(ኢ.ኤም.ኤፍ) በመንግስት የተደገፈው ጥቁር ሽብር በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ነው። አሁን ደግሞ… የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነውን ወጣት ሳሙኤል አወቀን በመግደል፤ ኢህአዴግ ራሱን ወደለየለት አምባገነን ስርአት ተቀይሯል።ሳሙኤል በምስራቅ ጎጃም ለፓርላማ እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ በቅርቡ ምርጫ ውስጥ ከተሳተፈ በኋላ፤ “እንገድልሃለን” የሚሉ ማስፈራሪያዎች ደርሰውት ነበር። ስለዚሁ ጉዳይ በቅርቡ ይህን ብሎነበር – ሳሙኤል አወቀ።የሳሙኤል አወቀ የአደራ ቃል~ውድ የደብረማርቆስ ከተማ ኗሪዎች ፤ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ከ25’0000 በላይ መራጮች(ኮረጆውን) እርሱት እና በተጨማሪም በ31 ዩኒቨርስቲ የምትገኙ ከ14,000 በላይ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ሌሎች ደጋፊዎች እና የኢሕአዴግ አባላትም የማያፍረው ብአዴን / ኢሕአዴግ ድምፅ መቀማቱ ሳያንስ በ21/08/2007 ዓም አፍነው ደብድበው ከሞት መትረፌ ቆጭቷቸው እሰር ቤት ለመወርወር ያለመከሰስ መብቴን እንኳን ተዳፍረው የሀሰት ክሰ እየፈጠሩ ነው!!!” በስልኬ እደተደወለም ያለፍላጎቴ ደሕንነት እያስገደደኝ ይገኛል!! ተገደልሁም ታሠርሁም ፤ ታፈንኩም ነፃነት አይቀርም እና ለማሰረጃነት የደሕንነቶችን ስም፤ ፎቶግራፍ ፤ እና አድራሻ እንዲሁም በሐሠት
ምሰክርነት እና ከሳሽነት የተደራጁ አካላት እና ዋና ተወካዮች የደብረማርቆስ ከተማ 04 ቀበሌ አመራሮች እና ፖሊስ ለታሪክ አሰመዘግባለሁ ማንኛውም የምከፍለው ዋጋ ለሀገሬ እና ለነፃነት ነው ከታሠርሁም ሕሊናዬ አይታሰርም ከገደሉኝም ትግሌን አደራ በተለይ የኔ ትውልድ አደራ ! አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም ትግላችን የነፃነት ጉዟችን ጎርባጣ መድረሻችን ነፃነት ታሪካችን ዘላለማዊ ነው!!!
(ከሳሙኤል አወቀ ዓለም – የሰማያዊ ፓርቲ የደብረ ማርቆስ የሕዝብ ተወካዮች እጩ ተወዳዳሪ)

በህይወት ሳለ... በሳሙኤል ላይ ከፍተኛ ድብደባ ከደሰበት በኋላ፤ ጉዳቱን የሚያሳይ ፎቶ።

በሳሙኤል አወቀ ጉዳይ የደብረማርቆስ ነዋሪ እጅግ በጣም አዝኗል። ይህን አስመልክቶ ጉዳዩን ከዘገቡት መሃል አንዱ  ጌታቸው ሽፈራው እንዲህ ብሏል። “ሳሙኤል አወቀ እስር፣ ድብደባ፣ ዛቻ እየተደረገበት ወደኋላ ሳይል ሲታገል የቆየ ወጣት ነው፡፡ በርካታ ምሁራን ቤታቸው ቁጭ ባሉበት ይህ ወጣት በድፍረት የምስኪኑን አርሶ አደር ስቃይ በየቀኑ ለሚዲያ ሲያጋልጥ ቆይቷል፡፡”

ሳሙኤል አወቀ

እንደጌታቸው ሽፈራው ዘገባ ከሆነ፤ “ለዚህ ሁሉ ግን በቀል ተፈፅሞበታል፡፡ ለነገዋ ኢትዮጵያ፣ ለነፃነት ያለመው ወጣት በትናንትናው ዕለት ተገድሎ ተገኝቷል፡፡”

ይህ ወጣት ከመገደሉ ጥቂት ቀናት በፊት ይህን ፅፎ ነበር፡፡

እናስርሃለን፣ እንገድልሃለን!

