Wednesday, 10 June 2015 11:17

 በይርጋ አበበ

     በየሳምንቱ እለተ ቅዳሜ ብቸኛው የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖሊሲ አማራጮቻቸው ዙሪያ የሚያደርጉትን የፖለቲካ ክርክር በቀጥታ ያስተላልፋል። ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ክርክራቸውን ያደርጋሉ። ገዥውን ፓርቲ ወክለው የፓርቲያቸውን ፖሊሲና የፖለቲካ አማራጮች ከሚያቀርቡት የኢህአዴግ የስራ ኃላፊዎች መካከል የሁለቱ ተጎራባች ክልሎች (ኦሮሚያና ደቡብ ክልል) ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝና አቶ ጁነዲን ሳዶ ይገኙበታል። በወቅቱ በቀጥታ ስርጭት ይተላለፍ የነበረውን የፓርቲዎች ክርክር ያዘጋጀው “ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ” የተባለ የሲቪክ ማህበር ነበር። ክርክሩም በጉጉት ይጠብቅ የነበረ ሲሆን በተለይም ለመራጩ ህዝብ የፖለቲካ ግንዛቤ የፈጠረ ነበር ይባልለታል። ይህ ከሆነ ዘንድሮ አስር ዓመት ሞላው የ1997 ዓ.ም ሶስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ።

 

ድህረ 97 ምርጫ

በሶስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሳይታሰብና ሳይጠበቅ የህዝብ ድጋፍ በማግኘት ወደ ስልጣን ለመውጣት ይበልጥ ተጠግቶ የነበረው ቅንጅት “ድምጼን ተቀማሁ” ብሎ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ እና ሰልፉን ለመበተን መንግስት በተጠቀመው የጸጥታ ሀይል መካከል ያልተመጣጠነ እርምጃ መውሰዱ የበርካቶችን ህይወት መቅጠፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። “ከዚያን ጊዜ በኋላ የገዥው ፓርቲ ዋና ትኩረት በምርጫ ዋዜማ ከእሱ ርዕዮተ ዓለም ውጭ የሚያቀነቅኑ የመገናኛ ብዙሃንን (በአገሪቱ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ብቸኛ የግል መገናኛ ብዙሃን የህትመት ውጤቶች ብቻ ሲሆኑ በተወሰነ መልኩ ሶስት የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎችም አሉ) ከውድድር ሜዳው እንዲወጡ ያደርጋል። በዚያው መጠን ደግሞ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንን ለፓርቲው ልሳንነት ይጠቀምባቸዋል። ይህ በመሆኑም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን ወደ ህዝቡ የሚያቀርቡበት መንገድ በሙሉ ዝግ ነው” ሲሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግስት ላይ የሚያቀርቡት አቤቱታ ነው።
በቅርቡ ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ድምጻቸውን ለኢህአዴግ እንደሰጡ የሚናገሩት እድሜያቸው በሰባዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሚገኝ አንዲት እናት ምክንያታቸውን ሲናገሩ “ለመምረጥ ያሰብኩት ሌላ ፓርቲ ነበር (የፓርቲውን ስም እየጠቀሱ) ነገር ግን በ97 እንደሆነው አይነት ግጭት በአገራችን እንዲደገም ስለማልፈልግ ኢህአዴግን መርጫለሁ” ሲሉ ለዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ተናግረዋል።
ከአዛውንቷ መራጭ አነጋገር እንደሚረዳው መንግስት በአገሪቱ ዜጎች ላይ “መጥፎ የስነ ልቦና ጫና መፍጠሩን ያሳያል” ሲሉ የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ ይናገራሉ። አቶ ሙሼ ሰሞኑን ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መንግስት በተለያዩ ዘዴዎች የመራጮችን ድምጽ ለማግኘት ከዘየዳቸው መንገዶች አንዱ በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ሙሼ በተለይ ከምርጫ በፊት “ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ሊጠናቀቅ ይችላል ከማለት ይልቅ ምርጫን ተከትሎ የሚፈጠርን ችግር ሁሉ እቋቋማለሁ ብሎ መናገር ምን ማለት እንደሆነ የቅኔ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም” በማለት መንግስትን ተችተዋል።
ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ (ቪኢኮድ) የሚባለው አገር በቀል የሲቪክ ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ደርሰህ በበኩላቸው “የዴሞክራሲያዊ መንግስት መገለጫዎች ሶስት ናቸው። እነሱም ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ የነቃ ህዝብ (ቫይብራንት) እና ነጻ መገናኛ ብዙሃን ናቸው። እነዚህ በሌሉበት ዴሞክራሲ አለ ማለት አይቻልም። የዘንድሮው ምርጫም ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ነበር ማለት ይከብዳል” ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።

ሲቪክ ማህበራት ሆይ ከወዴት ናችሁ?

