-ሰባት አባላቱ ተከላከሉ ተባሉ
አይኤስ በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አረመኔያዊ ግድያ ለማውገዝ፣ መንግሥት ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠርቶ በነበረው የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል›› ከተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ
አባላት መካከል ናትናኤል ያለምዘውድ የተባለው አባል፣ በሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈረደበት፡፡
በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን የወንጀል ክስ ሲሰማ የከረመው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ መናገሻ ወንጀል ችሎት በፍርዱ እንዳብራራው፤ ፍርደኛው ናትናኤል ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አብዮት አደባባይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል፡፡ ‹‹ወያኔ አረደን፣ ኢቲቪ ሌባ›› የሚል መፈክር በማሰማት፣ ከግብረ አበሮቹ ጋር መረበሹንም አመልክቷል፡፡ በፌዴራል ፖሊሶች ላይ ድንጋይ መወርወሩም ተመልክቷል፡፡ የሰዎችና በዕለቱ በሞባይል የተቀረፀ የቪዲዮ ማስረጃ ቀርቧል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮችን ካሰማ በኋላ ናትናኤል ተከላከል ቢባልም መከላከያ ምስክር እንደሌለው በመግለጹ፣ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ እንዳለው በፍርዱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ወገኖች የቅጣት አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቆ፣ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
ተከሳሽ ናትናኤል በሰላማዊ ሠልፉ ላይ ብጥብጥ የፈጠረውን ቡድን መምራቱን፣ በሠልፉ ላይ የተገኙት ብዛት ያላቸው ስለነበሩ ብጥብጡ በፖሊስ ኃይል ባይበተን ኖሮ፣ ውጤቱ የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ብጥብጡ ጠቅላላ ምርጫው ሊደረግ በነበረበት ዋዜማ የተደረገ ስለነበር ብጥብጡ አገር አቀፍ ሊሆን ይችል እንደነበር በመግለጽ፣ ቅጣቱ ከብዶ እንዲወስንለት ዓቃቤ ሕግ የክስ ማክበጃ ሐሳቡን ማቅረቡን ፍርዱ ያስረዳል፡፡
ፍርደኛው ናትናኤል ግን ‹‹ትምህርቴን አቋርጫለሁ፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት እንድጀምር ይፈቀድልኝ፤›› ከማለት ባለፈ ያቀረበው የቅጣት ማቅለያ እንደሌለ ፍርድ ቤቱ ፍርዱን ሲያነብ ተሰምቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ ላይ እንደገለጸው፣ ፍርደኛው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 490 (3) ማለትም፣ ስብሰባን ወይም ጉባዔን የማወክ ጥፋት የተፈጸመው በቡድን ወይም የጦር መሣሪያ በመያዝ ከሆነ፣ ከሰባት ዓመታት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ የሚደነግገውን መተላለፉን ጠቁሟል፡፡ ፍርደኛው መንግሥት በሊቢያ ኢትዮጵያውያን የተፈጸመባቸውን አሰቃቂ ግድያ በተመለከተ ሕዝቡ ሐዘኑን እንዲገልጽና ተቃውሞውን እንዲያሰማ በጠራው ሠልፍ ላይ ድርጊቱን በመፈጸሙ፣ ብጥብጡ የተፈጠረው አገራዊ ምርጫ በሚደረግበት ዋዜማ ከመሆኑ አንፃር ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ቀላል ሊሆን እንደማይችል የሚያመለክት መሆኑን ጠቁሞ፣ የወንጀሉን ደረጃ ከባድ ብሎታል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ፍርደኛው ከግብረ አበሮቹ ጋር በሚል ለማክበጃ የተጠቀመበትን ሐሳብ የወንጀሉ ማቋቋሚያ መሆኑን በመጠቆም፣ ማክበጃውን ውድቅ አድርጐበታል፡፡ ፍርደኛው የወንጀል ሪከርድ የሌለበት በመሆኑ አንድ ቅጣት ተቀንሶለት በሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ማትያስ መኩሪያ፣ ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤ የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና መሳይ የሚባል አንድ ወጣት በተመሳሳይ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ዓቃቤ ሕግ ሁለት የሰው ምስክሮች ካሰማባቸው በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክር ለማቅረብ የፈለጉት እርስ በርሳቸው ለመመሰካከር የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ምስክር መሆን እንደማይችሉ በመግለጽ ሌላ መከላከያ ካላቸው እንዲያቀርቡ አዟል፡፡ የመከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወይንሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ማስተዋል ፍቃዱና ቤተልሔም አካለ ወርቅ በቀረበባቸው ተመሳሳይ፣ ‹‹ሰላማዊ ሠልፍን ማወክና ብጥብጥ ማስነሳት ወንጀል›› የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን በመከላከያ ምስክርነት ለማሰማት ለሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ተቀጥረዋል፡፡