Wednesday, 27 May 2015 17:5

በይርጋ አበበ

 

 

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ሊነጋጋ ሲል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አንድ የምርጫ ጣቢያ ቅጥር ግቢ ተገኝተናል። ቁጥራቸው በርከት ያሉ  አዛውንት ሴቶች ድምጽ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያው ሲገቡ ይታያሉ። ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አደራ የተሰጣቸው የምርጫ አስተባባሪዎች ደግሞ አዛውንት እናቶችን ጨምሮ ሁሉንም ድምጽ የሚሰጡ ዜጎችን እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው ምክረ ሃሳብ ይለግሳሉ። አንዲት እናት ግን የአስተማሪው ሃሳብ ሊገባቸው አልቻለም። በተደጋጋሚ ጊዜ ቢነግራቸውም ሊገባቸው ስላልቻለ አስተማሪው “እንደዚህ አድርገው ምልክት ካላደረጉ (በአንዱ ተወዳዳሪ ፓርቲ ምልክት ላይ የመምረጫ ምልክት እያሳየ) ድምጽዎ ወዳቂ ይሆናል” አላቸው። ሴትዮዋ ደንገጥ ብለው “እንደሱ ካላደረኩ እወድቃለሁ” ሲሉ ተናገሩ።
በተመሳሳይ ዕለት የዝግጅት ክፍላችን የምርጫ ዘጋቢ ቡድን ከአመሻሹ ላይ ፒያሳ አካባቢ በአንድ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኙ ሶስት የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ የድምጽ አሰጣጡን ሂደትና ቆጠራውን የመታዘብ እድል ገጥሞት እየተመለከተ ነው። የድምጽ መስጫ ሰዓቱ ከተጠናቀቀ አምስት ደቂቃዎች ያለፉ ቢሆንም መራጮች ድምጽ ለመስጠት በምርጫ ጣቢያው ቅጥር ግቢ ስለተገኙ የመራጮችን ድምጽ ሰጥቶ የመውጣት መብታቸውን አስጠብቆ 12፡10 ሲሆን ምርጫ ጣቢያው ተዘጋ። ለመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎችን ስም ዝርዝር የያዘውን መዝገብ እና በምርጫው እለት ድምጽ የሰጡትን ሰዎች ስም ዝርዝር እያስተያዩ ልዩነቱን ካረጋገጡ በኋላ የጋዜጠኞችን ቡድን ጨምሮ ሌሎች ታዛቢዎች በተገኙበት ኮሮጆውን የመቆለፍና ቃለ ጉባዔ የመያዝ ስራ ተካሄደ። በመጨረሻም ወደማይቀረው የድምጽ ቆጠራ ሂደት ተሄደ።  የተቆለፉ ኮሮጆዎች ቁልፋቸው ተሰብሮ መዝጊያቸው ተከፈተና በውስጣቸው አጭቀው የያዙትን የወረቀት ክምር ማራገፍ ጀመሩ።
በድምጽ መስጫው እለት የነበሩ ክስተቶች
ገና ከማለዳው ጀምሮ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውረን በተመለከትነው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ላይ እንደታዘብነው ብዛት ባላቸው ምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች በቦታው አልተገኙም። መራጮች ድምጽ የሚሰጥበት ሰዓት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ቀኑን ሙሉ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየሄዱ ድምጻቸውን ሲሰጡ ውለዋል።
የድምጽ ቆጠራ ውጤት
በድምፅ ቆጠራ ቦታ በነበረን ቆይታ ከታዘብናቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ዋጋ አልባ ድምፆች ናቸው። እነዚህ ዋጋ አልባ የሆኑ ድምፆች  የዚህ ዓመቱን ምርጫ ለማከናወን ድምፅ በሚስጠበት ወቅት መራጮች መጠቀም ካለባቸው ምልክቶች ውጪ የሆኑ ናቸው።
ምርጫ ቦርድ ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት አንድ መራጭ ድምፁን መስጠት ለሚፈልገው ፓርቲ ወይም ተወዳዳሪ ግለሰብ ድምፁን ሰጠ የሚባለው ቀለምን በመጠቀም የጣት አሻራውን ወይም የኤክስ (X) ምልክት በሚፈልገው ተወዳዳሪ የምርጫ ምልክት ፊት ለፊት በሚገባ ማስቀመጥ ሲችል ነው። ይሄንኑ ጉዳይ በተመለከተ ከምርጫው በፊት በተለያዩ መገናኛ ብዙኋን ብዙ ሲባል ከርሟል፣ ምርጫ ቦርድ ምርጫው ከመካሄዱ ከአንድ ሳምንት በፊት ለመራጮች የድምፅ አሰጣጥ ስነስርአትን አስመልክቶ  በየአካባቢው ትምህርታዊ መግለጫን ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ በምርጫው እለትም መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊትም ቢሆን ድምፅ አሰጣጥን በተመለከተ በየምርጫ ጣቢያው አጠር ያሉ ማብራሪያውች ሲሰጡ ተመልክተናል። አንዳንዶች እንደውም “ማብራሪያውን በተደጋጋሚ ስለሰማን ድምፅ ብቻ ሰጥተን መሄድ የምንፈልገው” በማለት ቀጥታ ድምፅ ሰጥተው ሲወጡም ተመልክተናል።
