ከሁለት ዓመት በፊት በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት ከመንግሥት ሚዲያና ሕዝብ ከሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች ለረዥም ጊዜ ርቀው ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡም ቢሆን፣ ሕመሙ የፈጠረባቸው መጎሳቆል በግልጽ ይታይ ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን በአስመራ ስታድየም በተሰበሰበው ሕዝብ መሃል የተገኙት ለመጀመርያ ጊዜ ሙሉ ልብስ በመልበስ ነበር፡፡ ፊታቸው ላይ ደስታ ቢጤ የሚነበብባቸው እሳቸው ብቻ ይመስላሉ፡፡ እኚህ ግለሰብ የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው፡፡
በበዓሉ ላይ የታደመው ሕዝብ ሲታይ ግን ወጣቱ እንዳይገኝ የተከለከለ ይመስል በዕድሜ የገፉና መጎሳቆል የሚታይባቸው አዛውንቶች በብዛት ይታያሉ፡፡ ‹‹አስመራ ውስጥ ወጣት የለም እንዴ?›› የኤርትራ ቴሌቪዥን ጣቢያን በመመልከት ላይ የነበረ የአንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት ጥያቄ ነበር፡፡ አብረውት የነበሩት ሰዎች ለዚህ ጥያቄ መልስ ሳይሰጡ ጠያቂውን ወጣት ብቻ አየት አድርገው በቀጥታ ለበዓሉ ማድመቂያ ሲተላለፍ የነበረውን ዘፈን ማዳመጥ ቀጠሉ፡፡
ኤርትራውያን የነፃነት ቀናቸውን የሚያከብሩበት 24ኛው ዓመት ነው፡፡ ‹‹ነፃነት? ወይስ ባርነት?›› የሚል አማራጭ የቀረበለት ቢሆንም፣ የኤርትራ ሕዝብ ከሞላ ጎደል ከኢትዮጵያ ነፃነቱን ነበር የመረጠው፡፡ በኤርትራ ውስጥ ከሚከበሩት ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ በዓላት አውራው ይህ ነው፡፡ ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኤርትራ መርማሪ ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ግን፣ የወጣቱን ጥያቄ የሚመልስ ይመስላል፡፡ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት እየወደመች ካለችው ሶሪያ ቀጥላ፣ በዓለም ቁጥር አንድ ወጣት ዜጎቿ ወደ ስደት የሚጎርፉባት አገር መሆኗን ተመድ አረጋግጧል፡፡
ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት 484 ገጾች አሉት፡፡ ይኼው ሪፖርት በኤርትራ ባለፉት 24 ዓመታት የተፈጸመውና አሁን በመፈጸም ላይ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ከወጡ ሪፖርቶችና ወቀሳዎች የላቀና ሰፊ ይዘት ያለው ይመስላል፡፡ ኮሚሽኑ ወደ ኤርትራ ገብቶ የተሰጠውን የቤት ሥራ ለመሥራት ያቀረበው ጥያቄ በአስመራ መንግሥት ተቀባይነት በማጣቱ ወደ ኤርትራ መግባት ያልቻለ ቢሆንም፣ ከኤርትራ በተለያዩ ጊዜያቶችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ 550 ኤርትራዊያንን ስደተኞች ጋር በተደረጉ ቃለ ምልልሶች የተገኙ መረጃዎችን በሪፖርቱ አካቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 100 ሴቶች ሲሆኑ፣ ከ160 በላይ የጽሑፍ ማስረጃዎችና ሰነዶችም ተጠቅሟል፡፡
በኤርትራ መንግሥት የታቀደውና እ.ኤ.አ. በ1997 የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ውስጥ የሰፈሩት የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እሴቶች እንዴት እንደተደፈጠጡ፣ እንዲሁም የአገሪቱ ዜጎች እንዴት የስቃይ፣ የሞትና የእስራት ሰለባ እንደሆኑ ሪፖርቱ ያትታል፡፡
‹‹የጅምላ ጭፍጨፋ››
ሪፖርቱ እንደሚለው የኤርትራ መንግሥት በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸው የሰብዓዊ መብት ጥቃቶች ሆን ተብሎና ታስቦበት የሚደረጉ ናቸው፡፡ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸም የጅምላ ጭፍጨፋ ተደርጎ እንደሚወሰድም ኮሚሽኑ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ራሱን ወደ ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (ሕግደፍ) ብሎ ይቀይር እንጂ፣ በመጀመርያዎቹ ዓመታት ቃል የገባቸው የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ነፃነቶች መሸርሸር የጀመረው ከመነሻው እንደሆነም ሪፖርቱ ያትታል፡፡ የማሻሻያ ጥያቄ ያነሱትን ግለሰቦች (ቡድን 15) እና ነፃ ጋዜጠኞች አስሮአቸው እስካሁን የገቡበት አይታወቅም፡፡ በሦስቱም የመንግሥት አካላት ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይኖር አስፈጻሚው፣ ሙሉ ለሙሉ ራሱን ወደ ፈላጭ ቆራጭነት የቀየረ ሲሆን፣ ሕግ ተርጓሚውም ሆነ ሕግ አውጪው (ማን እንደሆነ አይታወቅም) ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥሩ ሥር እንደዋለ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በአብዛኛው የአስፈጻሚው ሥልጣንም በፕሬዚዳንቱ ላይ የተከማቸ እንደሆነ ያጠቃልላል፡፡
ሪፖርቱ ወደ ዝርዝር ውስጥ ሲገባ፣ ሕግደፍ (ሻዕቢያ) በቁጥራቸው በጣም የበዙ ሰላዮች ሕዝቡ ውስጥ በማስረግ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ሳይቀር አንዱ ሌላውን እንዲሰልለው በማድረግ፣ ያለአንዳች የሕግ ድጋፍ በሆነ ምክንያት የተጠረጠሩትን ማሰርና ዕርምጃ መውሰድ የተለመደ ተግባር እንደሆነ ያትታል፡፡ የዚህ ዓይነት አሠራርም በሰፊው ዘርግቷል ይላል፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ተግባራዊ ባለመሆኑ ምክንያት፣ የሚወጡት ሕጎች በዘልማድ የሚታወጁ እንጂ ምንም ዓይነት ሕግ አወጣጥ ሒደት የተከተሉ ባለመሆናቸው፣ የዜጎችን ግለሰባዊ መብቶች ለመደፍጠጥ የተመቸ መሆኑንም የኮሚሽኑ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ሕግ ተርጓሚውን በተመለከተ ዳኞች የሚሾሙት፣ የሚቀየሩትና የሚሻሩት በቀጥታ በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ እንደሆነ፣ ሥራቸውንና ውሳኔያቸውን በጦር አዛዦችና በፓርቲው አመራሮች በቀጥታ በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ላይ ተመሥርተው እንደሚያከናውኑ የኮሚሽኑ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡ ፍርድ ቤቶችን በበላይነት የሚቆጣጠር ምንም የሕግ ዕውቀት በሌላቸው የጦር አዛዦች በበላይነት የሚመሩት ልዩ ፍርድ ቤት መኖሩንም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
‹‹በአጠቃላይ ኤርትራዊያን ሕይወታቸውን እንኳን በራሳቸው የሚመሩበት ማኅበራዊ ነፃነት የላቸውም፤›› የሚለው የኮሚሽኑ ግኝት፣ ራሳቸውን በነፃነት የሚያስቡበት፣ የሚገልጹበትና የሚንቀሳቀሱበት ድባብ እንደሌለ ያስረዳል፡፡ ‹‹ማወቅ ያለባቸውና የሌለባቸው መረጃ ጭምር በመንግሥት ይወሰንላቸዋል፤›› የሚለው ሪፖርቱ፣ ‹‹ሌላው ቀርቶ ግለሰቦች ራሳቸውን በፍርኃት ማጥ ውስጥ በማስገባታቸው በነፃነት ማሰብ እንኳን አይችሉም፡፡ አንደኛው ሌላኛውን አያምንም፡፡ ቤተሰባቸውንም ጭምር፤›› ይላል፡፡
አንድ ግለሰብ ለአጣሪው ኮሚሽን እንዳለው፣ ‹‹ኤርትራ ውስጥ ሳለሁ ምንም ነገር ማሰብ እንደሌለብኝ ይሰማኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰዎቹ የማስበውን የሚያነቡ ስለሚመስለኝ በመፍራት ነው፡፡››
ተቃውሞ ያስነሳሉ ወይም የሆነ የተለየ አስተሳሰብ ያንፀባርቃሉ ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ለእስር እንደሚደረጉ፣ እንደሚሰወሩና አንዳንዶቹም የት እንደገቡ ሳይታወቅ እንደሚጠፉ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ እንደ ኮሚሽኑ ግኝት ማን የት እንደገባ፣ ለምን እንደተሰወረም መረጃ መጠየቅ ነውር ነው፡፡ ችግር ውስጥ ይከታል፡፡
በእስር ላይ ያሉ ግለሰቦች ለድብደባ፣ ለስቃይና ለተለያዩ ኢሰብዓዊ ጥቃቶች ከመጋለጣቸውም በተጨማሪ፣ በተለይ ሴቶች የተለያዩ ፆታዊ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ ማን ለምን ታሰረ ብሎ የሚጠይቅ ፍርድ ቤት አለመኖሩን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በአገሪቱ ቁጥራቸው የበዙ እስር ቤቶች ውስጥ አሉ፡፡ ታሳሪዎች እጅግ አሰቃቂ ለሆኑ ሰብዓዊ ጥቃቶች የተጋለጡ ናቸው፡፡ በጨለማ ታጉረው የሚውሉና ከማንም ጋር የማይገናኙ ቁጥራቸው የበዛ ዜጎች እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡
በተለይ ከአገራዊ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዜጎች፣ በተለያዩ መንገዶች ለከፋ ስቃይ እንደተዳረጉና ጠያቂም እንደሌላቸው በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ እንዲሰጥ የሚጠበቅበት ወታደራዊ ግዳጅ በጊዜና በመጠን ያልተወሰነ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ሙሉ ለሙሉ የሚጥስ ነው ይላል ሪፖርቱ፡፡
የአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ፣ ለወታደራዊ ግዳጅ የሚሰጠው አገልግሎት ከባርነት የማይተናነስ ነው፡፡ ሴቶችና ልጃገረዶች ለተለያዩ ዓይነት ፆታዊ ጥቃቶች እንደሚጋለጡ፣ ከወታደራዊ ካምፖች ለማምለጥ የሞከሩና በቁጥጥር ሥር የዋሉት በተለይ፣ የማይደርስባቸው ዓይነት ቅጣትና ስቃይ እንዲሁም የነፃነት መገፈፍ የለም ይላል ኮሚሽኑ፡፡ እንዲሁም ለራስ መቻል (Self-sufficiency) መርህ ሲባል ኤርትራዊያን ዜጎች ምንም ሳይከፈላቸው በነፃ ጉልበት በግዳጅ እንዲሠሩ ይደረጋልም ይላል፡፡
አገር ውስጥ ባለው እጅግ ውስብስብና አሳሳቢ የዜጎች ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ረገጣ መብዛት፣ ኤርትራዊያን የቀራቸው አገራቸውን ጥለው መሰደድ ብቻ እንዳደረገም አመልክቷል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው በእያንዳንዱ ወር በአማካይ አምስት ሺሕ ኤርትራዊያን ወደ ጎረቤት አገሮች የሚኮበልሉ ሲሆን፣ በተያዘው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በተገኘው መረጃ በኢትዮጵያ 106,859፣ በሱዳን 109,594 የኤርትራ ስደተኞች በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ እ.ኤ.አ. በ2014 ግማሽ ዓመት አካባቢ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ይፋ እንዳደረገው በችግር ላይ የወደቁ የኤርትራውያን ቁጥር 357,406 ነበር፡፡