(የገዥዎቻችን የሥራና የመግባቢያ ቋንቋ)

ሳሙኤል አወቀ

“ሀገሬ፣ ታሪክ፣ ሐይማኖት፣ ባሕልና ሸማግሌዎች አሏት፡፡ ነገር ግን ምነው ትንፍሽ የሚል ጠፋ? በየቀበሌው ጠያቂ የሌለው ጥቃቅን ንጉስ ነግሶብናል:: በደል እና ግፍ ራሳቸው እየፈፀሙ ለራሳቸው እንድንሰግድ የሚያደርግሥርዓት ተበጅቷል:: የቀበሌ ካድሬ የፍርድ ቤት ውሳኔ እንኳን አይገዛውም:: አላምንበትም አልተማከርሁበትም ይላል:: ወደየት ይደረሳል? ለማንስ ይነገራል? ከተመደበለት የቀበሌ ኮሚኒቲ ፖሊስ ጋር አብሮ ያስራል፡፡ ይገርፋል፡፡ ይደበድባል፡፡ ሲፈልግ የሀሠት ምሰክር አደራጅቶ እሰር ቤት ያሰወረውራል፡፡ የህዝብ ሮሮ ለነሱ ሙዚቃ ሆኗል፡፡ ሀይ ባይ፣ ገላጋይ፣ ገሳጭ አሥታራቂ ሽማግሌዎች እና የኃይማኖት መሪዎች በዓለማዊ ሕይወት ሕዝባቸውን ረስተዋል፡፡

“ማተቤ፣ ኃይማኖቴና ክብሬ ያሉ በአውሬ ተግባር ግፍ ተፈፅሞባቸው፣ ቶርች ተደርገው ወኀኒ ተዘግቶባቸዋል፡፡ የፖለቲካና የነፃነት፣ የፍትሕ የእኩልነት፣ ጥያቄ ያነሱ ኢትዮጵያውያን እንዳለሰው ተደርገው ወሕኒ ወርደዋል፡፡ ተሰደዋል፡፡ ተገድለዋል፡፡ አካላቸው ጎድሏል፡፡ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን እንዲሁ ተመሳሳይ ግፍ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አገራቸው አላስኖራቸው ብላ በስደት የበረሃ አወሬ የባሕር ዓሣ ቀለብ መሆናቸው ሳያንስ በፈላ ውሃ ተገሽረዋል፡፡ ከፎቅ ተወርውረዋል፡፡ የወሲብ ንግድ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በጅምላ ታፍነው አንገታቸውን ሲቀሉ አይተናል፡፡

“ብሔራዊ ውርደት በዓለም የታሪክ መዝገብ ተፅፎብናል፡፡ በሙሰናና በብልሹ አሰተዳደር ታንቀናል፡፡ የከተማ ክፉ ችጋር ጠብሶናል፡፡ ወጣቶች ሥራ አጥ ተደርገዋል፡፡ እህቶቻችን ጎዳና ላይ ናቸው፡፡ ስንቱ ጉድ ይፃፋል? ትላንት ኢህአፓ እንዲህ ተደረጉ ቀይ ሽብር ታውጆ ትውልድ እና እውቀት አለቀ ብለን በታሪካችን እያዘንን ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን ግን እጅግ የከፋ እና የአስተሳሰብ እድገት የተቀጨበት ነው! እናም ሽማግሌዎች እና የኃይማኖት አባቶች ከወዴት ናችሁ? ሀገሬ ኢትዮጵያ እርቅ ያስፈልጋታል? የኢትጵያዊያን የሰቆቃ እና የጣር ጬኸታችንን እያቃሰተ ነው:: የግፍ ፅዋው ሞልቶ ገንፍሏል:: አስርሃለሁ፣ ትገደላለህ፣ ትታፈናለህ፣ ትባረረላህ የገዥዎቻችን የሥራና የመግባቢያ ቋንቋ ሆኗል፡፡”

አዎ ከቀናት በፊት እንዲህ ብሎ የጻፈውን ወጣት፤ ኢህአዴጎች በግፍ ገድለውታል።

ጋዜጠኛ መልካም ሞላ ይህን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ዘግባለች።

የሰማያዊ ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ዞን ፀኃፊና በ2007 ዓ.ም ምርጫ የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪ የነበረው ወጣት ሳሙኤል አወቀ ተገደለ፡፡ ወጣት ሳሙኤል አወቀ ትናንት ሰኔ 8/2007 ዓ.ም ምሽት ላይ ወደ ቤቱ እየገባ በነበረበት ወቅት በሁለት ግለሰቦች ከፍተኛ ድብዳባ ከተፈፀመበት በኋላ ሆስፒታል ውስጥ ነፍሱ አልፋለች፡፡

ሳሙኤል አወቀ

Leave a Reply