Wednesday, 10 June 2015 11:15
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
- 1 ነጥብ 14 ሚሊዮን የሚሆኑት በምርጫው ተሳትፈዋል፣
- ከ400ሺ በላይ ኢሕአዴግ አልመረጡም፣
- 260ሺ ነዋሪዎች ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል፣
በ2007 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት መሰረት፣ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ 442 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር በማሸነፉ ቀጣዩን የኢትዮጵያ መንግስትን ሥርዓት መንግስት (government) ለመመስረት የሚያስችለውን ውጤት ማግኘቱ ከወዲሁ የተረጋገጠ ሆኗል። ይህን በምርጫ ቦርድ የተገለጸውን ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ከገዢው ፓርቲ ጋር በተቀናቃኝ የፖለቲካ አስተሳሰብ ከተወዳደሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዳንዶች ሲቀበሉት፣ አንዳንዶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ደግሞ የምርጫ ውጤቱን ውድቅ አድርገውታል።
በዚህ ጽሁፍ ሁሉንም የሀገር አቀፍ የምርጫ ውጤቶችን መሰረት አድርጎ ምልከታዎችን ለማስቀመጥ በቂ መረጃዎች እና ጊዜም የሚጠይቅ በመሆኑ ውስንነት አለው። ሆኖም ግን ገዢው ፓርቲ በከተሞች ውስጥ ያለውን የተቀባይነት ስፋትና ጥልቀት በወፍ በረር ለመቃኘት ይረዳን ዘንድ የአዲስ አበባን የምርጫ ውጤት በመጠቀም እንደማሳያነት እንውሰደው። ለአጠቃላይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ግን መረጃው ክፍተት እንደሚኖረው ከግምት በመውሰድ ወደ ዋናው ነጥብ እንሻገር።
አሁን ባለው ጊዜያዊ ውጤት መሰረት በአዲስ አበባ ከተወዳደሩት ሃያ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ማነፃጸሪያት በመውሰድ የተሰላ አቀራረብ መሆኑ ግንዛቤ ቢወሰድ ማሳያነቱ ከፍ ይላል። በአዲስ አበባ ለመምረጥ የተመዘገቡ የነዋሪዎች ቁጥር ብዛት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሲሆን ከተመዘገቡት ነዋሪዎች መካከል ወደ ምርጫ ጣቢያው በመሄድ ድምጽ የሰጡት 1 ነጥብ 14 ሚሊዮን ነዋሪዎች ናቸው። ድምጽ ተዓቅቦ ያደረጉ፣ ባዶ ወረቀት ሞልቶ በኮሮጆ የጨመረ፣ ድምጽ መስጫ ወረቀቱ ላይ ሙሉ ለሙሉ አንድ ትልቅ የኤክስ ምልከት ያስቀመጠ፣ በአንድም በሌላ መልኩ ለማንም የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ ላለመስጠት በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፅ መስጫ ቦታዎች ላይ የኤክስ ምልክት ያደረጉ እነዚህ በአንድ ላይ ሲደመሩ ከተመዘገበው ድምጽ ሰጪ ነዋሪዎች መካከል፣ 264ሺ 560 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ አልሰጡም።
ድምጽ ከሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ኢሕአዴግ 737ሺ 331፣ ሰማያዊ 186ሺ 875፣ መድረክ 145ሺ 416፣ ቅንጅት 24ሺ 382፣ ኢዴፓ 11ሺ 281፣መኢአድ 9ሺ 339፣ አንድነት 7ሺ 271፣ መአሕዴፓ 2ሺ 688፣ ወሕዴፓ 1ሺ 190፣ ኢራፓ 3ሺ 293፣ ኢዴአን 1ሺ 590፣ መኢብን 2ሺ 221፣ ኢፍዴኃግ 848፣ ገሥአፓ 392፣ ኢአዴድ 605፣ ኦብኮ 491፣ መዐሕድ 340፣ ኢስዴፓ 556፣ ዱደብዴፓ 180፣ ኢድህ 310፣ መኢዴፓ 78፣ አብኢፓ 45፣ ሰጎህዴድ 39 እና ትወብዴድ 36 ድምፅ አግኝተዋል።
አጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከነዋሪዎቹ ያገኙት ድምፅ ሲደመር 1 ሚሊየን 144 ሺህ 560 ሲሆን ድምፅ ተሰጥቶባቸው ወይም ባዶ ወረቀት ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ለየትኛውም ፓርቲ ያልተቆጠሩ የባከኑ 4ሺ 560 ድምፆች ናቸው። ኢሕአዴግን ያልመረጡ ነዋሪዎች ቁጥር 407ሺ 229 ናቸው። ሌላው የምርጫ ካርድ ተመዝግበው ወስደው ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ብዛት 260ሺ ነው።
ከላይ የሰፈሩት ቁጥሮች ምን ይነግሩናል?
