ለዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ በትግራይ ክልል በሰባት ዞኖች ውስጥ 38 የምርጫ ክልሎች፣ 1,150,646 ወንድ፣ 4,232,122 ሴት፣ በአጠቃላይ 2,382,768 መራጮች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል፡፡
ከእነዚህ መራጮች ውስጥ 98.3 በመቶ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ድምፅ መስጠታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በክልሉ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረዋል፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ለፓርላማ 38 ለክልል 152 በማቅረብ ሙሉ ተወዳዳሪዎች ይዞ የቀረበ ሲሆን፣ ዓረና/መድረክ ለፓርላማ 28 ለክልል ምክር ቤት 69 ዕጩ ተወዳዳሪዎች በማቅረብ ሁለተኛው ተፎካካሪ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እንዲሁም ኢዴፓ፣ ኢዲሕ፣ ኢፍዴኃግና ኢዴኣን በክልሉ በጥቂት ቦታዎች ዕጩዎቻቸውን በማቅረብ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የምርጫ ጣቢያዎች የዓረና ሁለት ታዋቂ ግለሰቦች፣ ማለትም የትግራይ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አሥራትና የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፣ በመቐለ ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ከአቶ ገብሩ ጋር የተወዳደሩት ታዋቂው የሕወሓት ታጋይ ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ ናቸው፡፡ በሁለቱ የቀድሞ የትግል ጓዶች መካከል ይኖራል ተብሎ የተጠበቀው ፉክክር የሚጠበቅ ነበር፡፡
አቶ ገብሩ አሥራት ለራሳቸው ድምፅ አልሰጡም
በክልሉ አወዛጋቢ ይሆናሉ ተብለው ከተጠቀሱት መካከል አቶ ገብሩ ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደረጉበትና የትውልድ ቦታቸው የሆነው መቐለ ከተማ አንዱ ሲሆን፣ በጋዜጠኞች ድምፅ ይሰጣሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት አቶ ገብሩ ግን ድምፅ አልሰጡም፡፡
አቶ ገብሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል የምርጫ ካርድ በሚወጣበት ወቅት ቀነ ገደቡ ሳይጠናቀቅ የካቲት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚመርጡበት የምርጫ ጣቢያ ካርድ ለመውሰድ በአካል ቀርበው ቢጠይቁም፣ ካርድ አልቋል ተብለው ተከልክለዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል ምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ በላይ በበኩላቸው፣ በወቅቱ ጉዳዩን በተመለከተ ጽሕፈት ቤታቸው የቀረበለት ቅሬታ ባይኖርም፣ ይህንን ሰምተው ለማረጋገጥ ባደረጉት ሙከራ አቶ ገብሩ በአካል ቀርበው ካርድ ለመውሰድ አለመጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ገብሩ ግን ድርጊቱ ሆን ተብሎ እሳቸውን ለማናደድና ለማደናቀፍ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ የምርጫ ጣቢያ (ዘስላሴ እንዷአባ አናንያ) አካባቢ የተወለዱት አቶ ገብሩ ባለፈው አራተኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ በዚሁ አካባቢ ድምፅ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ ከክልሉ የምርጫ አካባቢዎች መካከል የሚዲያ ትኩረት ስበው የነበሩት አክሱምና ዓደዋ ናቸው፡፡ በተከታታይ እነዚህን የምርጫ ጣቢያዎች ገዥው ፓርቲ ህወሓትን ወክለው የሚወዳደሩት የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንትና የሕወሓት ሊቀመንበር አቶ ዓባይ ወልዱና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በአካባቢው ድምፅ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ አቶ ዓባይ ወልዱ በመቐለ ዓዲሐውሲ ድምፅ የሰጡ ሲሆን፣ ዶ/ር ደብረ ጽዮን በአዲስ አበባ ድምፅ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የትውልድ ሥፍራ በዓደዋ የተወዳደሩት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ በተደጋጋሚ ያደርጉት እንደነበረው በአካባቢው ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበረ ቢሆንም፣ የመንግሥት ሚዲያዎችም ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሰው ሲጠባበቁ መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ነገር ግን ሳይመጡ ቀርተዋል፡፡ በአካባቢው ዓረና ትግራይን በመወከል ባለፈው ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የተፎካከሩት ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ በበኩላቸው በመቐለ ከተማ ለክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ ሆነው ነበር የቀረቡት፡፡ አቶ ዓባይ ያለ ተፎካካሪ በአክሱም አካባቢ የተወዳደሩ ቢሆንም፣ በአካባቢው ተገኝተው ድምፅ አልሰጡም፡፡ በዚህም ቅሬታ የተሰማቸው እንዳሉ ታውቋል፡፡
የምርጫው ሒደት
በተለያዩ የክልሉ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ከሌሊት ጀምሮ ወረፋ ይዘው ከንጋቱ 12 ሰዓት ድምፅ መስጠት ጀምረዋል፡፡ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዳላጋጠመ ከክልሉ ምርጫ ቦርድና ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎችም ምርጫው ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ ተጠናቆ ነበር፡፡ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ለመጀመርያ ጊዜ የመረጡ ወጣቶች ነበሩ፡፡
ከስድስት ሰዓት በፊት ሙሉ ለሙሉ ካጠናቀቁት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በሐውዜን ወረዳ የሚገኘው የጉሎ መኸዳ ምርጫ ጣቢያ ይገኝበታል፡፡
ሪፖርተር ተዘዋውሮ በታዘባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የሕዝብ ታዛቢዎች፣ የሕወሓት ወኪሎችና የሲቪክ ማኅበረሰብ የምርጫ ታዛቢዎች ነበሩ፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ዋና ተፎካካሪው የዓረና ፓርቲ ተወካዮች አላስቀመጠም፡፡ ይህንን በማስመልከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ፣ በዓብይ ዓዲ አካባቢ ለፓርላማ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡ ናቸው፡፡ ፓርቲያቸው በታዛቢነት በተለያዩ ቦታዎች የሰየማቸው ግለሰቦች በተለያዩ መንገዶች እንዳይታዘቡ መደረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ አንዳንዳቹ በሃይማኖት አባቶች ተለምነው፣ ሌሎችም ማስፈራሪያ ደርሷቸው በራሳቸው ፈቃድ እንዳይታዘቡ መከልከላቸውንና የተወሰኑትም ለእስራት መዳረጋቸውን ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ ቀደም ሲል በቅስቀሳ ወቅት በተሽከርካሪና በአባላት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች እንደደረሱባቸው ለመገናኛ ብዙኃን ሲገልጽ የቆየው ዓረና ፓርቲ፣ ሕጋዊ ሆኖ በአማራጭነት የቀረበ ቢሆንም በተግባር የተለያዩ የአፈና ድርጊቶች በድምፅ መስጫ ቀንም ጭምር እንደተፈጸሙበት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ አቶ ገብሩ አሥራት ‹‹ታዛቢዎቻችን ታስረውና ተከልክለው ምን ዓይነት ምርጫ ሊካሄድ ይችላል?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች አባላቱ ተባረው መራጮች በቡድን በቡድን በመሆን እንዲመርጡ መደረጋቸውንም ፓርቲው ይገልጻል፡፡
የፓርቲው ቅሬታ የቀረበላቸው የክልሉ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት የሚመለከቱት የፀጥታ ኃይሎችን እንጂ ቦርዱን እንደማይመለከት ገልጸው፣ የዓረናን ታዛቢዎች እንዳይታዘቡ የከለከለ አካል እንደሌለ ግን ተናግረዋል፡፡ በሕጉ መሠረት ከፓርቲው የቀረበላቸው መደበኛ ቅሬታ አለመኖሩንም አስረድተዋል፡፡ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ታዛቢዎች ያለፈቃድ ታዛቢ እንዲሆኑ በዓረና ፓርቲ ስማቸው መተላለፉ አግባብ አይደለም ተብሎ ለጽሕፈት ቤታቸው ቅሬታ ያቀረቡ አስፈጻሚዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ የዓረና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ካቀረቡት አቤቱታ አንዱ፣ ተጠባባቂ ታዛቢዎችን ፓርቲያቸው ቢያቀርብም የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ተቀባይነት እንዳያገኙ ማድረጉን ነበር፡፡
አቶ ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው በተለያዩ አካባቢዎች ችግሩ ያጋጠመ ቢሆንም፣ ‹‹ዓረና በተለያዩ ምክንያቶች ሕጋዊ ግዴታዎቹን ማሟላት አልቻለም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ዓረና ትግራይ በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች ባይኖሩትም፣ በሕዝብ ታዛቢዎች ፊት ምርጫው ተካሂዶ ቆጠራውም ያለ አንዳች እንከን መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የ90 ዓመቷ አዛውንት መራጭ
ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የምርጫ ጣቢያዎች አዛውንቶች፣ ዓይነ ስውራንና እርጉዞች ድምፃቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ወ/ሮ መግበይ መረሳ የተባሉት የ90 ዓመት አዛውንት ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ ድምፅ በሰጡበት የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ በሁለት የልጅ ልጆቻቸው ተደግፈውና ምርኩዝ ይዘው ድምፃቸውን የሰጡት ወ/ሮ መግበይ፣ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ በምርጫ መሳተፋቸውን ይናገራሉ፡፡ በንጉሡ ጊዜ አቶ በርሃ ካሳ የተባሉት ተወካይ ሲቀሰቅሱና ሲወዳደሩ ያስታውሳሉ፡፡
አዛውንቷ እንደሚሉት፣ የአሁኑ ምርጫ የሚካሄደው ሰላምና ፀጥታ በሰፈነበት ነው፡፡ በዚህ ዕድሜያቸው ለመምረጥ የገፋፋቸው ምን እንደሆነ ተጠይቀው፣ ‹‹ውድበይ ክመርፅ መፂአ›› [ድርጅቴን ለመምረጥ ነዋ] ብለዋል፡፡ ‹‹ውድበይ›› የሚል አገላለጽ ብዙዎቹ ሕወሓትን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ ‹‹ወያነ›› በሚል በስፋት የሚታወቀውን አገላለጽ በመወከል ሕዝቡ በስፋት የሚጠቀምበት ነው፡፡ ‹‹ይህንን በማየቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ፈጣሪዬ ዕድሜ ከሰጠኝ በሚቀጥለው ድርጅቴን እመርጣለሁ፤›› በማለት አዛውንቷ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
አዛውንቷ ወ/ሮ መግበይ፣ ባለፉት አምስት ጠቅላላ የምርጫ ዙሮች ድምፃቸውን የሰጡ መሆናቸውን ሲገልጹ፣ በዚያ ምርጫ ጣቢያ ለመጀመርያ ጊዜ ድምፅ የሚሰጡ አፍላ ወጣቶችም ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ወጣት ጽጌ ገብረ እግዚአብሔር አንዷ ናት፡፡ ዘንድሮ አሥረኛ ክፍል ጨርሳ ውጤት አልመጣላትም፡፡ ድምፅ ለመስጠት ያነሳሳት አሁን ያገኘችውን ነፃነት ማጣት ባለመፈለጓ እንደሆነም ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡
‹‹በመሠረቱ ዕድሜዬ ለመምረጥ ደርሷል፡፡ ስለዚህ መብቴን መጠቀም እፈልጋለሁ፡፡ ሠርቼ እንዲያልፍልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ይጠቅመኛል ያልኩትን ፓርቲ መርጫለሁ፤›› ብላለች፡፡ በአሁኑ ወቅት የፀጉር ሥራ ሥልጠና እየወሰደች የምትገኘው ጽጌ፣ ተደራጅታ ለመሥራት ዕቅድ እንዳላት ትናገራለች፡፡ ቤተሰቦቿም የሕወሓት አባላት ሆነው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ጽጌ ዕድሜዋ 18 ነው፡፡ በርከት ያሉ ሌሎች ወጣቶች ድምፃቸውን ለመጀመርያ ጊዜ ሲሰጡ ነበር፡፡
የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁ መጥተው ድምፃቸውን ሲሰጡ የዋሉ ሲሆን፣ ‹‹ሰላም›› በተባለው የምርጫ ጣቢያ ድምፃቸውን የሰጡ ሁለት ሙሽሮችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኢንጂነር ብርሃነ ገብረ አናንያና ወ/ሮ ፍሬሕይወት ታደሰ የተባሉት እነዚህ ወጣቶች የሠርግ ቀናቸውን ከዚሁ ከምርጫ ዕለት ጋር እንዲመቻች አድርገው ማቀዳቸውን ይናገራሉ፡፡
ኢንጂነር ብርሃነ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ‹‹ምርጫ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚደረግ ነው፡፡ የእኛም በሕይወታችን አንድ ጊዜ የሚደረግ ምርጫ ነው፡፡ ድርብ ደስታ ነው የፈጠረልኝ፤›› ብሏል፡፡ ሙሽራዋም በተመሳሳይ ይህንኑ ገልጻለች፡፡ ‹‹የሕይወቴ ምርጫ ከዚህ ምርጫ ጋር መገጣጠሙ ደስ ብሎኛል፤›› ብላለች፡፡
ማጠቃለያ
በመቐለ ከተማ በመዘዋወር ሲታዘብ ሪፖርተር ያገኘነው የዓረና አባል ወጣት ፍስሐ ፀጋዬ በሐውዜን አካባቢ ዓረናን ወክሎ ተወዳድሯል፡፡ በምርጫው ዋዜማ በአካባቢው በፀጥታ ኃይሎች መደብደቡን ይናገራል፡፡ የዓረና ፓርቲ በርካታ ደጋፊዎች አባላት ተደብድበው በምርጫው ዋዜማ ለሕክምና ሆስፒታል መላካቸውን ይናገራል፡፡
የክልሉ ምርጫ ቦርድ ግን የቀረበለት ሕጋዊ አቤቱታ እንደሌለ አስታውቋል፡፡ ዓረና ፓርቲ የሚያቀርባቸው ቅሬታዎች እንዳሉ ሆነው፣ በክልሉ የተካሄደው ምርጫ ያለምንም ችግር ነበር የተጠናቀቀው፡፡ የተወሰኑ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕወሓት በክልሉ መልካም አስተዳደርና ፍትሕ ማስፈን ቢያቅተውም የተገኘውን ሰላም ማጣት አይፈልጉም፡፡ የተሻለ አማራጭ ይዞ የቀረበ ተቃዋሚ ፓርቲም አላገኙም፡፡ አንዳንዶቹም ተቃዋሚ ፓርቲ መረጡም አልመረጡም ውጤቱ ላይ ምን ልዩነት እንደሚፈጥርም ጥርጣሬ አላቸው፡፡ አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ በአንድ የውጭ ድርጅት ውስጥ የሚሠራ ወጣት፣ ‹‹ድምፄን ሰጥቼያለሁ፡፡ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ ግን አያለሁ፤›› ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ጊዜያዊ ሪፖርት መሠረት፣ በትግራይ ክልል ለፓርላማ ከተመደቡት 38 ወንበሮች ሕወሓት 31 ወንበሮችን አሸንፏል፡፡ ሕወሓት ያሸነፋቸው ሪፖርት የተደረገላቸው 31 ምርጫ ክልሎች ቢሆኑም፣ የተቀሩት ሰባት የምርጫ ክልሎች ውጤት አልታወቀም፡