ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ የባህር ዳር ከተማ ንግድ መደብሮች በጊዜ መዘጋት ጀምረዋል፡፡ በምርጫው ዕለትም የሕዝቡና የተሸከርካሪዎች ተቀዛቅዞ፣ አብዛኛው ሕዝብ በሌሊት ወጥቶ ድምጽ ከመስጠት ውጭ እንደወትሮው በባህር ዳር
ጎዳናዎች ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ተዳክሞ ታይቷል፡፡ በቀድሞው የከተማዋ አስተዳደር በ17 ቀበሌዎች በአሁኑ አስተዳደራዊ መዋቅር ደግሞ በዘጠኝ ክፍለከተሞች የተደራጀችው ባህር ዳር ከተማ፣ ለ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ በከተማው ከሚኖረው ሕዝብ ውሰጥ ድምጽ ለመስጠት ከ92 ሺሕ በላይ ነዋሪ ተዝግቦ ነበር፡፡ የከተማው ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ማስተባበሪያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 86 ከመቶ ያህል የባህር ዳር ነዋሪ ግንቦት 16 2007 ዓ.ም. ድምጽ በመስጠት ተሳትፏል፡፡
ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ወይም በቀድሞው ጊዜ ቀበሌ 03ና 15 የነበሩት፣ ሕዳር 11 ወይም ቀበሌ 11፣ ጣና ክፍለ ከተማ (ቀበሌ 11)፣ ሽንብጥ (ቀበሌ 13)፣ በላይዘለቀ (ቀበሌ 07/08)፣ ሠፈረ ሰላም (ቀበሌ04)፣ ግሽ አባይ (ቀበሌ 12ና 16)፣ ሹም አቦክፍለከተማ (ቀበሌ 10) በሚባሉትና በሌሎችም የተደለደሉ 115 የምርጫ ጣቢዎች ውስጥ ምርጫ ሲካሔድ በዋለበት ዕለትም ሆነ ከምርጫው ዋዜማ በፊትም ቢሆን በሦስት ወገን የሚሰሙ ምርጫውን የተመለከቱ ድምጾች ነበሩ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ገዥው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ኢሕኣዴግና ምርጫ ቦርድ በየፊናቸው በባህር ዳር ሊካሔድ ስላለው ምርጫ ተናግረዋል፡፡
በምርጫው ዋዜማ ፓርቲዎች ምን አሉ
በባህር ዳር ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች መካከል ከምርጫው አስቀድሞ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሰማያዊና የኢትዮጵያውያውን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እንዲሁም የገዥው የብአዴን/ኢሕኣዴግ አመራሮች በፊናቸው የሚሉት አላቸው፡፡
በአማራ ክልል ከተወዳደሩት 16 የፖለቲካ ፓርቲዎችና አንድ የግል ዕጩ አኳያ፣ በሁሉም መስኩ ብኣዴን ፈርጣማ ነበር፡፡ በመላው አማራ ክልል ካቀረባቸው 137 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ባሻገር የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሒድ፣ በጀት ሲመድብ፣ ታዛቢ ሲያሰማራ ወዘተ. ከፍተኛውን የበላይነት ይዞ ነው፡፡ በአንጻሩ የብኣዴን ተፎካካሪዎች በራሳቸው የአቅም ችግርና በገዥው ፓርቲ ደረሱብን ባሏቸው ጫናዎች ከቅስቀሳ እንከ ታዛቢ ማሰማራት ባለው ሒደት ላይ ደካማ ሆነው ታይተዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 51፣ ለክልል ምክር ቤት 82፣ ኢዴፓ ለተወካዮች 56፣ ለክልል 25፣ መኢኣድ፣ ቅንጅት ለተወካዮች 37፣ ለክልል 22፣ አምድነት ለተወካዮች ምክር ቤት 24፣ ለክልል 28 ዕጩ ተመራጮችን ካስመዘገቡ መካከል ናቸው፡፡
ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ ኢዴኣን፣ አገሕዴፓ/ የአገው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ ብኣዴን/ በየ15 ቀኑ በጋራ ይነጋገራሉ፡፡ የባህር ዳር ከተማ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ፈንታ ደጀን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ብኣዴን ኢሕኣዴግ እንደ ፓርቲ የተቃሚዎቹ ተወዳዳሪ ቢሆንም፣ እንደመንግሥት ግን ተወዳዳሪዎቹ ላይ ጫና ይደረግባቸው እንደሆነ፣ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እገዛ ይፈልጉ እንደሆነ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ አቶ ፈንታ ደጀን በባህር ዳር ከተማ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የብኣዴን አመራር ናቸው፡፡ አቶ ፈንታ ለፓርቲዎች ይህንን ማድረጋችን ለዴሞክራሲ ስንል ነው ባይ ናቸው፡፡ ‹‹ይህንን የምናደርግበት ምክንያት ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓትና ለዴሞክራሲ መጎልበት የሚናቸውን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማገባት ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሆኖም በባህር ዳር ምርጫ ክልል በገዥው፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች የተነሱ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው አቶ ፈንታ ከሚጠቅሷቸው ችግሮች መካከል የፖስተር መቀደድ፣ የባነር ማስታወቂያ መነሳት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ያለመጣጣም ‹‹የመገፋፋት››፣ የሥነ ምግባር ደንብ ጥሰት በፓርቲዎች ሲፈጸሙ ነበር የሚሉት አቶ ፈንታ በተለይ አገዴፓ በገበያ ቀናትና በአብያተ ክርሲያናት ውስጥ ቅስቀሳ በማድረጉ ጥሰት ፈጽሟል ብለዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ክሶች ሲቀርቡበት የነበረው አገዴፓ ስህተቶቹን እንዲያርም መደረጉን፣ በጨለማ ስብሰባ ሲያካሒዱ የነበሩ ፓርቲዎች እንደነበሩም አቶ ፈንታ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች በውይይትና በመነጋገር መፈታታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ይልቅ በ2007ቱ ምርጫ ተራማጅ የነበረና ለመንግሥትም ስጋት መሆኑ የታየ ይመስል ነበር፡፡ በአጥፊነት መንግሥት ደጋግሞ ስሙን ሲያነሳው ከርሟል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ አባል አይደለም፡፡ አባል ያልሆነበት ምክንያትም ምክር ቤቱ ላይ እምነት ስለሌው እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሆኖም ሰማያዊን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ፓርቲዎች በባህር ዳር፣ በዘጌ መሸንቴ፣ በዘንዘልማና በጢስ አባይ ዙሪያ የታሰሩባቸው ታዛቢዎችና ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንደነሩ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዴምካራሲያዊ ፓርቲ(ኢዴፓ)ና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በባሕር ዳርና በዙሪያው በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ለተመራጭነት ያቀረቧቸው ዕጩዎችና የምርጫ ታዛቢዎች ላይ ምርጫው ሊካሔድ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ እሥራትና ድብደባ ሲፈጸምባቸው እንደነበር ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የአካባባው ምርጫ አስፈጻሚዎች ችግሩን እንደማያውቁት አስታወቀዋል፡፡