በ1997 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ በአዲስ አበባ ክልል የሚገኙትን ከሃያ ሶስት የሕዝብ ተወካዮች ወንበሮች ሃያ ሦስቱን ጠቅልሎ የወሰደው በወቅቱ በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ይመራ የነበረው የቅንጅት የፖለቲካ ፓርቲ ነበር። ቅንጅት ድምጽ ለመስጠት ከወጡት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ያገኘው የድምፅ ብዛትም የመራጩን ሕዝብ ከዘጠና በመቶ በላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በወቅቱም ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው ጊዜያዊ ውጤት ቅንጅንት በአዲስ አበባ ማሸነፉን የሚገልጽ ነበር። ገዢው ፓርቲም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምርጫን ቅንጅት ማሸነፉን መቀበሉ ይታወሳል። ሆኖም ግን በክልሎች በተደረገው ምርጫ ገዢው ፓርቲ ማሸነፉን ምርጫ ቦርድ ይፋ ቢያደርግም፣ ቅንጅትና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ውጤቱን አንቀበልም በማለታቸው ነገሮች ወደ አላስፈላጊ ሁኔታዎች ማምራታቸውም የሚታወስ ነው።
በዚህ በ97 ምርጫ በስፋት ይነሳ የነበረው እና በወቅቱም የመገናኛ ብዙሃን የተቆጣጠረው የተቃውሞ ድምፅ “protest vote” የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ ነበር። ይሄውም፣ “A protest vote is a vote cast in an election to demonstrate the caster’s dissatisfaction with the choice of the candidate or refusal of the current political system. In the latter case, protest vote may take the form of a valid vote; but instead of voting for the mainstream candidates, it is a vote in favor of a minority or fringe candidate from the far-right, far-left, or self-presenting as candidate foreign to the political system.”
ከላይ እንደሰፈረው፣ የተቃውሞ ድምፅ የሚባለው መራጩ ሕዝብ ደስተኛ ወይም እርካታ ያጣ መሆኑን በዕጩ ተመራጮች ላይ ወይም ያለውን ስርዓት ባለመቀበል ስሜቱን የሚገልፅበት መንገድ ነው። በተለይ ስርዓቱን ባለመቀበል ከሆነ፣ የተቃውሞው ድምጽ ዋጋ ሊኖረው ይችላል። ይሄውም በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ ዋና ተዋናይ የሆኑትን እጩ ተመራጮችን ወደጎን በማድረግ፣ አነስተኛ የፖለቲካ ውክልና ላላቸው ወይም ጽንፍ የያዘ ፖለቲካ ለሚያራምዱ እንዲሁም ላለው የፖለቲካው ስርዓቱ አዲስ ለሆኑ ኃይሎች የተቃውሞ ድምፃቸውን በመስጠት፣ ድምፃቸው ዋጋ እንዲኖረው ያደርጋሉ።
ከላይ በሰፈረው የተቃውሞ ድምፅ መግለጫ አውድ መሰረት፣ ገዢው ፓርቲ በ1997 ዓ.ም በተደረገው ሀገር ዓቀፍ ምርጫ በተለይ በአዲስ አበባ ቅንጅት ድምፅ ያገኘው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኢሕአዴግ በሰራቸው ስራዎች ባለመርካታቸው የተቃውሞ ድምጽ ለቅንጅት በመስጠት ስለቀጡን ነው ብለው ተከራክረዋል። ቅንጅት ከነበረው የፖለቲካ መሰረት ሆነ ከነበረው የፖለቲካ ተግባር መነሻነት ያገኘው ድምጽ ሳይሆን ሕዝቡ የሰጠው የተቃውሞ ድምፅ ነው በማለት የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተናግረዋል፣ ለማስረዳትም ብዙ ርቀት ሄደዋል። በጊዜውም የተሰጠው ድምፅ የተቃውሞ ይሁን የድጋፍ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው ድምፃቸውን መስጠታቸው ግን አከራካሪ ነጥብ አልነበረም። የ2007 ዓ.ም. የምርጫ ውጤት ግን የተለየ ነው።
