03 JUNE 2015 ተጻፈ በ 

ዘንድሮ በተካሄደው አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ የተሰጠበት ዕለት ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ሪፖርተር ተዘዋውሮ ከታዘባቸው አካባቢዎች መቐለና አቅራቢያው አንዱ ነበር፡፡

በክልሉ ዋና ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበው ዓረና ትግራይ (መድረክ) ሲሆን፣ ተወዳዳሪዎቹና ታዛቢዎቹ ተደብድበውና ታስረው የምርጫ ሒደት እንዳያዩ መደረጉን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ምርጫው እንደተጭበረበረና ውጤቱ ተቀባይነት እንደሌለው አክሏል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የዓረና ትግራይ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዓምዶም ገብረ ሥላሴ (በስልክ)፣ እንዲሁም የክልሉ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ (በአካል) በምርጫው ዕለት አመሻሽ ላይ ከድምፅ ቆጠራው በፊት በአካባቢው ተዘዋውሮ የምርጫ ሒደቱን የታዘበው የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ እንደ ዋና ተፎካካሪ ፓርቲ የምርጫው ሒደት ለእናንተ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ዓምዶም፡– የምርጫው ሒደት አስቸጋሪ ነበር፡፡ በመጀመርያ የዓረና ትግራይ ታዛቢዎች ተባረዋል፡፡ ማስፈራሪያ ደርሷቸው በራሳቸው የወጡም አሉ፡፡ ታስረው ያደሩም አሉ፡፡ የተደበደቡም ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ተቀባይነት የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ የሚያደርገው ማነው?

አቶ ዓምዶም፡– ከየአካባቢው የወረዳ አስተዳደሮች ኃላፊዎችና አንዳንድ የካቢኔ አባላት ታዛቢ አድርገን ያቀረብናቸው ሰዎች ራሳቸውን ከሒደቱ እንዲያገሉ ዘመድ አዝማድና የነፍስ አባቶቻቸውን ይዘው በመምጣት ተፅዕኖ አድርገዋል፡፡ አንዳንዶቹ እሽ ብለው ከሒደቱ ራሳቸውን አግለዋል፡፡ እምቢ ያሉት ይታሠራሉ ወይም ይደበደባሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የት የት አካባቢ ነው እንዲህ የተደረገው?

አቶ ዓምዶም፡- በመላ ትግራይ ነው እንዲህ የተደረገው፡፡ ለምሳሌ እኔ በምወዳደርበት በዓብይ ዓዲ ምርጫ ክልል ያቀረብናቸው ታዛቢዎች በዚሁ መልኩ እንዲያፈገፍጉ አድርገዋቸዋል፡፡ ከዚያም በተጠባባቂነት ያቀረብናቸው ታዛቢዎች ምርጫ ቦርድ አልተቀበላቸውም፣ ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ 

ሪፖርተር፡– ይኼን የተደረገው መቼ ነው?

አቶ ዓምዶም፡- ከምርጫው አንድና ሁለት ቀና በፊት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምን ምክንያት ነው ያልተቀበሉዋቸው? ሕጋዊ መሥፈርቶችን በሙሉ አሟልተዋል?

አቶ ዓምዶም፡- የተለያዩ ሰበብ ይፈጥራሉ፡፡ አንዳንዶቹ መታወቂያ የለህም በማለት፣ ሌሎችም የአባትህ ስም ትክክል አይደለም በሚሉ ሰበቦች ነው የሚከለክሉዋቸው፡፡ ለምሳሌ በዓብይ ዓዲ ምርጫ ጣቢያ ውስጥ ስምንት ታዛቢዎች አሉን፡፡ በደጉዓ ተምቤን አራት ታዛቢዎች ብቻ ነው ያሉን፡፡ በአጠቃላይ ያሉን የምርጫ ጣቢያዎች 57 ሲሆኑ፣ አንዳንዶችም በመሃል ተባረው አሥር ሰዎች ብቻ እየታዘቡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታዛቢዎች አለመኖራቸው በምርጫው ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ አሳድሯል?

አቶ ዓምዶም፡- ታዛቢ ያለውና የሌለው እኩል አይደለም፡፡ በደጋፊዎቻችን ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አለ፡፡ ለነገሩ ታዛቢ ኖረም አልነበረም ለወጉ ነው እንጂ ምንም ልዩነት አይፈጥርም፡፡ ታዛቢዎችን ባሉበትም ከሥርዓት ውጪ ሲፈጸም ሥነ ሥርዓት ቢሉ ምን ቢሉ ማንም አይሰማቸውም፡፡ እያዩም ብዙ ነገር ነው የሚሠራው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ቦታዎች ላይ በአንድ ለአምስት ተደራጅተው የሚመርጡ አሉ፡፡ የምርጫው ዋነኛ ምሰሶ የሆነው ሚስጥራዊነት የለም ማለት ነው፡፡ በአንድ የምርጫ ክልልም በድምፅ መስጫ ቦታ ላይ ተቀምጦ የሚያስሞላ ካድሬ በዓይኔ አይቻለሁ፡፡ ‹‹ለምን?›› ስንል ‹‹እስክርቢቶና ቀለም የሚያቀብል ነው፤›› ብለውናል፡፡

እንዲሁም ሕንጣሎ ዋጅራት በተባለ አካባቢ የቀበሌ አስተዳደሮች ወረቀቱን እየተቀበሉ ሲሞሉላቸው እንደዋሉ አረጋግጠናል፡፡ እንዲያው በራሳችን ነው የምንሞላው ያሉ ወጣቶች፣ ‹‹የለም አትሞሉም›› በመባላቸው መጠነኛ ግጭት ተነስቶ ነበር፡፡ በሑመራ አካባቢ ተወዳዳሪዎቻችን ታስረው ነው የዋሉት፡፡ በውቅሮ ክልተ አውላዕሎ እንዲሁም በመቐለ ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞናል፡፡ በሐውዜንም ተወዳዳሪያችን [በምርጫው ዋዜማ] ተደብድቧል፡፡ አፅቢ ወንበርታ ቋሚ ታዛቢ እያለህ ለምን ተንቀሳቀስክ በሚል አስረውታል፡፡ በቆላ ተምቤንም ወርቅ አምባ በተባለ አካባቢ ታዛቢያችንን አስረውት ነው የዋለው፡፡ በተለይ እዚህ አካባቢ የአካባቢው የምርጫ አስፈጻሚ ተወካይ ‹‹ታዛቢው ትክክል ነው፣ ልቀቁት ይታዘብ›› ቢልም፣ ‹‹አንተ ምን አገባህ?›› በማለት ሳይሰሙት ቀርተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለመሆኑ በቂ ታዛቢዎችና ተወዳዳሪዎች አቅርበናል ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ዓምዶም፡- አዎ፡፡ በቂ ተወዳዳሪዎችና ታዛቢዎች አቅርበን ነበር፡፡ በመላ ትግራይ በቂ ታዛቢዎች አዘጋጅተን ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ግን ታዛቢዎቻችን እንዳይታዘቡ ተደርገዋል፡፡ ምርጫ ተደርጓል ለማለት ይከብዳል፡፡

Leave a Reply