31 MAY 2015 ተጻፈ በ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ካደረገው የ442 የፓርላማ መቀመጫ ውጤት ውስጥ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ሙሉ ለሙሉ አሸነፉ፡፡ በቦርዱ ጊዜያዊ የውጤት መግለጫ መሠረት፣ በምርጫው የተወዳደሩ ተቃዋሚ

ፓርቲዎች አንድም የፓርላማ ወንበር አላገኙም፡፡ ይህም ውጤት በመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ጊዜያዊ ውጤት ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ ካደረገ በኋላ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል፡፡ የአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትም ወደ ውድቀቱ እየተሽቆለቆለ ነው ብለዋል፡፡ የ2007 ጊዜያዊ የምርጫ ውጤትም ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑን እየጠቀሱ ይገኛሉ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ‹‹በአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር ዋናው ነገር አሠሪ ሕግ መኖሩ ነው፡፡ ይህ ካለ በማንኛውም ጊዜ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊመጣ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የልማት ፖሊሲና አስተዳደር የዶክትሬት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ኢዮብ ባልቻ ግን፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ማለት በርካታ ፓርቲዎች መኖራቸው ብቻ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም በአገሪቷ ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃዋሚና ጠንካራ ሆነው ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት ሥርዓት ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ መብዛት ይልቅም ፓርቲዎቹ የሚንቀሳቀሱበት ተቀባይነት ያለው ሥርዓት መኖሩ ነው ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ማበብ ወሳኝ የሆነው ነገር ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮተ ዓለምን የሚከተለው የኢሕአዴግ ፓርቲ የራሱን ኃይል ሲያደራጅ ቆይታል፡፡ ይህ ገዢ ፓርቲም የአገሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ከመቆጣጠሩም ባለፈ በልማታዊ ትርክት እየተደገፈ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ለዚህ ዓይነት ድል የበቃው ተቃዋሚዎች ለሕዝቡ አማራጭ ሐሳብ ማቅረብ ባለመቻላቸው መሆኑን አቶ ሬድዋን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሕዝቡ ምንም እንኳን ቅሬታ ቢኖረውም፣ ከተቃዋሚዎች የቀረበለት አማራጭ ስለሌለ ከእኛ ጋር መቀጠሉን ያመላከተ ውጤት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ተመራማሪው አቶ ኢዮብ ግን ኢሕአዴግ በየደረጃው የፈጠረው የሕዝብ አደረጃጀት ሕዝቡን ለመቆጣጠር፣ ለማታለል፣ ለመቅጣትና ለመሸለም ዓይነተኛ መንገድ ስለሆነለት ይህንን ዓይነት ውጤት በቀላሉ ሊያገኝ ችሏል ብለዋል፡፡ በፓርቲና በመንግሥት መካከል ያለው መዋቅር ልዩነት የለውም የሚሉት አቶ ኢዮብ፣ የገዢው ፓርቲ ፍላጐት ከሌሎች ማናቸውንም ዓይነት ፍላጐቶች ቀድመው ይታያሉ ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአንድ ለአምስት አደረጃጀት፣ የልማት ሠራዊት አደረጃጀት፣ የወጣት ሊግ፣ የሴቶች ሊግና ሌሎችም አደረጃጀቶች ኢሕአዴግ ምርጫውን እንዲያሸንፍ አስችለውታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሬድዋን ግን ኢሕአዴግ በአርሶ አደሩ፣ በዝቅተኛውና በመካከለኛው ኅብረተሰብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ ማሸነፉን ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በበኩላቸው፣ ‹‹ምርጫው ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረጉት የምርጫ ቅስቀሳና ያቀረቡት የዕጩዎች ብዛት የዚህ ማሳያ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ አሳታፊ የሆነ የውድድር ሜዳ አዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ ውጪ ሕዝቡ ይጠቅመኛል ብሎ ድምፁን የሰጠውን ውጤት ተቀብሎ ማወጅ ነው የምርጫ ቦርድ ሥራ፤›› ብለዋል፡፡ የቦርዱ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አማራጭ ሐሳቦቻቸውን ለሕዝብ ለመግለጽ ያደረጉት ፉክክር፣ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ መኖር አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ፓርቲዎቹ ተወዳድረው ያገኙት ውጤት ሌላው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በምሳሌነት ባቀረቡት የምሥራቅ ሸዋ የምርጫ ውጤት መድረክ 12,834 ድምፅ ሲያገኝ፣ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ 40,357 ድምፅ አግኝቷል ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይህን የዶክተሩን ሐሳብ አይቀበሉትም፡፡ ምክንያቱም ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ያገኙት የድምፅ ልዩነት እጅግ ሰፊ ነው በማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ ተቃዋሚዎች ምንም ድምፅ አለማግኘታቸው ሌላው ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

አቶ ሬድዋን በ2007 ምርጫ ድምፃቸውን ለኢሕአዴግ ያልሰጡትን ዜጐች አሁን ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግርና የመንግሥት አገልግሎትን አሳታፊነትን በማስተካከል በቀጣይ የእነዚህን ዜጐች ድምፅ እንደሚያገኙ እምነት አላቸው፡፡ ተመራማሪው አቶ ኢዮብ ግን ኢሕአዴግ ይህን የማድረግ ብቃቱም ሆነ ፍላጐቱ ስለሌለው፣ ተቃዋሚዎች ጠንክረው በመሥራትና የተሻለ ስትራቴጂ በመከተል የመረጧቸው ዜጐችን የሚያገለግሉበትን መንገድ ሊፈልጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ቦርዱ ባወጣው ጊዜያዊ ውጤት መሠረት በትግራይ ክልል ሕወሓት/ኢሕአዴግ ካሉት 38 መቀመጫዎች 31 ሲያገኝ፣ በአማራ ክልል ካሉት 138 መቀመጫዎች ብአዴን/ኢሕአዴግ 107ቱን ማሸነፍ ችሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ከ178 የፓርላማ መቀመጫዎች 150 ሲያገኝ፣ በደቡብ ክልል ደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ከ123 መቀመጫዎች 95ቱን ማግኘት ችሏል፡፡

በአፋር ክልል አብዴፓ ከስምንት መቀመጫዎች ስድስት አግኝቷል፡፡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ቤጉሕዴፓ ከዘጠኝ መቀመጫዎች ሰባት አግኝቷል፡፡ በጋምቤላ ክልል ጋሕዴን ከሦስት መቀመጫዎች ሦስቱንም አግኝቷል፡፡ በሐረሪ ከሁለት መቀመጫዎች ሐብሊና ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ አንድ አንድ ማግኘታቸውን የቦርዱ ጊዜያዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል ሶሕዴፓ ከ23 መቀመጫዎች 16 አግኝቷል፡፡ በአዲስ አበባ ካሉት 23 መቀመጫዎች ኢሕአዴግ 23ቱን ማሸነፉ ተገልጿል፡፡

ኢሕአዴግና አጋሮቹ በጊዜያዊ ውጤት ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ አስነሳ

Leave a Reply