Wednesday, 27 May 2015 17:47

 

 

መልክ ያለው ሆድ ውስጥ ነው ይባላል። የሰው ልጅ መልክም ሆነ ጤንነት ከሚመገበው ምግብ እንደሚመነጭ ነው ይሄ አባባል የሚጠቁመን። በተለይ በታዳጊ ሀገራት ያለን ሰዎች የምንመገባቸው ምግቦች ረሀባችንን ከማስታገስ በዘለለ የሚሰጡን የጤና ጠቀሜታ ምን ያህል እንደሆነ የመገንዘብ እድሉ ብዙም የለንም። በዛሬው ጤና አምዳችን በአካባቢያችን በቀላሉ የምናገኛቸው እና አብዛኞቻችን የምናዘወትራቸው የምግብ አይነቶች ለሰውነታችን የሚሰጡት የጤና ጠቀሜታ እና ህመምን እንድንቋቋም የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ምን እንደሆነ ይዘን ቀርበናል። እነዚህን መረጃዎች ሀርቨርድ ዩኒቨርስቲ እና ሌሎች የስነ-ምግብ ተቋማት ይዘዋቸው ከወጡት ጥናቶች አጣቅሰን ያቀረብናቸው ሲሆን፤ ለዛሬው ያቀረብናቸውም የምንመገባቸውን ምግቦች ምን ያህል እናውቃቸዋለን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ያግዙናል ብለን እናስባለን።

ሽንኩርት

በየእለት አመጋገባችን ውስጥ ሁላችንም ሳናካትተው የማንውለው ነገር ቢኖር ሽንኩርት ነው። ሽንኩርትን አብዛኞቻችን ለምግባችን ማጣፈጫነት ከመጠቀማችን በተጨማሪ ለጤንነታችን ያለውን ጠቀሜታ ልብ ላንለው እንችላለን። ነገር ግን ሽንኩርት ፀረ ባክቴሪያ፣ እና ፀረ ሴፕቲክ የሆኑ የማቃጠል ባህሪይ ያሉት በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ኢንፌክሽንን የመከላከል አቅም አለው። ሽንኩርት በሳልፈር፣ ፖታሲየም፣ ቫይታሚን ቢ፣ ሲ እንዲሁም በቃጫ (fiber) የበለፀገ የምግብ አይነት ነው። በተቃራኒው ደግሞ የስብ፣ የኮልስትሮል እና የሶዲየም ይዘቱ ዝቅተኛ ነው።

ሽንኩርት ከላይ የተጠቀሱት የንጥረ ነገር ይዘቱ ታዲያ ለተለያዩ የጤና ጥቅሞች እንዲውል አድርጎታል። ከእነዚህ መካከልም ለትኩሳት፣ ለጉንፋን እና ለሳል እንዲሁም ለጉሮሮ ህመም እና ለአለርጂ መድሃኒት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሽንኩርት የእንቅልፍ መዛባትን እና የአፍንጫ መድማትን የሚፈውስ ሲሆን፣ ለምግብ ልመት የሚያገለግሉ ፈሳሾች ከሰውነታችን እንዲመነጩ በማገዝም የምግብ ልመትን ያፋጥናል። ሽንኩርት በሰውነት ውስጥ ኢንሱሊን በብዛት እንዲመረት በማድረግ የስኳር በሽታን የመከላከል አቅም አለው። እንዲሁም የአጥንት መሳሳትን እና የመገጣጠሚያ እብጠትን ይከላከላል። ሽንኩርት የውሃ፣ የፕሮቲን፣ ስታርች እና የተለያዩ ማእድናት ይዘቱ ከፍተኛ በመሆኑ አንድ ሰው ከ100 እስከ 150 ግራም ሽንኩርት እንዲመገብ ይመከራል።

የሽንኩርት የጤና ጠቀሜታ በዚህ የሚያበቃ አይደለም። በሽንኩርት ውስጥ ያሉት ቫይታሚን ኤ፣ ሲ እና ኢ በቆዳችን ላይ የሚያርፈውን የፀሐይ ጨረር እንድንቋቋም በማድረግ በቆዳችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ይከላከሉልናል። ከዚህ በተጨማሪም ቆዳችን ለቡጉር፣ ለባክቴሪያ እና ለኢንፌክሽን እንዳይጋለጥ የማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ሽንኩርት ለሰው ልጅ ፀጉርም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ፀጉር የተፈጥሮ ቀለሙን ይዞ እንዲቆይ የማድረግ፣ ፎረፎር እንዳይዘን እንዲሁም ልስልስ ፀጉር እንዲኖረን ያደርጋል። በአጠቃላይ ቀይም ሆነ ነጭ ሽንኩርት ከማቃጠላቸው ጀምሮ በውስጣቸው ያለው ንጥረ ነገር ከፍተኛ የሆነ የጤና ጠቀሜታ አለው።

አቮካዶ

አቮካዶ ክሬም እና ቅባት ያለው የፍራፍሬ አይነት ነው። አቮካዶ የስነ-ምግብ ይዘቱ ከፍተኛ የሆነ እና 20 ያህል የቫይታሚን አይነቶች ያሉት ነው። የአሜሪካ ብሔራዊ ስነ-ምግብ ተቋም ያወጣው አንድ መረጃ እንዳመለከተው፣ 40 ግራም መጠን ያለው አቮካዶ ብቻ 64 ካሎሪዎች፣ 6ግራም ስብ፣ 4 ግራም ካርቦ ሃይድሬት፣ 3 ግራም ቃጫ (Fiber) እና 1 ግራም ፕሮቲን ይዞ ተገኝቷል። በተቃራኒው ደግሞ ምንም ስኳር ይዘት እንደሌለበት ተገልጿል።

አቮካዶ ከፍተኛ የሆነ ቫይታሚን ሲ፣ ኢ፣ ኬ እና ቢ 6 ምንጭ ነው። በመሆኑም ከመጠን ያለፈ ውፍረትን፣ የስኳር ህመምን እንዲሁም የልብ በሽታን በከፍተኛ ደረጃ የመከላከል አቅም አለው። ከዚህ በተጨማሪም በአቮካዶ ውስጥ የሚገኙት ሊቲየን እና ዚያታንቲን የተባሉ ንጥረ ነገሮች ለአይን ጤንነት በጣም አስፈላጊ ናቸው። በአቮካዶ ውስጥ የሚገኘው ቫይታሚን ኬ በበኩሉ የአጥንታችንን የካልሲየም ይዘት በመጨመር ለአጥንት ጥንካሬ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል። በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው ቫይታሚን ኬ ዝቅተኛ በሚሆን ጊዜ አጥንታችን በቀላሉ ለመሰበር የተጋለጠ ነው። በመሆኑም በቀን ግማሽ አቮካዶን ብንመገብ በቀን ልናገኘው ከሚገባው የቫይታሚን ኬ መጠን 25 በመቶውን እናገኛለን ይላሉ ጥናቶች። በአቮካዶ ውስጥ የሚገኘው ፖቲሲየም ንጥረ ነገርም የደም ግፊትን ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በአቮካዶ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች የልብ እና ከልብ ህመም ጋረ ተያያዥነት ያላቸውን ህመሞች የመከላከል ከፍተኛ አቅምም አላቸው።

አቮካዶን መመገብ በደም ውስጥ ያለውን ስኳር ለማስተካከል፣ የሚመረተውን የኢንሱሊን መጠን ለማመጣጠን እንዲሁም የሰውነት ክብደታችን የተመጣጠነ እንዲሆን ያግዛል። አቮካዶን ስንመገብ በቀላሉ የመጥገብ ስሜት ስለሚሰማን ብዙ ባለመመገብ የሰውነታችን ክብደት የተመጣጠነ እንዲሆን ማድረግ እንደምንችል ጥናቶች ያመለክታሉ።

ቲማቲም

ቲማቲም መሠረታዊ የሆኑ የስነ-ምግብ ጠቀሜታዎችን ከመስጠትም የበለጠ አገልግሎት እንዳለው ነው የስነ-ምግብ ባለሞያዎች የሚገልፁት። ቲማቲም ከስነ-ምግብነት በዘለለም በሽታዎችን የመከላከል እንዲሁም በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች አሉት። ቲማቲም በከፍተኛ ደረጃ በቫይታሚን ኤ፣ ሲ እና ፎሊክ አሲድ የበለፀገ ነው። በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ ክሎሪን፣ ቤታ ካሮቲን እንዲሁም ሊቴን የተባሉ ንጥረ ነገሮች አሉት። በተለይ አልፋ ሊፖኢክ አሲድ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው ግሉኮስ ወደ ሃይል እንዲቀየር በማድረግ የሰውነትን ግሉኮስ የማመጣጠን ስራ ይሰራል።

ቲማቲም ዋንኛው የቫይታሚን ሲ እና አንቲ ኦክሲዳንት ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ የሆነ ካንሰርን የመከላከል አቅም አለው። ይህም የሚሆነው ካንሰርን የሚያመጣውን የሴል ክፍፍል በማስቀረት ነው። ከዚህ በተጨማሪም በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ቲማቲምን በብዛት መመገብ የፕሮስቴት ካንሰርን የመከላከል አቅምን ያዳብራል። ከፕሮስቴት ካንሰር በተጨማሪም በእለት ምግባቸው ውስጥ ቲማቲምን የሚያካትቱ ሰዎች ለሳምባ ካንሰር እና ሆድ ካንሰር የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ቲማቲምን መመገብ በተጨማሪም የደም ግፊትን፣ የልብ በሽታን እንዲሁም የስኳር ህመምን (በተለይ 2ኛ ደረጃውን) የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው። ጭንቀትን ማስወገድ እንዲሁም የሰውነታችን ቆዳ እንዳይጎዳ እና እንዳይደርቅ የማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታም አለው።

ቃሪያ

ቃሪያ በአብዛኛው ቅመማ ቅመም በሚመገቡ ሀገራት የሚዘወተር የአትክልት አይነት ነው። በተለይ በሀገራችን ቃሪያን በጥሬው የምንመገበው ሲሆን፣ ሌሎች ሀገራት ግን ፈጭተው እና በተለያየ መልኩ ጥቅም ላይ ሲያውሉት ይታያሉ። ያም ሆነ ይህ ግን ቃሪያ ለጤናችን የሚሰጠው ጠቀሜታ በርካታ ነው። ቃሪያ አቃጠለም፣ አላቃጠልም የሚኖረው ጠቀሜታ ተመሳሳይ እንደሆነ እና በውስጡ የሚይዛቸው ነገሮችም አንድ አይነት መሆናቸውን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ቃሪያ ምንም አይነት ስብ የሌለው አትክልት ሲሆን፣ በርካታ አይነት ቫይታሚኖች እና ማዕድናት አሉት። ከእነዚህ ቫይታሚኖች መካከል አንዱ ቫይታሚን ሲ ሲሆን፣ ይህ ቫይታሚንም ኢንፌክሽንን የመከላከል፣ ለጥርስ፣ ለድድ እና ለደም ስሮች ጤንነት በጣም ወሳኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቃሪያ ለአይን ጤንነትን፣ ለልብ ህመም እና ለካንሰር ጤንነትም ወሳኝ ነው።

የስነ-ምግብ ባለሞያዎች እንደሚገልጹት ቃሪያ የምግብ ልመትን የማፋጠን፣ እንደ ጉንፋን፣ የጉሮሮ ህመም እና ትኩሳት የመሳሰሉትን ህመሞች የመፈወስ ሃይል አለው። በቃሪያ ውስጥ የሚገኙት ካልሲየም እና ቫይታሚን ሲ የተባሉት ንጥረ ነገሮች ሰውነታችን በቀላሉ በበሽታዎች እንዳይጠቃ ያግዛል። በተጨማሪም ለመገጣጠሚያ ህመም፣ ለጥርስ ህመም እና ለብሮንካይት ችግር እንደመፍትሄ ይወሰዳሉ። የደም ዝውውርን ማስተካከል፣ የኮሌስትሮል መጠንን ማመጣጠን፣ የሆድ ድርቀትን የመከላከል ጠቀሜታም አለው። ከዚህ በተጨማሪም ቃሪያ የሰውነትን ክብደት የተመጣጠነ እንዲሆን ያግዛል።

Leave a Reply