጮች በቤት ቁጥር ወይም የመራጭነት ምዝገባ ያከናወኑበት ቀን ከመዝገቡ ተረጋግጦ ሲመርጡ ተስተውሏል፡፡

ታሪኩ ደምሴ ለምርጫ ክልል አምስት (መርካቶ አካባቢ) ድምፅ መስጠት የተገኘ ሲሆን፣ በዘንድሮው ምርጫ ድምፁን የሰጠውን ፓርቲ ስም ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

ታሪኩ በመራጭነት በተመዘገበበት የምርጫ ክልል 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ፡፡ በ2002 ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ በዚህ ምርጫ ክልል አብላጫ ድምፅ አግኝቶ ያሸነፈው መድረክ ነበር፡፡ መድረክን የወከሉት አቶ ግርማ ሰይፉ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ዘንድሮ ኢሕአዴግን ወክለው በዚህ የምርጫ ክልል የሚወዳደሩት ይኼው የምርጫ ክልል የሚገኝበት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ አዛሉ ጥላሁን ናቸው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ለመወዳደር ተመዝግበው የነበሩት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በዕጣ ከውድድር ውጪ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ለመምረጥ የነበረው ሠልፍ ማለዳ ከነበረው አሁን ጋብ ብሏል፡፡

 መቐለ

በመቐለ እየተካሄደ ባለው ምርጫ ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማና ከዓረና መድረክ ደግሞ አቶ ገብሩ አሥራት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወዳደራሉ፡፡ ዶ/ር አዲስ ዓለም ለሪፖርተር፣ ‹‹ለ17 ዓመታት ከሕዝቡ ጋር ታግዬ ባመጣሁት የዴሞክራሲያዊ መብት ለመምረጥና ለመመረጥ በመብቃቴ ደስተኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ገብሩ የምርጫ ካርድ ስለሌላቸው እንደማይመርጡ፣ የዓረና/መድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ገብሩ የምርጫ ካርድ ያልወሰዱት አልቋል ተብለው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ አቶ አምዶም በህንጣሎ ዋጅራት፣ በሀገረ ሰላም፣ በሽሬ፣ በሃውዜን፣ በኢሮንብና በሌሎችም አካባቢዎች የዓረና/መድረክ ታዛቢዎች እየተባረሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቶ አምዶም፣ ‹‹አንዳንዶቹ ታዛቢዎች በቤተሰቦቻቸውና በሃይማኖት አባቶች ተፅዕኖ ተደርጐባቸው ከታዛቢነት ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ በምትካቸው ያቀረብናቸው ታዛቢዎች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ተቀባይነት አጥተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ እንዳይታዘቡ እየተደረጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመቐሌ ከሚገኙትና ሪፖርተር ከጐበኛቸው አምስት የምርጫ ክልሎች መካከል በሁለቱ ላይ ዓረና/መድረክ ታዛቢዎች አልነበሩትም፡፡

ጅማና አጋሮ

በጅማ ምርጫው ከማለዳው 12  ሰዓት የተጀመረ ሲሆን፣ በአጋሮ ደግሞ በ11፡30 ሰዓት ተጀምሯል፡፡ አጋሮ ዝናብ እየዘነበ ነበር፡፡ በምርጫ ክልሉ ኦሕዴድ፣ መድረክ፣ ሰማያዊና ኢዴፓ ይወዳደራሉ፡፡ በሁለቱ ከተሞች በብቸኝነት የሚታዩት የኦሕዴድ ፖስተሮች ብቻ ነበሩ፡፡ በክልል በሚገኙት 1,525 የምርጫ ጣቢያዎች የአፍሪካ ኅብረት፣ የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕዝብ ታዛቢዎች ተሰማርተዋል፡፡ 18 ዕጩዎች ለፌዴራል ምክር ቤት ይወዳደራሉ፡፡ በርካታ መራጮች ድምፃቸውን የሰጡ ሲሆን፣ የምርጫ ሒደቱ በሰላማዊ ሁኔታ እየተካሄደ ነው፡፡