የኤርትራ መንግሥት አገር ጥሎ መውጣትን በወንጀልነት በመፈረጁ በዚህ መሠረት ድንበር አካባቢ የተገኘ ያለምንም ጥያቄ የሚያስገድል ሕግ ማውጣቱንም ሪፖርቱ አካቷል፡፡
በመሆኑም ወደ አውሮፓ አገሮች ሲሻገሩ በየየብሱና በየባህሩ ሕይወታቸው የሚያልፈው ኤርትራዊያን በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሲሆኑ፣ በባህር ጠረፎችና በድንበር አካባቢ በወታደሮች የሚገደሉም ቁጥር ሥፍር የላቸውም ይላል ሪፖርቱ፡፡
በአጠቃላይ አጣሪው ኮሚሽን በኤርትራ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ባለው ሁሉም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚ ተቋማት መካከል የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ ደኅንነት ቢሮ፣ የኤርትራ ፖሊስ ኃይል፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ ገዥው ድርጅት ሻዕቢያ፣ ፕሬዚዳንቱና የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት በዋናነት ተጠያቂ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ እንደሚለው በሕገወጥ በተዘረጋው ሰንሰለት መሠረት የሚገኘው መረጃ ሕዝቡ እጅግ ጥልቅ በሆነ ፍርኃትና ድንጋጤ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ ‹‹It Is Not Law That Rules Eritreans, But Fear›› [ኤርትራዊያኑን የሚገዙት በሕግ ሳይሆን በፍርኃት ነው] ይላል በድምዳሜው፡፡
አጣሪው ኮሚሽን በምክረ ሐሳቡ የኤርትራ መንግሥት ዜጎችን በፍርኃት ድባብ ከመግዛት ወጥቶ ሰብዓዊ መብቶች እንዲያረጋግጥ ተገቢነት ባለው የሕግ አግባብ እንዲሠራ፣ አግባብነት ያለውና ነፃ የፍትሕ ተቋም እንዲያቋቁምና እንዲሁም ዜጎች ከመግደልና ከማሰቃየት እንዲቆጠብ ያሳስባል፡፡ የት እንዳሉ ያልታወቁ ግለሰቦች ያሉበት እንዲታወቅና ከዚህ ሁሉ ፈላጭ ቆራጭ ድርጊቱ እንዲቆጠብም ይጠይቃል፡፡ ተመድና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የኤርትራ መንግሥት በኤርትራ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ጅምላ ጭፍጨፋ በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ መሆኑን አውቀው አስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወሰዱም ይጠይቃል፡፡
ኮሚሽኑ በማጠቃለያው የኤትርትራ መንግሥት በሕዝቡ ላይ የሚፈጽመው ሥፍር ቁጥር የሌለው የሰብዓዊ ጥቃት እንደማስተባበያ የሚጠቀምበት የአገር ሉዓላዊነት መሆኑን ጠቁሞ፣ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ችግር በድርድር እንዲፈታም ጠይቋል፡፡
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጣሪ ኮሚሽኑ ያወጣውን ሪፖርት በመቃወም መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ ‹‹መሠረት የሌለው የፖለቲካ ጥቃት›› ብሎታል፡፡ ሚኒስቴሩ እንደሚለው፣ ሪፖርቱ የኤርትራ ሉዓላዊነትንና የሚታዩ ለውጦች ላይ የተቃጣና ኤርትራን ለማተራመስ እንደ ሽፋን የተቀመጠ መሣሪያ ነው፡፡
አምኒስቲ ኢንተርናሽናል ቀደም ሲል ባወጣው ሪፖርት፣ በኤርትራ ውስጥ ከአሥር ሺሕ በላይ የህሊና እስረኞች መኖራቸውን የጠቆመ ሲሆን፣ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር በበኩሉ ነፃ ፕሬስን በመደፍጠጥ ኤርትራን በቁጥር አንድ ማስፈሩ ይታወሳል፡፡