በአንፃራዊነት ከአስር ዓመታት በኋላ የተደረገው የ2007 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ አዲስ የመራጮችን ባሕሪ ይዞ ብቅ ብሏል። ይሄውም የምርጫ ካርድ ከወሰዱት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል 260ሺ የሚሆኑት ወደ ምርጫው ጣቢያ ዝርም አላሉም። ወደ ምርጫ ጣቢያ ከወጡት ነዋሪዎች መካከል ድምፃቸውን ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሰጡ ወገንተኛ ሳይሆኑ አምክነዋል። ከእነዚህ ከመከኑት ድምፆች መካከል ባዶ ወይም ምንም አይነት ምልክት ያላረፈበት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ጠቅልለው ወደ ኮሮጆ የጨመሩት የነዋሪዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። አስገራሚው ነገር ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ ምርጫ ጣቢያ ድረስ ሄደው፣ ምልክት አልባ ባዶ የምርጫ ወረቀት ጠቅልለው ሲከቱ ነዋሪዎቹ ምንስ እያሉ ነው? በድምጸ ተአቅቦ ከመኖሪያቸው ካልተንቀሳቀሱት ነዋሪዎች ድምፃቸውስ በምን ይለያሉ? ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ አንሰጥም ያሉ የድምፀ ተአቅቦ ድምፆችን ከተቃውሞ ድምጽ ጋር አንድ አድርጎ መደምደምስ ይቻል ይሆን?
ድምጸ ተአቅቦ ሲባል ምን ማለት ነው? Abstention is simply an act of not voting. It is often considered to be a clear sign of the luck of popular legitimacy and roots of representative democracy, as depressed voter turnout endanger the credibility of the whole voting system. If the protest vote takes a forum of a blank vote, it may or may not be tailed into the final result depending on the rules. Thus, it may either result in spoilt vote or if the electoral system accepts to take it into account, as a ‘none of the above’ vote.
ከላይ እንደሰፈረው ድምጸ ተአቅቦ፣ ድምጽ አለመስጠት ነው። ይህ የሚያሳየው ሕዝባዊ ቅቡልነት እና ስር ያለው የውክልና ዴሞክራሲ መጓደሉን ነው። የተሰላቹ የመራጮች ቁጥር ከበዙም የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል። የተቃውሞ ድምፁ ግን በባዶ የምርጫ ወረቀት በመስጠት የሚገለጽ ከሆነ፣ አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ መኖሩ የሚታወቀው በምርጫው ሕግ ነው። ይህም ሲባል፣ የተበላሸ ድምጽ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ወይም የምርጫ ሕጉ ድምፅ እንደተሰጠ የሚቆጥረው ከሆነ ለማንም የማይደመር ድምጽ ይሆናል።
ከላይ ከሰፈሩት ማሳያዎች አንፃር የተቃውሞ ድምፅ፣ ድምፀ ተአቅቦ እና ምልክት አልባ ባዶ ድምጽ መካከል መሰረታዊ ልዩነቶች እንዳሉ መረዳት ይቻላል። ይህም ማለት 260ሺ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ድምጸ ተአቅቦ አድርጓል። 4ሺ 560 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰጡት ድምፅ ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ያልተደረመ፣ የመከነ ድምጽ ሆኗል። እንዲሁም አጠቃላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ድምጽ አሰጣጥን ስንመለከተው የተቃውሞ ድምፅ አሰጣጥ ተከትሏል ለማለት በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ወጥነት ያለው የድምጽ አሰጣጥ ስርዓትን የተከተለ አይደለም። ከዚህም በላይ፣ ከዚህ በፊት በኢሕአዴግን ስራዎች ያልረኩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተቃውሞ ድምፃቸውን ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሰጡ ነበር የሚለውን አስተሳሰብንም ጥያቄ ውስጥ ከጣሉት አንዱና ዋነኛው ነጥብ፣ 260ሺ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ድምጽ ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጪ መሆኑ ነው። ይሄውም ለተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ ለገዢው ፓርቲ ድምፃችን አንሰጥም፤ ወደ ምርጫ ጣቢያ አንሄድም፣ ብለው ሳይመርጡ ቀርተዋል።
አጠቃላይ የአዲስ አባባን የምርጫ ሂደት ስንደምረው፣ በኢሕአዴግ በኩል የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ፍላጎት ለመመለስ በጣም ረጅም ርቀት እንደሚቀረው ለመገንዘብ በጣም ቀላል የቁጥር ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። ለምርጫ ከወጣው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል 64 ነጥብ 42 በመቶ የነዋሪዎችን ድምጽ ብቻ ነው ማግኘት የቻለው። በአሃዝ ሲቀመጥ 407ሺ 229 ነዋሪዎች አልመረጡትም። እንዲሁም 260ሺ ነዋሪዎች ድምጸ ተአቅቦ አድርገውበታል። ይህ ማለት የ667ሺ 229 ነዋሪዎች ፍላጎት ማርካት አልቻለም። ይህ ማለት ተመዝግበው ድምጽ ከሰጡት እና ተመዝግበው ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉትን ደምረን ለአጠቃላይ ተመዝጋቢዎች ስናካፍለው 47 ነጥብ 66 በመቶ ብቻ የነዋሪዎቹን ድምጽ ማግኘት የቻለው።
ከዚህ አንፃር ኢሕአዴግ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ መሰረታዊ የለውጥ እርምጃዎች መውሰድ ካልቻለ በቀጣዩ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ላይ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ይህ ውጤት አመላካች ነው። በተለይ የኢሕአዴግ የፖለቲካ አመራር ከሕዝብ ጥቅም መነሻነት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ውስጥ ለዘመናት የተከማቹ በኔትዎርክ የተያያዙ አስፈፃሚ አካሎችን በተገቢው መልኩ መፈተሸና መበተን ይጠበቅበታል።
ከተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች አንፃር የአዲስ አበባን የምርጫ ሂደት ስንደምረው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ የምርጫ ክልል ውስጥ ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን ስራዎች አለመስራታቸው ቁጥሮቹ ገላጭ ናቸው። አጠቃላይ ያገኙት የመራጮች ድምፅ 407ሺ 229 ሲሆን ይህ አሃዝ 260ሺ ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉ ነዋሪዎችን አይጨምርም። እንዲሁም እድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ ሆኖም ግን ወደ ምርጫ ምዝገባ ቦታዎች ያልሄዱ ነዋሪዎችንም ታሳቢ ማድረግ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚገባ ነው።
ከዚህ አንፃር ተቃዋሚዎች በአጠቃላይ ድምጽ ከሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ያገኙት 35 ነጥብ 58 በመቶ ሲሆን ተመዝግበው ድምጽ የሰጡ እና ተመዝግበው ድምጸ ተዓቅቦ ካደረጉ ነዋሪዎች መካከል ያገኙት 29 በመቶ ብቻ ድምጽ ነው። ይህ የሚያሳየው ተቃዋሚዎች ከተመዘገበው መራጭ ያላቸውን ርቀት ነው። እዚህ ላይ መነሳት ያለበትም ዋናው ነጥብ በአንድ ቢያንስ በሁለት የፖለቲካ ኃይሎች ሆነው አለመቅረባቸው ሌላው ክፍተታቸው ነው። ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አሁንም በጣም የገዘፈ የቤትስራ እንደሚጠብቃቸው አጠያያቂ አይደለም።
በመጨረሻ የሚነሳው የምርጫ ቦርድ የገለልተኝነት ጥያቄ ነው። በተለይ ከገዢው ፓርቲ ጋር በማቆራኘት የሚነሱትን ቅሬታዎች ከላይ የሰፈሩት ቁጥሮች በራሳቸው ምላሽ ይሰጣሉ። ይህም ሲባል 260ሺ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ወደ ምርጫው ጣቢያ አልመጡም። ድምፅ ከሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ኢሕአዴግ ያሸነፈው 64 ነጥብ 42 በመቶ ሲሆን ከአጠቃላይ ተመዝጋቢ ደግሞ 47 በመቶ ነው። ስለዚህም ምርጫ ቦርድ የተለየ ተልዕኮ ቢኖረው ኢሕአዴግ በዚህ መልኩ ብቻ አሸናፊ አይሆንም ብሎ ማሰብ ስለሚቻል ነው።
ሌላው በመገናኛ ብዙሃን በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተደረገው የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት እና የማኅበራዊ ፍትህ ክርክሮች ሩብ ሚሊዮን የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ፍላጐት ተደራሽ አለማድረጉ በታሳቢነት መወሰድ ያለበት ነጥብ ነው።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
- 1 ነጥብ 14 ሚሊዮን የሚሆኑት በምርጫው ተሳትፈዋል፣
- ከ400ሺ በላይ ኢሕአዴግ አልመረጡም፣
- 260ሺ ነዋሪዎች ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል