የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከናወነው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ መሠረታዊ የሆኑ ሕገ መንግሥታዊና ሌሎች የምርጫ ሕጎችን በጣሰ ሁኔታ የተከናወነ በመሆኑ፣ ይኼንን የሕግ ጥሰት የሚያጣራ ገለልተኛ የሆነ አጣሪ አካል እንዲቋቋም ጠየቀ፡፡
ፓርቲው ይህን ጥያቄ ያቀረበው ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡
በዕለቱ መግለጫውን የሰጡት የወቅቱ የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲናና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡
‹‹ምርጫው የአገሪቱን ሕገ መንግሥትና ያሉትንም ሕግጋት ሁሉ የጣሰ ነው፡፡ ስለሆነም ወገንተኛ ያልሆኑ ዜጎች ያሉበት ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ፣ በምርጫው ሒደት የተከሰቱት የሕግ ጥሰቶች እንዲያጣራ መድረክ አበክሮ ይጠይቃል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ከምርጫው ዕለት ቀደም ብሎ በከፍተኛ ሁኔታ መሠረታዊ የሕገ መንግሥት፣ የምርጫ ሕግጋትና ሌሎች የሥነ ምግባር ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብለዋል፡፡
ለአብነትም ያህል ሲጠቅሱ፣ ‹‹ለመድረክ 303 የፓርላማ ተወዳዳሪዎችን አዘጋጅተን ያቀረብን ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ ግን ዕውቅና የሰጠልን ለ270 ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱንም የሚያስረዳን አካል አልነበረም፤›› በማለት መድረክ መጉላላት የጀመረው ከምርጫው ዕለት ቀደም ብሎ እንደነበር አውስተዋል፡፡
ሌላው ፕሬዚዳንቱና ሌሎች የመድረክ አመራሮች ያነሱት ነጥብ ደግሞ፣ ከምርጫው ቀደም ብለው የተከናወኑት የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫና የምርጫ ቅስቀሳ በችግር ውስጥ መከናወናቸውን ነው፡፡
‹‹የምርጫው ዕለት ሲቃረብ ደግሞ ዕጩ ተወዳዳሪዎቻችን ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የዘንድሮ ምርጫ የምርጫ ሕጎችን፣ የሥነ ምግባር ደንቦችንና ሕገ መንግሥቱንም ጭምር የጣሰ የምርጫ ሒደትና አፈጻጸም ያሳየ መሆኑን መድረክ ገምግሟል ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ፓርቲው ደርሷል፤›› በማለት አክለው አብራርተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው አመራሮች የታሰሩ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን መንግሥት እንዳፈታ ጠይቀዋል፡፡