በቅርቡ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገውን ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት እንደማይቀበሉ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መግለጫ አውጥተዋል። መግለጫ ካወጡት ፓርቲዎች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በዘንድሮው ምርጫ ነጻ የሲቪክ ማህበራት በታዛቢነት አልተገኙም ሲል አስታውቋል። ምርጫውን የታዘቡትን የሲቪክ ማህበራትም “ኢህአዴግ ራሱ ያደራጃቸውና አባብሎ ወደ ታዛቢነት ያሰማራቸው ናቸው” ሲል መኢአድ የሲቪክ ማህበራትን አስተያየት ውድቅ አድርጓል፡፡ ሰማያዊ ፓቲ በበኩሉ “የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን መታዘብ ያልፈለገው በምርጫው ለውጥ እንደማይመጣ ስለተረዳ ነው። የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድንም ቢሆን የእንጨት ድስት ነው። ምርጫውንም በሚገባ ታዝቧል ብለን አናምንም” ብሏል። ፓርቲው አያይዞም፤የአገር ውስጥ ታዛቢ ሲቪክ ማህበራትም በነጻነት ምርጫውን እንዳልታዘቡ በመግለጫው አስታውቋል።
አገር በቀሉ ሲቪክ ማህበር ቪኢኮድ ግን በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዳላደርግ ያገደኝ ምርጫ ቦርድ እንጅ እኔ ስንፍና ይዞኝ አይደልም ሲል ሊቀመንበሩ አቶ ታደለ ደርሰህ ለሰንደቅ ተናግረዋል። አቶ ታደለ በተሻሻለው አዲሱ የምርጫ ህግ አዋጅ መሰረት አንድ ሲቪክ ማህበር ምርጫውን የሚታዘብ ከሆነ በቅድመ ምርጫው ወቅት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አይሰጥም። ትምህርት የሚሰጥ ከሆነ ደግሞ ምርጫውን መታዘብ አይችልም ብሎ ስለከለከለን የታዘብነው ምርጫ የለም” ብለዋል። አቶ ታደለ አያይዘውም አዲሱ የምርጫ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ግን በ1997 ዓ.ም ለሶስት ወራት በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል የምርጫ ትምህርቶችን የሰጡ መሆኑን ተናግረው በምርጫው እለትም በበርካታ የምርጫ ክልሎች ላይ ድርጅታቸው መታዘቡን ተናግረዋል። በ2002 እና በ2007 ምርጫ ግን መታዘብም ሆነ ማስተማር ተከልክለናል በማለት በዘንድሮው ምርጫ እነሱን ጨምሮ በርካታ ሲቪክ ማህበራት በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ያላደረጉበትን ምክንያት ተናግረዋል።

ምርጫ ቦርድ አቅሙና ገለልተኛነቱ ምን ያህል ነው?

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 102 “የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ” ተብሎ በተደነገገው መሰረት በ1999 ዓ.ም ምርጫ ቦርድን በኃላፊነት እየመሩ ያሉት ፕሮፌሰር መርጋ በቃና የዘንድሮውን ምርጫ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የጽ/ቤታቸውን ገጽታ የሚመለከት መግለጫ ሲሰጡ ተደምጠዋል። የቦርድ ሰብሳቢው በቅርቡ ምርጫው ሊካሄድ ሶስት ቀናት ሲቀረው በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ሆነ ከምርጫው ሶስት ቀናት በኋላ የምርጫውን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ባደረጉበት ወቅት “ቦርዱ የማስፈጸም ብቃቱ በየጊዜው እያደገ መጥቷል። ባለፉትን ምርጫዎች የታዩትን ድክመቶች እንደ ግብአት በመጠቀም ራሱን እያሳደገ ያለ ቦርድ ነው” በማለት ተናግረው ነበር።
የፕሮፌሰር መርጋ በቃናን አስተያየት ግን በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች አስተያየት ሰጭዎች አይቀበሉትም። በፕሮፌሰር መርጋ በቃና አስተያየት ከማይስማሙት አስተያየት ሰጪዎች መካከል የመጀመሪያው ሰው አቶ ሙሼ ሰሙ ናቸው። አቶ ሙሼ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን የማስፈጸም አቅሙ በእጅጉ ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራሉ። አቶ ሙሼ “ነጋዴ በሌለበት ንግድ ሚኒስቴር ማቋቋም ትርጉም የለውም” በማለት ምርጫ ቦርድ የተቋቋመው ነጻና ፍትሃዊ የምርጫ ስርዓት ባልተዘረጋበት ሁኔታ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም ምርጫ ቦርድ የማይከሰስ፣ የማይተችና ጥያቄ የማይነሳበት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙሼ በዚህ ሁኔታ የቦርዱ ገለልተኛነት ሚና ትርጉም ያጣብኛል” ሲሉ መጠይቅ አስቀምጠዋል።
የቦርዱ አባላት በተለይም ኃላፊዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሾማቸውንም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ሲቃወሙ ቆይተዋል። ምክንያታቸውን ሲያቀርቡም የአገሪቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘንድሮውን ጨምሮ በሁሉም ምርጫዎች ያለምንም ተቀናቃኝ የያዘው ኢህአዴግ ነው። በዚህም ምክንያት የራሱን ፈቃድ የሚሞሉለትንና የልቡን የሚያደርሱለትን እንጅ ገለልተኛና ከማንም የማይወግኑ ሰዎችን መሾም አይችልም። በመሆኑም ምርጫ ቦርድ እንደገና በገለልተኛና የማንም ወገንተኝነት በሌላቸው ምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎችና አገር ወዳድ ዜጎች ሊዋቀር ይገባል ሲሉ ደጋግመው ሲናገሩ ቆይተዋል።

የፓርቲዎቹ ቀጣይ እጣ ፈንታና ለአገሪቱ የሚያበረክቱት ሚና

ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው ምርጫ የአሸናፊውን ፓርቲ ማንነት በገለጸበት ወቅትም ሆነ በ2002 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው ውጤት በርካቶች የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ መውደቁን ተናግረዋል። እንዲያውም አንዳንዶች “ይህንን ስርዓት (የኢህአዴግን አስተዳደር) በምርጫ አሸንፎ መንግስት መመስረት የማይታሰብ ነው” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ የምርጫ አዋጁንና ሌሎች የአገሪቱን ህጎች ማሻሻል እንደሚገባ ተናግረዋል። የምርጫ አዋጁና የምርጫ ቦርድ አወቃቀር ካልተሻሻለ በአገሪቱ የሚካሄዱ ምርጫዎችም ሆነ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ አደጋ ላይ ይወድቃል ብለው ይናገራሉ።
መንግስት ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፓርላማ ባይገቡም የፖሊሲ አማራጭ ካላቸው አብረው ሊሰሩ የሚችሉበት እድል እንዳለ ይናገራል። ለዚህም እቅዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቁሞ ያለፉትን አምስት ዓመታት ውይይት ሲያደርጉ መክረማቸው ይታወሳል። በርካታ የተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን “ጥርስ የሌለው አንበሳ” እንደሆነ የሚተቹ ሲሆን ምክንያታቸውም “አንዳችም ፖለቲካዊ ውሳኔ መወሰን አይችልም” ሲሉ ይናገራሉ። የጋራ ምክር ቤቱ  አባል የሆኑ ፓርቲዎችም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት እንዳለፈው ጊዜ በምክር ቤቱ ብቻ የተወሰነ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደማይገባ ኢዴፓ ገልጿል።
በቅርቡ የጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ “የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በፓርላማ ወንበር ባይኖራቸውም አገር የሚለውጥ ሀሳብ እስካመጡ ድረስ ገዥው ፓርቲ አብሯቸው ለመስራትዝግጁ ነው” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

Leave a Reply