27 MAY 2015

በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦና አካባቢዋ የሚደረገው ምርጫ ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት በመሆኑ የብዙዎችን ቀልብ ይስባል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)

የትጥቅ ትግል በሚያካሂድበት ወቅት በ1983 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ያደርግ የነበረውን ግስጋሴ፣ በአምቦ አካባቢ ሕዝብ ድጋፍ የነበረው ወታደራዊ ደርግ የኢሕአዴግን ጥቃት መመከት ችሎ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የአምቦና አካባቢዋ ሕዝብ ከደርግ ሠራዊት ጋር ተባብሮ በፅናት መዋጋቱ ይነገራል፡፡

ይሁን እንጂ በስተኋላ ኢሕአዴግ ኃይሉን አጠናክሮ በአምቦና በጉደር ከተሞች አካባቢ የነበረውን የደርግ መከላከያ መስመር ጥሶ አዲስ አበባን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. መቆጣጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ የኢሕአዴግና የአምቦ አካባቢ ሕዝብ ቁርሾ የሚጀመረው ከዚያን ወቅት ነው፡፡

ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በሚያካሂዳቸው አገራዊ ምርጫዎች በአብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲያሸንፉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ የነበራቸው በመሆኑ፣ ቀደም ሲል ይመሩት የነበረው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በምዕራብ ሸዋ ዞን በአብዛኛው ጊዜ ሲያሸንፍ ቆይቷል፡፡

ይህ ታሪክ በምርጫ 2002 ተቀይሮ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግን ወክለው የተወዳደሩትና የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ዮሐንስ ምትኩ ዶ/ር መረራን አሸንፈዋል፡፡ በዘንድሮ አምስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ በዶ/ር መረራ የኦሮሞ ሕዝቦች ኮንግረስና በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይመራ የነበረው ኦፌዴን ጥምረት ከሆነው ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ማን ያሸንፍ ይሆን የሚለው ጥያቄ በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚካሄደውን ምርጫ አጓጊ አድርጎታል፡፡

ኦፌኮ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነውን መድረክ ወክሎ ወደ ምርጫ ገብቷል፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎቻቸውን ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን አሰማርተዋል፡፡

የምርጫ ዋዜማ

በምርጫው ዋዜማ ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. የአምቦ ከተማ ሕዝብ የተለመደውን የዕለት ተዕለት ኑሮውን በማካሄድ ላይ ነበር፡፡ በከተማው የተጠናከረ ጥበቃ መኖሩ ታይቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት አምቦና አካባቢዋን በመዘዋወር ሲጠብቁ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ አድማ በታኝ ኃይል ከነሙሉ ትጥቁ በየፖሊስ ጣቢያው ሰፍሯል፡፡

ከአምቦ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በጉደር ከተማ በተመሳሳይ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ሲዘዋወሩ የነበረ ሲሆን፣ አድማ በታኝ ኃይልም ዝግጁ ሆኖ ሲጠባበቅ ማየት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በአምቦና በጉደር አካባቢ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በፒክአፕ ተሽከርካሪዎች ዋናውን አስፋልት መንገድ ፓትሮል ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የጋራ ማስተር ፕላን ዝግጅት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ መፍጠሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በወቅቱ የአምቦ ከተማ ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በምርጫው ሒደት ላይ የራሱን ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች በአምቦ የሚካሄደውን ምርጫ ውጥረት የሰፈነበት እንዲሆን አድርገውታል፡፡

በአምቦ ከተማ በምርጫው ዋዜማ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለባጃጆችና ቡና ቤቶች ሥራ ከቀዘቀዘ አምስት ስድስትና ቀናት እንደተቆጠሩ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከ12 ሰዓት በኋላ አብዛኛው የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወደ መኖሪያ ቤቱ ከቷል፡፡ ምግብ ቤትና መጠጥ ቤቶች ማምሻውን ጭር ብለው ተስተውሏል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሆቴልና አበበች መታፈሪያ ያሉ ትላልቅና ታዋቂ ሆቴሎች የምግብ አዳራሾቻቸው ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ ደንበኞች ብቻ ሲስተናገዱ ታይተዋል፡፡

የምርጫ ዝግጅት

የምዕራብ ሸዋ ዞን የምርጫ አስተባባሪና የአምቦ አንድ የምርጫ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁንዴሳ ማዴሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ለምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 533,444 ነው፡፡ በዞኑ 11 የምርጫ ክልል 862 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ አሥር ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን አቶ ሁንዴሳ ተናግረዋል፡፡ ለተወካዮች ምክር ቤት 62፣ ለክልል ምክር ቤት 137 በአጠቃላይ 199 ዕጩዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ውስጥ 176 ወንድ፣ 23 ሴቶች ናቸው፡፡

ለጋዜጠኞች መረጃ ያለመታከት ይሰጡ የነበሩት አቶ ሁንዴሳ፣ በምርጫ ዋዜማ ለምርጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በሰዓቱ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በከተማ ለሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ድንኳንና መብራት እንዲገባላቸው የተደረገ ሲሆን፣ በገጠር ለሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ዳስ፣ የእጅ ባትሪዎችና ሻማ ተገዝቶ መላኩን አስታውቀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ 114 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአምቦ ከተማ ስድስት ቀበሌዎች (ሦስት የከተማ፣ ሦስት የገጠር ቀበሌዎች) ሕዝብ ብዛት ከ100,000 በላይ ይገመታል፡፡ በአምቦ ከተማ 31 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ በአምቦ ከተማ 22,849 ነዋሪዎች በመራጭነት ተመዝግበዋል፡፡ በሦስቱ የገጠር ቀበሌዎች 33,169 ነዋሪዎች በመራጭነት ተመዝግበው ካርድ ወስደዋል፡፡

በአምቦ ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘጠኝ፣ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ 18 ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ኦሕዴድ (ኢሕአዴግ)፣ ኦፌኮ (መድረክ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ቅንጅት፣ አንድነት፣ መላው ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦሕዴፓ)፣ መኢብንና የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) ናቸው፡፡

ፀጥታን በተመለከተ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ እስከ ምርጫ ጣቢያ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ የአካባቢው፣ የዞን ፖሊስና የአካባቢው ፀጥታ ዘርፍ አካላት ጋር በመቀናጀት ሚሊሻና ታጣቂዎችን በማደራጀት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አቶ ሁንዴሳ ተናግረዋል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እስከ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ከምርጫው ቀደም ሲል የዞኑ የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ በምርጫ ሕጉ ዙሪያ ትምህርት ሰጥቷል፡፡ ‹‹የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብን በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደናል፡፡ ምንም እንኳ መድረክ የሥነ ምግባር ሕጉን ባይፈርምም በውይይቱ ተካፋይ ሆኗል፤›› ያሉት አቶ ሁንዴሳ ኢሕአዴግ፣ መድረክና ገሥአፓ የሚገኙበት የጋራ መድረክ አቋቁመው በሥነ ምግባር ሕጉ ዙሪያ ሲወያዩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በአምቦ ከተማ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጨመዳ ለሪፖርተር እንደገለጹት ፓርቲያቸው ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ አቋቁመን የሚገጥሙንን ጥቃቅን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ስንፈታ ቆይተናል፤›› ያሉት አቶ አሸናፊ፣ ፖስተር ተቀዳደደብኝ የሚሉ ቅሬታዎች ከገዢው ፓርቲና ከመድረክ መቅረባቸውን፣ የምርጫ ቅስቀሳ በተከለከሉ ሥፍራዎች (እንደ ትምህርት ቤት ባሉ ቦታዎች) ማካሄድና ያልተገቡ ዘፈኖች (ግጭት ሊጭሩ የሚችሉ) ማሰማት ችግሮች በመድረክ በኩል ነበሩ፡፡ ‹‹እነዚህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ቦርዱም ባለበት የጋራ መድረክ ተነጋግረን ፈተናቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ቅድመ ምርጫው ሰላማዊ እንደነበር አቶ አሸናፊ አረጋግጠዋል፡፡

ኦፌኮ/መድረክ በአምቦ፣ በጉደርና በሌሎችም ከተሞች ሰፊ የቅስቀሳ ዘመቻ አካሂዷል፡፡ ከምርጫው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በአምቦ ከተማ በርካታ ሕዝብ የተሳተፈበት ስብሰባ አካሂዷል፡፡ የኦፌኮ ሊቀመንበርና የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መድረክ የተሳካ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂዷል፡፡ ‹‹ከምርጫ 97 የበለጠ የቅስቀሳ ሥራ ሠርተናል፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ‹‹ሜዳው የተስተካከለ ባይሆንም ችግሮችን ተቋቁመን ሰፊ የቅስቀሳ ሥራ ሠርተናል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር መረራ በቅስቀሳ ወቅት በአምቦና በጉደር ከተሞች ችግር እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ትምህርት ቤት፣ ቤተ ክርስቲያን አለ እያሉ የምርጫ ቅስቀሳ እናዳናካሂድ ከልክለውናል፡፡ በገበያ ቀንም ቅስቀሳ እንዳናካሂድ ተከልክለናል፡፡ ተማሪዎች እንዳይገኙልን በዕረፍት ቀን (ቅዳሜና እሑድ) ከልክለው በሥራ ቀን እንድናካሂድ ያደርጋሉ፤›› ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም ‹‹አጠቃላይ የምርጫውን ሒደት ያበላሸው አንድ ለአምስት የሚሉት ፖለቲካ ነው፡፡ የቀበሌ አለቆች ሕዝቡን ድምፅ የምትሰጡት በተደራጀ መልክ ነው በማለት፣ ሕዝቡ ድምፁን ለገዢው ፓርቲ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የምርጫ ዕለት

እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የአምቦና የጉደር ከተማ ነዋሪዎች ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በየምርጫው ጣቢያ ተሰልፈዋል፡፡ በተለይ በጉደር ከተማ መራጩ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ለመምረጥ ረዥም ሠልፍ ይዞ ተስተውሏል፡፡

በአምቦ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫው ሒደት በሰዓቱ (ከጠዋቱ 12 ሰዓት) መጀመሩን ተመልክቷል፡፡ በየምርጫ ጣቢያው አምስት የሕዝብ ታዛቢዎች የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ከመጀመሩ አስቀድመው ተገኝተዋል፡፡ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች ተወካዮቻቸውን ያስቀመጡት ኢሕአዴግ፣ መድረክና ኢዴፓ ብቻ ናቸው፡፡ የተቀሩት ስድስት ፓርቲዎች በአብዛኛው ጣቢያዎች ታዛቢዎቻቸውን እንዳላስቀመጡ ታይቷል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ አቶ አዲሱ ፈቃዱ ፓርቲያቸው በሰው ኃይልና በበጀት እጥረት ምክንያት ተወካዮቹን በየምርጫ ጣቢያው ማስቀመጥ እንዳልቻለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ የገሥአፓ ተወካይ አቶ አሸናፊ ጅፋራ ድርጅታቸው በተቻለ መጠን በአብዛኛው ምርጫ ጣቢያቸው ታዛቢዎች የመደበ ቢሆንም፣ በሰው ኃይልና በበጀት እጥረት ሁሉንም የምርጫ ጣቢያ ማዳረስ እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡

በአምቦ ከተማ በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ የተመዘገበው ሕዝብ በአማካይ ከ600 እስከ 700 ነው፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎቹ በሚገባ የሠለጠኑ ይመስላሉ፡፡ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ማለዳ በአምቦ ከተማ ሪፖርተር ከደረሰባቸው በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ03-ሀ-1፣ በ01-ለ-2፣ 02-ሀ-12፣ 04-ሀ-2እና በሌሎችም ጣቢያዎች መራጩን ሕዝብ በተቀላጠፈ ሁኔታ ሲያስተናግዱ ታይተዋል፡፡ በመሆኑም ማለዳ የታየው ሠልፍ ረፋዱ ላይ (ከአራት ሰዓት በኋላ) በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች አልታየም፡፡

በየምርጫ ጣቢያው መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት ስለ ድምፅ አሰጣጡ በቂ ማብራሪያ የተሰጣቸው ቢሆንም፣ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች በድምፅ መስጠቱ ሒደት ላይ ግራ ሲጋቡ ታይተዋል፡፡ አንዳንድ አዛውንቶች የድምፅ መስጫ ወረቀቱን ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ አንድ እናት የድምፅ መስጫ ወረቀቱን በሚስጥር ድምፅ መስጫ ክፍል ውስጥ አስቀምጠው ሲወጡ ተስተውሏል፡፡

በአምቦ ከተማ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ድምፁን ሰጥቶ ሲወጣ ታይቷል፡፡ በምርጫ ጣቢያ 03-ሀ-1 ድምፃቸውን ሰጥተው ሲወጡ ሪፖርተር ያገኛቸው ሻለቃ ታምራት ዓሊ፣ በድምፅ አሰጣጡ ሒደት መርካታቸውን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት የ59 ዓመቱ ሻለቃ ታምራት በቂ ገለጻ እንደተደረገላቸው፣ ያለምንም ችግር መርጠው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የምርጫ ክርክሩ በቂ ግንዛቤ አስጨብጦናል፡፡ ዛሬም ያለምንም ግርግር መርጠን ወጥተናል፤›› ብለዋል፡፡ በምርጫ ጣቢያ 04-ሀ-2 የመረጡት ወ/ሮ በቀለች ታደለ ከቤተ ክርስቲያን መልስ ቁርሳቸውን ሳይበሉ ድምፃቸውን ለመስጠት እንደመጡ ገልጸዋል፡፡ የ78 ዓመቷ ወ/ሮ በቀለች በሁለት ልጆቻቸው እየተጦሩ እንደሚኖሩ ገልጸው በንጉሡ ሥርዓት እከሌን ምረጡ እየተባሉ ይመርጡ እንደነበር፣ በዘመነ ደርግ ምርጫ አለመምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ደርግ መሬት ወርሶብኝ ስለነበር ተቀይሜ መምረጥ አልፈለግኩም ነበር፡፡ አሁን ግን በነፃነት የምንፈልገውን እየመረጥን ነው፡፡ ያለምንም ችግር የምወደውን መርጫለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በድምፅ አሰጣጡ ሒደት ላይ አንዳንድ ችግሮች መከሰታቸው አልቀረም፡፡ በምርጫ ጣቢያ 04-ሀ-2 ያገኘነው የኦፌኮ/መድረክ ታዛቢ ወጣት ዋቅጅራ ቃበታ የተማሪ መታወቂያ ይዞ በመምጣቱ ወደ ምርጫ ጣቢያው እንዳይገባ መደረጉን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ‹‹ከሌሊቱ 11 ሰዓት በምርጫ ጣቢያው የተገኘሁ ቢሆንም፣ የምርጫ ኃላፊዎቹ የትምህርት ቤት መታወቂያ ተቀባይነት የለውም፡፡ የቀበሌ መታወቂያ አምጣ በማለት እንዳልገባ ከልክለውኛል፡፡ የካርድ ቆጠራ ሲካሄድና ኮሮጆ ሲከፈት መታዘብ አልቻልኩም፡፡ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች መጥተው 12፡25 ሰዓት ሲሆን ነው ተፈቅዶልኝ የገባሁት፤›› ብሏል፡፡

የምርጫ ጣቢያ ኃላፊው አቶ ሊካሣ ኢርካታ ችግሩ መፈጠሩን አምነዋል፡፡ ‹‹የመድረክ ተወካይ ነኝ ብሎ ሲመጣ መታወቂያ ጠየቅነው፡፡ ያሳየን መታወቂያ የትምህርት ቤት ብቻ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ማሳየት ያለበት የቀበሌ ነዋሪነት መታወቂያ ነው በሚል አስቁመነዋል፡፡ በኋላ የዞኑ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ሁንዴሳ መጥቶ አግባብነት እንዳለው ካስረዳን በኋላ አስገብቸዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በኦዶ ሊበን የምርጫ ጣቢያ የተገኘው ፌሌንበር ዲቦ የተባለ የመድረክ ተወካይ፣ የኦሕዴድ ካድሬዎችና ታጣቂዎች ወደ ምርጫ ጣቢያው በተደጋጋሚ ገብተዋል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ወጣት ፌሌንበር ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የምርጫ ሕጉ ታጣቂዎች ከምርጫ ጣቢያው 500 ሜትር መራቅ አለባቸው ቢልም አንዳንድ ታጣቂዎች ወደ ምርጫ ጣቢያው ዘልቀው እንደገቡ ተናግሯል፡፡

‹‹ካድሬዎችም ከመረጡ በኋላ የምርጫ ጣቢያውን ለቀው መሄድ ቢኖርባቸውም በምርጫ ጣቢያው ውስጥ ሲዞሩ ይታያሉ፡፡ ታጣቂዎችም በሩ ላይ ይታያሉ፤›› ብሏል፡፡ የኦዶ ሊበን ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ሙሴ አቤቱታውን አስተባብለዋል፡፡ ‹‹ወደ ምርጫ ጣቢያው የገባ ታጣቂ የለም፡፡ ከ500 ሜትር ርቀት ላይ ፀጥታ ለማስከበር የተሰማሩ ፖሊሶች ይኖራሉ፡፡ ምንም የተፈጠረ ችግር የለም፤›› ብለዋል፡፡

በአምቦ ከተማ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የተለያዩ ቦታዎች በምርጫ ጣቢያ አቅራቢያ የክልሉ ፖሊስ አባላት ታይተዋል፡፡ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በር ላይ ፖሊሶችና የአካባቢ ታጣቂዎች ተስተውለዋል፡፡ በአምቦ 03-ለ-1 የምርጫ ጣቢያ (አውራ ጎዳና ግቢ ውስጥ) የታጠቁ የፖሊስ አባላት ተስተውለዋል፡፡

ሌላው ችግር በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርጫ ወረቀቶች ተሟልተው አለመቅረብ ነው፡፡ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ከ5,000 በላይ ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 3,578 ተማሪዎች በመራጭነት ተመዝግበዋል፡፡ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው፣ በእያንዳንዱ ጣቢያ 700 ያህል ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡ በሥፍራው የነበረች የምርጫ አስተባባሪ ዓለም አድነው በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ የምርጫ ወረቀቶች ጉድለት መታየቱን ገልጻለች፡፡ በዚህም ምክንያት 70 ያህል ተማሪዎች በወቅቱ መምረጥ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ አሳውቀው ከአዲስ አበባ የምርጫ ወረቀት እስኪመጣ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ዓለም ተናግራለች፡፡

በድምፅ መስጫ ዕለት የጠነከረ ቅሬታ ያሰሙት ዶ/ር መረራ ናቸው፡፡ ‹‹በተለያዩ አካባቢዎች ታዛቢዎችን በታጣቂ ኃይሎች ተባረውብናል፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ጀልዱ፣ ጨልያና ጅባት በተባሉ ቦታዎች ታዛቢዎች በመባረራቸው ምክንያት ምርጫው የተካሄደው ታዛቢዎቻችን በሌሉበት ነው ብለዋል፡፡

