ሰኞ በግእዝ ሰኑይ፣ በዕብራይስጥ ሺኒ ፣ በዐረቢኛ የውመልኢ ሰነይ ትባላለች ። በእንግሊዝኛ ሰንደይ (Sunday) ስትባል ፀሐይ የምትመለክበት እለት ለማለት ሲሆን በፈረንሳይኛ ላንዲ (Lundi) ይሏታል ጨረቃ የምትመለክበት እለት ለማለት ነው።
በመፅሐፍ ቅዱስ የስነፍጥረት አፈጣጠር መሰረት እግዚአብሔር በዚች እለት የፈጠረው አንድ ፍጥረት ጠፈርን (ሰማይ) ብቻ ነው። ከመሬት (አፈር) ጋር ተዋህዶ የነበረውን ውሃ ከሶስት ከከፈለ በኋላ አንደኛውን ባለበት እንዲረጋ አድርጎ፤ ጠፈር (ሰማይ) አለው ፤ ሁለተኛውን ከመሬት ጋር እንደተቀላቀለ (ድፍርስ እንደሆነ) ከጠፈር በላይ አደረገው ስሙም ሐኖስ ይባላል። ሶተኛውንም ከውሃ ጋር እንደተቀላቀለ ከጠፈር በታች ተወው። ዘፍ 1÷6
በሰሙነ ሕማማት በየእለቱ የተደረጉትን ግብራት ስንመለከት፡- ሰኞ፡- ጌታ ቢታንያ ከምትባል መንደር ሲወጣ ይራባል ። ወዲያውም ቅጠሏ የለመለመች በለስ አይቶ ወደ እርሷ ቀረበ፣ ከቅጠልም በቀር ለርሃቡ ማስታገሻ ፍሬን አላገኘባትም፤ረገማት፡፡ በዚህም እለተ ሰኑይ መርገመ በለስ እየተባለች ትጠራለች፡፡ (ማር 11፥14)
በሰኞ እለት ጌታ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዶ ሌላ ድንቅ ስራ አደረገ፡፡ ቤተ መቅደሱ ቤተ ጸሎት ቤተ አምልኮ መሆኑ ቀርቶ መሸጫና መለወጫ (ቤተ ምስያጥ) ሆኖ አገኘው፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት” (ማቴ. 22፥13) ብሎ የሚሸጡትን ገለባበጠባቸው፣ ገርፎም አባረራቸው፡፡
በእንዲህ ያለ ሁኔታ ቤተ መቅደስን ስላጸዳ ሰኞ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ትባላለች፤ ዳግመኛም ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀንም ትባላለች፡፡
ሰኞ በእሑድ እና በማክሰኞ መሀከል የምትገኝ በብዙ አገሮች የሳምንቱ ሁለተኛ ቀን፣ በሌሎች ብዙዎች ዘንድ (ለምሣሌ፦ የአውሮፓ አገሮች) ደግሞ የመጀመሪያ ቀን ወይም እለት ናት።
የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እሑድ በሆነባቸው አገሮችም ጭምር ብዙዎች ሰኞን የመጀመሪያ አድርገው ይወስዷታል። ይህም በአብዛኛው ለብዙ ሰራተኞችና ተማሪዎች ከቅዳሜ እና እሑድ እረፍት በኋላ የመጀመሪያው የሥራ ወይም የትምህርት ቀን በመሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህ እውነታ ሰኞን በአንዳንዶች ዘንድ እንደ መጥፎ ቀን እንዲቆጠር አድርጎታል።
በዚህ አመት የፈረንጆቹ 2015 ዓ/ም ሰኔ 1 (June) ሰኞ ቀን የዋለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ (በግእዝ) ዘመን አቆጣጠርም እንዲሁም ሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ/ም ሰኞ ቀን ውሏል። የግሪጎሪያን የዘመን አቆጣጠር ተጠቃሚ የሆኑት ምእራባውያን የ2015ን ሰኔና ሰኞ የአመቱ 152ኛ ቀናቸው እንደሆነና አመቱን ለማጠናቀቅ 213 ቀናት እንደሚቀሯቸው የተገነዘቡበት እንጂ ሌላ ሳይንሳዊ ወይም ሐይማኖታዊ ትንተና ሳያቀርቡበት ሸኝተውታል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንዶች ዘንድ ሰኔ አንድ ሰኞ ቀን ከዋለ መጥፎ ነው የሚል ምንም ሳይንሳዊም ሆነ ኃይማኖታዊ መሠረት የሌለው አጉል እምነት አለ። “ሰኔና ሰኞ” መነሻው አንድ ሰኞ ቀን በዋለ ሰኔ አንድ ተግባር ላይ በዋለ አዋጅ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል። አዋጁ በኢትዮጵያ ውስጥ መኪና የሚነዳበትን የመንገዱን ክፍል የቀየረ ነበር፤ በመንገዱ በግራ ክፍል መነዳቱ ቀርቶ በቀኝ ክፍል እንዲነዳ የሚያዝ አዋጅ ነበረ። በተፈጠረው ለውጥ ብዙ አደጋ በመድረሱ፡ ከዚያ ጀምሮ ሰኔና ሰኞ ሲገጣጠሙ እንደመጥፎ እድል ይታያል።
ሰኞን ለጊዜው እንተወውና ሰኔ 1 ቀን ግን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የማይረሳ፣ ግድያ፣ ጭፍጨፋ፣ እስራትና ግርፋት የተፈፀመበትና በታሪካችን ከተመዘገቡት ጥቁር ቀናት አንዱ ነው ። ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ/ም !
በምርጫ 97 የመለስ መንግስት: የህዝብ ድምጽ ማጭበርበሩን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ኢትዮጵያውያንን በግፍ የገደለበት፣ ህዝብ በነጻነት ወጥቶ የራሱን መሪ እንዲመርጥ በይፋ ከተቀሰቀሰ ቦኋላ በገጠመው ሽንፈት አፍሮ ኮሮጆ በመገልበጥ አሸናፊነቱን ባወጀ የምርጫ 97 ማግሥት ድምጼ ይከበር ብሎ በሰላማዊ መንገድ አደባባይ የወጣውን ሰላማዊ ሰልፈኛ ያስጨፈጨፈበት 10 ኛ አመት ላይ ደርሰናል ።
የምርጫ 97 ውጤት በመቀልበስ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የፈለገው የኢሕአዴግ አገዛዝ አጋዚ የተባለውን ነፍሰ ገዳይ ጦር በከተማ አሰማርቶ ሰኔ 1 ቀን 1997 የፈጸመው ጭፍጨፋ ፋሽስት ጣሊያን በአገራችን ህዝብ ላይ ከፈጸመቺው የሚተናነስ አይደለም።
በሰኔ አንድ 1997 የጀመረው ግዲያ እስከ ህዳር 1998 ቀጥሎ ከ200 በላይ ንጹሃን ዜጎች ህይወት መቀጠፉና ከሺ በላይ ለአካለ ጉዳተኛነት መዳረጋቸው እንዲሁም ቁጥራቸው ከአንድ መቶ ሺ በላይ የሆኑት ወደ ተለያዩ እስር ቤት ተጉዘው ለአመታት እንዲታሰሩ መደረጉ ተስፋ ተሰንጎበት የነበረውን ሰላማዊ ትግል ጥያቄ ውስጥ የገባበትም ነው ሰኔ አንድ ።
ሰኔ አንድ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሰማእታት መታሰቢያ እለት ነው።
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሰማእታት!