በኢትዮጵያና በመካከለኛው ደቡብ አሜሪካ በምትገኘው ቦሊቪያ ያለው ርቀት 12,398 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ቦሊቪያ ዋና ከተማ ላፓዝ አድካሚ በሆነ የአውሮፕላን ጉዞ 15 ሰዓታትና 32 ደቂቃ ይፈጃል፡፡
እነዚህ አገሮች በታሪካቸው ጠንካራ የሚባል የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሌላቸው ሲሆን፣ በቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስማቸው አንድ ላይ መጠራት ጀምሯል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ከግሉተን ነፃ የሆነው የእህል ምርታቸው ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የጤና ባለሙያዎች ዘንድ በስንዴ እንዲሁም በተለያዩ እህሎች ውስጥ የሚገኘው ግሉተን የተባለው ፕሮቲን ሴሊያክ የሚባል የትንሽ አንጀት ሕመም የሚያስከትለው ንጥረ ነገር በኢትዮጵያው ጤፍና በቦሊቪያ ኪኒዋ ውስጥ የለም፡፡ ይህ እነዚህን የእህል ዝርያዎች ታላቅ እንዳደረጋቸው አስተያየት በመሰጠት ላይ ነው፡፡
ኪኒዋ የሚባለው እህል ቦሊቪያ ውስጥ አልቲፕላኖ በሚባለው ኮረብታማ ሥፍራ ላይ ከ3,000 ዓመተ ዓለም በፊት ጀምሮ ይበቅል የነበረ እህል ነው፡፡ በተለያዩ አፈ ታሪኮች እንደሚነገረው ይኼ እህል በዛው አካባቢ ነዋሪ ለነበሩት አይማራ ለተባሉት ሕዝቦች ከአምላክ የተሰጠ ስጦታ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለጤፍም የሚሰሙ አፈ ታሪኮች ከኪኒዋ የተለዩ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ጽሑፎች ከሰው ልጅ አፈጣጠር፣ በጥንት ዘመን ሕዝብን እየቀጠቀጠ ይገዛ ከነበረ ድራገን ጋር ያያይዙታል፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ጥንታዊ እህሎች ጤናን ማዕከል ያደረገ የኑሮ ዘዬን እንከተላለን በሚሉ ምዕራባውያን ዘንድ ከግሉተን ነፃ በመሆናቸው እየተሞገሱና እየተወደሱ ይገኛሉ፡፡ በፕሮቲን ሙሉ ለሙሉ የበለፀገው፣ በፋይበር (አሠር) የተሞላው እንዲሁም ጠቃሚ የሆነ አሚኖ አሲድ እንዲሁም የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን መያዙ ኪኒዋን በአጭር ጊዜ ውስጥ የምዕራቡ ዓለም ተመራጭና አማራጭ ምግብ አድርገውታል፡፡ የዚህ ምግብ ተወዳጅነትና ተመራጭነትም እህሉን በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት እ.ኤ.አ. 2013 ዓ.ም. ‹‹ዓለም አቀፍ የኪኒዋ ዓመት›› ተብሎ እንዲሰየም አስችሎታል፡፡ የኪኒዋ ዓለም አቀፍ ዕውቅናና እንደ አማራጭ ምግብ መታየት ለአካባቢው ከምግብነት ከመዋል አልፎ እንደ ዓለም አቀፍ ሸቀጥ እንዲታይና የኪኒዋን ዋጋ ለአካባቢው በማይታሰብ ሁኔታ ጨምሮታል፡፡ የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያሳዩትም በተለይም ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ የኪኒዋ ዋጋ በሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡ የአንዱ ምርቃት የአንዱ እርግማን እንደሚባለው ይህ አዲስ ለውጥ ለቦሊቪያውያን ጉዳት ነበር፡፡
