ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩትና መምህራን ትምህርት ኮሌጅን (ፔዳጎጂ) በማቆራኘት የተመሠረተው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ52 ዓመታት ታሪክ አለው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በምርመራ ዘርፍ ለአገሪቱ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችንና
አዳዲስ ንድፈ ሐሳቦችን በማፍለቅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ይነገራል፡፡ በምርምር ያገኛቸውን ውጤቶች በመተግበር የማኅበረሰቡን ችግር በመፍታት አገሪቱ ያላትን እሴቶች በመጠበቅና በማሳደግ የሚጠበቅበትን አገራዊ ተልዕኮ እየተወጣ እንደሚገኝም ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት በአማርኛ ቋንቋ ላይ የተደረጉ የምርምር ውጤቶችን መሠረት በማድረግ በቋንቋው ላይ የሚታየውን ችግር በተግባር ለመፍታት የሚያስችል ‹‹የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም›› (አቋማተ) ዘንድሮ መሥርቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ሥር የተቋቋመው አቋማተ የራሱ አደረጃጀት ያለው ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ያሉት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምሁራን ከምርምሩ ባሻገር ችግሩን በተግባር ለመቅረፍ የሚያስችል ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያስችል ዕውቅና ኃላፊነት ያለው ተቋም መሆኑ በመመሥረቻው ሰነዱ ላይ ተመልክቷል፡፡ የተቋሙን ዓላማና ተግባር ለማስተዋወቅ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በመንፈቀ ሚያዝያ ተዘጋጅቶ በነበረው በዓል ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ ስለዩኒቨርሲቲው፣ ስለመርሑና ስለተቋቋመው ማዕከል ዓላማና ግብ በመድረኩ ላይ የሰጡትን ገለጻ ሔኖክ ያሬድ እንዲህ አጠናቅሮታል፡፡
•ስለዩኒቨርሲቲው
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተ 52 ዓመታት ሆኖታል፡፡ እንደመነሻ የሚወሰደው ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ በሒደታችን ስምንት ግቢዎች ያሉት ዩኒቨርሲቲ ሆኗል፡፡ በመደበኛ የምንቀበላቸው ተማሪዎች 20,000 ሲሆኑ የርቀትን የማታውንና ድኅረ ምረቃውን ጨምሮ በአጠቃላይ 45,000 ተማሪዎች አሉን፡፡ የመምህራኑ ቁጥርም 1,700 ነው፡፡
በምናንቀሳቅሰው የሀብት መጠን ሲታይ በባሕር ዳር በጣም ግዙፉ የሰው ኃይል የሚያንቀሳቅሰው ዩኒቨርሲቲያችን ነው ብለን እንወስደዋለን፡፡ በጀታችንም በከተማው በጀት በእጅጉ የበለጠ ነው፡፡ ስለዚህ ባሕር ዳር ከተማ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው ያለችው የምንለው በየትም ስፍራ ስለሚገኝ ነው፡፡ ከተማውን የመለጠጥ ሥራ ሠርተናል ማለት ነው፡፡ ወደ ፏፏቴው ሲኬድ የሕክምና ኮሌጅ ቁጥር 2፣ ወደ ጎንደር ሲኬድ የግብርና ኮሌጅ፣ ወደ አዲስ አበባ ስትኼዱ የሕግና የቴክኖሎጂ ቁጥር 2፣ ወደ ኤርፖርት ሲኬድ የማሪታይም አካዴሚና የሕክምና ኮሌጅ ቁጥር አንድ ይገኛሉ፡፡
•‹‹ራዕይ ጥበብ 2017››