አምቦ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በሚወዳደሩበት በተወለዱበት በቶኬ አካባቢ በሚገኘው የጉደር ከተማ መምረጥ እንደማይችሉ ታወቀ፡፡ ከምርጫ ጋር በተገናኙ ሥራዎች ተወጥረው የምርጫ ካርድ ሳይወስዱ እንዳለፋቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በ114 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በምርጫው ሒደት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ሒደቱ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ እንደሆነና ረዣዥም ሠልፎች እንደታዩም ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው ጣቢያዎች ተስተውለዋል፡፡ መራጮች በጠዋት የመጡት ወደ ሥራ ለመግባትና ሌሎች የማኅበራዊ ኃላፊነቶቻቸውን ለመወጣት እንደሆነም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን የምርጫ አስተባባሪ አቶ ሁንዴሳ ማደሳ 533,444 ዜጎች በመራጭነት መመዝገባቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዞኑ 11 የምርጫ ክልሎችና 862 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ ዘጠኝ ዕጩዎች ለፌዴራል፣ 18 ዕጩዎች ደግሞ ለክልል ምክር ቤቶች ይወዳደራሉ፡፡

የምርጫ አስፈጻሚዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት የምርጫ ቁሳቁሶች በጊዜው ቀርበዋል፡፡ ሦስት ፓርቲዎች ብቻ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎቻቸውን አሰማርተዋል፡፡ ኦፌኮ፣ ኦሕዴድና ኢዴፓ ታዛቢዎች ቢያሰማሩም ሌሎቹ ስድስት ፓርቲዎች ግን በአብዛኛዎቹ ጣቢያዎች ታዛቢ የላቸውም፡፡ አምስት የሕዝብ ታዛቢዎችም አሉ፡፡

ዶ/ር መረራ ፓርቲያቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን የተሳካ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንዲያውም ከምርጫ 97 የተሻለ ቅስቀሳ ነው ያደረግነው፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር መረራ የኦፌኮ ታዛቢዎች ከአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች መባረራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ጀልዱ፣ ጮልያና ጅባት ጣቢያዎች ይህ የተፈጸመባቸው ቦታዎች እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ሁንዴሳ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጉዳዮቹን ለመመርመር ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ የመድረክ (ኦፌኮ) ተወካዮች የያዟቸው ሰነዶች ትክክል አልነበሩም፤›› ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ያልተመዘገቡ፣ ሌሎች ደግሞ የምርጫ ሕጉን የጣሱ እንደነበሩም አስገንዝበዋል፡፡ የምርጫ ታዛቢዎች ቢሆኑም የወከሉትን ፓርቲ ምልክት እያሳዩ እንደነበርም አመልክተዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ከኦሕዴዱ አቶ ዮሐንስ ምትኩ ጋር ይወዳደራሉ፡፡ አቶ ዮሐንስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ የቀድሞው የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡

ባህር ዳር

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በባህር ዳርና በዙሪያው በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ለተመራጭነት ያቀረቧቸው ዕጩዎችና የምርጫ ታዛቢዎች ላይ ምርጫው ሊካሄድ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ እስራትና ድብደባ ሲፈጸምባቸው እንደነበር ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የአካባቢው ምርጫ አስፈጻሚዎች ችግሩን እንደማያውቁት አስታውቀዋል፡፡

ሻምበል ያየህይራድ ዘለቀ የኢዴፓ ተወካይና በባህር ዳር ምርጫ ክልል ፓርቲያቸውን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ ሻምበል ያየህይራድ በባህር ዳር ከተማ  ለሪፖርተር የምርጫ ዘጋቢ እንዳስታወቁት፣ እሳቸው በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልልም ሆነ በባህር ዳር ዙሪያ በሚገኙት ዘጌ መሸንቲ፣ ጢስ ዓባይ-ዘንዘልማ የምርጫ ክልሎች ውስጥ የኢዴፓ አባላት ላይ እስራትና እንግልት ተፈጽሟል፡፡ በተለይ በዘጌ መሸንቲና በጢስ ዓባይ-ዘንዘልማ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለታዛቢነት ተመድበው የነበሩት ሁለት የፓርቲው ተወካዮች ዓርብ ታስረው በማግሥቱ መፈታታቸውን ገልጸዋል፡፡ በምን ምክንያት እንደታሰሩ እንዳላወቁ ገልጸዋል፡፡ የፖስተሮች መቀደድ፣ የባነር ማስታወቂያዎች መነሳት ሲያጋጥሙ ከነበሩ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ሻምበል ያየህይራድ አስታውቀዋል፡፡ በጎንጂ፣ በቆለላ፣ በአዴት ምርጫ ክልሎች እንዲወዳደሩ ያቀረባቸው ዕጩዎች በምርጫ ቦርድ መሰረዛቸውንና የተሠረዙበት ምክንያትም ለኢዴፓ እንዳልተገለጸለት ተናግረዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲም ተመሳሳይ ጫና ሲደርስበት እንደቆየ አስታውቋል፡፡ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ያቀረባቸው ዕጩዎች ላይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ለበርካታ ጊዜያት እስራትና ድብደባ ተፈጽሟል፡፡ በተለይ ሲነን በምትባለው ወረዳ በርካታ አባላቱ ሲታሰሩ እንደነበር አቶ ናትናኤል ገልጸዋል፡፡ በባህር ዳር ምርጫ ክልል እንዲወዳደሩ ካቀረባቸው ሁለት ዕጩዎች አንዱ ተሰርዘው፣ በአንድ አባል ብቻ ለመወዳደር መገደዱን አስታውቀዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የባህር ዳር ጽሕፈት ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ማሩ ዳኜም በርካታ እንግልት በአባሎች ላይ ሲደርስ መቆየቱን ገልጸው፣ ሚዲያው በሚደርስብን በደልና እንግልት ላይ ዝምታን መርጧል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡  ሰማያዊ ፓርቲ በአገር አቀፍ ደረጃ 200 ዕጩዎች አንደተሰረዙበት ሲገልጽ፣ ኢዴፓ በበኩሉ 90 ዕጩዎች እንደተሰረዙበት ይፋ አድርጓል፡፡

የባህር ዳርና ዙሪያው የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች በበኩላቸው ታሰሩ ስለተባሉት የሁለቱ ፓርቲዎች አባላት የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ አቶ ገረመው አሥራት የባህር ዳር ምርጫ ክልል፣ የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ናቸው፡፡ አቶ ገረመው ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ፓርቲዎች በደብዳቤ የደረሱባቸውን ችግሮች ማሳወቅ ሲኖርባቸው፣ ቦርዱ ከሰማያዊም ሆነ ከኢዴፓ በጽሑፍ የደረሰው ምንም ዓይነት አቤቱታ የለም፡፡ በዘጌ መሸንቲ ምርጫ ክልል የምርጫ አስተባባሪዎች ኢዴፓ ታስረውብኝ ነበር ስላላቸው የምርጫ ታዛቢዎች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም የምረጡኝ ቅስቀሳ ካበቃ በኋላ እስከ ቅዳሜ ድረስ ኢዴፓ ቅሰቀሳ ሲያካሂድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አቶ ፈንታ ደጀን የባህር ዳር ከተማ የፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት ሰብሳቢና የብአዴን ሥራ አስፈጻሚ አባል ናቸው፡፡ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ኢዴፓ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ቢሆንም ታስረው ነበሩ ስለተባሉት አባሎቹ ያቀረበው አቤቱታ የለም፡፡

ሐዋሳ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲን ወክለው ለፓርላማ የሚወዳደሩት አቶ ሲዳ ኃይሌ በንጋት ኮከብ ቁጥር 1 ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፃቸውን የሰጡት 2፡30 ሰዓት ገደማ ነበር፡፡ በትናንትናው ዕለት አንድ ዛሬ ደግሞ አንድ የፓርቲው ታዛቢዎች መታሰራቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለእስራቱ ምክንያት በመታወቂያ ካርድ ላይ በተመዘገበ የስህተት ስም ነው ብለዋል፡፡ የሲዳማና የሐዋሳ ከተማ የምርጫ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዱካሞ ታዛቢዎቹ መታሰራቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ትናንት የታሰሩት ታዛቢ እንደተባለው በስም የፊደል ስህተት ሳይሆን፣ የሌላ ፓርቲ የታዛቢነት መታወቂያ ይዘው በመገኘታቸው ነው ብለዋል፡፡ ግለሰቡ የአንድነት ፓርቲ አይደሉም ብለዋል፡፡ የሁለቱም ታዛቢ እስረኞች ጉዳይ ተጣርቶ ወደ ታዛቢነት የሚመለሱ ከሆነ እየተነጋገሩበት መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በሐዋሳ ከተማና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መራጮች በብዛት ወጥተው እየመረጡ ናቸው፡፡

ወላይታ/ቦሎሶ ሶሬ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከጠዋቱ 4፡10 ቦሎሶ ሶሬ ምርጫ ጣቢያ ሲደርሱ፣ ሕዝቡ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡ የመረጡትም ከመራጮች ጋር ተሠልፈው ወረፋ ሲደርሳቸው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹በተወለድኩበት አካባቢ መጥቼ በመምረጤ በጣም ደስታ ይሰማኛል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ ነው፡፡ እናሸንፋለን ብለን እንጠብቃለን፤›› ብለዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚፎካከሩት የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ አቶ ቀኙ ሴባና የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዕጩና በአካባቢው ታዋቂ የሆኑት ሙዚቀኛ አቶ ደስታ ዳአ፣ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ባለው የድምፅ አሰጣጥ ሒደት ደስተኛ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ከተመዘገቡት 8,000 ያህል መራጮች ግማሽ ያህሉ ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡

ነቀምት

በምሥራቅ ወለጋ ዞን በነቀምት ዙሪያ ምርጫ ክልል በ99 የምርጫ ጣቢያዎች 75,074 መራጮች ተመዝግበው ድምፃቸውን እየሰጡ ነው፡፡ የሚፎካከሩት ፓርቲዎች አራት ናቸው፡፡ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ፣ መድረክ፣ ኢዴፓና መኦሕዴፓ ናቸው፡፡ በአካባቢው ከፍተኛ ዝናብ ስለነበር ብዙዎች በጃንጥላ ተጠልለው ነው ድምፅ የሰጡት፡፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግን ወክለው ይወዳደራሉ፡፡ ተፎካካሪዎቻቸው ከመድረክ አቶ ታሪኩ ደሳለኝ፣ ከኢዴፓ አቶ ኃይለየሱስ ፊጤ፣ ከመኦሕዴፓ አቶ ሰኚ ታደሰ ናቸው፡፡ በአካባቢው የኦሕዴድ/ኢሕአዴግና የመድረክ ታዛቢዎች ናቸው በብዛት የሚታዩት፡፡

ደቡብ ክልል

በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን በቦሎሶ ሶሬ ምርጫ ክልል 01 ጠቅላላ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ መራጮች ቤተ ክርስቲያን በመሄዳቸው ምክንያት የመራጮች ቁጥር ዝቅተኛ እንደነበር ሪፖርተራችን ዘግቧል፡፡ በዚህ ምርጫ ከመድረክ በስተቀር ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ይወዳደራሉ፡፡ በወላይታ ዞን ሐረካት 3 የምርጫ ጣቢያ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ደኢሕዴግ/ኢሕአዴግን ወክለው ይወዳደራሉ፡፡ በእዚህ ምርጫ ክልል መራጮች በብዛት ታይተዋል፡፡ የመድረኩ ፕሮፌሰር በየነና የደኢሕዴግ/ኢሕአዴግ አቶ ዮሴፍ ዳኢሞ የሚወዳደሩበት የሐዲያ ዞን ማካማ 02 ምርጫ ክልል መራጮች በብዛት ወጥተው እየመረጡ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታዛቢዎችም አሉ፡፡

አዲስ አበባ

ምርጫ ክልል 17

የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ በቀለ ከኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የኢዴፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ እንዲሁም የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮን ያገናኘው የምርጫ ክልል 17 ምርጫ በከፍተኛ ተሳትፎ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው የምርጫ ጣቢያዎች ቺቺንያ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ጣቢያ በስተቀር ረጃጅም ሠልፎች ታይተዋል፡፡

ይህ ነው የሚባሉ ግድፈቶች ባይስተዋሉም በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎችን አላስቀመጡም፡፡ በተጨማሪም የምርጫ ሒደቱ ላይ ማብራሪያ እየተሰጠም ጭምር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌላቸው መራጮችም ታይተዋል፡፡

ተጻፈ በ 

Leave a Reply