በየቀኑ ዋና ምግብ የነበረ ይህ እህል በአይማራ ላሉት ሕዝቦች ከምዕራባውያን ፍላጎትና ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የማይቀመስ ሆነ፡፡ በሌላ በኩል ዓለም ኪኒዋን ሊስተካከል ወይም ሊተካ የሚችል እንደ ሌላ ምግብ አማራጭ ሊጠቀሙበት የሚችሉ ቀጣዩን ‹‹ታላቅ እህል›› (ሱፐር ግሬይን) እየፈለገ ነው፡፡ ፍለጋው እንደተሳካና ጤፍ ቀጣዩ ታላቅ እህል (ሱፐር ግሬይን) እንደሆነ የተለያዩ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው፡፡ ጤፍን አስመልክቶ የሀፊንግተን ፖስት ‹‹ኢዝ ጤፍ ዘ ኒው ሱፐር ፉድ›› በሚለው የ2006 ዘገባው ጤፍ በየትኛውም የአየር ንብረት የሚበቅል ተመራጭ እህል እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ በዚሁ ዘገባ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተለመደው እንጀራ በተጨማሪም ጤፍ በዳቦ፣ በፓንኬክ እንዲሁም በብስኩቶች መልክ ሊበላ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡ ይኼው ሪፖርት ጨምሮ እንደሚያስረዳው ጤፍ ከሌሎች እህሎች በተለየ መልኩ 50 በመቶ ብልጫ ፕሮቲን፣ አምስት እጥፍ ፋይበር (አሠር) እንዲሁም ከሩዝ የበለጠ ካልሺየም እንደያዘም ይጠቅሳል፡፡
ሌላኛው ከምግብ ጋር የተያያዘው ‹‹ፉድስ ፎር ቤተር ሄልዝ›› የሚባለው ድረ ገጽም ጤፍ በካልሺየም፣ በማንጋኔዝ እንዲሁም በአይረን የበለፀገ እንደሆነ ዘግቧል፡፡ ይኼው ድረ ገጽ በሌሎች እህሎች ባልተለመደ መልኩ ጤፍ ቫይታሚን ሲ ይዟል ይላል፡፡ ከእነዚህ ጽሑፎች በተጨማሪ የተለያዩ ምርምሮች ጤፍ ከፍተኛ የሆነ ካርቦሃይድሬት ቢይዝም ግሊስሚክ የሚባለውና በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን የሚያመለክተው ንጥረ ነገር ዝቅተኛ እንደሆነ ነው፡፡ ሪፖርቶቹ እንደሚያስረዱት ኢትዮጵያ ይኼንን የልብ ሕመምን የሚቀንስ፣ ከኮሌስትሮል እንዲሁም ካላስፈላጊ ውፍረት (ኦቤሲቲ) እና የስኳር ሕመም የሚከላከለውን ይኼንን ጥንታዊ ጤፍ በምስጢር ይዛው እንደነበር ዘግበዋል፡፡
ቻይና ፖስት፣ ቢቢሲ፣ ዘጋርዲያንና እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጤፍን ዓለም አቀፍ ከፍተኛ ዕውቅና እየሰጡት ነው፡፡ የሚያስገርመው ግን ጤፍ ለዘመናት ምንም ዓይነት ለሰውነትና ለጤና ጥቅም እንደሌለው በተለያዩ የውጭ አገርም ሆነ የኢትዮጵያ ኤክስፐርቶች ተነግሯል፡፡ ከአይረን ውጪ ምንም ንጥረ ነገር እንደሌለው ብዙ ጊዜ በተለያዩ አካላት ይሰማ ነበር፡፡ ለተለያዩ ስፖርተኞችም አቋም መውደቅም ጤፍ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ሁሉ ይነገራል፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ግን የእነዚህን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቀልብ መሳቡ እንዲሁም በሆሊውድ ዝነኛ ሰዎች እንደ ቪክቶሪያ ቤካምና ግዋኔዝ ፓልትሮው ያሉ ሰዎች ተቀባይነትን ማግኘቱ ብዙዎች ስለ ጤፍ ቆም ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ ይኼንን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግሥት ጤፍን ወደ ውጭ አገር አይላክም የሚለውን ለዓመታት ዕግድ አንስቷል፡፡ አገሪቷም 80 ሺሕ ኩንታል ጤፍ ወደ ውጭ አገር ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኗን የኢትዮጵያ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ገልጿል፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛው ጤፍ በምን መንገድ ሊላክ ነው የሚለው መረጃ ግልፅ ያልሆነላቸው ቢሆንም፣ አሁን ያለውን የዓለም አቀፍ ገበያ በማየት የጤፍን መላክ ጉዳይ በጥርጣሬ እንዲሁም በፍራቻ እያዩት ነው፡፡
ይህን ዕርምጃ ከቦሊቪያ ዕጣ ፈንታም ጋር ያያያዙትም አልታጡም፡፡ ቦሊቪያውያን ኪኒዋን በተመለከተ የገጠማቸው ዕጣ በጤፍ ላይ ሊከሰት ይችላል የሚል ፍራቻም አለ፡፡ የኪኒዋ ዓለም አቀፍ ዝና ጣራ በነካ ማግስት ለቦሊቪያውያንም ዋጋውም ናረ፡፡ ይህ የዋጋ ንረት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ላይ አለመረጋጋትን እንዲሁም ግጭቶችን አስከትሏል፡፡ የጤፍ የወጪ ንግድ ፍራቻም ጤፍ ወደ ውጭ አገር በተላከ ማግስት አገር ውስጥ ያለው ዋጋ ቢጨምርስ የሚል ነው፡፡
ይህ ፍራቻ ግን የጤፍን የወጪ ንግድ በበላይነት እየተቆጣጠረ ላለው የኢትዮጵያ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አልተሰማውም፡፡ በዚሁ ኤጀንሲ ሲስተምስ ፕሮግራምስ ዋና ዳይሬክተር አቶ ነጋ ውብነህ ከኪኒዋ ልምድ ትምህርት እንደቀሰሙና የጤፍ የወጪ ንግድም በጥንቃቄ፣ ጥብቅ በሆነና ቁጥጥርን መሠረት ባደረጉ መንገዶች እንደሚሆን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአሁን ወቅት የወጪ ንግድ ዕገዳም የኢትዮጵያ መንግሥት ያነሳበት ጤፍ በዓለም አቀፍ ሚዲያ ‹‹ታላቅ››፣ በተለያዩ ንጥረ ነገር የበለፀገ እንዲሁም ከግሉተን ነፃ መሆኑን ጋር ተያይዞ ትልቅ ስም በማግኘቱ እንደሆነ አቶ ነጋ ይናገራሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ የጤፍ መገኛ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋና አምራች ናት፡፡ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጤፍን የወጪ ንግድ ከሚያደርጉ አገሮች ውስጥ የለችበትም፡፡ በወጪ ንግድ ከፍተኛ ደረጃን ካገኙ አሥሩ አገሮች ተርታም አልተመደበችም፤›› ይላሉ አቶ ነጋ፡፡
በጤፍ የወጪ ንግድ ውስጥ ዋና የሚባሉ አገሮች ስፔን፣ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ዩጋንዳ፣ ካሜሮንና ደቡብ አፍሪካ እንደሆኑ አቶ ነጋ ጠቅሰዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ከመጣው ምግብ ኢትዮጵያም መጠቀም እንዳለባት አቶ ነጋ አጥብቀው ያምናሉ፡፡ ጤፍ የብዙ ኢትዮጵያውያን ዋና ምግብ እንደመሆኑ መጠን ጥንቃቄና ቁጥጥር ባለበት መንገድ ስትራቴጂዎች ተቀይሰው እየተካሄዱ ነው፡፡ የተለያዩ አገራዊ እንዲሁም የክልል ቢሮዎች ይኼንን የጤፍ የወጪ ንግድ በጥንቃቄ ለማካሄድ በኮሚቴ ተዋቅረዋል፡፡ አቶ ነጋ እንደገለጹት ይኼ ልዩ ኮሚቴ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የንግድ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም የኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያሉበት ነው፡፡
እንደ አቶ ነጋ የጤፍ የወጪ ንግድ ለሁሉም ክፍት ሳይሆን ለሚመለከታቸውና ለተመረጡ 48 ኮመርሻል እርሻዎች ነው፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳስረዱት እነዚህ ኮመርሻል የእርሻ ቦታዎች ጤፍን ከመትከል ጀምሮ፣ በዱቄት መልክ መፍጨት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ደረጃ በሚመጥን መልኩ አሽገው መላክ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ለአቶ ነጋ ከጤፍ የአገር ውስጥ ግብይት ጋር የሚገናኝ ነገር አይደለም፡፡ የኮመርሻል የእርሻ ቦታዎቹ ከተመረጡበት ጥቂት መስፈርቶች ውስጥ 20 ሔክታርና ከዚያ በላይ ለእርሻ የሚሆን መሬት ያላቸው፣ ሜካናይዝድ የእርሻ መንገዶችን የሚጠቀሙ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያላቸው እንዲሁም ጤፉ ከተመረተ በኋላ የተለያዩ ተጨማሪ ዕሴቶችን ሊጨምሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ጤፍን በዱቄት መልኩ የወጪ ንግድ ማድረግ ዝቅተኛው መስፈርት እንደሆነም አቶ ነጋ ይናገራሉ፡፡
አቶ ነጋ እንዳስረዱት ከአበቃቀሉ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ውጤት ያለውን ሒደት የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ይቆጣጠራሉ፡፡ ከተለያዩ የጤፍ አምራቾችም እንዳይገዙ ለማድረግ በአንድ ሔክታር መሬት ምን ያህል ምርት ያገኛሉ በሚለው መቆጣጠሪያ ዘዴ እንደሚገመግሟቸው አቶ ነጋ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ኮመርሻል የእርሻ ቦታዎቹ የሚጠቀሙበትን የአስተራረስ ዘዴ፣ ለመፍጨት የሚጠቀሙበትን የመፍጫ ማሽን፣ የማሸጊያ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ሌሎች ክትትሎች ለግብይት እስኪቀርቡ ድረስ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ክትትል ያደርጉባቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም ጋር በጥምረት እንደሚሠሩ አቶ ነጋ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ጤፍ የዲኤንኤ ምልክት ይደረግበታል፡፡ ይኼም ሁኔታ ምርቶቹን ካመረቷቸው ኮመርሻል እርሻዎች ጋር በቀጥታ ለማያያዝም ይጠቅማል ይላሉ አቶ ነጋ፡፡ ይኼንንም ተግባር ለማከናወን አንድ ኩባንያ ኃላፊነቱን የሚወስድ ሲሆን፣ የማረጋገጫ ሠርቲፊኬቶችን እንዲሁም ያመረተውን ኮመርሻል ፋርም የሚያመላክትን ሥራ ይሠራል፡፡
‹‹በእነዚህ ምርቶች ላይ የጤና እክሎች ቢገኙ ያመረታቸውን አካል ተከታትሎ ማግኘት ያስችላል፤›› ብለዋል አቶ ነጋ፡፡ ምንም እንኳን የጤፍ የወጪ ንግድ ዕግድ ቢነሳም አሁንም የጤፍን እህል ሳይፈጭ መላክ በጥብቅ ክልክል ነው፡፡ ጤፍን ፈጭቶ መላክ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ከማስገኘቱም በተጨማሪ ለብዙዎች የሥራ ዕድልም ይፈጥራል ብለው ያምናሉ፡፡ ጤፍን የመፍጨት ሒደትም የኢትዮጵያ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲም ከሚያበረታታው አግሮ ፕሮሰሲንግ (የግብርና ምርቶች ውጤትን በተለያዩ መልክ ተደራሽ ማድረግ) ከሚለው ጉዳይ ጋር እንደሚሄድም አቶ ነጋ አስረድተዋል፡፡ ለወደፊትም ጤፍ በፓስታ በብስኩት መልክ እንደሚላክም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ዓለም የጤፍን እንዲሁም ከግሉተን ነፃ የሆኑ ምግቦችን ከፍ እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አቶ ነጋ በአጠቃላይ ከግሉተን ነፃ የሆኑ ምግቦች የግብይት ዋጋ በዓመት ከአራት ቢሊዮን እስከ 12 ቢሊዮን ድረስ እንደሚገመትም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዘግይታ ገበያውን ለመቀላቀል ከማሰቧ አንፃር ምርቱን ጥንታዊና ከግሉተን ነፃ በሚል መልክ የማስተዋወቅ ሥራ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ አበክረው ይናገራሉ፡፡ ‹‹የዓለም አቀፍ ቀልብ ወደ ጤፍ እየተሳበ ቢሆንም አሁንም የተወሰነ ገበያ ነው ያለው፡፡ ይኼም ከፍተኛ የማስተዋወቅ ሥራ ይጠብቀዋል፤›› ይላሉ፡፡ የዓለም አቀፍ ግብይት ጋር ተያይዞ የጤፍ ዋጋ ቢጨምርስ የሚለውን ፍራቻ መሠረት ከአቅርቦት ጋር የተያያዘ ሳይሆን የጤፍ ነጋዴዎች በሚያቀርቡት የዋጋ መላምት ሊወደድ መቻሉ እንደሆነ አልደበቁም፡፡ ይኼ ሁኔታ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሊቀዛቀዝ እንደሚችል የሚያምኑት አቶ ነጋ፣ የዚህ ወጪ ንግድ ያለውን የአገር ውስጥ አቅርቦት በምንም መልኩ እንደማይነካ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም አቶ ነጋ እንደ ምሳሌ የሚያቀርቡት የሰሊጥን የወጪ ንግድ ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የወጪ ገበያ ይጨምራል በማለት በሰሊጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ቢከማቹም ይኼ ሳይሆን በተቃራኒው ሰሊጥ ዋጋው አሽቆልቁሏል፡፡
የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጤፍን አስመልክቶ የሚናገሩት በዓመታት ውስጥ መጨመሩን ነው፡፡ በአርባ ምንጭ አካባቢ ለባለፉት ሃያ ዓመታት በጤፍ ንግድ ላይ የሚተዳደሩት አቶ ማስረሻ ጫኔ ከባለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ ከአንድ ሺሕ ብር በታች የጤፍ ዋጋ ወርዶ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡ በአርባ ምንጭ አካባቢ ማኛ (አንደኛ ደረጃ) የሚባለው ጤፍ በኩንታል 1,400 ብር ሲሆን በአዲስ አበባ 1,900 ብር ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የጤፍ ዋጋ በኩንታል 130 ብር መሆኑን አቶ ማስረሻ ተናግረዋል፡፡ ይኼም የሚያሳየው የውጭ አገር ፍላጎት ሳይኖር የጤፍ ዋጋ እየጨመረ መሆኑን ነው፡፡
በደቃቅነቱ የሚታወቀውና 1/32 ኢንች ዲያሜትር ያለው ጤፍ ከስድስት ሚሊዮን በላይ በሆኑ በትናንሽ መሬት የሚያርሱ ገበሬዎች ይመረታል፡፡ ከዓመታት በፊት ገበሬዎቹ ከሚጠቀሙት ማዳበሪያና በአፈር መርዛማነት ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ምርት ማምረት አልቻሉም፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግን የኢትዮጵያ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ምርታማነት ለመጨመር ባደረገው እንቅስቃሴ ከ10 እስከ 12 ኩንታል በሔክታር ይገኝ የነበረውን ምርት ወደ 25 እስከ 26 ኩንታል መጨመር ችሏል፡፡ ይኼም በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ 1.5 ሚሊዮን ገበሬዎች ላይ ተግባራዊ ሆኗል፡፡
አቶ ነጋ እንደሚሉት ይህ አቅርቦት የመጨመር ጉዳይ በአገሪቷ ውስጥ እየጨመረ ያለውን ፍላጎት ያሟላል፡፡ ጤፍ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በትናንሽ መሬት በገበሬዎች የሚመረት ሲሆን፣ ሁለት በመቶ የሚሆነው አቅርቦት ደግሞ በኮመርሻል እርሻ የሚመረት ነው፡፡ እነዚህ 48 ኮመርሻል የእርሻ ቦታዎች በዚህ ውስጥ እንዳልተካተቱ አቶ ነጋ ተናግረዋል፡፡
‹‹በአገር ውስጥ ባለው ገበያ ምንም ጫና አያመጣም፤›› በማለትም አቶ ነጋ ያረጋግጣሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ነጋ ብቻ ሳይሆኑ የግብርና የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ደምስ ጫንያለው በበቆሎና በገብስ ላይ የተሠራ ምርምርን አስመልክተው ሲናገሩ፣ የእህሎቹ ምርታማነት በባለፉት ዓመታት ውስጥ በሰባት በመቶ ያህል መጨመሩን ነው፡፡ ይኼንንም በመመልከት የጤፍ ምርታማነትም በዓመታት እንደጨመረ ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳን የጤፍን የወጪ ንግድ አስመልክቶ ብዙዎች ፍራቻ ቢኖራቸውም፣ ዶ/ር ደምስ መንግሥት የጤፍን የወጪ ንግድ ዕግድ የጣለው አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩና አሁን ደግሞ ዕግዱን ለማንሳቱ ሁኔታው በመስተካከሉ ነው ይላሉ፡፡ ብዙዎች ጤፍ ዋና እህል በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግለት ይገባል ብለው ቢናገሩም፣ ዶ/ር ደምስ ግን ከሌሎች እህሎች በተለየ መልኩ መታየት እንዴለበት ይናገራሉ፡፡
‹‹የጤፍ ገበያ በአሁን ወቅት ከእጃችን ወጥቷል፡፡ የጤፍ አምራቾች ያልሆኑ አገሮችም በጤፍ ተጠቃሚ የሆኑበት ጊዜ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ቢሆንም ግን የአቶ ነጋን የነጋዴዎችና የደላላዎች የዋጋ መላ ምት ዋጋውን ሊጨምረው ይችላል የሚለውንም ሐሳብም ይጋራሉ፡፡ ከ97 በመቶ በላይ በአምስት ሔክታር መሬት የሚመረተው የጤፍ አቅርቦት ለአገር ውስጥ ገበያ በቂ ነው ብለውም ዶክተሩ ያምናሉ፡፡ እህሉንም እንዳለ ለመላክም ከፍተኛ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራት አለበትም በማለት ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሔ እንደ ዋና ጥያቄ መመለስ አለበት ብለው የሚያስቡት የጤፍ ፍላጎትና አቅርቦት ምን ያህል የተመጣጠነ ነው የሚለው ነው፡፡ በተለይም ጤፍን ወደ ውጭ መላክ የሚለውን ሐሳብ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ የሚቃወሙት ሲሆን፣ በተለይም የጤፍ የባለቤትነት መብት ዓለም አቀፍ ላይ አከራካሪ በሆነበት ሁኔታ መሞከር የለበትም ይላሉ፡፡ ኮመርሻል የእርሻ ቦታዎች ጤፍን ሊያመርቱ ነው የሚለውን ሐሳብ አስመልክቶ ከፍተኛ ጥንቃቄና ማረም የሚያስፈልገውን ጤፍ በምን መንገድ ሊያመርቱ ይችላሉ የሚለውን ሐሳብ ጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብተውታል ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡፡
በጤፍ የወጪ ንግድ ሒደት የአገር ውስጥ ገበያውን ሊያዛባው ይችላል፣ በተለይ የነጋዴዎችና የደላላዎች የዋጋ መላ ምት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለው ያምናሉ፡፡ ‹‹የጤፍ ወጪ ንግድ በሚሰማበት ሰዓት የጤፍ ዋጋ ሦስት ሺሕ ብር ሊሆን ይችላል፤›› ይላሉ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡፡ ቢሆንም ባለው የዓለም አቀፉ የንግድ ሥርዓት የጤፍ የወጪ ንግድ አስገዳጅ ከሆነ ተፈጭቶና ታሽጎ መላኩ ላለው ማኅበረሰብ ሥራ ስለሚፈጥርም እንደሚደግፉት ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡
የዋጋ ንረት ከተከሰተም መንግሥት የዋጋ ጣሪያ ማድረግ ሊገደድ የሚችልበት አጋጣሚም ሊፈጠር እንደሚችል ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ገልጸዋል፡፡
ጤፍ በ48 ኮመርሻል እርሻ ቦታዎች ለመላክ የተመረጡበትን ሁኔታ ከተዘረጋው የነፃ ሥርዓት ግብይት ጋር የሚሆን አይደለም ይላሉ፡፡
ምንም እንኳን የተለያዩ አስተያየቶች ቢኖሩም፣ አቶ ነጋ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ውስጥ የሚገኙ የኮመርሻል የእርሻ ቦታዎች ላይ ጤፍ ለመላክ ምርት ተጀምሯል፡፡ በዚህ ወቅትም ትልልቅ የሆኑ ዓለም አቀፍ የምግብ ኮርፖሬሽኖች በጤፍ ላይ ፍላጎት አሳድረዋል፡፡ ስምምነት ላይ ባይደረስም የእንግሊዙ ቴስኮ፣ የአሜሪካው ጄኔራል ሚል እንዲሁም ስሙ ያልተጠራ የሆላንድ ካምፓኒ ፍላጎት እንዳሳዩ አቶ ነጋ ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ገበያ ጤፍ በቶን 150 ዶላር ያህል ሲሆን፣ እንደ ጤፉ ዓይነትም ዋጋው ይለያያል፡፡