‹‹ታዛቢዎቻችን ላይ ዘመቻ ነው የተካሄደው፡፡ ማስፈራራት፣ በገንዘብ ለመግዛት መሞከር፣ ከዚህ አልፎ አልበገር ያለውን በጠመንጃ የማባረር ተግባር በሰፊው ተፈጽሟል፡፡ የታሰሩና የተደበደቡ ታዛቢዎችም አሉ፤›› ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት አቶ ሁንዴሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አንዳንድ የመድረክ ታዛቢዎች ተገቢውን መረጃ ይዘው ባለመቅረባቸው ከታዛቢነት ተገልለዋል፡፡ ‹‹ከተመዘገበ መታወቂያ ውጪ የተለየ መታወቂያ ይዘው በመምጣታቸው የተከለከሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በምርጫ ቦርድ በታዛቢነት የተመዘገቡ ግለሰቦች ሳይሆኑ፣ ሌሎች ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በታዛቢነት እንዳይገኙ ተከልክለዋል፤›› ብለዋል አቶ ሁንዴሳ፡፡

አያይዘውም አንዳንድ የመድረክ ተወካዮች በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የምርጫ ሕጉ የሚከለክለውን ድርጊት ሲፈጽሙ በመገኘታቸው፣ ከምርጫ ጣቢያዎች እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአንዳንድ ጣቢያዎች የመድረክ ታዛቢዎች የፓርቲውን ምልክት ለሕዝብ ሲያሳዩ በመታየታቸው በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፣ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ባለመቻላቸው ከምርጫ ጣቢያዎቹ እንዲወጡ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሁንዴሳ ከመድረክ የቀረቡትን አቤቱታዎች ለማጣራት መሞከራቸውን ገልጸው አንዳንድ ታሰሩ የተባሉ ግለሰቦች ጉዳዩ ስህተት መሆኑን፣ ሌሎች ደግሞ በግለሰብ ጠብ ታስረው የተፈቱ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር መረራ በበኩላቸው ባቢች፣ ወልሮጌና ጨካ በተባሉ አካባቢዎች በመድረክ ደጋፊዎችና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ፍጥጫ ተፈጥሮ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ከአምቦ አልፎ ሚዳቀኝ በሚባል አካባቢ ግጭት ተፈጥሮ ተኩስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አቶ ሁንዴሳ ይህን በተመለከተ የደረሳቸው ሪፖርት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ቆጠራ

በአምቦ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት በሮቻቸውን ዘግተዋል፡፡ ቆጠራው በሰዓቱ ተጀምሯል፡፡ ሪፖርተር በተገኘባቸው አንዳንድ ጣቢያዎች መድረክና ኢሕአዴግ ብርቱ ተፎካካሪ መሆናቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ቀላል የማይባሉ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ምንም ዓይነት ምልክት ያልተደረገባቸው በመሆኑ ሲመክኑም ታይቷል፡፡ በአምቦ 03-ለ-1 የምርጫ ጣቢያ ቆጠራው ሲካሄድ ሁለት የታጠቁ ፖሊሶች (አንድ ወንድና ሴት) ቆጠራው የሚካሄድበት ክፍል ውስጥ ገብተው የቆጠራውን ሒደት ሲከታተሉ ታይተዋል፡፡ የቆጠራው ሒደት በአንዳንድ ጣቢያዎች እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት ዘልቋል፡፡

ውጤት

የምርጫ ጊዜያዊ ውጤቶች በአምቦና በጉደር ከተሞች ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ መለጠፍ ተጀምሯል፡፡ ሪፖርተር በተገኘባቸው ጣቢያዎች በሮች ላይ ጥቂት ወጣቶች የምርጫ ውጤቶችን ሲያነቡ ነበር፡፡

አቶ ሁንዴሳ በፓርቲዎች አካባቢ የምርጫ ውጤትን አምኖ የመቀበልና ያለመቀበል ሁኔታ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የቆጠራ ሒደቱ ሲጠናቀቅ አንፈርምም ብለው የወጡም አሉ፡፡ ይህን እኛ ምንም ማድረግ አንችልም፤›› ብለዋል፡፡ በምርጫው ማግስት ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የክልሉ ፖሊስ በአምቦ ከተማ የተጠናከረ ጥበቃ ሲያካሂድ ነበር፡፡

Leave a Reply