ሆኖም በእለቱ ከምሽቱ 12 ሰአት በኋላ  የድምፅ ቆጠራው ሲጀመር የታየው እውነታ ግን ፈፅሞ ከዚህ የተለየ ነበር። ኮሮጆዎቹ   ተከፍተው ቆጠራው ሲጀመር ቀላል የማይባል ድምፅ ባክኖ ተገኝቷል። የተሰጡት ድምፆች ከባከኑባቸው ምክንያቶች መካከል በሁለት ተፎካካሪዎች መካከል በሚገኝ አዋሳኝ ቦታ ላይ ምልክት ማድረግ፣ ምንም አይነት ምልክት አለማድረግ፣ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ተወዳዳሪዎች ላይ ምልክት ማድረግ፣ የጣት አሻራን በሚጠቀሙበት ወቅት ቀለሙን በማብዛት ማጠፍና ይህንንም ተከትሎ በሌላኛወ ተወዳዳሪ ላይ ቀለሙ ማረፍ በዋና ችግርነት ታይተዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ መራጮች ድምፅ መስጫን ወረቀቱን በመውሰድ በምትኩ ነጭ ወረቀት ኮሮጆው ውስጥ ከተው የተገኙበት ሁኔታም ነበር። አንዳንድ ድምፅ ሰጪዎች የድምፅ አሰጣጥን በተመለከተ ግንዛቤ ያላቸው ቢመስልም ሆን ብለው በድምፅ መስጫ ወረቀቶቹ ላይ  የተለያዩ ፅሁፎችን በመፃፍ ኮሮጆዎቹ  ውስጥ ከተው የተገኙበት ሁኔታም ነበር። ከድምፅ  አሰጣጥ ስነስርአት ጋር በተያያዘ የባከኑት ድምፆች ምክንያቶቻቸው   ምን እንደሆነ የተወሰነ ዳሰሳዊ ጥናት የሚጠይቁ ይመስላል። ድምፆቹ በመባከናቸው ተወዳዳሪ ፓርቲዎቹም ሆኑ ደምፅ ሰጪው ግለሰብ ተጎጂዎች ናቸው። የባከኑት ድምፆች ብዛት ሲታይ ደግሞ ድምፆቹ ለተመራጩ አካል ቢደርሱ ኖሮ ምን ያህል ልዩነትን እንደሚፈጥሩ መገመት አያስቸግርም።
እውን ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን ተወጥቷል?
የምርጫውን ውጤት ለህዝብ ይፋ የማድረግ ኃላፊነት ያለው ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑ በህግ የተደነደገገ ጉዳይ ነው። ውጤት ከመግለጽም በላይ ምርጫውን ከመጀመሪያው ሂደት ጀምሮ አሸናፊ የሆነው ፓርቲ መንግስት እስከሚመሰርትበት ጊዜ ድረስ የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት ነው። በዚህ በኩል የምርጫውን ቅድመ ሁኔታ በተመለከተ ከምርጫው ከሶስት ቀናት ቀደም ብሎ ሀሙስ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም የቦርዱን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን ጨምሮ የቦርዱ ኃላፊዎች በሂልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የምርጫው ቅድመ ዝግጅት በሚገባ የተከናወነ መሆኑን አረጋግጠው ነበር። ነገር ግን በምርጫው እለት የታየው በህዝብ ገንዘብ የተዘጋጀውን ጠቅላላ ምርጫ ዋጋ የሚያሳጡ የህዝብ ድምፆች ናቸው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምርጫ ቦርድ የቤት ስራውን በሚገባ ባለመስራቱ እንደሆነ አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ።
ለባከኑ ድምጾች ሁሉም አካላት ማለትም ምርጫ ቦርድ፣ መንግስት፣ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሃን እና መራጩ ህዝብ የየራሳቸውን ድርሻ የሚወስዱ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ ግን የሚበልጠውን ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል።
በሀገር አቀፉ ምርጫ ማግስት የወጡ ድምጾች
ምርጫው ግንቦት 16 ቀን መጠናቀቁን ተከትሎ ምርጫውን የታዘቡት የሲቪክ ማህበራት ጥምረት እና መንግስት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በግሉ የድምጽ አሰጣጡን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ አንዳንዶች ለጋዜጠኞች አንዳንዶች ደግሞ በድረ ገጻቸው አቋማቸውን ገልጸዋል። እንደሚጠበቀው የመንግስት የሲቪክ ማህበራቱ ጥምረት እና የምርጫ ቦርድ መግለጫ ድምጽ አሰጣጡ በትክክል እንደተካሄደ ሲገልጹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በዕጩዎቻቸው፣ በታዛቢዎችና በደጋፊዎቻቸው ላይ የአፈና፣ የማሳደድ፣ የማሰርና የመሳሰሉ ሕገወጥ ተግባራት በገዢው ፓርቲና በደጋፊዎቹ መፈፀማቸውን ይናገራሉ።
በመጨረሻም በአዲስ አበባ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ሰኞ ዕለት ጠዋት የምርጫው ውጤት የተለጠፈ ሲሆን፤ አጠቃላይ ጊዜያዊ ውጤቱን እስከ ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደርጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።¾

Leave a Reply