ተቋሙ አሁን የሚመራበት ሒደት ‹‹ራዕይ ጥበብ 2017›› የሚል ነው፡፡ መልዕክታችን ጥበብ ዓርማችን ቀለማችን ሰማያዊ ነው፡፡ ዕውቀትን፣ ከአካባቢ የተገኘ ልምድን፣ ከመጽሐፍም ሆነ ከሰዎች የተገኘ ዕውቀትና አጠቃላይ ክህሎትን አጣምረን በቀን ተቀን ተግባራችን ስንጠቀምባቸው ጥበብ ይሆናሉ ብለን በመተርጐም፣ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚሰጡ ማንኛውም ሥልጠናዎች ውስጣዊ ለውጥን እንዲያመጡ በማሰብ መርሑን ተጠቅመናል፡፡
•ስለ አማርኛ ማበልፀጊያ ተቋም
የዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ ዕውቀትን መጠቀም፣ መጠበቅ፣ ማስተላለፍ ማዳበር ናቸው፡፡ ይህን ከአማርኛ ቋንቋ ጋር አያይዘን በምናነሳበት ጊዜ አማርኛ ዋነኛ ሀብታችንና መግባቢያችን ስለሆነ ይህንን ቋንቋ የመጠቀም፣ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምበትም የማድረግ ኃላፊነት አለብን ማለት ነው፡፡
ከዚህ አኳያ በእሳቤያችን ያየነው ነጥብ አለ፡፡ በመጠቀም አኳያ አማርኛን በምናይበት ወቅት ተማርን ያልን ሰዎች ሳንቀር ብዙዎቻችንን ዕፀዋትን፣ ለምሳሌ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግቢ ያሉትን በአማርኛ መሰየም የምንችል ስንቶቻችን ነን? ከሣር ጀምሮ ከቅጠል ከአበባ፣ ከዛፍ እያንዳንዷን በአማርኛ መናገር የሚችልስ ስንት ሰው ነው? ያሉትን በርካታ ወፎች እያንዳንዱን መሰየም የሚችል ስንት ነው? በጣና ሐይቅ ከ30 በላይ የዓሣ ዝርያዎች እያንዳንዱን በአማርኛ መሰየም የሚችል ስንት ነው? ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ልጅ የሆነ ፈረስ፣ አባት የሆነ ፈረስ እንዴት ይባላል? ብለን ብናሰፋው ያለብንን እጅግ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ያሳያል፡፡ በኔ በራሴ ልምድ ሳየው ገጠር በነበርኩ ጊዜ ስማቸውን የምጠራቸው ወፎች ናቸው አእምሮዬ ውስጥ ያሉት፡፡ ከተማ ስገባ ያዳበርኩት የጨመርኩት በጣም ትንሽ ነው፡፡ ይኸም ከአጠቃቀም ጋር የተያያዘ አንድ ችግር ነው፡፡
ሁለተኛው ችግር የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞችን ጨምሮ ቋንቋውን መግለጽ የሚችሉ ቃላት እያሉ፣ ባዕድ ቃላትን መጠቀም ይታያል፡፡ በርካታ ተናጋሪዎች ‹‹ፕሪንስፕሉ››፣ ‹‹ወርዶቹ›› ወዘተረፈ የሚሉ ቃላትን በብዛት ወደ አማርኛ እየገቡ ነው፡፡ ከእንግሊዝኛ ተወስዶ በአማርኛ ማባዛት፣ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቅይጥን ጨምሮ በርካታ የአጠቃቀም ችግሮች አሉ፡፡
ስለዚህ ይህ የአጠቃቀም ችግር የአማርኛ ማበልፀጊያ ተቋም እንድናቋቁም ከገፋፉን ነገሮች አንዱ ነው፡፡
•ቋንቋውን ስለመጠበቅ
ሁለተኛው ጭብጥ ቋንቋውን የመጠበቅ ሲሆን ሌላው ሥነ ጽሑፋችንን በተመለከተ በርካታ ጽሑፎች በአማርኛ እየወጡ ነው ወይ? በሌሎች ሙያዎች ለምሳሌ እንደፊዚክስ ያሉ፡፡
የማዳበር ሥራን በምርምርና በትርጓሜ እንዲሁም አዳዲስን ቃላት ከቴክኖሎጂው ጋር ተያይዞ በመተርጐም ይመጣል፡፡ እነዚያ ቃላት በአማርኛ ምን መሆን እንዳለባቸው ወዲያውኑ የመፍጠርና ወደ ማኅበረሰቡ ገብተው ጠቀሜታ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ነው፡፡ እዚህ ጋ በርካታ ነገሮችን እንዳሉ ከውጩ እየወሰድን ነው፡፡ ክፍተት እንዳለ በመረዳት እንደባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መጀመሪያ ሥራ የጀመርነው በወፎች ስያሜ ነው፡፡ እስቲ ቋንቋውን ከማዳበርና ለአካባቢው ጠቃሚ ከመሆን አኳያ ብለን ለዩኒቨርስቲያችን ማኅበረሰብ ማስታወቂያ አወጣን፡፡
በባሕር ዳር ዙርያ ያሉትን ወፎች በአማርኛ አዘጋጅቶ ለሚያቀርብ ዩኒቨርሲቲው በገንዘብ ይደግፋል አልን፡፡ በዚሁ መሠረት አንድ የግብርና ኮሌጅ ተመራማሪ ጽፈውልን፡፡ ለስርጭት በቅቷል፡፡
ሁለተኛው ሥራችን የዓሣዎች ስም እንዲጻፍ ማድረግ ነበር፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የ20ዎቹ የዓሣ ዝርያዎች ስም በሌላ ተመራማሪ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ቢሆንም የመተርጐሙ ሥራ አቅሙ ያላቸው ቢወስዱት ጥሩ ነው፡፡ የአባባሎች፣ የተረት ተረት (ሥነ ቃል) የመሳሰሉት እንዲጻፉ ማስታወቂያ ብናወጣም ሰዎች አልመጡም፣ አልተጻፉም፡፡
ይህ በመሆኑም በሰዎች የማጻፉ ነገር የተወሰነ ርቀት ቢወስደንም በፈለግነው ስፋት ሊወስደን እንደማይችል ስለተገነዘብን የአማርኛ ማበልፀጊያ ተቋም ለምን አናቋቁምም ብለን ተነሣን፡፡ ተቋሙ በዋናነት በዩኒቨርሲቲው ቢቋቋምም በቋንቋ ላይ የሚሠሩ ምሁራን፣ ጸሐፍት፣ ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች፣ ሳይንቲስቶች እየጠራን በየዓመቱ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈ ጽሑፍን የምናከብርበት፣ የምናደንቅበት፣ ዕውቅና የምንሰጥበት፣ በተያያዘ መንገድም ሰውን ወደ ማንበብ የምናመጣበት መድረክ ለምን አናደርገውም በሚል እሳቤ የቋንቋ የማበልፀጊያ ማዕከሉ ተቋቁሟል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሐሳብ ረድቶናል፡፡
•የአማርኛ ሳምንት
የአማርኛ ማበልፀጊያ ማዕከል ይፋ የተደረገበት መድረክ የመጀመርያችን መገናኛ ነው፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ ግን በየዓመቱ የአማርኛ ቋንቋ ሳምንት ብለን በየዓመቱ የምናደርገው ይሆናል፡፡ በዚሁ ዓመታዊ ዝግጅት ለማድረግ ያሰብነው በየትም ቦታ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር በየዓመቱ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ ጽሑፎችን የሚገመግም የሊቃውንት ስብስብ ፈጥረን ብልጫ የሚያገኙ የሚሸለሙበት ይሆናል፡፡
በተለያዩ ዘርፎች በሳይንስ፣ በሕክምና፣ በምሕንድስና፣ በፖለቲካ፣ ምርጥ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እየተባሉ ምርጦቹ ይለያሉ፡፡ በምዕራባውያን የዓመቱ ተመራጭ፣ ተሻጭ ምርጥ መጽሐፍ ብለው የሚያወጡበት ባህል አላቸው፡፡ እኛጋም ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው ሐሳባችን በአማርኛ ወጥነት ያለው ጽሑፍ ሲሆን ሁለተኛው የትርጉም ሥራ ነው፡፡ ሐሳቦች በተለያዩ አገሮች በሌላ ቋንቋ ይጻፋሉ፡፡ እነኚያ ጽሑፎች ወደ አማርኛ ተተርጉመው ሐሳባቸውን ልናውቃቸው ይገባል፡፡ ይህንን የሚያደርጉ ምርጥ ሰዎች ዕውቅና እንዲሰጣቸው እንፈልጋለን፡፡
ሌላኛው ደግሞ ለሕዝብ በተለይ በቀን ተቀን የሚመስጡና በጭውውት፣ በድራማ፣ በቴአትር የሚቀርቡ ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚያ ሥራዎች ቋንቋውን በሚጠብቅ አግባብ የተሠሩትን መርጦ ዕውቅና መስጠት የሚልም ሐሳብ አለን፡፡
በሌላ በኩልም የመገናኛ ብዙኃን የሕትመት ውጤቶችን አወዳድሮ የትኛው ነው ሥርዓት ጠብቆ ያለው በሚል ዕውቅና የሚሰጥበት ይሆናል፡፡
አጠቃላይ እይታችን ይኽ ነው፡፡ የፈረንሣይ ቋንቋን የመጠበቅ ሕግ የሚታወቅ ነው፡፡ ከነርሱ እኛም የምንወስደው ስላለ ጠለቅ ብለን እናስበዋለን፡፡
•ፒኤችዲ በአማርኛ
በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተማሪዎች እስከ ፒኤችዲ ድረስ የመመረቂያ ሥራቸውን በአማርኛ እንዲጽፉ የማድረግ ሐሳብ አለን፡፡ እንዲጽፉም ነግረናቸዋል፡፡ በተለይ በሕግ፣ በማኅበረሰብ ሳይንስ ተጀምሮ ቀስ በቀስ ወደ ምሕንድስና ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ እንዲገባ የሚል ሐሳብ አለን፡፡