ሻምበል ያየህይራድ ዘለቀ የኢዴፓ ተወካይና በባህር ዳር ምርጫ ክልል ፓርቲያቸውን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ ሻምበል ያየህይራድ በባህር ዳር ከተማ ለሪፖርተር የምርጫ ዘጋቢ እንዳስታወቁት፣ እሳቸው በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልልም ሆነ በባህር ዳር ዙሪያ በሚገኙት ዘጌ መሸንቲ፣ ጢስ አባይ-ዘንዘልማ የምርጫ ክልሎች ውስጥ የኢዴፓ አባላት ላይ እሥራትና እንግልት ተፈጽሟል፡፡ በተለይ በዘጌ መሸንቲና በጢስ አባይ-ዘንዘልማ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለታዛቢነት ተመድበው የነበሩት ሁለት የፓርቲው ተወካዮች አርብ ዕለት ታሥረው በማግሥቱ መፈታታቸውን ገልጸዋል፡፡ በምን ምክንያት እንደታሰሩ እንዳላወቁ ገልጸዋል፡፡ የፖስተሮች መቀደድ፣ የባነር ማስታወቂያዎች መነሳት ሲያጋጥሙ ከነበሩ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ሻምበል ያየህይራድ አስታውቀዋል፡፡ በጎንጂ፣ በቆለላ፣ በአዴት ምርጫ ክልሎች እንዲወዳደሩ ያቀረባቸው ዕጩዎች በምርጫ ቦርድ መሰረዛቸውንና የተሠረዙበት ምክንያትም ለኢዴፓ እንዳልተገለጸት ተናግረዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲም ተመሳሳይ ጫና ሲደርስበት እንደቆየ አስታውቋል፡፡ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዘኖች ያቀረባቸው ዕጩዎች ላይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ለበርካታ ጊዜያት እሥራትና ድብደባ ተፈጽሟል፡፡ በተለይ ሲነን በምትባለው ወረዳ በርካታ አባላቱ ሲታሰሩ እንደነበር አቶ ናትናኤል ገልጸዋል፡፡ በባህር ዳር ምርጫ ክልል እንዲወዳደሩ ካቀረባቸው ሁለት ዕጩዎች አንዱ ተሰርዘው፣ በአንድ አባል ብቻ ለተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር መገደዱን አስታውቀዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የባህር ዳር ጽሕፈት ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ማሩ ዳኜም በርካታ እንግልት በአባሎች ላይ ሲደርስ መቆየቱን ገልጸው፣ ሚዲያው በሚደርስብን በድልና እንግልት ላይ ዝምታን መርጧል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በአገርአቀፍ ደረጃ 200 ዕጩዎች አንደተሰረዙበት ሲገልጽ፣ ኢዴፓ በበኩሉ 90 ዕጩዎች እንደተዘሩበት ይፋ አድርጓል፡፡
የባህር ዳርና ዙሪያው የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች በበኩላቸው ታሠሩ ስለተባሉት የሁለቱ ፓርቲዎች አባላት የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ አቶ ገረመው አሥራት የባህር ዳር ምርጫ ክልል፣ የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ናቸው፡፡ አቶ ገረመው ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ፓርቲዎች በደብዳቤ የደረሱባቸውን ችግሮች ማሳወቅ ሲኖርባቸው፣ ቦርዱ ከሰማያዊም ሆነ ከኢዴፓ በጽሑፍ የደረሰው ምንም ዓይነት አቤቱታ የለም፡፡ በዘጌ መሸንቲ ምርጫ ክልል የምርጫ አስተባባሪዎች ኢዴፓ ታስረውብኝ ነበር ስላላቸው የምርጫ ታዛቢዎች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ ‹‹አንድም ዕጩ ሆነ ታዛቢ ስለመታሠሩ ምንም የመጣ አቤቱታ የለም፡፡ እርግጥ ቀደም ሲል በምዕራብ ጎጃም ውስጥ በምትገኝ አንዲት ወረዳ ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ተይዞ ነበር፡፡ ማንነቱ ሲጠየቅ ዕጩ ነኝ እናንተ ልትጠይቁኝ አይገባም በማለት ግጭት ተፈጥሮ ታስሮ ነበር፡፡ ይሄ ሰው ታስሮ የነበረው በዕጩ ምዝገባ ጊዜ ሲሆን ያኔውኑ ተለቋል፤›› በማለት አቶ ፈንታ ስለፓርቲዎቹ ቅሬታ ከሪፖርተር ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ነበር፡፡ ምርጫው ሊካሄድ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ ዘጌ መሸንቲም ሆነ ጭስ አባይ ላይ አንድም ሰው አልታሰረም ካሉ በኋላ ‹‹የታሠረ፣ የተደበደበ፣ የተሰረዘ እኔ የማውቀው ዕጩ የለም፤›› በማለት በተቀናቃኝ ፓርቲዎች በኩል ለሪፖርተር ያነሷቸውን ቅሬታዎች እንደማያውቋቸው ገልጸዋል፡፡
የፓርቲዎች የዕጩ ተወዳዳሪ ወኪል ታዛቢ መመዝገብ ያለበት የምርጫ ቀን ከመድረሱ አሥር ቀናት በፊት ሲሆን፣ መመሪያ ቀጥር 3/2001 አንቀጽ 19 ላይ በሰፈረው መሠረት ፓርቲዎች ታዛቢዎቻቸውን በማቅረብ እንዲያስመዘግቡ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ምርጫው አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመወከል ለሚገኑ ታዛቢዎች መታወቂያ ሲሰጥ እንደነበር በባህር ዳር ዙሪያ ከሚገኙ ምርጫ አስተባባሪዎች ተገልጿል፡፡
በምርጫው ዕለት ያልታዩት የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ታዛቢ ብቻም ሳይሆን ዕጩዎቻቸውን ማስዝገብና ለምርጫ ማወዳደር እንዳይችሉ መደረጋቸውን ሲገልጹ ከርመዋል፡፡ ያለምንም ማብራሪያ ዕጩዮቼ ተሰርዘውብኛል ካለው ኢዴፓ እስከ ሰማያዊ ፓርቲ በተወዳዳሪ ዕጩ ስረዛ ምርጫ ቦርድን አጥብቀው ሲኮንኑ ከርመዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ 200 ዕጩዎቹ፣ ኢዴፓም ከ90 በላይ ተወዳዳሪዎቹ መሰረዛቸውን በማስመልከት ደጋግመው ሲጠይቁና ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ከከረሙ ፓርቲዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ድምጽ በተሰጠበት ዕለት በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎችን ማየት አልተቻለም፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስለጉዳዩ ሲጠየቁም፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች አንዳልመጡና እንዳላነጋገሯቸው ጠቅሰዋል፡፡ በአንጻሩ የብኣዴን/ኢህኣዴግ ታዛቢዎች በሁሉም የባህር ዳር ምርጫ ክልልና በዙሪያው በሚገኙ ምርጫ ጣቢዎች ሁሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡
የክልሉም ሆነ የባህር ዳር ከተማ ምርጫ አሳታፊነቱና ለሌሎች ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የሰጠው ቦታ ፍትሃዊ ነው ብሎ ብአዴን ያምናል ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ፈንታ፣ ‹‹በአማራ ክልል ለተወካዮች ምክር ቤት 137 ወንበር አለ፡፡ ለክልል ምክር ቤት 292 ወንበር አለ፡፡ ለእነዚህ ወንበሮች ዕጩ የማቅረብ ሥራ ሠርተናል፡፡ እነሱም [ተቃዋሚዎች] ዕጩ የማቅረብ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ቀድመው ያላፈሩትን አባልና ዕጩ በዚህ ወቅት ሊያገኙ አይችሉም፡፡ ይህ ዓይነት ነገር ገጥሟቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ብኣዴን ስለፈለገ ወይም ስላልፈለገ ዕጩ ከማቅረብ የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ እስከሁን በመደበኛ ሁኔታ እየሔድን ነው የነበረው፤›› ብለዋል፡፡
በአንጻሩ ተቃዋሚዎች የሚሰረዙባቸው ዕጩዎች ብቻ ሳይሆኑ ታዛቢዎች መሆናቸውንም ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በባህር ዳር ምርጫ ክልል ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢትጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የታዛቢነት መታወቂያ ከሰጣቸው ከ60 በላይ ታዛቢዎች ውስጥ አብዛኞቹ እንዳልተገኙለት የባህር ዳር ከተማ የኢዴፓ አመራርና ፓርቲውን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት ሻምበል ያየህይራድ ዘለቀ ናቸው፡፡ ሻምበል ያየህራድ የፓርቲው ታዛቢዎች ያልተገኙት በፍርሃት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ሁለት ታዛቢዎች መታወቂያችሁ ላይ ፎቶግራችሁ አልተለጠፈበትም ተብለው ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ ከተወዳደሩባቸውና ጠንካራ ፉክክር ይኖራቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት አካባቢዎች አንዱ የባህር ዳር ዙሪያ ዘንዘልማ ምርጫ ክልል ቢሆንም፣ ሪፖርተር በተገኘበት የዘንዘልማ ሚካኤል ምርጫ ቁጥር 2፣ በብኣዴንና ከሕዝብ ታዛቢዎች እንዲሁም ዘግይተውም ቢሆን ከሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ታዛቢዎች ታይተዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የኢዴፓ ታዛቢዎች በቦታው አልተገኙም ነበር፡፡ በባህር ዳር ምርጫ ክልል ዶክተር በቃሉ አጥናፍና አቶ ወርቁ ጥላሁን የተባሉትን ዕጩዎች በመወከል ከሰማያዊ ፓርቲ የተገኙ የምርጫ ታዛቢዎች ቁጥርም የሉም በሚያስብል መጠን ተገኝተዋል፡፡
በባህር ዳር ምርጫ ክልል ካሉት 115 ምርጫ ጣቢዎች፣ 663 መራጮች የተመዘገቡበት የሰፈረ ሰላም 04-2ለ ምርጫ ጣቢያ የብኣዴን፣ የኢዴፓና የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ታዛቢዎች ተገኝተዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢ አቶ እንደሻው አቤ ‹‹…ችግሮች አይከሰቱም አይባልም፡፡ ጥቃቅን ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ለምሳሌ ለአረጋውያን በድምጽ መስጫ ጣቢያ ውስጥ የድምጽ አሰጣጥ ገለጻ መስጠት ተገቢ ባለመሆኑ ይህ ሒደት ከድምጽ መስጫው ውጭ እንዲደረግ ከብኣዴን፣ ከሕዝብ ታዛቢዎችና ከሲቪክ ማኅበራት ታዛቢዎች ጋር ተነጋግረን እየተስተካከለ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ አቶ ደረጄ ተሾመ የኢዴፓ ዕጩ ተዋወዳዳሪ ታዛቢ ናቸው፡፡ ድምጽ አሰጣጡ ጥሩ አካሔድ ማሳየቱን ገልጸው፣ ሆኖም አረጋውያንን በተመለከተ ከሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አንዳንድ አስገራሚ ክስተቶችንም መታዘብ ተችሏል፡፡ ገነቱ በላይ በሽንብጥ ክፍለከተማ ምርጫ ጣቢያ 1-ሀ-1 አስተባባሪ ናቸው፡፡ በዚህ ጣቢያ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ 851 መራጮች ድምጽ እየሰጡ በነበረበት ዕለት ያልተለመደ አሠራር ሲካሔድ ታይቷል፡፡
በምርጫ ጣቢያው አንድ ወጣት አቅመ ደካሞችና አረጋውያንን እንዲሁም የአካል ጉዳት ያለባቸውን መራጮች ለማገዝ በሚል በምስጢር ድምጽ መስጫ ቦታው አብሮ ሲገባ ታይቷል፡፡ የምርጫ አስተባባሪው የወጣቱን ገለልተኛነት፣ የትኛውንም ፓርቲ ያልወከለና ያልወገነ እንደሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ወጣቱ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ባልተገኘበት ምርጫ ጣቢያ በፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ ታዛቢዎች ወንበር ላይ ተቀምጦ ታይቷል፡፡
ምርጫው መጠናቀቁን ተከትሎ በባህር ዳር ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ከሚጠበቀው 92, 379 መራጭ ሕዝብ ውስጥ 86 ከመቶ ያህሉ ድምጹን መስጠቱን የባህር ዳር ምርጫ ክልል አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል፡፡ በባህር ዳር ከተማ በሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች በሁሉም የምርጫ ውጤቶች መለጠፋቸውም ታውቋል፡፡ እስካሁንም ከየትኛውም ተወዳዳሪ ፓርቲ አንድም ቅሬታም ሆነ ክስ እንዳልደረሳቸው ለጽሕፈት ቤታቸው እንዳልቀረበ የገለጹት በባህር ዳር ምርጫ ክልል የምርጫ አስተባባሪው አቶ ገረመው አሥራት ናቸው፡፡